በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 43

ይሖዋን ብቻ አምልኩ

ይሖዋን ብቻ አምልኩ

“ይሖዋ እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ . . . አምላክ ነው።”—ናሆም 1:2

መዝሙር 51 ራሳችንን ለአምላክ ወስነናል!

ማስተዋወቂያ *

1. ይሖዋ ብቻ ሊመለክ የሚገባው ለምንድን ነው?

ይሖዋ ፈጣሪያችንና ሕይወት ሰጪያችን በመሆኑ ልናመልክ የሚገባው እሱን ብቻ ነው። (ራእይ 4:11) ይሁንና ይህን ማድረግ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ለይሖዋ ፍቅርና አክብሮት ቢኖረንም እንኳ ለእሱ ብቻ የሚገባውን አምልኮ እንዳናቀርብ እንቅፋት የሚሆኑብን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥመን የሚችለው እንዴት እንደሆነ ማወቃችን አስፈላጊ ነው። በመጀመሪያ ግን ይሖዋን ብቻ ማምለክ የትኞቹን ነገሮች እንደሚያካትት እንመልከት።

2. በዘፀአት 34:14 መሠረት ይሖዋን ብቻ የምናመልክ ከሆነ ምን አናደርግም?

2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ ይሖዋን ብቻ ማምለክ ለእሱ ጥልቅ ፍቅር ከማዳበር ጋር ተያይዞ ተገልጿል። በመሆኑም ይሖዋ በልባችን ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን ቦታ፣ ማንኛውም አካል ወይም ነገር እንዲይዝ አንፈቅድም።ዘፀአት 34:14ን አንብብ።

3. ይሖዋን የምንወደው እንዲያው በጭፍን አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

3 ይሖዋን የምንወደው እንዲያው በጭፍን አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋን የወደድነው ስለ እሱ ባወቅናቸው ነገሮች ላይ ተመሥርተን ነው። ግሩም ለሆኑት የይሖዋ ባሕርያት አድናቆት አዳብረናል። እሱ የሚወዳቸውንና የሚጠላቸውን ነገሮች አውቀናል፤ እኛም የእሱ ዓይነት አመለካከት አለን። ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ የተረዳን ከመሆኑም ሌላ ዓላማውን እንደግፋለን። ይሖዋ ወዳጆቹ የመሆን አጋጣሚ ስለከፈተልን እንዳከበረን ይሰማናል። (መዝ. 25:14) ስለ ፈጣሪያችን የምንማረው እያንዳንዱ ነገር ወደ እሱ ይበልጥ እንድንቀርብ ያነሳሳናል።—ያዕ. 4:8

4. (ሀ) ዲያብሎስ ይሖዋን ብቻ እንዳናመልክ ለማድረግ በምን ይጠቀማል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

4 ይህን ሥርዓት የሚቆጣጠረው ዲያብሎስ ነው፤ በመሆኑም ይህን ሥርዓት በመጠቀም፣ ተፈጥሯዊ ለሆኑ ፍላጎቶቻችን ከልክ ያለፈ ቦታ እንድንሰጥ እንዲሁም በድክመቶቻችን እንድንሸነፍ ለማድረግ ይሞክራል። (ኤፌ. 2:1-3፤ 1 ዮሐ. 5:19) ዓላማው ለሌሎች ነገሮች ያለን ፍቅር፣ ለይሖዋ ብቻ ልናቀርብ የሚገባውን አምልኮ እንዲሻማብን ማድረግ ነው። ዲያብሎስ ይህን ሊያደርግ የሚችልባቸውን ሁለት አቅጣጫዎች እስቲ እንመልከት። አንደኛ፣ ሀብትን እንድናሳድድ ሊፈትነን ይችላል፤ ሁለተኛ ደግሞ ተገቢ ያልሆነ የመዝናኛ ምርጫ እንድናደርግ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይሞክራል።

በገንዘብ ፍቅር እንዳትጠመዱ ተጠንቀቁ

5. በገንዘብ ፍቅር እንዳንጠመድ መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው?

