በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 42

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት አድርገው እንዲጠመቁ መርዳት—ክፍል ሁለት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት አድርገው እንዲጠመቁ መርዳት—ክፍል ሁለት

“ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ።”—1 ጢሞ. 4:16

መዝሙር 77 በጨለማ ዓለም ውስጥ ብርሃን ማብራት

ማስተዋወቂያ *

1. ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ሕይወት አድን እንደሆነ እንዴት እናውቃለን?

ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ሕይወት አድን ነው! ይህን እንዴት እናውቃለን? ኢየሱስ በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ የሚገኘውን ትእዛዝ ሲሰጥ ‘ሂዱና ሰዎችን እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ ብሎ ነበር። ጥምቀት ምን ያህል አስፈላጊ ነው? መዳን ለማግኘት የሚያስፈልግ ብቃት ነው። እጩ ተጠማቂው፣ የመዳን በር የተከፈተው ኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት በመሞቱና ከሞት በመነሳቱ መሆኑን ሊያምን ይገባል። ሐዋርያው ጴጥሮስ የእምነት አጋሮቹን “ጥምቀት በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት እናንተን እያዳናችሁ ነው” ያላቸው ለዚህ ነው። (1 ጴጥ. 3:21) በመሆኑም አንድ ሰው ሲጠመቅ መዳን የማግኘት አጋጣሚ ይከፈትለታል።

2. ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 4:1, 2 ከማስተማሩ ሥራ ጋር በተያያዘ ምን የሚሰጠን ሐሳብ አለ?

2 ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ‘የማስተማር ጥበብ’ ማዳበር ይኖርብናል። (2 ጢሞቴዎስ 4:1, 2ን አንብብ።) ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ ያዘዘን ‘ሂዱና ሰዎችን እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ በማለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስም በዚህ ሥራ ‘መጽናት’ እንደሚያስፈልግ ተናግሯል፤ ምክንያቱም ‘ይህን በማድረግ ራሳችንንም ሆነ የሚሰሙንን እናድናለን።’ ከዚህ አንጻር ጳውሎስ “ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ” ማለቱ የተገባ ነው። (1 ጢሞ. 4:16) ማስተማር ደቀ መዛሙርት ከማድረግ ጋር የተያያዘ ሥራ ስለሆነ ጥሩ አስተማሪዎች መሆን እንፈልጋለን።

3. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከመምራት ጋር በተያያዘ በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

3 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች እያስጠናን ነው። ሆኖም ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው እነዚህን ሰዎች ተጠምቀው የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ እንፈልጋለን። በዚህ ርዕስ ላይ፣ እያንዳንዱ አስተማሪ ጥናቱ እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ ለመርዳት ሊወስዳቸው የሚገቡ አምስት ተጨማሪ እርምጃዎችን እንመለከታለን።

አስተማሪው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሆን አድርጉ

አስተማሪው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ችሎታችሁን ለማሻሻል፣ ተሞክሮ ያላቸውን አስተማሪዎች ምክር ጠይቁ (ከአንቀጽ 4-6⁠ን ተመልከት) *

4. አንድ አስተማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲመራ ራሱን መግዛት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

4 ከአምላክ ቃል የምናስተምረውን ነገር እንወደዋለን። በመሆኑም ስለምንወደው ነገር ብዙ ለማውራት እንፈተን ይሆናል። ይሁንና በመጠበቂያ ግንብ ጥናት፣ በጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትም ሆነ በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት ጥናቱን የሚመራው ሰው ብዙ ማውራት የለበትም። አስተማሪው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሆን፣ ጥናቱን የሚመራው ክርስቲያን ራሱን መግዛት ይኖርበታል፤ ስለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ወይም ርዕሰ ጉዳይ የሚያውቀውን ነገር ሁሉ ላለማብራራት መጠንቀቅ አለበት። * (ዮሐ. 16:12) እኛ ራሳችን በተጠመቅንበት ወቅት የነበረንን እውቀት አሁን ካለን እውቀት ጋር ማወዳደር እንችላለን። በዚያ ወቅት የምናውቀው፣ መሠረታዊ የሆኑትን ትምህርቶች ብቻ ሊሆን ይችላል። (ዕብ. 6:1) ዛሬ ያለንን እውቀት ያካበትነው ለዓመታት ስንማር ከቆየን በኋላ ነው፤ እንግዲያው ለአዲሱ ተማሪያችን ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ለማሳወቅ መሞከር የለብንም።

