በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ “አውሎ ነፋስ” እየተቃረበ ሲመጣ ሰዎች ማስጠንቀቂያውን መስማት ያስፈልጋቸዋል!

አምላክ የፍርድ እርምጃ ሲወስድ ሁልጊዜ በቂ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል?

አምላክ የፍርድ እርምጃ ሲወስድ ሁልጊዜ በቂ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል?

የአየር ትንበያ ባለሙያው የራዳር ምስሉን እየተመለከተ ነው። አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ኃይለኛ ዝናብ ብዙ ሰዎች ወደሚኖሩበት አካባቢ እየመጣ እንደሆነ አስተዋለ። ባለሙያው፣ የነዋሪዎቹ ደህንነት ስለሚያሳስበው አደጋው ከመድረሱ በፊት ሰዎቹን ለማስጠንቀቅ የቻለውን ሁሉ ያደርጋል።

በተመሳሳይም ይሖዋ፣ እየመጣ ስላለው እንደ “አውሎ ነፋስ” ያለ አደጋ የምድርን ነዋሪዎች እያስጠነቀቀ ነው፤ ይህ “አውሎ ነፋስ” ሰዎች በአየር ትንበያ ዘገባዎች ላይ ከሚሰሟቸው አደጋዎች ሁሉ የከፋ ነው። ለመሆኑ ይሖዋ ሰዎችን እያስጠነቀቀ ያለው እንዴት ነው? ይሖዋ፣ ሰዎች ማስጠንቀቂያውን ሰምተው እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላቸው በቂ ጊዜ እንደሚሰጣቸው እርግጠኛ የምንሆነው ለምንድን ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በመጀመሪያ፣ ይሖዋ በጥንት ዘመን ማስጠንቀቂያ የሰጠባቸውን አንዳንድ ወቅቶች እንመርምር።

አምላክ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ የሰጠባቸው ጊዜያት

በጥንት ዘመን ይሖዋ የእሱን ትእዛዝ ሆን ብለው በሚጥሱ ሰዎች ላይ የሚወስደውን እንደ “አውሎ ነፋስ” ያለ የፍርድ እርምጃ በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (ምሳሌ 10:25፤ ኤር. 30:23) በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ይሖዋ፣ ማስጠንቀቂያው የሚመለከታቸውን ሰዎች አስቀድሞ ስለ ጥፋቱ አሳውቋቸዋል፤ እንዲሁም ከእሱ ፈቃድ ጋር ለመስማማት ምን ማስተካከያ ማድረግ እንዳለባቸው ነግሯቸዋል። (2 ነገ. 17:12-15፤ ነህ. 9:29, 30) ሰዎች አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲያደርጉ ለማነሳሳት ሲል ብዙውን ጊዜ በምድር ላይ ያሉ ታማኝ አገልጋዮቹን ይጠቀም ነበር፤ እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች የእሱን ፍርድ የሚያሳውቁ ከመሆኑም ሌላ ሰዎች አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ያበረታቱ ነበር።—አሞጽ 3:7

ከእነዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች አንዱ ኖኅ ነው። ኖኅ በዘመኑ የነበሩትን ሥነ ምግባር የጎደላቸውና ዓመፀኛ የሆኑ ሰዎች በምድር ላይ ስለሚመጣው የጥፋት ውኃ ለበርካታ ዓመታት በድፍረት አስጠንቅቋል። (ዘፍ. 6:9-13, 17) በተጨማሪም ከጥፋቱ ለመትረፍ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ነግሯቸዋል፤ በዚህም የተነሳ ኖኅ ከጊዜ በኋላ “የጽድቅ ሰባኪ” ተብሎ ተጠርቷል።—2 ጴጥ. 2:5

