በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 44

ልጆቻችሁ ሲያድጉ አምላክን ለማገልገል ይመርጡ ይሆን?

ልጆቻችሁ ሲያድጉ አምላክን ለማገልገል ይመርጡ ይሆን?

“ኢየሱስም በአካልና በጥበብ እያደገ እንዲሁም በአምላክና በሰው ፊት ይበልጥ ሞገስ እያገኘ ሄደ።”—ሉቃስ 2:52

መዝሙር 134 ልጆች ከአምላክ በአደራ የተሰጡ ናቸው

ማስተዋወቂያ *

1. አንድ ሰው ሊያደርገው የሚችለው ከሁሉ የተሻለ ውሳኔ ምንድን ነው?

አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች የሚያደርጉት ምርጫ በልጆቻቸው ላይ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል። ወላጆች መጥፎ ምርጫ ካደረጉ ልጆቻቸው ለችግር ሊዳረጉ ይችላሉ። ጥሩ ምርጫ ካደረጉ ግን ልጆቻቸው ደስተኛና አርኪ ሕይወት የሚኖሩበት ከሁሉ የተሻለ አጋጣሚ ያገኛሉ። እርግጥ ነው፣ ልጆችም ጥሩ ውሳኔዎች ማድረግ ይኖርባቸዋል። አንድ ሰው ሊያደርገው የሚችለው ከሁሉ የተሻለ ውሳኔ አፍቃሪ አባታችን የሆነውን ይሖዋን ማገልገል ነው።—መዝ. 73:28

2. ኢየሱስም ሆነ ወላጆቹ የትኞቹን ጥሩ ምርጫዎች አድርገዋል?

2 የኢየሱስ ወላጆች፣ ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲያገለግሉ ለመርዳት ቁርጥ ውሳኔ አድርገው ነበር፤ ያደረጓቸው ምርጫዎች በሕይወታቸው ውስጥ ዋነኛው ግባቸው ይህ እንደነበር ይጠቁማሉ። (ሉቃስ 2:40, 41, 52) ኢየሱስም ቢሆን በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ያለውን ድርሻ ለመወጣት የሚረዱትን ጥሩ ምርጫዎች አድርጓል። (ማቴ. 4:1-10) ኢየሱስ አድጎ ደግ፣ ታማኝና ደፋር ሰው ሆኗል፤ ፈሪሃ አምላክ ያለው ማንኛውም ወላጅ እንዲህ ያለ ልጅ ቢኖረው እንደሚኮራና እንደሚደሰት የታወቀ ነው።

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመረምራለን፦ ይሖዋ ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ የትኞቹን ጥሩ ምርጫዎች አድርጓል? ክርስቲያን ወላጆች፣ የኢየሱስ ሰብዓዊ ወላጆች ካደረጓቸው ምርጫዎች ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? ክርስቲያን ወጣቶችስ ኢየሱስ ካደረጋቸው ምርጫዎች ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

ከይሖዋ ተማሩ

4. ይሖዋ ከልጁ ጋር በተያያዘ የትኛውን ጥሩ ምርጫ አድርጓል?

4 ይሖዋ ለኢየሱስ በጣም ጥሩ ወላጆች መርጦለታል። (ማቴ. 1:18-23፤ ሉቃስ 1:26-38) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ማርያም ከልብ በመነጨ ስሜት የተናገረቻቸው ሐሳቦች ለይሖዋና ለቃሉ ያላትን ጥልቅ ፍቅር ያሳያሉ። (ሉቃስ 1:46-55) ዮሴፍም ቢሆን ለይሖዋ መመሪያ የሰጠው ምላሽ አምላክን እንደሚፈራና እሱን ማስደሰት እንደሚፈልግ ይጠቁማል።—ማቴ. 1:24

5-6. ይሖዋ ልጁ የትኞቹ ሁኔታዎች እንዲያጋጥሙት ፈቅዷል?