5 ሁላችንም ብንሆን በቂ ምግብ፣ ጥሩ ልብስና ተስማሚ መኖሪያ ለማግኘት መፈለጋችን ተፈጥሯዊ ነገር ነው። ይሁን እንጂ የገንዘብ ፍቅር እንዳይጠናወተን መጠንቀቅ ይኖርብናል። በሰይጣን ዓለም ውስጥ ብዙ ሰዎች ገንዘብን እና ገንዘብ ሊገዛቸው የሚችላቸውን ነገሮች ይወዳሉ። (2 ጢሞ. 3:2) ኢየሱስ እንዲህ ያለው ፍቅር ለተከታዮቹ ፈተና ሊሆንባቸው እንደሚችል ያውቅ ነበር። በመሆኑም እንዲህ ብሏል፦ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም።” (ማቴ. 6:24) በአንድ በኩል ይሖዋን እያመለከ በሌላ በኩል ደግሞ ሀብት ለማካበት ከፍተኛ ጥረት የሚያደርግና ብዙ ጊዜ የሚያባክን ሰው፣ ሁለት ጌቶችን ለማገልገል እየሞከረ ነው ሊባል ይችላል። እንዲህ ያለው ሰው ይሖዋን ብቻ እያመለከ ነው ማለት አይቻልም።

አንዳንድ ሎዶቅያውያን ለራሳቸው የነበራቸው አመለካከት . . . ይሖዋ እና ኢየሱስ ለእነሱ የነበራቸው አመለካከት (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)

6. ኢየሱስ በሎዶቅያ ለነበረው ጉባኤ ከተናገረው ሐሳብ ምን ትምህርት እናገኛለን?

6 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. መገባደጃ አካባቢ በሎዶቅያ ከተማ የሚገኘው ጉባኤ አባላት “ሀብታም ነኝ፤ ደግሞም ብዙ ሀብት አከማችቻለሁ፤ ምንም ነገር አያስፈልገኝም” ብለው ይኩራሩ ነበር። ይሖዋና ኢየሱስ ግን “ጎስቋላ፣ ምስኪን፣ ድሃ፣ ዕውርና [የተራቆቱ]” እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸው ነበር። ኢየሱስ ለእነዚህ ክርስቲያኖች ምክር የሰጣቸው፣ ሀብታም በመሆናቸው ሳይሆን ለገንዘብ ያላቸው ፍቅር ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና እያበላሸባቸው ስለነበር ነው። (ራእይ 3:14-17) ሀብት የማካበት ፍላጎት በልባችን ውስጥ እያቆጠቆጠ እንደሆነ ካስተዋልን አስተሳሰባችንን ለማስተካከል አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። (1 ጢሞ. 6:7, 8) እንዲህ ዓይነት እርምጃ ካልወሰድን ልባችን ይከፋፈላል፤ ይሖዋም ለእሱ የምናቀርበውን አምልኮ አይቀበልም። ይሖዋ የሚፈልገው “እሱ ብቻ እንዲመለክ” ነው። (ዘዳ. 4:24) ለመሆኑ ለገንዘብ ባለን አመለካከት ረገድ ሚዛናችንን ልንስት የምንችለው እንዴት ነው?

7-9. ዴቪድ የተባለው ሽማግሌ ካጋጠመው ነገር ምን ትምህርት አግኝተሃል?

7 በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረውንና የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ በትጋት የሚያገለግለውን ዴቪድን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ዴቪድ ተቀጥሮ ይሠራ በነበረበት ወቅት ታታሪ ሠራተኛ እንደነበር ይናገራል። በሚሠራበት ድርጅት ውስጥ እድገት ያገኘ ከመሆኑም ባሻገር በተሰማራበት መስክ በአገሩ ውስጥ አሉ ከተባሉ ባለሙያዎች አንዱ መሆን ችሎ ነበር። ዴቪድ “በዚያ ወቅት፣ እንዲህ ያለ ስኬት ያገኘሁት ይሖዋ ስለባረከኝ እንደሆነ አስብ ነበር” ብሏል። ሆኖም ይህ እውነት ነበር?

