በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 42

እውነትን እንዳገኛችሁ እርግጠኛ ሁኑ

እውነትን እንዳገኛችሁ እርግጠኛ ሁኑ

“ሁሉንም ነገር መርምሩ፤ መልካም የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ።”—1 ተሰ. 5:21

መዝሙር 142 ተስፋችንን አጥብቀን እንያዝ

ማስተዋወቂያ *

1. ብዙ ሰዎች ግራ የተጋቡት ለምንድን ነው?

በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን እንደሆኑና አምላክን በትክክለኛው መንገድ እንደሚያመልኩ የሚናገሩ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖቶች አሉ። በዚህ የተነሳ ብዙ ሰዎች ግራ ተጋብተዋል። “እውነተኛው ሃይማኖት አንድ ብቻ ነው ወይስ አምላክ ሁሉንም ሃይማኖቶች ይቀበላል?” ብለው ይጠይቃሉ። እኛስ እውነትን እንደምናስተምር እንዲሁም ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ የሚያመልኩት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ እንደሆኑ እርግጠኞች ነን? ለመሆኑ ስለዚህ ነገር ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ መሆን ይቻላል? እስቲ ማስረጃዎቹን እንመርምር።

2. ሐዋርያው ጳውሎስ እውነትን እንዳገኘ እርግጠኛ የሆነው ለምን ነበር? (1 ተሰሎንቄ 1:5)

2 ሐዋርያው ጳውሎስ እውነትን እንዳገኘ ሙሉ እምነት ነበረው። (1 ተሰሎንቄ 1:5ን አንብብ።) እምነቱ እንዲሁ በስሜት ላይ ብቻ የተመሠረተ አልነበረም። ጳውሎስ የአምላክን ቃል በትጋት ያጠና ነበር። “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ” እንደሆኑ ያምን ነበር። (2 ጢሞ. 3:16) በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ያደረገው ጥናት ምን ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል? ኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ እንደሆነ የሚያሳይ የማያሻማ ማስረጃ አግኝቷል። የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ይህን ማስረጃ ችላ ብለውት ነበር። እነዚህ ግብዝ የሃይማኖት መሪዎች አምላክን እንደሚወክሉ ቢናገሩም በሥራቸው ክደውታል። (ቲቶ 1:16) ጳውሎስ ግን ከእነሱ የተለየ አቋም ይዟል፤ የፈለገውን ብቻ ሳይሆን ሙሉውን የአምላክ ቃል ለመቀበል መርጧል። “የአምላክን ፈቃድ ሁሉ” ለማስተማርና ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ነበር።—ሥራ 20:27

3. ጠንካራ እምነት ለማዳበር ለሁሉም ጥያቄዎቻችን መልስ ማግኘት አለብን? (“ ‘ዘርዝረን ልንጨርስ የማንችላቸው’ የይሖዋ ሐሳቦችና ሥራዎች” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

3 አንዳንዶች እውነተኛው ሃይማኖት መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ የማይመልሳቸውን ጨምሮ ሁሉንም ጥያቄዎቻቸውን ሊመልስላቸው እንደሚገባ ይሰማቸዋል። ሆኖም እንዲህ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው? እስቲ የጳውሎስን ምሳሌ እንመልከት። ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን “ሁሉንም ነገር [እንዲመረምሩ]” አበረታቷቸዋል፤ ሆኖም እሱ ራሱ ያልተረዳቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ አምኖ ተቀብሏል። (1 ተሰ. 5:21) “እውቀታችን ከፊል ነው” እንዲሁም “በብረት መስተዋት ብዥ ያለ ምስል ይታየናል” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 13:9, 12) ጳውሎስ ያልተረዳቸው ነገሮች እንደነበሩ ሁሉ እኛም የማንረዳቸው ነገሮች ይኖራሉ። ይሁንና ጳውሎስ የይሖዋን ዓላማ በተመለከተ መሠረታዊ የሆኑትን እውነቶች ተረድቶ ነበር። እውነትን እንዳገኘ እርግጠኛ ለመሆን የሚያስችል በቂ እውቀት ነበረው!

4. እውነትን እንዳገኘን እርግጠኛ ለመሆን የሚረዳን ምንድን ነው? እውነተኛ ክርስቲያኖችን በተመለከተ ምን እንመረምራለን?

