በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጆሴፍ ራዘርፎርድ እና ሌሎች ወንድሞች አውሮፓን በጎበኙበት ወቅት

1920—የዛሬ መቶ ዓመት

1920—የዛሬ መቶ ዓመት

በ1920ዎቹ መባቻ ላይ የይሖዋ ሕዝቦች ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን ሥራ ለማከናወን በጣም ጓጉተው ነበር። ለ1920 የመረጡት የዓመት ጥቅስ “ኃይሌም ዝማሬዬም ጌታ ነው” የሚል ነበር።—መዝ. 118:14 ኪንግ ጄምስ ቨርዥን

ይሖዋ ለእነዚህ ቀናተኛ ሰባኪዎች ኃይል ሰጥቷቸዋል። በዚያ ዓመት የኮልፖርተሮች ወይም የአቅኚዎች ብዛት ከ225 ወደ 350 ከፍ ብሎ ነበር። በተጨማሪም የስብከቱ ሥራቸውን ለዋናው መሥሪያ ቤት ሪፖርት ያደረጉ አስፋፊዎች ብዛት ለመጀመሪያ ጊዜ ከ8,000 በላይ ሆኖ ነበር። ይሖዋም በሥራቸው ጥሩ ውጤት እንዲያገኙ በማድረግ ባርኳቸዋል።

አስደናቂ ቅንዓት ማሳየት

መጋቢት 21, 1920 በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ሥራ በበላይነት ይመራ የነበረው ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ “ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” የሚል ርዕስ ያለው ንግግር አቅርቦ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ፣ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በዚህ ንግግር ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። ኒው ዮርክ ሲቲ ውስጥ ትልቅ ከሚባሉት ቲያትር ቤቶች አንደኛውን ተከራዩ፤ እንዲሁም 320,000 ገደማ የሚሆኑ መጋበዣዎችን አሰራጩ።

“ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” የሚለውን ንግግር የሚያስተዋውቅ ጋዜጣ

ሰዎች የሰጡት ምላሽ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ከጠበቁት በላይ ነበር። ንግግሩ በሚቀርብበት ዕለት ከ5,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቲያትር ቤቱን ግጥም አድርገው ሞሉት፤ ቦታው ከመሙላቱ የተነሳ 7,000 የሚያህሉ ሰዎች ለመመለስ ተገድደዋል። መጠበቂያ ግንብ ስለዚህ ስብሰባ ሲገልጽ “ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ካደረጓቸው እጅግ ስኬታማ ስብሰባዎች አንዱ ነው” ብሏል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ “ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” የሚለውን መልእክት በማወጁ ሥራ የታወቁ ሆኑ። በእርግጥ የመንግሥቱ መልእክት ይበልጥ በስፋት መሰበክ እንደሚኖርበት በወቅቱ አልተገነዘቡም ነበር። ያም ሆኖ ቅንዓታቸው አስደናቂ ነበር። በ1902 ስብሰባዎች ላይ መገኘት የጀመረችው አይዳ ኦምስቴድ እንዲህ ብላለች፦ “መላው የሰው ዘር ከፊቱ ታላላቅ በረከቶች እንደሚጠብቁት ተገንዝበን ነበር፤ ስለዚህ በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች ይህን ምሥራች ከመናገር ጨርሶ ወደኋላ አላልንም።”

የራሳችንን ጽሑፍ ማተም

በቤቴል ያሉ ወንድሞች፣ መንፈሳዊ ምግብ ያለማቋረጥ እንዲቀርብ ለማድረግ ሲሉ አንዳንድ ጽሑፎችን ራሳቸው ማተም ጀመሩ። የሕትመት መሣሪያ ገዙ፤ ከዚያም በ35 መርትል ጎዳና፣ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኝ አንድ የተከራዩት ሕንፃ ውስጥ ማተሚያውን ገጠሙት፤ ይህ ሕንፃ የሚገኘው ከቤቴል ብዙም ሳይርቅ ነበር።

ሊዮ ፔል እና ዎልተር ኬስለር የቤቴል አገልግሎታቸውን የጀመሩት ጥር 1920 ነበር። ሁኔታውን አስታውሶ ሲናገር ዎልተር እንዲህ ብሏል፦ “እዚያ ስንደርስ የሕትመት የበላይ ተመልካቹ አየንና ‘ከምሳ በፊት አንድ ሰዓት ተኩል አላችሁ’ አለን። ከዚያም መጽሐፎች የያዙ ካርቶኖች ከምድር ቤት እንድናመጣ ሥራ ሰጠን።”