8 ዴቪድ፣ ሥራው ከይሖዋ ጋር ባለው ዝምድና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ እንዳለ የሚጠቁሙ ምልክቶችን እያደር መመልከት ጀመረ። እንዲህ ብሏል፦ “በጉባኤ ስብሰባዎች ሌላው ቀርቶ በአገልግሎት ላይም እንኳ በሥራዬ ላይ ስላጋጠሙኝ ችግሮች እንደማውጠነጥን አስተዋልኩ። የማገኘው ገንዘብ ብዙ ቢሆንም የሚሰማኝ ውጥረት እየጨመረ ከመሄዱም ሌላ በትዳሬ ውስጥ ችግሮች ያጋጥሙኝ ጀመር።”

9 ዴቪድ በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች መገምገም እንዳለበት ተገነዘበ። “ያለሁበትን ሁኔታ ለማስተካከል ቁርጥ ውሳኔ አደረግኩ” ብሏል። ዴቪድ በሥራ ፕሮግራሙ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ስለፈለገ ያሰበውን ነገር ለአሠሪው ነገረው። ውጤቱ ምን ሆነ? ከሥራው ተባረረ! ታዲያ ምን አደረገ? ዴቪድ “በቀጣዩ ቀን፣ ላልተወሰነ ጊዜ ረዳት አቅኚ ሆኜ ለማገልገል አመለከትኩ” ብሏል። ዴቪድና ባለቤቱ መተዳደሪያ ለማግኘት የጽዳት ሥራ መሥራት ጀመሩ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዴቪድ የዘወትር አቅኚ ሆነ፤ ውሎ አድሮ ባለቤቱም አብራው በአቅኚነት ማገልገል ጀመረች። እነዚህ ባልና ሚስት፣ ብዙዎች ዝቅ አድርገው የሚመለከቱትን ሥራ ለመሥራት መርጠዋል፤ ሆኖም እነሱን በዋነኝነት የሚያሳስባቸው የሥራው ዓይነት አይደለም። ገቢያቸው ቀድሞ ከሚያገኙት አንድ አሥረኛ ያህል ብቻ ቢሆንም በየወሩ ወጪያቸውን ለመሸፈን የሚበቃ ነው። ፍላጎታቸው በሕይወታቸው ውስጥ ለይሖዋ ቅድሚያ መስጠት ነው፤ ደግሞም ይሖዋ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚያስቀድሙ ሰዎችን እንደሚንከባከብ በራሳቸው ሕይወት ተመልክተዋል።—ማቴ. 6:31-33

10. ልባችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

10 ሀብታምም ሆንን ድሃ ልባችንን መጠበቅ ያስፈልገናል። ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? የገንዘብ ፍቅር እንዳያድርብህ ተጠንቀቅ። ሰብዓዊ ሥራህን ለአምላክ ከምታቀርበው አገልግሎት እንዳታስቀድም ጥንቃቄ አድርግ። ለመሆኑ እንዲህ ዓይነት አዝማሚያ እንዳለህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በስብሰባዎች ወይም በአገልግሎት ላይ እያለሁ ብዙውን ጊዜ ስለ ሥራዬ አስባለሁ? ለወደፊቱ ጊዜ የሚሆን በቂ ገንዘብ የማስቀመጥ ጉዳይ ሁልጊዜ ያስጨንቀኛል? ገንዘብና ቁሳዊ ነገሮች በትዳሬ ውስጥ ችግር እንዲፈጠር እያደረጉ ነው? ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገል የሚሆን ጊዜ ለማግኘት እስካስቻለኝ ድረስ ሌሎች ዝቅ አድርገው የሚመለከቱትን ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ ነኝ?’ (1 ጢሞ. 6:9-12) በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ በምታሰላስልበት ወቅት፣ ይሖዋ እንደሚወድህና እሱን ለሚያመልኩት ሰዎች “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት ቃል እንደገባ አስታውስ። ሐዋርያው ጳውሎስ “አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን” በማለት የጻፈው ለዚህ ነው።—ዕብ. 13:5, 6

መዝናኛችሁን በጥንቃቄ ምረጡ

11. አንድ ሰው የሚመርጠው መዝናኛ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድርበት ይችላል?