ኖኅ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ከጥፋት ውኃ በፊት የነበሩት ሰዎች፣ አምላክ ለእሱ የሰጠውን መልእክት ለመስማት ፈቃደኛ አልሆኑም። እነዚህ ሰዎች ጨርሶ እምነት እንደሌላቸው አሳይተዋል። በዚህም የተነሳ “የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ [ወሰዳቸው]።” (ማቴ. 24:39፤ ዕብ. 11:7) እነዚህ ሰዎች አምላክ በቂ ማስጠንቀቂያ እንዳልሰጣቸው በመግለጽ ሊያሳብቡ አይችሉም።

በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ይሖዋ እንደ “አውሎ ነፋስ” ያለ የፍርድ እርምጃ እንደሚወስድ ለሰዎች ማስጠንቀቂያ የሰጠው እርምጃ ከመውሰዱ ከአጭር ጊዜ በፊት ነው። ያም ቢሆን የፍርድ እርምጃው የሚመለከታቸው ሰዎች ማስጠንቀቂያውን ሰምተው ማስተካከያ እንዲያደርጉ በቂ ጊዜ ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በጥንቷ ግብፅ ላይ አሥር መቅሰፍቶች ባወረደበት ወቅት አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ሰባተኛው መቅሰፍት ይኸውም የበረዶ ውርጅብኝ ከመድረሱ በፊት የነበረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ በዚህ ወቅት ይሖዋ ሙሴንና አሮንን በመላክ ለፈርዖንና ለአገልጋዮቹ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ይሖዋ ማስጠንቀቂያውን የሰጠው ከአንድ ቀን በፊት ከመሆኑ አንጻር ሰዎቹ መጠለያ መፈለግና ከበረዶ ውርጅብኙ ማምለጥ የሚችሉበት በቂ ጊዜ አግኝተው ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ከፈርዖን አገልጋዮች መካከል የይሖዋን ቃል የፈሩ ሁሉ አገልጋዮቻቸውንና ከብቶቻቸውን በፍጥነት ወደ ቤት አስገቡ፤ ሆኖም የይሖዋን ቃል ከቁም ነገር ያልቆጠሩት ሁሉ አገልጋዮቻቸውንና ከብቶቻቸውን እዚያው መስክ ላይ እንዳሉ ተዉአቸው።” (ዘፀ. 9:18-21) ከዚህ በግልፅ ማየት እንደሚቻለው ይሖዋ በቂ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፤ በመሆኑም ማስጠንቀቂያውን ሰምተው አፋጣኝ እርምጃ የወሰዱት ሰዎች ከከፋ ጉዳት ማምለጥ ችለዋል።

በተመሳሳይም ከአሥረኛው መቅሰፍት በፊት ይሖዋ፣ ፈርዖንንና አገልጋዮቹን አስጠንቅቋቸዋል። ይሁንና ማስጠንቀቂያውን ለመስማት አሻፈረኝ አሉ። (ዘፀ. 4:22, 23) በዚህም ምክንያት እነዚህ ሰዎች የበኩር ልጆቻቸውን አጡ። ይህ ምንኛ የሚያሳዝን ነው! (ዘፀ. 11:4-10፤ 12:29) ሆኖም ማስጠንቀቂያውን ሰምተው እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ጊዜ ነበራቸው? በሚገባ! ሙሴ አሥረኛውን መቅሰፍት በተመለከተ እስራኤላውያንን ያስጠነቀቃቸውና ቤተሰባቸውን ማትረፍ ስለሚችሉበት መንገድ መመሪያ የሰጣቸው መቅሰፍቱ ከመድረሱ ከአጭር ጊዜ በፊት ነው። (ዘፀ. 12:21-28) ማስጠንቀቂያውን ሰምተው እርምጃ የወሰዱት ምን ያህል ሰዎች ናቸው? አንዳንዶች እንደሚገምቱት ሦስት ሚሊዮን ሰዎች ከአምላክ የፍርድ እርምጃ ተርፈው ከግብፅ ወጥተዋል፤ ከእነዚህ መካከል እስራኤላውያን እንዲሁም “እጅግ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” የተባሉት እስራኤላዊ ያልሆኑ ሰዎችና ግብፃውያን ይገኙበታል።—ዘፀ. 12:38 ግርጌ