ሊዮ ደግሞ በቀጣዩ ቀን የተፈጠረውን ሲተርክ እንዲህ ብሏል፦ “የሕንፃውን ግድግዳ እንድናጸዳ ተጠየቅን። እንደዚያ ዓይነት ቆሻሻ አጽድቼ አላውቅም። የጌታ ሥራ ስለሆነ ግን ደስ እያለን ሠራነው።”

መጠበቂያ ግንብ ይታተምበት የነበረው የሕትመት መሣሪያ

በጥቂት ሳምንታት ውስጥ፣ ቀናተኛ የሆኑ ፈቃደኛ አገልጋዮች መጠበቂያ ግንብ ማተም ጀመሩ። በመጀመሪያው ፎቅ ላይ የሚገኘውን ማተሚያ ማሽን ተጠቅመው የየካቲት 1, 1920 የመጠበቂያ ግንብ እትምን 60,000 ቅጂዎች አተሙ። በዚሁ ጊዜ ወንድሞች ባትልሺፕ ብለው የጠሩትን ማተሚያ ማሽን ምድር ቤት ውስጥ ገጠሙ። ከሚያዝያ 14, 1920 እትም ጀምሮ ወርቃማው ዘመን የተባለው መጽሔትም በእነዚህ ማሽኖች መታተም ጀመረ። ይሖዋ የእነዚህን ፈቃደኛ ሠራተኞች ጥረት እንደባረከው በግልጽ ይታይ ነበር።

“የጌታ ሥራ ስለሆነ . . . ደስ እያለን ሠራነው”

“በሰላም እንኑር”

የይሖዋ ታማኝ ሕዝቦች የስብከት እንቅስቃሴያቸውንና አንድነታቸውን እንደገና አጠናከሩ። ይሁንና ከ1917 እስከ 1919 ባሉት አስቸጋሪ ጊዜያት አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ድርጅቱን ጥለው ወጥተው ነበር። ታዲያ እነሱን ለመርዳት ምን ይደረግ ይሆን?

የሚያዝያ 1, 1920 መጠበቂያ ግንብ “በሰላም እንኑር” የሚል ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። ይህ ርዕስ የሚከተለውን ሞቅ ያለ ግብዣ አቅርቦ ነበር፦ “የጌታ መንፈስ ያለው . . . ማንኛውም ሰው ከኋላው ያሉትን ነገሮች ለመርሳት፣ . . . በአንድነት ለመኖር እንዲሁም እንደ አንድ አካል ሆኖ ለመቀጠል ፈቃደኛ እንደሚሆን እርግጠኞች ነን።”

ብዙዎች በደግነት የቀረበውን ይህን ግብዣ ተቀበሉ። አንድ ባልና ሚስት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ባለፈው ዓመትና ከዚያ በፊት ባለው ጊዜ፣ ሌሎች በስብከቱ ሥራ በትጋት ሲካፈሉ እኛ እጃችንን አጣጥፈን መቀመጣችን ስህተት እንደነበር ተሰምቶናል፤ ከዚህ በኋላ መቼም እንዲህ ዓይነት ስህተት እንደማንሠራ ተስፋ እናደርጋለን።” ዳግም የተነቃቁት እነዚህ አገልጋዮች ከፊታቸው ብዙ ሥራ ይጠብቃቸው ነበር።

“ZG”ን ማሰራጨት

ሰኔ 21, 1920 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች “ZG”ን ለማሰራጨት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ጀመሩ። “ZG” በለስላሳ ሽፋን የተዘጋጀ ያለቀለት ሚስጥር * (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እትም ነው። በ1918 ይህ መጽሐፍ ሲታገድ በርካታ ቅጂዎች መጋዘን ውስጥ ተቀምጠው ነበር።