5 ይሖዋ ለኢየሱስ ሀብታም ወላጆችን እንዳልመረጠለት ልብ በሉ። ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ ያቀረቡት መሥዋዕት ድሆች እንደነበሩ ይጠቁማል። (ሉቃስ 2:24) ዮሴፍ በናዝሬት ከነበረው መኖሪያ ቤቱ አጠገብ የእንጨት ሥራ የሚሠራበት አነስተኛ ቦታ ሳይኖረው አይቀርም። ዮሴፍና ማርያም ቢያንስ ሰባት ልጆች የነበሯቸው ከመሆኑ አንጻር ቤተሰቡ በቁሳዊ ያን ያህል እንዳልነበረው መገመት ይቻላል።—ማቴ. 13:55, 56

6 ይሖዋ ኢየሱስን ከአንዳንድ አደጋዎች የጠበቀው ቢሆንም ምንም ዓይነት ችግር እንዳያጋጥመው አልተከላከለለትም። (ማቴ. 2:13-15) ለምሳሌ ያህል፣ ከኢየሱስ ዘመዶች መካከል አንዳንዶቹ በእሱ አያምኑም ነበር። የገዛ ቤተሰቦቹ መጀመሪያ ላይ የእሱን መሲሕነት አለመቀበላቸው ኢየሱስን ምን ያህል ኣሳዝኖት እንደሚሆን መገመት ይቻላል። (ማር. 3:21፤ ዮሐ. 7:5) በተጨማሪም ኢየሱስ የአሳዳጊ አባቱ የዮሴፍ ሞት ያስከተለበትን ሐዘን መቋቋም ሳያስፈልገው አልቀረም። ኢየሱስ የቤቱ የመጀመሪያ ልጅ እንደመሆኑ መጠን ከዮሴፍ ሞት በኋላ የአባቱን ሥራ ተረክቦ ሊሆን ይችላል። (ማር. 6:3) በዕድሜ ከፍ እያለ ሲሄድ ቤተሰቡን የመንከባከብ ኃላፊነቱን መወጣት ያለበት እንዴት እንደሆነ ተምሯል። የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገር ለማሟላት ጠንክሮ መሥራት ሳያስፈልገው አልቀረም። በመሆኑም ሙሉ ቀን በሥራ ሲደክሙ መዋል ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ ያውቃል።

ወላጆች፣ ልጆቻችሁን ከአምላክ ቃል ምክር ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ በማስተማር በሕይወት ውስጥ ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች አዘጋጇቸው (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት) *

7. (ሀ) ባለትዳሮች ልጅ ከማሳደግ ጋር በተያያዘ የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቃቸው አስፈላጊ ነው? (ለ) በምሳሌ 2:1-6 መሠረት ወላጆች ልጆቻቸውን ምን ሊያሠለጥኗቸው ይገባል?

7 ባለትዳሮች ከሆናችሁና ልጅ መውለድ የምትፈልጉ ከሆነ ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘ይሖዋ ውድ የሆነን ሕይወት በኃላፊነት ሊሰጠን የሚችል ትሑትና መንፈሳዊ አመለካከት ያለን ሰዎች ነን?’ (መዝ. 127:3, 4) ወላጆች ከሆናችሁ ደግሞ ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘ጠንክሮ የመሥራትን አስፈላጊነት ለልጆቼ እያስተማርኩ ነው?’ (መክ. 3:12, 13) ‘ልጆቼን በሰይጣን ዓለም ውስጥ ሊያጋጥማቸው ከሚችለው አካላዊና ሥነ ምግባራዊ አደጋ ለመጠበቅ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አደርጋለሁ?’ (ምሳሌ 22:3) ልጆቻችሁን ሊያጋጥሟቸው ከሚችሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሁሉ ልትከልሏቸው አትችሉም። ይህ የማይቻል ነገር ነው። ሆኖም ከአምላክ ቃል ምክር ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ በማስተማር በሕይወት ውስጥ ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች ቀስ በቀስ ልታዘጋጇቸው ትችላላችሁ። (ምሳሌ 2:1-6ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል፣ የቅርብ ዘመዳችሁ ይሖዋን ማገልገሉን ቢያቆም የአምላክን ቃል ተጠቅማችሁ ለይሖዋ ታማኝ የመሆንን አስፈላጊነት ለልጆቻችሁ አስተምሯቸው። (መዝ. 31:23) አሊያም ደግሞ የምትወዱትን ሰው በሞት ካጣችሁ ልጆቻችሁ የአምላክ ቃል ሐዘንን ለመቋቋምና ሰላም ለማግኘት የሚረዳው እንዴት እንደሆነ እንዲያስተውሉ እርዷቸው።—2 ቆሮ. 1:3, 4፤ 2 ጢሞ. 3:16

ከዮሴፍና ከማርያም ተማሩ

8. በዘዳግም 6:6, 7 መሠረት ዮሴፍና ማርያም ምን ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር?

