በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወንድም ራዘርፎርድ በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ በተካሄደው ትልቅ ስብሰባ ላይ ንግግር ሲያቀርብ፣ 1919

1919—የዛሬ መቶ ዓመት

1919—የዛሬ መቶ ዓመት

ከአራት ዓመት በላይ የቆየው ታላቁ ጦርነት (ከጊዜ በኋላ አንደኛው የዓለም ጦርነት ተብሏል) በ1919 አብቅቶ ነበር። ቀደም ባለው ዓመት መገባደጃ አካባቢ፣ መንግሥታት መዋጋታቸውን ያቆሙ ሲሆን ጥር 18, 1919 ደግሞ የፓሪስ የሰላም ስብሰባ ተጀመረ። ይህ ስብሰባ ካሳካቸው ጉዳዮች አንዱ የቬርሳይ ስምምነት ነው፤ የቬርሳይ ስምምነት የኅብረ ብሔሩ ጦር ከጀርመን ጋር ያካሂድ የነበረው ጦርነት በይፋ እንዲያበቃ ያደረገ ውል ነው። ስምምነቱ የተፈረመው ሰኔ 28, 1919 ነው።

ይህ ስምምነት፣ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የተባለ አዲስ ድርጅት እንዲቋቋምም አድርጓል። የድርጅቱ ዓላማ “ዓለም አቀፍ ትብብርን ማበረታታትና በዓለም ዙሪያ ሰላምና ደህንነት እንዲኖር ማድረግ” ነበር። በርካታ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ለዚህ ድርጅት ድጋፍ ሰጡ። የአሜሪካ የክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት ፌዴራላዊ ጉባኤ፣ የቃል ኪዳኑ ማኅበር “የአምላክን መንግሥት በምድር ላይ የሚወክል ፖለቲካዊ ምልክት” እንደሆነ በመግለጽ ይህን ድርጅት አወድሶት ነበር። ይህ ጉባኤ፣ ወደ ፓሪሱ የሰላም ስብሰባ ልዑካኑን በመላክ ለቃል ኪዳኑ ማኅበር ድጋፉን ገልጿል። ከእነዚህ ልዑካን አንዱ፣ ስብሰባው “በዓለም ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል” በማለት ተናግሯል።

በእርግጥም አዲስ ምዕራፍ ጀምሮ ነበር፤ ይሁንና ይህ እንዲሆን ያደረጉት በዚያ የሰላም ስብሰባ ላይ የተካፈሉት ሰዎች አይደሉም። በ1919 ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ፤ በዚህ ዓመት ይሖዋ፣ የስብከቱን ሥራ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሕዝቦቹን አበረታቷቸዋል። በመጀመሪያ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ትልቅ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋቸው ነበር።

ከባድ ውሳኔ

ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ

የዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ዳይሬክተሮች ዓመታዊ ምርጫ ሊካሄድ የታቀደው ቅዳሜ፣ ጥር 4, 1919 ነበር። በወቅቱ የይሖዋን ሕዝቦች ግንባር ቀደም ሆኖ ይመራ የነበረው ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድና ሌሎች ሰባት ወንድሞች ፍትሕ የጎደለው ፍርድ ተፈርዶባቸው አትላንታ፣ ጆርጂያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ታስረው ነበር። በመሆኑም ‘ከታሰሩት ወንድሞች መካከል የሥራ አመራር አባላት የሆኑት እንደገና ይመረጡ? ወይስ በሌሎች ይተኩ?’ የሚለው ጥያቄ መልስ ያሻው ነበር።