5. (ሀ) በ1 ተሰሎንቄ 2:13 መሠረት ጥናታችን ምን እንዲገነዘብ እንፈልጋለን? (ለ) ጥናታችን ስለሚማረው ነገር የሚሰማውን እንዲገልጽ ማበረታታት የምንችለው እንዴት ነው?

5 ጥናታችን የሚማረው ነገር የመነጨው በመንፈስ መሪነት ከተጻፈው የአምላክ ቃል መሆኑን እንዲያውቅ እንፈልጋለን። (1 ተሰሎንቄ 2:13ን አንብብ።) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ተማሪው ስለሚማረው ነገር ምን እንደሚሰማው እንዲገልጽ አበረታታው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ሁልጊዜ አንተ ከማብራራት ይልቅ አንዳንዶቹን ጥቅሶች እሱ እንዲያብራራ ጠይቀው። ተማሪው የአምላክን ቃል በሕይወቱ ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችል እንዲያስተውል እርዳው። ጥናትህ ስላነበባቸው ጥቅሶች ያለውን አመለካከት እና ስሜት እንዲገልጽ ለማበረታታት የአመለካከት ጥያቄዎች አቅርብለት። (ሉቃስ 10:25-28) ለምሳሌ ያህል፣ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልትጠይቀው ትችላለህ፦ “ይህ ጥቅስ ስለ የትኛው የይሖዋ ባሕርይ አስተምሮሃል?” “ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መማርህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?” “አሁን ስለተማርከው ነገር ምን ይሰማሃል?” (ምሳሌ 20:5) ቁም ነገሩ፣ ተማሪው ብዙ ነገር ማወቁ ሳይሆን የተማረውን ነገር መውደዱና ተግባራዊ ማድረጉ ነው።

6. ጥናት ስንመራ ተሞክሮ ያካበቱ አስፋፊዎችን መጋበዝ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

6 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትመራ ተሞክሮ ያካበቱ አስፋፊዎችን በጥናቱ ላይ እንዲገኙ ትጋብዛለህ? ከሆነ ጥናቱን የምትመራበትን መንገድ በተመለከተ ሐሳብ እንዲሰጡህ ልትጠይቃቸው ትችላለህ፤ እንዲሁም አስተማሪው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልግህ እንደሆነ ጠይቃቸው። የማስተማር ችሎታህን ማሻሻል የምትፈልግ ከሆነ ትሑት መሆን ይኖርብሃል። (ከሐዋርያት ሥራ 18:24-26 ጋር አወዳድር።) ከጥናቱ በኋላ፣ ተሞክሮ ያካበተውን አስፋፊ ‘ተማሪው የሚማረው ነገር እየገባው ይመስልሃል?’ ብለህ ጠይቀው። ለአንድ ሳምንት ወይም ከዚያ በላይ የማትኖር ከሆነ ደግሞ ይሄው አስፋፊ ጥናቱን እንዲመራልህ ልትጠይቀው ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ ጥናቱ እንዳይቋረጥ ያደርጋል፤ ተማሪውም የጥናቱን አስፈላጊነት እንዲገነዘብ ያስችላል። ጥናቱ “የአንተ” ስለሆነ ሌላ ሰው ሊመራው እንደማይችል ፈጽሞ ሊሰማህ አይገባም። ደግሞም ለጥናትህ ከሁሉ የተሻለውን ነገር ማድረግ ትፈልጋለህ፤ ዋነኛው ዓላማህ ጥናትህ በቀጣይነት እውነትን እንዲማር መርዳት ነው።