11 ይሖዋ በሕይወታችን ደስተኛ እንድንሆን ይፈልጋል፤ ለደስታችን አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ደግሞ መዝናኛ ነው። እንዲያውም የአምላክ ቃል “ሰው ከመብላትና ከመጠጣት እንዲሁም ተግቶ በመሥራት እርካታ ከማግኘት የሚሻለው ነገር የለም” ይላል። (መክ. 2:24) ይሁንና በዓለም ላይ ያለው አብዛኛው መዝናኛ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል። ሰዎች ልል የሥነ ምግባር አቋም እንዲኖራቸው ያደርጋል፤ እንዲሁም የአምላክ ቃል የሚያወግዛቸውን ነገሮች አቅልለው እንዲመለከቱ ይባስ ብሎም እነዚህን ነገሮች እንዲወዱ ያበረታታል።

መዝናኛህን የሚያዘጋጀው ማን ነው? (ከአንቀጽ 11-14⁠ን ተመልከት) *

12. በ1 ቆሮንቶስ 10:21, 22 መሠረት መዝናኛችንን በጥንቃቄ መምረጥ ያለብን ለምንድን ነው?

12 ይሖዋን ብቻ ማምለክ እንፈልጋለን፤ በመሆኑም በአንድ በኩል “ከይሖዋ ማዕድ” እየተመገብን በሌላ በኩል ደግሞ “ከአጋንንት ማዕድ” መቋደስ አንችልም። (1 ቆሮንቶስ 10:21, 22ን አንብብ።) በአንድ ገበታ ላይ አብሮ መመገብ ብዙውን ጊዜ የወዳጅነት ምልክት እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። ዓመፅን፣ መናፍስታዊ ድርጊትን፣ የሥነ ምግባር ብልግናን ወይም ሌሎች ሥጋዊ አስተሳሰቦችንና ምኞቶችን የሚያስፋፉ መዝናኛዎችን የምንመርጥ ከሆነ የአምላክ ጠላቶች ካዘጋጁት ገበታ እየተመገብን ያለን ያህል ነው። እንዲህ ማድረግ ራሳችንን የሚጎዳ ከመሆኑም ሌላ ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ያበላሽብናል።

13-14. በያዕቆብ 1:14, 15 መሠረት መጥፎ ምኞቶችን የሚቀሰቅሱ ነገሮችን ወደ አእምሯችን እንዳናስገባ መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

13 መዝናኛ ከምግብ ጋር የሚመሳሰልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት። ምግብ ስንበላ ወደ አፋችን የምናስገባውን ነገር መምረጥ እንችላለን። አንዴ ምግቡን ከዋጥነው በኋላ ግን በምግቡ ውስጥ ያሉት ንጥረ ነገሮች ከሰውነታችን ጋር የሚዋሃዱበትን መንገድ መቆጣጠር አንችልም። ጥሩ ምግብ ጤናማ እንድንሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል፤ ጤናማ ያልሆነ ምግብ ግን በጤንነታችን ላይ ጉዳት ያስከትላል። የምንመገበው ምግብ የሚያስከትለው ውጤት በአንድ ጀምበር የሚታይ ባይሆንም እንኳ ውሎ አድሮ መታየቱ አይቀርም።