ኢቫንደር ጆኤል ካዋርድ

በእስር ላይ የነበረው ወንድም ራዘርፎርድ የድርጅቱ የወደፊት ሁኔታ አሳስቦት ነበር። አንዳንድ ወንድሞች፣ ሌላ ሰው ፕሬዚዳንት ሆኖ ቢመረጥ ይሻላል የሚል ስሜት እንዳላቸው ያውቅ ነበር። በዚህ የተነሳ ለተሰብሳቢዎቹ ደብዳቤ በመጻፍ፣ ኢቫንደር ጆኤል ካዋርድ ፕሬዚዳንት እንዲሆን የድጋፍ ሐሳብ አቅርቦ ነበር። ራዘርፎርድ፣ ስለ ወንድም ካዋርድ ሲጽፍ “ረጋ ያለ፣” “አስተዋይ” እና “ለጌታ ታማኝ” ሰው መሆኑን ገልጿል። ይሁን እንጂ ብዙ ወንድሞች ምርጫው ከስድስት ወር በኋላ ቢካሄድ የተሻለ እንደሆነ ተሰማቸው። ለታሰሩት ወንድሞች የሚከራከሩት ጠበቆችም በዚህ ሐሳብ ተስማሙ። ውይይቱ እየቀጠለ ሲሄድ አንዳንድ ወንድሞች መበሳጨት ጀመሩ።

ሪቻርድ ሃርቪ ባርበር

በዚህ ጊዜ ግን በመካከላቸው የነገሠውን ውጥረት የሚያረግብ ሁኔታ እንደተፈጠረ ወንድም ሪቻርድ ሃርቪ ባርበር ከጊዜ በኋላ ተናግሯል። ስብሰባው ላይ ከነበሩት ወንድሞች አንዱ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “የሕግ ባለሙያ አይደለሁም፤ ሆኖም የታማኝነትን ሕግ አውቃለሁ። አምላክ ታማኝ እንድንሆን ይጠብቅብናል። ምርጫ በማካሄድ ወንድም ራዘርፎርድን እንደገና ፕሬዚዳንት አድርጎ ከመምረጥ የተሻለ፣ ታማኝ መሆናችንን ማሳየት የምንችልበት መንገድ ያለ አይመስለኝም።”—መዝ. 18:25

አሌክሳንደር ሂዩ ማክሚላን

ከታሰሩት ወንድሞች አንዱ የሆነው አሌክሳንደር ሂዩ ማክሚላን ሁኔታውን ያስታውሳል፤ በቀጣዩ ቀን ወንድም ራዘርፎርድ፣ ማክሚላን የታሰረበትን ክፍል ግድግዳ ካንኳኳ በኋላ “እጅህን ወደ ውጭ ስደድ” አለው። ከዚያም ወንድም ራዘርፎርድ የቴሌግራም መልእክት ሰጠው። ማክሚላን በአጭሩ የተጻፈውን መልእክት ሲያይ ሐሳቡ ወዲያው ገባው። መልእክቱ እንዲህ ይላል፦ “ራዘርፎርድ ዋይዝ ቫን ባርበር አንደርሰን ቡሊ እና ስፒል ፕሬዚዳንት የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ የሥራ አመራር አባላት ሁላችሁንም እንወዳችኋለን።” ይህም፣ ሁሉም ዳይሬክተሮች በድጋሚ እንደተመረጡ እንዲሁም ጆሴፍ ራዘርፎርድ እና ዊልያም ቫን አምበርግ የሥራ አመራር አባላት እንዲሆኑ እንደገና መመረጣቸውን የሚጠቁም ነበር። በመሆኑም ወንድም ራዘርፎርድ ፕሬዚዳንት ሆኖ ማገልገሉን ቀጠለ።

ከእስር ተፈቱ!

ታማኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ እስር ላይ ያሉትን ስምንት ወንድሞች ለማስፈታት የሚያስችል ፊርማ ማሰባሰብ ጀመሩ። እነዚህ ደፋር ወንድሞችና እህቶች ከ700,000 በላይ ፊርማዎችን ማሰባሰብ ችለዋል። ሆኖም ፊርማዎቹን ለመንግሥት ከማቅረባቸው በፊት ረቡዕ፣ መጋቢት 26, 1919 ወንድም ራዘርፎርድም ሆነ ኃላፊነት ያላቸው ሌሎቹ ወንድሞች ከእስር ተፈቱ።

ወንድም ራዘርፎርድ ወደ ቤት ሲመለስ ለተቀበሉት ወንድሞች ባቀረበው ንግግር ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ሁላችንም ያጋጠመን ሁኔታ ከዚህ በኋላ ለሚጠብቀን ከባድ ጊዜ የሚያዘጋጀን እንደሆነ አምናለሁ። . . . የታገላችሁት ወንድሞቻችሁን ከእስር ለማስፈታት ብቻ አይደለም። ዋናው ዓላማ ይህ አይደለም። . . . ስትታገሉ የነበረው ስለ እውነት ለመመሥከር ነው፤ ደግሞም በዚህ ሥራ የተሳተፉ ሁሉ አስደናቂ በረከት አግኝተዋል።”