4 እውነትን እንዳገኘን እርግጠኛ እንድንሆን የሚረዳን አንዱ ነገር በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጉትን ነገር ኢየሱስ ከተወው የአምልኮ ሥርዓት ጋር ማነጻጸር ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች (1) ከጣዖት አምልኮ እንደሚርቁ፣ (2) ለይሖዋ ስም አክብሮት እንዳላቸው፣ (3) እውነትን እንደሚወዱ እንዲሁም (4) አንዳቸው ለሌላው የጠለቀ ፍቅር እንዳላቸው የሚያሳዩት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

ከጣዖት አምልኮ እንርቃለን

5. አምላክን በትክክለኛው መንገድ ማምለክን በተመለከተ ከኢየሱስ ምን እንማራለን? እሱ ያስተማረውን ትምህርት ተግባራዊ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

5 ኢየሱስ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ስላለው በሰማይ ሳለም ሆነ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ እሱን ብቻ አምልኳል። (ሉቃስ 4:8) ደቀ መዛሙርቱም ይሖዋን ብቻ እንዲያመልኩ አስተምሯል። ኢየሱስም ሆነ ታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ምስሎችን ለአምልኮ ተጠቅመው አያውቁም። አምላክ መንፈስ ስለሆነ የሰው ልጆች የሚሠሩት ማንኛውም ነገር የይሖዋን ክብር በጥቂቱም እንኳ ሊያንጸባርቅ አይችልም! (ኢሳ. 46:5) ይሁንና ቅዱሳን ተብለው የሚጠሩ አካላትን ምስል መሥራትንና ለእነሱ መጸለይን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ከአሥርቱ ትእዛዛት መካከል በሁለተኛው ላይ ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “በላይ በሰማያት ወይም በታች በምድር . . . ባለ በማንኛውም ነገር አምሳል የተቀረጸን ቅርጽ ወይም የተሠራን ምስል ለራስህ አታድርግ። አትስገድላቸው።” (ዘፀ. 20:4, 5) አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች ይህን ትእዛዝ መረዳት አይከብዳቸውም።

6. በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የትኛውን የአምልኮ ሥርዓት ይከተላሉ?

6 የታሪክ ምሁራን የጥንቶቹ ክርስቲያኖች አምላክን ብቻ ያመልኩ እንደነበር ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተባለው መጽሐፍ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ምስሎችን በአምልኮ ቦታቸው ሊጠቀሙ ቀርቶ ሐሳቡ እንኳ “በጣም ሊዘገንናቸው እንደሚችል” ይገልጻል። በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የተዉትን የአምልኮ ሥርዓት ይከተላሉ። “ለቅዱሳን” ወይም ለመላእክት፣ ሌላው ቀርቶ ለኢየሱስ እንኳ አንጸልይም። በተጨማሪም ለመንግሥታትና ለብሔራዊ ዓርማዎች አምልኮ አከል ክብር አንሰጥም። ምንም ይምጣ ምን፣ ኢየሱስ “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ” በማለት የሰጠውን ትእዛዝ ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።—ማቴ. 4:10

7. በይሖዋ ምሥክሮችና በሌሎች ሃይማኖቶች መካከል ምን ግልጽ ልዩነት ይታያል?

7 በዘመናችን በርካታ ሰዎች ታዋቂ የሃይማኖት መሪዎችን ይከተላሉ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ለእነዚህ ሰዎች ያላቸው አድናቆት ከአምልኮ አይተናነስም። ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው ይጎርፋሉ፣ መጽሐፎቻቸውን ይገዛሉ እንዲሁም እነሱን ለመደገፍ ብዙ ገንዘብ ይሰጣሉ። አንዳንድ ሰዎች ከእነሱ አንደበት የሚወጣውን ማንኛውም ቃል ያለአንዳች ጥርጣሬ ይቀበላሉ። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ ራሱ ፊታቸው ቢቆም እንኳ ይህን ያህል መደሰታቸው ያጠራጥራል! ከዚህ በተቃራኒ እውነተኛዎቹ የይሖዋ አምላኪዎች የቀሳውስት ሥርዓት የላቸውም። አመራር የሚሰጡንን ሰዎች የምናከብር ቢሆንም ኢየሱስ “ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” በማለት ያስተማረውን ግልጽ ትምህርት እንቀበላለን። (ማቴ. 23:8-10) ለሃይማኖት መሪዎችም ሆነ ለፖለቲካ ገዢዎች ከልክ ያለፈ ክብር አንሰጥም። በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች የሚያራምዱትን ሃይማኖታዊ ወይም ፖለቲካዊ አቋም አንደግፍም። ከዚህ ይልቅ የገለልተኝነት አቋማችንን በመጠበቅ ከዓለም የተለየን ለመሆን ጥረት እናደርጋለን። ይህ አቋማችን ክርስቲያን ነን ከሚሉ በርካታ ሃይማኖቶች የተለየን ያደርገናል።—ዮሐ. 18:36