14 በተመሳሳይም መዝናኛ ስንመርጥ ወደ አእምሯችን የምናስገባውን ነገር መቆጣጠር እንችላለን። አንዴ ወደ አእምሯችን ከገባ በኋላ ግን መዝናኛው በአእምሯችንና በልባችን ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ መቆጣጠር አንችልም። ጥሩ መዝናኛ መንፈሳችንን ያድስልናል፤ ጤናማ ያልሆነ መዝናኛ ግን ይጎዳናል። (ያዕቆብ 1:14, 15ን አንብብ።) መጥፎ መዝናኛ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ወዲያውኑ ግልጽ ባይሆንም እንኳ ውሎ አድሮ መታየቱ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ የሚሰጠን ለዚህ ነው፦ “አትታለሉ፤ አምላክ አይዘበትበትም። አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል፤ ምክንያቱም ለሥጋው ብሎ የሚዘራ ከሥጋው መበስበስን ያጭዳል።” (ገላ. 6:7, 8) በእርግጥም ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች ከሚያበረታታ ማንኛውም መዝናኛ መራቃችን በጣም አስፈላጊ ነው!—መዝ. 97:10

15. ይሖዋ ምን አስደሳች ስጦታ አዘጋጅቶልናል?

15 ብዙ የይሖዋ አገልጋዮች JW ብሮድካስቲንግ የተባለውን የኢንተርኔት የቴሌቪዥን ጣቢያችንን መመልከት ያስደስታቸዋል። * ሜርሊን የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “JW ብሮድካስቲንግ ይበልጥ አዎንታዊ እንድሆን ረድቶኛል፤ ፕሮግራሞቹን ስከታተል መጥፎ ነገር እንዳልመለከት ጥንቃቄ ማድረግ አያስፈልገኝም። ብቸኝነት ወይም የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሲሰማኝ፣ የሚያበረታታ ንግግር ወይም የማለዳ አምልኮ ፕሮግራም እመለከታለሁ። ይህም ወደ ይሖዋ እና ወደ ድርጅቱ ይበልጥ እንደቀረብኩ እንዲሰማኝ ያደርገኛል። የJW ብሮድካስቲንግ ዝግጅት በሕይወቴ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል።” አንተስ ይሖዋ ካዘጋጀው ከዚህ ስጦታ እየተጠቀምክ ነው? JW ብሮድካስቲንግ ላይ በየወሩ ከሚወጣው አዲስ ፕሮግራም በተጨማሪ ቀደም ሲል የወጡ በርካታ የኦዲዮና የቪዲዮ ፕሮግራሞችን እንዲሁም የሚያነቃቁ መዝሙሮችን በመምረጫው አማካኝነት ማግኘት ይቻላል።

16-17. በመዝናኛ ከምናሳልፈው ጊዜ ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ ማድረግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

16 ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ ሊያሳስበን የሚገባው የመዝናኛው ዓይነት ብቻ ሳይሆን በመዝናናት የምናሳልፈው ጊዜም ጭምር ነው። ጥንቃቄ ካላደረግን ይሖዋን ለማገልገል ከምናሳልፈው የበለጠ ጊዜ በመዝናኛ ልናሳልፍ እንችላለን። ብዙዎች በመዝናኛ የሚያሳልፉትን ጊዜ መቆጣጠር ተፈታታኝ ሆኖባቸዋል። አቢጋኤል የተባለች የ18 ዓመት ወጣት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ቀኑን በተለያዩ ነገሮች ተወጥሬ ካሳለፍኩ በኋላ ቴሌቪዥን መመልከት ትንሽ ዘና ለማለት ይረዳኛል። ካልተጠነቀቅኩ ግን እዚያው ቴሌቪዥኑ ላይ ተተክዬ ሰዓታት ሊያልፉ ይችላሉ።” ሳሙኤል የተባለ ወጣት ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “አጫጭር ቪዲዮዎችን ለማየት ኢንተርኔት ላይ እገባና ሳላስበው ብዙ ቪዲዮዎችን እመለከታለሁ። አንድ ቪዲዮ በማየት እጀምራለሁ፤ ከዚያም ሳላውቀው ሦስት ወይም አራት ሰዓት ያልፋል።”