ይህን ጽሑፍ በማሰራጨቱ ሥራ፣ ኮልፖርተሮች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም አስፋፊዎች እንዲካፈሉ ግብዣ ቀረበላቸው። “በየጉባኤው የሚገኝ ማንኛውም የተጠመቀ ግለሰብ በሥራው መካፈል ከቻለ በደስታ እንዲህ ሊያደርግ ይገባል። የእያንዳንዱ ሰው መፈክር ‘ይህን አንድ ነገር አደርጋለሁ’ የሚል ይሁን፤ እሱም ZGን ማሰራጨት ነው።” ኤድመንድ ሁፐር በኋላ ላይ እንደተናገረው ብዙዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ወደ ቤት ሄደው ያገለገሉት በዚህ ዘመቻ ወቅት ነበር። አክሎ ሲናገር “ካሰብነው በላይ በስፋት የተሠራው ይህ ሥራ ምን እንደሚጠይቅ በትክክል የገባን ያኔ ነበር” ብሏል።

በአውሮፓ ሥራውን እንደገና ማደራጀት

በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በሌሎች አገሮች ካሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር መገናኘት አስቸጋሪ ሆኖ ነበር። ስለዚህ ወንድም ራዘርፎርድ እነዚህን ወንድሞች ማበረታታት እና የስብከቱን እንቅስቃሴ እንደገና ማደራጀት ፈለገ። በመሆኑም ነሐሴ 12, 1920 ወንድም ራዘርፎርድ ከሌሎች አራት ወንድሞች ጋር ሆኖ ሰፋ ያለ ጉብኝት ለማድረግ ጉዞ ጀመረ፤ ጉብኝቱ ብሪታንያንና ሌሎች የአውሮፓ አገሮችን እንዲሁም መካከለኛው ምሥራቅን የሚያጠቃልል ነበር።

ወንድም ራዘርፎርድ ግብፅ ውስጥ

ራዘርፎርድ ብሪታንያን በጎበኘበት ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ሦስት ትላልቅ ስብሰባዎችንና 12 ሕዝባዊ ስብሰባዎችን አድርገዋል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ 50,000 ያህል ሰው እንደተገኘ ይገመታል። መጠበቂያ ግንብ ስለ ጉብኝቱ ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞች ተነቃቅተዋል እንዲሁም ተበረታትተዋል። አብረው ጊዜ የማሳለፍና የማገልገል አጋጣሚ አግኝተዋል፤ በዚህም የተነሳ ብዙዎች ተደስተዋል።” ወንድም ራዘርፎርድ “ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” የሚለውን ንግግር ፓሪስ ውስጥም አቀረበ። ንግግሩ ሲጀምር አዳራሹ ጢም ብሎ ሞልቶ ነበር። ሦስት መቶ ሰዎች ተጨማሪ መረጃ ማግኘት እንደሚፈልጉ ገለጹ።

ለንደን በሚገኘው ሮያል አልበርት አዳራሽ የሚቀርበውን ንግግር የሚያስተዋውቅ ፖስተር

ከዚያ በኋላ ባሉት ሳምንታት ወንድሞች አቴንስን፣ ኢየሩሳሌምን እና ካይሮን ጎበኙ። በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ ፍላጎት ያላቸው ሰዎችን ለመርዳት ሲባል ወንድም ራዘርፎርድ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ባለችው በራማላ ቅርንጫፍ ቢሮ አቋቋመ። ከዚያም ወደ አውሮፓ ተመልሶ የማዕከላዊ አውሮፓ ቢሮን አቋቋመ፤ በዚያም ጽሑፎች እንዲታተሙ ዝግጅት አደረገ።

በወንድሞች ላይ የደረሰውን ግፍ ማጋለጥ

መስከረም 1920 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ወርቃማው ዘመን የተባለውን መጽሔት ቁጥር 27 እትም አወጡ። ይህ ልዩ እትም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በ1918 የደረሰባቸውን ስደት የሚያጋልጥ ነበር። ይህን መጽሔት ለማተም፣ ቀደም ሲል የተጠቀሰው ባትልሺፕ የተባለው የሕትመት መሣሪያ ቀንና ሌሊት ይሠራ ነበር፤ በመሆኑም ከአራት ሚሊዮን የሚበልጡ ቅጂዎችን ማተም ተችሏል።

ኤማ ማርቲን፣ ፖሊሶች ያነሱት ፎቶግራፍ

መጽሔቱ ላይ ኤማ ማርቲን የተባለች እህት የገጠማት አስገራሚ ነገር ወጥቶ ነበር። እህት ማርቲን በሳን በርናንዲኖ፣ ካሊፎርኒያ የምታገለግል ኮልፖርተር ነበረች። መጋቢት 17, 1918 እህት ማርቲን እንዲሁም ኤድዋርድ ሃም፣ ኤድዋርድ ጁሊየስ ሶነንበርግ እና ኧርነስት ስቲቨንስ የተባሉ ሦስት ወንድሞች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሚያደርጉት አነስተኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ነበር።