8 የኢየሱስ ሰብዓዊ ወላጆች ኢየሱስን የአምላክን ሞገስ በሚያስገኝለት መንገድ አሳድገውታል፤ እንዲህ ለማድረግ የረዳቸው ይሖዋ ለወላጆች የሰጠውን መመሪያ መታዘዛቸው ነው። (ዘዳግም 6:6, 7ን አንብብ።) ዮሴፍና ማርያም ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው፤ ደግሞም ልጆቻቸው ለይሖዋ እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር እንዲያዳብሩ ለመርዳት ትልቅ ቦታ ይሰጡ ነበር።

9. ዮሴፍና ማርያም ምን ጥሩ ምርጫ አድርገዋል?

9 ዮሴፍና ማርያም በቤተሰብ ደረጃ ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ይዘው ለመቀጠል መርጠዋል። ቤተሰቡ በናዝሬት ባለው ምኩራብ በሚደረጉት ሳምንታዊ ስብሰባዎች ላይም ሆነ በኢየሩሳሌም በሚከበረው ዓመታዊ የፋሲካ በዓል ላይ ይገኝ እንደነበር ጥርጥር የለውም። (ሉቃስ 2:41፤ 4:16) ዮሴፍና ማርያም፣ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዙ አጋጣሚውን ለልጆቻቸው ስለ ይሖዋ ሕዝቦች ታሪክ ለማስተማር ሳይጠቀሙበት አልቀሩም፤ ምናልባትም በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ወደተጠቀሱት ቦታዎች ሲደርሱ በዚያ ስለተከናወኑት ነገሮች ነግረዋቸው ሊሆን ይችላል። የቤተሰባቸው ቁጥር እያደገ ሲሄድ ዮሴፍና ማርያም መንፈሳዊ ልማዳቸውን ይዘው መቀጠል ሊከብዳቸው እንደሚችል የታወቀ ነው። ሆኖም እንዲህ ማድረጋቸው ያስገኘላቸውን ጥቅም አስቡ! ለይሖዋ አምልኮ ቅድሚያ መስጠታቸው የቤተሰባቸው መንፈሳዊነት ተጠብቆ እንዲቀጥል ረድቷቸዋል።

10. ክርስቲያን ወላጆች ዮሴፍና ማርያም ከተዉት ምሳሌ ምን ሊማሩ ይችላሉ?

10 ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች ዮሴፍና ማርያም ከተዉት ምሳሌ ምን ይማራሉ? ከሁሉ በላይ በቃልም ሆነ በድርጊት ለይሖዋ ያላችሁን ጥልቅ ፍቅር ልጆቻችሁ እንዲያዩ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ትማራላችሁ። ለልጆቻችሁ ልትሰጡ የምትችሉት ትልቁ ስጦታ ይሖዋን እንዲወዱ መርዳት እንደሆነ አትርሱ። በተጨማሪም ልጆቻችሁ ጥሩ የጥናት፣ የጸሎት፣ የስብሰባና የአገልግሎት ልማድ ማዳበር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንዲገነዘቡ እርዷቸው፤ ይህ ለልጆቻችሁ ልታስተምሩ ከምትችሏቸው በጣም አስፈላጊ ትምህርቶች መካከል አንዱ ነው። (1 ጢሞ. 6:6) እርግጥ ነው፣ ለልጆቻችሁ የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች ማሟላት ይኖርባችኋል። (1 ጢሞ. 5:8) ሆኖም ከዚህ አሮጌ ሥርዓት በሕይወት ተርፈው አምላክ ወዳዘጋጀው አዲስ ዓለም እንዲገቡ የሚያስችላቸው ከይሖዋ ጋር ያላቸው የጠበቀ ዝምድና እንጂ ቁሳዊ ሀብት እንዳልሆነ አስታውሱ። *ሕዝ. 7:19፤ 1 ጢሞ. 4:8