ትምህርቱን እንደምትወዱትና እንደምታምኑበት በሚያሳይ መንገድ አስተምሩ

የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉበትን መንገድ ለጥናቶቻችሁ ለማስረዳት የሌሎችን ተሞክሮ አካፍሏቸው (ከአንቀጽ 7-9⁠ን ተመልከት) *

7. ተማሪው የሚማረውን ነገር ይበልጥ እንዲወደው ምን ሊረዳው ይችላል?

7 ጥናትህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች እንደምትወዳቸውና እንደምታምንባቸው መመልከቱ ይጠቅመዋል። (1 ተሰ. 1:5) ይህ እሱም የሚማረውን ነገር ይበልጥ እንዲወደው ሊረዳው ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ ማድረግ በሕይወትህ ውስጥ እንዴት እንደጠቀመህ ልትነግረው ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጠቃሚ ምክር እሱንም እንደሚረዳው እንዲገነዘብ ያስችለዋል።

8. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህን ለመርዳት ሌላስ ምን ማድረግ ትችላለህ? ይህን ማድረግ አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

8 መጽሐፍ ቅዱስን በምታጠኑበት ወቅት፣ ለጥናትህ እንደ እሱ ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጠሟቸውና እነዚህን ሁኔታዎች መቋቋም የቻሉ ሰዎችን ተሞክሮ ንገረው። በጉባኤህ ውስጥ ጥናትህን የሚጠቅም ተሞክሮ ያለው አስፋፊ ካለ በጥናቱ ላይ እንዲገኝ ጋብዘው። አሊያም ደግሞ jw.org ላይ “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል * በሚለው ዓምድ ሥር የሚወጡ የሚያበረታቱ ተሞክሮዎችን ልታሳየው ትችላለህ። እንዲህ ያሉት ርዕሶች እና ቪዲዮዎች፣ ተማሪው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ ማድረጉ የጥበብ እርምጃ መሆኑን እንዲያስተውል ይረዱታል።

9. ጥናትህ የተማረውን ነገር ለቤተሰቦቹና ለጓደኞቹ እንዲናገር ማበረታታት የምትችለው እንዴት ነው?

9 ጥናትህ ባለትዳር ከሆነ የትዳር ጓደኛውም እያጠናች ነው? ካልሆነ ባለቤቱን በጥናቱ ላይ እንድትገኝ ጋብዛት። ጥናትህ የተማረውን ነገር ለቤተሰቦቹና ለጓደኞቹ እንዲናገር አበረታታው። (ዮሐ. 1:40-45) ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ጥናትህን “ይህን እውነት ለቤተሰብህ አባላት ማስረዳት የምትችለው እንዴት ነው?” ወይም “ይህን ትምህርት ለጓደኛህ ለማስረዳት የትኛውን ጥቅስ ትጠቀማለህ?” ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ። በዚህ መንገድ ጥናትህ አስተማሪ እንዲሆን ታሠለጥነዋለህ። ከዚያም ብቃቱን ሲያሟላ ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኖ በአገልግሎት መካፈል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የሚፈልግ ሰው ያውቅ እንደሆነ ጥናትህን ልትጠይቀው ትችላለህ። የሚያውቀው ሰው ካለ፣ ግለሰቡን ወዲያውኑ አግኝተህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር ጋብዘው። መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናው እንዴት ነው? * የሚለውን ቪዲዮ አሳየው።

ጥናታችሁ በጉባኤው ውስጥ ወዳጆች እንዲያፈራ አበረታቱት

በጉባኤው ውስጥ ወዳጆች እንዲያፈሩ ጥናቶቻችሁን አበረታቷቸው (ከአንቀጽ 10-11⁠ን ተመልከት) *

10. አስተማሪዎች በ1 ተሰሎንቄ 2:7, 8 ላይ የተገለጸውን የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