ለይሖዋ ስም አክብሮት አለን

እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሌሎች ስለ ይሖዋ የመናገር መብት በማግኘታቸው ኩራት ይሰማቸዋል (ከአንቀጽ 8-10⁠ን ተመልከት) *

8. ይሖዋ ስሙ እንዲከበርና በስፋት እንዲታወቅ እንደሚፈልግ በምን እናውቃለን?

8 በአንድ ወቅት ኢየሱስ “አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። ይሖዋም ከሰማይ በሚያስገመግም ድምፅ ስሙን እንደሚያከብረው በመግለጽ መልስ ሰጥቷል። (ዮሐ. 12:28) ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ የአባቱ ስም እንዲከበር አድርጓል። (ዮሐ. 17:26) እውነተኛ ክርስቲያኖችም የአምላክን ስም የመጠቀምና ለሌሎች የማሳወቅ መብት በማግኘታቸው ኩራት ይሰማቸዋል።

9. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ለአምላክ ስም አክብሮት እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው?

9 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ “ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ . . . ለእነሱ ትኩረት [ሰጠ]።” (ሥራ 15:14) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት እነዚህ ክርስቲያኖች የአምላክን ስም የመጠቀምና ለሌሎች የማሳወቅ መብት በማግኘታቸው ኩራት ይሰማቸው ነበር። በአገልግሎታቸውም ሆነ በጻፏቸው መልእክቶች ላይ የአምላክን ስም በስፋት ተጠቅመዋል። * እንዲህ በማድረግ የአምላክን ስም የሚያሳውቁት ብቸኛዎቹ ሰዎች እነሱ መሆናቸውን አስመሥክረዋል።—ሥራ 2:14, 21

10. የይሖዋ ምሥክሮች ለይሖዋ ስም የቆሙ ሰዎች መሆናቸውን የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

10 የይሖዋ ምሥክሮች ለይሖዋ ስም የቆሙ ብቸኛዎቹ ሰዎች መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነው? እስቲ ማስረጃዎቹን እንመልከት። በዛሬው ጊዜ በርካታ የሃይማኖት መሪዎች የአምላክ ስም እንዳይታወቅ ለማድረግ የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል። የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው ላይ አውጥተዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ፣ ሰዎች በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ የአምላክን ስም እንዳይጠቀሙ እስከመከልከል ደርሰዋል። * ለይሖዋ ስም የሚገባውን ክብር እየሰጡ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ እንደሆኑ ማን ሊክድ ይችላል? ከየትኛውም ሃይማኖት ይበልጥ የአምላክን ስም ለማሳወቅ ጥረት እያደረግን ነው! በዚህ ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች ከሚለው መጠሪያችን ጋር ተስማምተን ለመኖር የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን። (ኢሳ. 43:10-12) አዲስ ዓለም ትርጉም የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ከ240 ሚሊዮን በሚበልጡ ቅጂዎች አዘጋጅተናል፤ ይህ ትርጉም የአምላክን ስም ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ባወጡባቸው ቦታዎች ሁሉ ላይ መልሶ አስገብቷል። ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋን ስም የሚያሳውቁ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች እናዘጋጃለን!

እውነትን እንወዳለን

11. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እውነትን እንደሚወዱ ያሳዩት እንዴት ነው?