ክርስቲያን ወላጆች፣ ለልጆቻቸው መንፈሳዊነት የሚጠቅሙ ጥሩ ምርጫዎችን ሲያደርጉ ማየት በጣም ያስደስታል! (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት) *

11. (ሀ) በ1 ጢሞቴዎስ 6:17-19 ላይ የሚገኘው ምክር ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ጥሩ ምርጫ እንዲያደርጉ የሚረዳቸው እንዴት ነው? (ለ) በቤተሰብ ደረጃ የትኞቹን ግቦች ልታወጡ ትችላላችሁ? እንዲህ ማድረጋችሁስ ምን በረከት ያስገኝላችኋል? (“ የትኞቹን ግቦች ልታወጡ ትችላላችሁ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

11 በርካታ ክርስቲያን ወላጆች ለልጆቻቸው መንፈሳዊነት የሚጠቅሙ ጥሩ ምርጫዎችን እያደረጉ እንዳሉ ማየት ምንኛ የሚያስደስት ነው! ከልጆቻቸው ጋር አዘውትረው በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ይካፈላሉ። በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም ምሥራቹን ይሰብካሉ። እንዲያውም አንዳንድ ቤተሰቦች እምብዛም ወዳልተሰበከባቸው አካባቢዎች ሄደው ያገለግላሉ። ሌሎች ደግሞ ቤቴልን ይጎበኛሉ ወይም በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ይካፈላሉ። ቤተሰቦች እንዲህ ባሉ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ወጪ ማውጣት እንደሚጠይቅባቸው የታወቀ ነው፤ አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎችም ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። ሆኖም እንዲህ በማድረጋቸው የሚያገኟቸው ጥቅሞች በመንፈሳዊ ባለጸጋ ያደርጓቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:17-19ን አንብብ።) እንዲህ ባሉ ቤተሰቦች ውስጥ የሚያድጉ ልጆች አብዛኛውን ጊዜ በልጅነታቸው ያዳበሯቸውን ጥሩ ልማዶች ይዘው የሚቀጥሉ ከመሆኑም ሌላ ወላጆቻቸው በዚህ መንገድ ስላሳደጓቸው ደስተኞች ናቸው! *ምሳሌ 10:22

ከኢየሱስ ተማሩ

12. ኢየሱስ ካደገ በኋላ ምን ማድረግ ያስፈልገው ነበር?

12 በሰማይ የሚኖረው የኢየሱስ አባት ሁሌም ጥሩ ምርጫዎችን ያደርጋል፤ የኢየሱስ ሰብዓዊ ወላጆችም ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎችን አድርገዋል። ኢየሱስ ካደገ በኋላ ግን የራሱን ምርጫዎች ማድረግ ነበረበት። (ገላ. 6:5) እኛ የመምረጥ ነፃነት እንዳለን ሁሉ እሱም የመምረጥ ነፃነት ነበረው። የራሱን ፍላጎት ለማስቀደም መምረጥ ይችል ነበር። እሱ ግን ከይሖዋ ጋር ያለውን ጥሩ ዝምድና ጠብቆ ለመኖር መርጧል። (ዮሐ. 8:29) በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

ወጣቶች፣ የወላጆቻችሁን መመሪያ ፈጽሞ ችላ አትበሉ (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት) *

13. ኢየሱስ ገና ልጅ ሳለ የትኞቹን ጥሩ ምርጫዎች አድርጓል?

13 ኢየሱስ ልጅ ሳለ ለወላጆቹ ለመገዛት መርጧል። ከእነሱ የተሻለ እውቀት እንዳለው በማሰብ የወላጆቹን መመሪያ ችላ አላለም። ከዚህ ይልቅ ‘እንደ ወትሮው ይገዛላቸው ነበር።’ (ሉቃስ 2:51) ኢየሱስ የቤቱ የመጀመሪያ ልጅ መሆኑ ያስከተለበትን ኃላፊነት በቁም ነገር ይመለከት እንደነበር ጥርጥር የለውም። በቁሳዊ ረገድ ለቤተሰቡ የተወሰነ ድጋፍ ለማድረግ ሲል የአሳዳጊ አባቱን ሙያ በትጋት ይማር ነበር።

14. ኢየሱስ የአምላክን ቃል በትጋት ያጠና እንደነበር እንዴት እናውቃለን?