ከወንድሞቻችን የፍርድ ሂደት ጋር የተያያዙት ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት ጉዳዩ የይሖዋ እጅ ያለበት ይመስላል። ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ግንቦት 14, 1919 የሚከተለውን ውሳኔ አስተላለፈ፦ “ተከሳሾቹ . . . ከአድልዎ ነፃ የሆነ ፍርድ የማግኘት መብታቸው አልተከበረላቸውም፤ በዚህም ምክንያት፣ የተላለፈባቸው ብያኔ ተሽሯል።” ወንድሞች የተከሰሱት በከባድ ወንጀል ነበር፤ በመሆኑም የተለቀቁት ምሕረት ተደርጎላቸው ወይም ቅጣታቸው እንዲቀንስ ተደርጎ ብቻ ቢሆን ኖሮ የወንጀል ሪከርድ ይኖራቸው ነበር። ከዚያ በኋላም ሌላ ክስ ስላልተመሠረተባቸው ጀጅ ራዘርፎርድ በዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፊት ለይሖዋ ሕዝቦች ጥብቅና ለመቆም የሚያስችለውን ሕጋዊ ብቃት አላጣም፤ ደግሞም ከእስር ከተፈታ በኋላ በተደጋጋሚ ጊዜያት ይህን አድርጓል።

ለስብከቱ ሥራ ቆርጠው ተነሱ

ወንድም ማክሚላን እንዲህ ብሏል፦ “ጌታ ወደ ሰማይ እስኪወስደን ድረስ እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ አልፈለግንም። የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማወቅ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብን ተሰምቶን ነበር።”

ሆኖም በዋናው መሥሪያ ቤት ያሉት ወንድሞች ለዓመታት ሲያከናውኑት የነበረውን ሥራ መቀጠል አልቻሉም። ለምን? ምክንያቱም ጽሑፎችን ለማተም የሚጠቀሙባቸው ፕሌቶች በሙሉ ወንድሞች ታስረው በነበረበት ወቅት ተበላሽተው ነበር። ይህም ተስፋ አስቆረጣቸው፤ እንዲያውም አንዳንድ ወንድሞች የስብከቱ ሥራ እንዳበቃ ተሰማቸው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የሚሰብኩትን የመንግሥቱን መልእክት መስማት የሚፈልግ ሰው ይኖር ይሆን? ለዚህ ጥያቄ መልስ ማግኘት እንዲቻል ወንድም ራዘርፎርድ ንግግር ለመስጠት ወሰነ። ከዚያም ንግግሩን እንዲያዳምጡ ሰዎችን ለመጋበዝ አሰቡ። ወንድም ማክሚላን፣ “ንግግሩን ለመስማት ማንም ሰው ካልመጣ ሥራችንን ጨርሰናል ማለት ነው” ብሎ ነበር።

ወንድም ራዘርፎርድ “ለተጨነቀው የሰው ዘር ተስፋ” በሚል ርዕስ በሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ ያቀረበውን ንግግር የሚያስተዋውቅ ጋዜጣ፣ 1919

በመሆኑም ወንድም ራዘርፎርድ በጠና ታሞ የነበረ ቢሆንም እሁድ፣ ግንቦት 4, 1919 “ለተጨነቀው የሰው ዘር ተስፋ” የሚለውን ንግግር በሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ አቀረበ። ንግግሩን ለማዳመጥ 3,500 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የተገኙ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ቦታው ስለጠበበ እንዲመለሱ ተደርጓል። በቀጣዩ ቀን ደግሞ ሌሎች 1,500 ሰዎች ንግግሩን አዳመጡ። በዚህ መንገድ ወንድሞች ለጥያቄያቸው መልስ አገኙ፤ በእርግጥም መልእክቱን መስማት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ!