በስብሰባው ላይ ከተገኙት ሰዎች አንዱ ግን እዚያ የመጣው መጽሐፍ ቅዱስ ለመማር አልነበረም። ይህ ሰው በኋላ ላይ ቃሉን ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦ “ወደዚህ ስብሰባ የሄድኩት . . . በአቃቤ ሕጉ ቢሮ ትእዛዝ ነው። ስብሰባው ላይ የተገኘሁት ለክስ የሚሆን ማስረጃ ለማግኘት ነበር።” ግለሰቡ እየፈለገ የነበረውን ማስረጃ አገኘ፤ ማስረጃው ያለቀለት ሚስጥር (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ነበር። ከጥቂት ቀናት በኋላ እህት ማርቲንና ሦስቱ ወንድሞች ተያዙ፤ ከዚያም የታገደ መጽሐፍ በማሰራጨታቸው ተከሰሱ።

ኤማና ሦስቱ ወንድሞች ጥፋተኛ ናችሁ ተብለው የሦስት ዓመት እስር ተበየነባቸው። ይግባኝ ለማለት ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ ስላልተሳካ ግንቦት 17, 1920 እስር ቤት ተላኩ። ብዙም ሳይቆይ ግን ሁኔታዎች ተስተካከሉ።

ሰኔ 20, 1920 ወንድም ራዘርፎርድ፣ ሳን ፍራንሲስኮ ውስጥ በተካሄደ ትልቅ ስብሰባ ላይ የእነሱን ተሞክሮ ተናገረ። ተሰብሳቢዎቹ በወንድሞች ላይ የደረሰው ግፍ ስላሳዘናቸው ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ቴሌግራም እንዲላክ ተስማሙ። ቴሌግራሙ እንዲህ ይላል፦ “በሚስዝ ማርቲን ላይ የተበየነው ፍርድ . . . ፍትሕ የጎደለው እንደሆነ እናምናለን። የፌደራሉ ባለሥልጣናት፣ ሚስዝ ማርቲንን . . . ለማጥመድ . . . እንዲሁም ወህኒ እንድትወርድ የሚያደርግ ክስ ለመመሥረት ሥልጣናቸውን መጠቀማቸው . . . አግባብነት የሌለው ድርጊት . . . በመሆኑ እናወግዘዋለን።”

በቀጣዩ ቀን ፕሬዚዳንት ውድሮ ዊልሰን፣ በእህት ማርቲን እንዲሁም በወንድም ሃም፣ በወንድም ሶነንበርግ እና በወንድም ስቲቨንስ ላይ የተበየነውን ፍርድ ሻሩት። በግፍ የተበየነባቸው እስራትም በዚሁ አበቃ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በ1920 ብዙ የሚያስደስታቸው ነገር አግኝተው ነበር። በዋናው መሥሪያ ቤት የሚከናወነው ሥራ እያደገ ሄዶ ነበር። በተጨማሪም እውነተኛ ክርስቲያኖች የአምላክ መንግሥት የሰው ልጆችን ችግሮች እንደሚያስወግድ በማወጁ ሥራ ከመቼው ጊዜ ይበልጥ በቅንዓት ተካፍለው ነበር። (ማቴ. 24:14) በቀጣዩ ዓመት ማለትም በ1921 የመንግሥቱን እውነት በማወጁ ሥራ ከዚህም ይበልጥ ተሳትፎ አድርገዋል።

^ አን.18 ያለቀለት ሚስጥር (እንግሊዝኛ)፣ የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ሰባተኛ ጥራዝ ነው። “ZG” በለስላሳ ሽፋን የተዘጋጀ የዚህ መጽሐፍ እትም ነው፤ ታትሞ የወጣውም በመጋቢት 1, 1918 መጠበቂያ ግንብ ላይ ነበር። “Z” የጽዮን መጠበቂያ ግንብ የመጀመሪያ ፊደል ሲሆን “G” ደግሞ ሰባተኛው የእንግሊዝኛ ፊደል ነው፤ ይህም ጥራዙ ሰባተኛ መሆኑን ያመለክታል።