እነዚህ ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት ምንጊዜም ቢሆን ይሖዋ፣ ሰዎች የእሱን ማስጠንቀቂያ ሰምተው እርምጃ የሚወስዱበት በቂ ጊዜ እንዲያገኙ ያደርጋል። (ዘዳ. 32:4) አምላክ እንዲህ እንዲያደርግ የሚያነሳሳው ምንድን ነው? ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደገለጸው ይሖዋ “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ [አይፈልግም]።” (2 ጴጥ. 3:9) አዎ፣ አምላክ ለሰዎች ያስባል። የፍርድ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ሰዎች ንስሐ እንዲገቡና ምክሩን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ይፈልጋል።—ኢሳ. 48:17, 18፤ ሮም 2:4

በዛሬው ጊዜ አምላክ የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ መስማት

በዛሬው ጊዜም፣ ሰዎች ሁሉ በምድር ዙሪያ እየተነገረ ያለውን አጣዳፊ ጥሪ ሰምተው እርምጃ መውሰድ አለባቸው። ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ፣ አሁን ያለው ሥርዓት ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት እንደሚጠፋ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር። (ማቴ. 24:21) አምላክ ወደፊት የሚወስደውን የፍርድ እርምጃ አስመልክቶ ዝርዝር ሐሳቦችን የያዘ ትንቢት ለተከታዮቹ ነግሯቸዋል፤ ይህ ትንቢት፣ ጥፋቱ የሚደርስበት ጊዜ እየተቃረበ ሲሄድ ስለሚፈጸሙት ክንውኖች ይገልጻል። በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ የምንመለከታቸው ትላልቅ ክንውኖች ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ ናቸው።—ማቴ. 24:3-12፤ ሉቃስ 21:10-13

ከዚህ ትንቢት አንጻር ይሖዋ፣ በፍቅር ላይ የተመሠረተውን የእሱን አገዛዝ እንዲደግፉ ሰዎችን ሁሉ እያሳሰበ ነው። ታዛዥ የሆኑ ሰዎች በዛሬው ጊዜ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው፣ ወደፊት ደግሞ ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ በረከት እንዲያገኙ ይፈልጋል። (2 ጴጥ. 3:13) ሰዎች እሱ በገባው ቃል ላይ እምነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ሲል ይሖዋ ሕይወት አድን የሆነ መልእክት ይኸውም “የመንግሥቱ ምሥራች” እንዲሰበክ እያደረገ ነው፤ ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ይህ ምሥራች “ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል።” (ማቴ. 24:14) “ምሥክር” የሚሆነውን ይህን መልእክት እንዲያውጁ አምላክ 240 ገደማ በሚሆኑ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ እውነተኛ አገልጋዮቹን አደራጅቷቸዋል። ይሖዋ፣ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ማስጠንቀቂያውን እንዲሰሙና ወደፊት ከሚወስደው እንደ “አውሎ ነፋስ” ያለ የፍርድ እርምጃ እንዲተርፉ ይፈልጋል።—ሶፎ. 1:14, 15፤ 2:2, 3

እንግዲያው ሊነሳ የሚገባው ወሳኝ ጥያቄ ‘ይሖዋ፣ ሰዎች ማስጠንቀቂያውን ሰምተው እርምጃ የሚወስዱበት በቂ ጊዜ ይሰጣል?’ የሚለው አይደለም። ማስረጃው እንደሚያሳየው ይሖዋ ምንጊዜም እንዲህ ያደርጋል። አሳሳቢው ጉዳይ፣ ‘ሰዎች ጊዜው ከማለቁ በፊት የአምላክን ማስጠንቀቂያ ለመስማት ፈቃደኞች ይሆናሉ?’ የሚለው ነው። በመሆኑም የአምላክ መልእክተኞች እንደመሆናችን መጠን የተቻለውን ያህል ብዙ ሰዎች በዚህ ሥርዓት ላይ ከሚመጣው ጥፋት እንዲተርፉ መርዳታችንን እንቀጥል።