10 አስተማሪዎች ለጥናቶቻቸው ልባዊ አሳቢነት ሊያሳዩአቸው ይገባል። ጥናቶችህን የወደፊት መንፈሳዊ ወንድሞችህ ወይም እህቶችህ እንደሆኑ አድርገህ ተመልከታቸው። (1 ተሰሎንቄ 2:7, 8ን አንብብ።) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በዓለም ያሉ ወዳጆቻቸውን መተውና ይሖዋን ለማገልገል አስፈላጊ የሆኑትን ለውጦች ማድረግ ቀላል እንደማይሆንላቸው የታወቀ ነው። በጉባኤ ውስጥ እውነተኛ ወዳጆች እንዲያገኙ ልንረዳቸው ይገባል። በምታጠኑበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ወቅቶችም ከጥናትህ ጋር አብረኸው ጊዜ በማሳለፍ ጓደኛ ልትሆነው ትችላለህ። ስልክ በመደወል፣ አጭር መልእክት በመላክ ወይም ለማጥናት ከመገናኘታችሁ በፊት ጎራ ብለህ በመጠየቅ ጥናትህን ከልብ እንደምታስብለት አሳየው።

11. ጥናቶቻችን በጉባኤው ውስጥ ምን እንዲያገኙ እንፈልጋለን? ለምንስ?

11 “ልጅን የሚያሳድገው መንደሩ በሙሉ ነው” የሚል አባባል አለ። በእኛ ሁኔታ ደግሞ “አንድን ሰው ደቀ መዝሙር የሚያደርገው መላው ጉባኤ ነው” ሊባል ይችላል። ውጤታማ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች፣ ጥናቶቻቸው ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኗቸው የጉባኤው አስፋፊዎች ጋር እንዲቀራረቡ የሚያደርጉት ለዚህ ነው። ይህም ተማሪዎቹ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር መሆን እንዲያስደስታቸው ያደርጋል፤ እነዚህ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ እርዳታ ሊሰጧቸው እንዲሁም ችግር ሲያጋጥማቸው ሊያበረታቷቸው ይችላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን በሙሉ በጉባኤው ውስጥ እንደሚፈለጉና የመንፈሳዊ ቤተሰባችን አካል እንደሆኑ እንዲሰማቸው እንፈልጋለን። እርስ በርሱ ወደሚዋደደው ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበራችን እንዲሳቡ እንፈልጋለን። ይህም ጥናቶቻችን፣ ይሖዋን እንዳይወዱ እንቅፋት ከሚሆኑባቸው ሰዎች ጋር ያላቸውን ቅርርብ ማቋረጥ ቀላል እንዲሆንላቸው ያደርጋል። (ምሳሌ 13:20) የቀድሞ ጓደኞቻቸው ቢያገልሏቸውም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ እውነተኛ ወዳጆች እንደሚያገኙ ያውቃሉ።—ማር. 10:29, 30፤ 1 ጴጥ. 4:4

ራስን የመወሰንንና የመጠመቅን አስፈላጊነት ጎላ አድርጋችሁ ግለጹ

ቅን ልብ ያላቸው ጥናቶች ደረጃ በደረጃ ለጥምቀት ብቁ ይሆናሉ! (ከአንቀጽ 12-13⁠ን ተመልከት)

12. ራስን ስለ መወሰንና ስለ መጠመቅ ከጥናታችን ጋር መነጋገር ያለብን ለምንድን ነው?

12 ራስን መወሰንና መጠመቅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ከጥናታችሁ ጋር በግልጽ ተነጋገሩ። ደግሞም ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናበት ዓላማ ተጠምቀው ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት ነው። ተማሪው ለጥቂት ወራት መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት ካጠና በተለይ ደግሞ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ከጀመረ በኋላ የጥናቱ ዓላማ ግልጽ ሊሆንለት ይገባል፤ መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናው የይሖዋ ምሥክር እንዲሆን ነው።

13. ተማሪው ለጥምቀት ብቁ ለመሆን የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ይኖርበታል?