17 በመዝናኛ የምታሳልፈውን ጊዜ መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው? የመጀመሪያው እርምጃ በመዝናኛ ምን ያህል ጊዜ እያሳለፍክ እንዳለህ ማወቅ ነው። በአንድ ሳምንት ውስጥ በመዝናኛ የምታሳልፈውን ጊዜ ለምን አትመዘግብም? ቴሌቪዥን በመመልከት፣ ኢንተርኔት በማሰስ እና በሞባይልህ ጌም በመጫወት የምታሳልፈውን ጊዜ ጻፍ። በመዝናኛ ከመጠን ያለፈ ጊዜ እያሳለፍክ እንዳለህ ከተሰማህ ፕሮግራም ለማውጣት ሞክር። ፕሮግራም ስታወጣ በመጀመሪያ፣ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች ቅድሚያ ስጥ፤ ከዚያ የተረፈውን ጊዜ ለመዝናኛ ልትጠቀምበት ትችላለህ። በመቀጠልም ፕሮግራምህን በጥብቅ ለመከተል እንዲረዳህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። እንዲህ ካደረግህ ለግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ለቤተሰብ አምልኮ፣ ለጉባኤ ስብሰባዎች እንዲሁም በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ በመካፈል ይሖዋን ለማገልገል የሚሆን ጊዜና ጉልበት ይኖርሃል። በተጨማሪም በመዝናኛ በምታሳልፈው ጊዜ ረገድ የጥፋተኝነት ስሜት አይሰማህም።

ምንጊዜም ይሖዋን ብቻ አምልኩ

18-19. የምናመልከው ይሖዋን ብቻ እንደሆነ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

18 ሐዋርያው ጴጥሮስ በደብዳቤው ላይ ስለ ሰይጣን ዓለም ጥፋትና ስለ መጪው አዲስ ዓለም ከገለጸ በኋላ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እነዚህን ነገሮች እየተጠባበቃችሁ ስለሆነ በመጨረሻ በእሱ ፊት ቆሻሻና እድፍ ሳይኖርባችሁ በሰላም እንድትገኙ የተቻላችሁን ጥረት አድርጉ” ብሏል። (2 ጴጥ. 3:14) ይህን ምክር በመከተል ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ የምናደርግ ከሆነ ይሖዋን ብቻ እንደምናመልክ እናሳያለን።

19 ሰይጣንና የእሱ ሥርዓት፣ ቅድሚያ መስጠት ላለብን ነገሮች ቅድሚያ እንዳንሰጥ እኛን መፈተናቸውን ይቀጥላሉ። (ሉቃስ 4:13) ሆኖም የሚያጋጥመን ተፈታታኝ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ በልባችን ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን ቦታ ለማንኛውም አካል ወይም ነገር አንሰጥም። ለይሖዋ ብቻ የሚገባውን ነገር ለእሱ ለመስጠት ይኸውም እሱን ብቻ ለማምለክ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል!

መዝሙር 30 አባቴ፣ አምላኬና ወዳጄ

^ አን.5 ይሖዋን ማምለክ ያስደስተናል። ይሁን እንጂ እያመለክን ያለነው እሱን ብቻ ነው? በሕይወታችን ውስጥ የምናደርጋቸው ውሳኔዎች የዚህን ጥያቄ መልስ ይጠቁማሉ። የምናመልከው ይሖዋን ብቻ መሆን አለመሆኑን ማወቅ እንድንችል እስቲ ጉዳዩን ከሁለት አቅጣጫዎች አንጻር እንመርምር።

^ አን.15 በአንዳንድ አካባቢዎች JW ብሮድካስቲንግ በሳተላይትም ይተላለፋል።

^ አን.54 የሥዕሎቹ መግለጫ፦ ንጽሕናው ባልተጠበቀ ኩሽና ውስጥ የተዘጋጀ ምግብ መብላት እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ታዲያ በዓመፅ፣ በመናፍስታዊ ድርጊቶች ወይም በሥነ ምግባር ብልግና የተበከለ መዝናኛ ማየት ይኖርብናል?