11 ኢየሱስ ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ለሚገልጸው እውነት ፍቅር ነበረው። ከዚህ እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ ይኖር የነበረ ከመሆኑም ሌላ ይህን እውነት ለሌሎች አሳውቋል። (ዮሐ. 18:37) የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮችም ለእውነት ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው። (ዮሐ. 4:23, 24) እንዲያውም ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስትናን “የእውነት መንገድ” በማለት ጠርቶታል። (2 ጴጥ. 2:2) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ለእውነት ጥልቅ ፍቅር ስለነበራቸው ከእውነት ጋር የሚቃረኑ ሃይማኖታዊ ሐሳቦችን፣ ወጎችንና የግል አመለካከቶችን አይቀበሉም ነበር። (ቆላ. 2:8) በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም የሚያምኑበት ነገርና አኗኗሯቸው፣ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ቃል ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ጥረት ያደርጋሉ፤ በዚህ መንገድ ‘በእውነት ውስጥ እንደሚመላለሱ’ ያሳያሉ።—3 ዮሐ. 3, 4

12. አመራር የሚሰጡን ወንድሞች ስለ አንድ እውነት ያለንን ግንዛቤ በተመለከተ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሲገነዘቡ ምን ያደርጋሉ? እንዲህ ያለ እርምጃ የሚወስዱትስ ለምንድን ነው?

12 በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች ስለ እውነት የተሟላ ወይም ፍጹም ግንዛቤ እንዳላቸው አይናገሩም። ከመሠረተ ትምህርትና ከድርጅታዊ አሠራር ጋር በተያያዘ ስህተት የሠሩባቸው ጊዜያት አሉ። ይህ ሊያስገርመን አይገባም። ቅዱሳን መጻሕፍት ትክክለኛው እውቀት በጊዜ ሂደት እየጨመረ እንደሚሄድ ይናገራሉ። (ቆላ. 1:9, 10) ይሖዋ እውነትን የሚገልጠው ቀስ በቀስ ነው፤ እኛም የእውነት ብርሃን እየደመቀ እስኪሄድ በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኞች መሆን አለብን። (ምሳሌ 4:18) አመራር የሚሰጡን ወንድሞች አንድን እውነት በተመለከተ ያለን ግንዛቤ መስተካከል እንዳለበት ሲገነዘቡ አስፈላጊውን ማስተካከያ ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። ክርስቲያን ነን የሚሉ በርካታ ሃይማኖቶች ማስተካከያ የሚያደርጉት ተከታዮቻቸውን ለማስደሰት ወይም ወደ ዓለም ይበልጥ ለመቅረብ ሲሉ ነው፤ የይሖዋ ድርጅት ግን ማስተካከያዎችን የሚያደርገው ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብና ኢየሱስ የተወውን የአምልኮ ሥርዓት በጥብቅ ለመከተል ሲል ነው። (ያዕ. 4:4) ማስተካከያዎችን ለማድረግ የሚያነሳሳን ዘመን አመጣሽ አስተሳሰቦችን ለመደገፍ ወይም ብዙኃኑን ለማስደሰት ያለን ፍላጎት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለን ግንዛቤ ከበፊቱ ይበልጥ እየጠራ መሄዱ ነው። እውነትን እንወዳለን!—1 ተሰ. 2:3, 4

አንዳችን ለሌላው የጠለቀ ፍቅር አለን

13. እውነተኛ ክርስቲያኖች ተለይተው የሚታወቁበት ዋነኛው ባሕርይ ምንድን ነው? በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ባሕርይ የሚያሳዩት እንዴት ነው?

13 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ተለይቶ ከሚታወቅባቸው ባሕርያት መካከል ዋነኛው ፍቅር ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐ. 13:34, 35) በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም እውነተኛ ፍቅርና አንድነት አላቸው። ከሌላ ከየትኛውም ድርጅት በተለየ መልኩ የወንድማማች ማኅበራችን ብሔር፣ የቆዳ ቀለምና የኑሮ ደረጃ የማይለየው የጠበቀ አንድነት አለው። በሳምንታዊ ስብሰባዎቻችንና በትላልቅ ስብሰባዎቻችን ላይ ይህን እውነተኛ ፍቅር በግልጽ ማየት ይቻላል። ይህ እውነታ አምልኳችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው ያረጋግጥልናል።

14. በቆላስይስ 3:12-14 መሠረት አንዳችን ለሌላው የጠለቀ ፍቅር እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