13 ቅን ልብ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ለጥምቀት ብቁ ለመሆን ደረጃ በደረጃ ሊወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎች አሉ። በመጀመሪያ ተማሪው ይሖዋን ማወቅና መውደድ እንዲሁም በእሱ ላይ እምነት ማሳደር ይኖርበታል። (ዮሐ. 3:16፤ 17:3) ከዚያም ተማሪው ከይሖዋ እና በጉባኤው ውስጥ ካሉ ክርስቲያኖች ጋር ወዳጅነት ይመሠርታል። (ዕብ. 10:24, 25፤ ያዕ. 4:8) ውሎ አድሮም ተማሪው ከኃጢአቱ ንስሐ ገብቶ መጥፎ ልማዶቹን ያስወግዳል። (ሥራ 3:19) በተጨማሪም እምነቱ የተማረውን ነገር ለሌሎች እንዲናገር ያነሳሳዋል። (2 ቆሮ. 4:13) ከዚያም ራሱን ለይሖዋ ይወስናል፤ ይህን ውሳኔውን ለማሳየትም ይጠመቃል። (1 ጴጥ. 3:21፤ 4:2) ግለሰቡ ይህን እርምጃ የሚወስድበት ቀን ምንኛ አስደሳች ይሆናል! ተማሪው እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ የሚያስችለውን እያንዳንዱን እርምጃ ሲወስድ ከልብ አመስግነው፤ እንዲሁም እድገት ማድረጉን እንዲቀጥል አበረታታው።

የተማሪውን እድገት በየጊዜው ገምግሙ

14. አንድ አስተማሪ የተማሪውን እድገት መገምገም የሚችለው እንዴት ነው?

14 ተማሪው እድገት አድርጎ ራሱን እንዲወስንና እንዲጠመቅ በምንረዳበት ወቅት ታጋሽ መሆን ያስፈልገናል። ሆኖም ግለሰቡ ይሖዋ አምላክን የማገልገል ፍላጎት እንዳለው መገምገም የሚያስፈልገን ጊዜ አለ። ተማሪው የኢየሱስን ትእዛዛት ለመከተል እየሞከረ እንደሆነ የሚጠቁም ነገር አለ? ወይስ ፍላጎቱ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማግኘት ብቻ ነው?

15. አንድ ተማሪ እድገት እያደረገ መሆኑን የሚጠቁሙት ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

15 ተማሪው የሚያደርገውን እድገት በየጊዜው ገምግም። ለምሳሌ፣ ተማሪው ለይሖዋ ያለውን ፍቅር ይገልጻል? ወደ ይሖዋ ይጸልያል? (መዝ. 116:1, 2) መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ያስደስተዋል? (መዝ. 119:97) ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ ይገኛል? (መዝ. 22:22) በሕይወቱ ውስጥ አንዳንድ አስፈላጊ ማስተካከያዎችን እያደረገ ነው? (መዝ. 119:112) የሚማረውን ነገር ለቤተሰቡና ለጓደኞቹ መናገር ጀምሯል? (መዝ. 9:1) ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋ ምሥክር መሆን ይፈልጋል? (መዝ. 40:8) ተማሪው ከላይ ከተጠቀሱት ነገሮች መካከል በየትኛውም አቅጣጫ እድገት እያደረገ ካልሆነ ምክንያቱን በዘዴ ለማወቅ ጥረት አድርግ፤ ከዚያም ስለ ጉዳዩ በደግነት ሆኖም በግልጽ አነጋግረው። *

16. አንድን ሰው ማስጠናትህን ማቆም ይኖርብህ እንደሆነ ለመወሰን የሚረዳህ ነገር ምንድን ነው?