14 ኢየሱስ፣ ተአምራዊ በሆነ መንገድ እንደተወለደና የአምላክ መልእክተኞች ስለ እሱ ምን እንደተናገሩ ከወላጆቹ ሳይሰማ አልቀረም። (ሉቃስ 2:8-19, 25-38) ሆኖም ከወላጆቹ በሰማው ነገር ብቻ ረክቶ አልተቀመጠም፤ ከዚህ ይልቅ ቅዱሳን መጻሕፍትን በግሉ ያጠና ነበር። ኢየሱስ የአምላክን ቃል በትጋት ያጠና እንደነበር እንዴት እናውቃለን? ምክንያቱም ኢየሱስ ገና ልጅ እያለ በኢየሩሳሌም የነበሩት አስተማሪዎች “በመረዳት ችሎታውና በመልሱ ተደንቀው” እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሉቃስ 2:46, 47) በተጨማሪም ኢየሱስ ገና የ12 ዓመት ልጅ እያለ የአምላክን ቃል በሚገባ በመመርመር ይሖዋ አባቱ እንደሆነ በእርግጠኝነት ማወቅ ችሎ ነበር።—ሉቃስ 2:42, 43, 49

15. ኢየሱስ የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም እንደመረጠ ያሳየው እንዴት ነው?

15 ኢየሱስ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ስለሚጫወተው ሚና ካወቀ በኋላ ይህን ኃላፊነት ለመቀበል መርጧል። (ዮሐ. 6:38) በብዙዎች ዘንድ እንደሚጠላ ማወቁ የተሰጠው ኃላፊነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እንዲያስብ ሳያደርገው አልቀረም። ያም ሆኖ ራሱን ለይሖዋ ለማስገዛት መርጧል። ኢየሱስ በ29 ዓ.ም. ሲጠመቅ በሕይወቱ ውስጥ ዋነኛው ትኩረቱ የይሖዋን ፈቃድ መፈጸም ነበር። (ዕብ. 10:5-7) በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ለመሞት እያጣጣረ በነበረበት ጊዜም እንኳ የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም ያለውን ቁርጠኝነት አላላላም።—ዮሐ. 19:30

16. ልጆች ከኢየሱስ የሚያገኙት አንዱ ትምህርት ምንድን ነው?

16 ወላጆቻችሁን ታዘዙ። ልክ እንደ ዮሴፍና ማርያም ሁሉ የእናንተም ወላጆች ፍጹማን አይደሉም። ሆኖም ይሖዋ ለወላጆቻችሁ እናንተን የመጠበቅ፣ የማሠልጠንና የመምራት ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። የእነሱን ምክር ከፍ አድርጋችሁ የምትመለከቱና ሥልጣናቸውን የምታከብሩ ከሆነ “መልካም” ይሆንላችኋል።—ኤፌ. 6:1-4

17. በኢያሱ 24:15 መሠረት ወጣቶች የትኛውን ምርጫ ማድረግ አለባቸው?

17 ማንን እንደምታገለግሉ ምረጡ። ይሖዋ ማን እንደሆነ፣ ዓላማው ምን እንደሆነና የእሱ ፈቃድ ከእናንተ ሕይወት ጋር የሚገናኘው እንዴት እንደሆነ ለራሳችሁ ማረጋገጥ አለባችሁ። (ሮም 12:2) እንዲህ ካደረጋችሁ በሕይወታችሁ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ውሳኔ ማድረግ ማለትም ይሖዋን ለማገልገል መምረጥ ትችላላችሁ። (ኢያሱ 24:15ን አንብብ፤ መክ. 12:1) መጽሐፍ ቅዱስን የምታነቡበትና የምታጠኑበት ቋሚ ፕሮግራም ካላችሁ ለይሖዋ ያላችሁ ፍቅር እያደገ ይሄዳል፤ እንዲሁም እምነታችሁ ይበልጥ ይጠናከራል።

18. ወጣቶች የትኛውን ምርጫ ሊያደርጉ ይገባል? ይህን ምርጫ ማድረጋቸውስ ምን ውጤት ያስገኛል?