14 ቅዱሳን መጻሕፍት ‘አንዳችን ለሌላው የጠለቀ ፍቅር እንዲኖረን’ ይመክሩናል። (1 ጴጥ. 4:8) እንዲህ ያለውን ፍቅር የምናሳይበት አንዱ መንገድ እርስ በርስ ይቅር መባባልና አንዳችን የሌላውን ድክመት ችለን ማለፍ ነው። በተጨማሪም ቅር ያሰኙንን ጨምሮ በጉባኤ ውስጥ ላሉ ሁሉ ልግስናና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን። (ቆላስይስ 3:12-14ን አንብብ።) እንዲህ ያለ ፍቅር ማሳየታችን እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችን የሚረጋገጥበት ዋነኛው መንገድ ነው።

“አንድ እምነት”

15. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች የተዉትን የአምልኮ ሥርዓት የምንከተልባቸው ሌሎች መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

15 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች የተዉትን የአምልኮ ሥርዓት የምንከተልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ለምሳሌ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን፣ ሽማግሌዎችንና የጉባኤ አገልጋዮችን የሚያካትተው የድርጅታችን መዋቅር በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ሐዋርያት ያቋቋሙትን ሥርዓት የሚከተል ነው። (ፊልጵ. 1:1፤ ቲቶ 1:5) ስለ ፆታ ግንኙነት፣ ስለ ጋብቻና ስለ ደም ቅድስና ያለን አመለካከት እንዲሁም ጉባኤውን ንስሐ ከማይገቡ ኃጢአተኞች ለመጠበቅ የምናደርገው ጥረት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ይከተሉት በነበረው አሠራር ላይ የተመሠረተ ነው።—ሥራ 15:28, 29፤ 1 ቆሮ. 5:11-13፤ 6:9, 10፤ ዕብ. 13:4

16. በኤፌሶን 4:4-6 ላይ ካለው ሐሳብ ምን እንማራለን?

16 ኢየሱስ የእሱ ደቀ መዛሙርት እንደሆኑ ከሚናገሩት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ እውነተኛ እንዳልሆኑ ተናግሯል። (ማቴ. 7:21-23) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ብዙዎች “ለአምላክ ያደሩ መስለው” ብቻ እንደሚታዩ አስጠንቅቋል። (2 ጢሞ. 3:1, 5) ሆኖም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው “አንድ እምነት” እንዳለ በቀጥታ ይናገራል።—ኤፌሶን 4:4-6ን አንብብ።

17. በዛሬው ጊዜ ኢየሱስ ያስተማረውን ትምህርት እየፈጸሙና እውነተኛውን አንድ እምነት እየተከተሉ ያሉት እነማን ናቸው?

17 በዛሬው ጊዜ የእውነተኛው አንድ እምነት ተከታዮች እነማን ናቸው? ማስረጃዎቹን መርምረናል። በተጨማሪም ኢየሱስ ያስተማረውንና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ይከተሉ የነበሩትን የአምልኮ ሥርዓት ተመልክተናል። መልሱ አንድና አንድ ብቻ ነው፦ የይሖዋ ምሥክሮች። ከይሖዋ ሕዝቦች አንዱ መሆን እንዲሁም ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ እውነቱን ማወቅ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! እንግዲያው ያገኘነውን እውነት ምንጊዜም አጥብቀን እንያዝ።

መዝሙር 3 ኃይላችን፣ ተስፋችን፣ ትምክህታችን

^ አን.5 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ኢየሱስ የተወውን የአምልኮ ሥርዓት እንዲሁም የጥንቶቹ ደቀ መዛሙርት ይህን ሥርዓት የተከተሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች ይህን የእውነተኛ አምልኮ ሥርዓት እየተከተሉ እንዳሉ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን እንመረምራለን።

^ አን.9 በሐምሌ 1, 2010 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 6 ላይ የወጣውን “በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች በአምላክ ስም ተጠቅመው ነበር?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

^ አን.10 ለምሳሌ ያህል፣ በ2008 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ በካቶሊክ ሃይማኖታዊ አገልግሎቶች፣ መዝሙሮች ወይም ቅዳሴዎች ላይ “የአምላክን ስም መጠቀም አሊያም መጥራት ተገቢ እንዳልሆነ” ገልጸዋል።

^ አን.63 የሥዕሉ መግለጫ፦ የይሖዋ ድርጅት አዲስ ዓለም ትርጉምን ከ200 በሚበልጡ ቋንቋዎች አዘጋጅቷል፤ ዓላማው ሰዎች የአምላክን ስም የያዘውን ይህን መጽሐፍ ቅዱስ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲያነብቡ መርዳት ነው።