ወንድሞች ከዚያ በኋላ ያደረጉት ነገር፣ የይሖዋ ምሥክሮች እስከ ዛሬም ድረስ ምሥራቹን ለሚሰብኩበት መንገድ መሠረት ጥሏል።

ለተጨማሪ እድገት መዘጋጀት

የነሐሴ 1, 1919 መጠበቂያ ግንብ በመስከረም መጀመሪያ ላይ በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ ትልቅ ስብሰባ እንደሚካሄድ ገልጾ ነበር። በሚዙሪ የሚኖር ክላረንስ ቢቲ የተባለ ወጣት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ “ሁሉም ሰው በስብሰባው ላይ መገኘት እንዳለበት ተሰምቶት ነበር” ብሏል። በዚህ ስብሰባ ላይ ከ6,000 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች ተገኝተዋል፤ ይህም ከተጠበቀው በእጅጉ የላቀ ቁጥር ነበር። በአቅራቢያው ባለው በኢሪ ሐይቅ ከ200 የሚበልጡ ሰዎች መጠመቃቸው ደግሞ ደስታቸው እጥፍ ድርብ እንዲሆን አድርጓል።

ጥቅምት 1, 1919 የወጣው የመጀመሪያው የወርቃማው ዘመን እትም ሽፋን

ስብሰባው በተጀመረ በአምስተኛው ቀን ማለትም መስከረም 5, 1919 ወንድም ራዘርፎርድ ባቀረበው “ለረዳት ሠራተኞች የቀረበ ጥሪ” በሚለው ንግግር ላይ ወርቃማው ዘመን * የተባለ አዲስ መጽሔት መውጣቱን አበሰረ። ይህ መጽሔት “ጉልህ ቦታ የሚሰጣቸው ወቅታዊ ዜናዎችን ይዞ የሚወጣ ሲሆን እነዚህ ታላላቅ ክንውኖች እየተፈጸሙ ያሉበትን ምክንያት ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያብራራል።”

ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በዚህ አዲስ ጽሑፍ ተጠቅመው በድፍረት እንዲሰብኩ ተበረታተዋል። ሥራው እንዴት እንደሚደራጅ የሚገልጽ አንድ ደብዳቤ እንዲህ ይል ነበር፦ “እያንዳንዱ የተጠመቀ ክርስቲያን፣ ማገልገል ትልቅ መብት መሆኑን ማስታወስ እንዲሁም አሁኑኑ አጋጣሚውን በመጠቀም፣ ለዓለም ሁሉ በሚሰጠው በዚህ ታላቅ ምሥክርነት የበኩሉን ድርሻ ማበርከት ይኖርበታል።” ብዙዎች ለቀረበው ጥሪ አስደናቂ ምላሽ ሰጡ! እስከ ታኅሣሥ ባለው ጊዜ ውስጥ ቀናተኛ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ከ50,000 የሚበልጡ ሰዎችን ለአዲሱ መጽሔት ኮንትራት ማስገባት ችለዋል።

በብሩክሊን ኒው ዮርክ የሚገኙ ወንድሞች ወርቃማው ዘመን የተባለውን ጽሑፍ በጫነ መኪና አጠገብ

በ1919 ማብቂያ ላይ የይሖዋ አገልጋዮች እንደገና ተደራጅተውና ተነቃቅተው ሥራቸውን ጀምረው ነበር። በተጨማሪም ከመጨረሻው ዘመን ጋር በተያያዘ የተነገሩ አንዳንድ ወሳኝ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። በሚልክያስ 3:1-4 ላይ የተነገረው የአምላክን ሕዝቦች የመመርመሩና የማንጻቱ ሥራ ተጠናቅቆ ነበር። የይሖዋ ሕዝቦች ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ መንፈሳዊ ምርኮ ነፃ ወጥተዋል፤ እንዲሁም ኢየሱስ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ ሾሟል። * (ራእይ 18:2, 4፤ ማቴ. 24:45) በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ይሖዋ እንዲያከናውኑ ለሚፈልገው ሥራ ዝግጁ ሆነው ነበር።

^ አን.22 ወርቃማው ዘመን በ1937 መጽናኛ የተባለ ሲሆን በ1946 ደግሞ ንቁ! ተብሏል።