18 በሕይወታችሁ ውስጥ የይሖዋን ፈቃድ ለማስቀደም ምረጡ። የሰይጣን ዓለም ተሰጥኦዋችሁን የራሳችሁን ፍላጎት ለማሟላት ከተጠቀማችሁበት ደስተኛ እንደምትሆኑ ሊያሳምናችሁ ይሞክራል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፣ ቁሳዊ ሀብት በማካበት ላይ ያተኮረ ሕይወት የሚመሩ ሰዎች “ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ” ይወጋሉ። (1 ጢሞ. 6:9, 10) በሌላ በኩል ይሖዋን የምትሰሙና የእሱን ፈቃድ ለማስቀደም የምትመርጡ ከሆነ ሕይወታችሁ ስኬታማ ይሆናል፤ እንዲሁም ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወን ትችላላችሁ።—ኢያሱ 1:8

ምን ምርጫ ታደርጉ ይሆን?

19. ወላጆች ምን ማስታወስ አለባቸው?

19 እናንተ ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲያገለግሉ ለመርዳት አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ አድርጉ። በይሖዋ ከታመናችሁ፣ እሱ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች እንድታደርጉ ይረዳችኋል። (ምሳሌ 3:5, 6) በልጆቻችሁ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ከምትናገሩት ነገር ይበልጥ የምታደርጉት ነገር እንደሆነ አስታውሱ። ስለዚህ ልጆቻችሁ የይሖዋን ሞገስ እንዲያገኙ የሚረዷቸውን ምርጫዎች አድርጉ።

20. ወጣቶች ይሖዋን ለማገልገል ከመረጡ ምን በረከት ያገኛሉ?

20 እናንተ ወጣቶች፣ ወላጆቻችሁ በሕይወታችሁ ውስጥ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ምርጫዎች እንድታደርጉ ሊረዷችሁ ይችላሉ። የአምላክን ሞገስ ማግኘት አለማግኘታችሁ የተመካው ግን በራሳችሁ ላይ ነው። እንግዲያው የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል በሰማይ የሚኖረውን አፍቃሪ አባታችሁን ለማገልገል ምረጡ። (1 ጢሞ. 4:16) እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ በዛሬው ጊዜ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የተሞላ አርኪና አስደሳች ሕይወት ይኖራችኋል፤ ወደፊት ደግሞ ከዚህ እጅግ የላቀ ደስታ ታገኛላችሁ!

መዝሙር 133 በወጣትነታችሁ ይሖዋን አምልኩ

^ አን.5 ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው አድገው ይሖዋን በደስታ እንዲያገለግሉ ይፈልጋሉ። ልጆቻቸው እዚህ ግብ ላይ እንዲደርሱ ከፈለጉ ወላጆች የትኞቹን ምርጫዎች ማድረግ ይኖርባቸዋል? ክርስቲያን ወጣቶችስ በሕይወታቸው ውስጥ እውነተኛ ስኬት ለማግኘት የትኞቹን ምርጫዎች ማድረግ አለባቸው? ይህ የጥናት ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

^ አን.11 በጥቅምት 2011 ንቁ! ገጽ 20 ላይ የወጣውን “ወላጆቼን በማንም አልለውጣቸውም” የሚለውን ሣጥንና በመጋቢት 8፣ 1999 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 25 ላይ የወጣውን “ለወላጆቻቸው የጻፉት ልዩ ደብዳቤ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.66 የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢየሱስ ገና ሕፃን ሳለ ማርያም በልቡ ውስጥ የይሖዋ ፍቅር እንዲቀረጽ ለማድረግ ጥረት እንዳደረገች ግልጽ ነው። በዛሬው ጊዜ ያሉ እናቶችም በልጆቻቸው ልብ ውስጥ የይሖዋ ፍቅር እንዲቀረጽ ማድረግ ይችላሉ።

^ አን.68 የሥዕሉ መግለጫ፦ ከሁኔታዎች መረዳት እንደምንችለው ዮሴፍ ከቤተሰቡ ጋር አዘውትሮ ወደ ምኩራብ ይሄድ ነበር። በዛሬው ጊዜ ያሉ አባቶችም ከቤተሰባቸው ጋር በጉባኤ ስብሰባ ላይ መገኘት ያስደስታቸዋል።

^ አን.70 የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢየሱስ ከአባቱ ጠቃሚ ሙያ ተምሯል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶችም ከአባታቸው የተለያዩ ሙያዎችን መማር ይችላሉ።