16 አንድን ሰው ማስጠናትህን ማቆም ይኖርብህ እንደሆነ በየጊዜው ገምግም። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ተማሪው ለጥናቱ አይዘጋጅም? ስብሰባዎች ላይ መገኘት አያስደስተውም? አንዳንድ መጥፎ ልማዶቹን አልተወም? አሁንም የሐሰት ሃይማኖት አባል ነው?’ መልስህ አዎ ከሆነ ግለሰቡን ማስጠናትህን መቀጠል፣ ውኃ እንዲነካው የማይፈልግን ሰው ዋና ለማስተማር እንደ መሞከር ነው! ተማሪው ለሚማረው ነገር አድናቆት ከሌለውና ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆነ ጥናቱን መቀጠልህ ምን ትርጉም አለው?

17. በ1 ጢሞቴዎስ 4:16 መሠረት ሁሉም አስተማሪዎች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

17 ደቀ መዛሙርት የማድረግ ኃላፊነታችንን ከፍ አድርገን እንመለከታለን፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት አድርገው እንዲጠመቁ መርዳት እንፈልጋለን። በመሆኑም አስተማሪው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሆን እናደርጋለን። እንዲሁም ትምህርቱን እንደምንወደውና እንደምናምንበት በሚያሳይ መንገድ እናስተምራለን። ተማሪው በጉባኤው ውስጥ ወዳጆች እንዲያፈራ እናበረታታዋለን። ራስን የመወሰንንና የመጠመቅን አስፈላጊነት ጎላ አድርገን እንገልጽለታለን፤ የተማሪውን እድገትም በየጊዜው እንገመግማለን። (“ አስተማሪዎች፣ ተማሪዎቻቸው ለጥምቀት እንዲበቁ ለመርዳት ሊወስዷቸው የሚገቡ እርምጃዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በዚህ ሕይወት አድን ሥራ በመካፈላችን ደስተኞች ነን! እንግዲያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት አድርገው እንዲጠመቁ ለመርዳት የምንችለውን ሁሉ እናድርግ።

መዝሙር 79 ጸንተው እንዲቆሙ አስተምሯቸው

^ አን.5 ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠና አስተሳሰባቸው፣ ስሜታቸውና ምግባራቸው ይሖዋ ከሚፈልገው ነገር ጋር እንዲስማማ የመርዳት መብት እናገኛለን። ይህ ርዕስ የማስተማር ችሎታችንን ማሻሻል የምንችልባቸውን ተጨማሪ መንገዶች ያብራራል።

^ አን.4 በመስከረም 2016 የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ ላይ የወጣውን “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ ማድረግ የሌሉብን ነገሮች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.8 ስለ እኛ > ተሞክሮዎች በሚለው ሥር ይገኛል።

^ አን.9 JW Library® ላይ ሚዲያ > ስብሰባዎቻችን እና አገልግሎታችን > ለአገልግሎት የምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች በሚለው ሥር ይገኛል።

^ አን.15 በመጋቢት 2020 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡትን “ለይሖዋ ያለህ ፍቅርና አድናቆት ለመጠመቅ ያነሳሳሃል” እና “ለመጠመቅ ዝግጁ ነህ?” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።

^ አን.77 የሥዕሉ መግለጫ፦ ጥናቱ ካለቀ በኋላ፣ ተሞክሮ ያላት እህት ጥናቱን ለምትመራው እህት ምክር እየሰጠቻት፤ በጥናቱ ወቅት ብዙ ላለማውራት እንድትጠነቀቅ ሐሳብ እየሰጠቻት ነው።

^ አን.79 የሥዕሉ መግለጫ፦ ተማሪዋ ጥሩ ሚስት መሆን ስለምትችልበት መንገድ እያጠናች። የተማረችውን ነገር በኋላ ላይ ለባሏ ስትነግረው።

^ አን.81 የሥዕሉ መግለጫ፦ ተማሪዋና ባለቤቷ በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በተዋወቀቻት አንዲት እህት ቤት ተጋብዘው።