በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

1921—የዛሬ መቶ ዓመት

1921—የዛሬ መቶ ዓመት

“ታዲያ በዚህ ዓመት የሚጠብቀን ሥራ ምንድን ነው?” የጥር 1, 1921 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ቀናተኛ ለሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይህን ጥያቄ አቅርቦ ነበር። መጠበቂያ ግንቡ መልሱን ለመስጠት፣ ስለ ስብከት ተልእኮ የሚገልጸውን ኢሳይያስ 61:1, 2⁠ን ጠቀሰ። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ የዋህ ለሆኑ ሰዎች ምሥራች እንድናገር ቀብቶኛል። . . . ይሖዋ በጎ ፈቃድ የሚያሳይበትን ዓመት፣ አምላካችን የሚበቀልበትንም ቀን እንዳውጅ . . . ልኮኛል።”

ደፋር ሰባኪዎች

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ተልእኳቸውን ለመፈጸም ደፋሮች መሆን ያስፈልጋቸው ነበር። የዋህ ለሆኑ ሰዎች “ምሥራች” ለክፉዎች ደግሞ አምላካችን ‘ስለሚበቀልበት ቀን’ ማወጅ ነበረባቸው።

በካናዳ የሚኖረው ወንድም ጆን ሄንሪ ሆስከን ተቃውሞ ቢያጋጥመውም በድፍረት ይሰብክ ነበር። በ1921 መጀመሪያ አካባቢ ከአንድ የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን ሰባኪ ጋር ተገናኘ። በውይይቱ መጀመሪያ ላይ ወንድም ሆስከን እንዲህ አለ፦ “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አስደሳች ውይይት ማድረግ እንችላለን፤ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ካልተስማማን ደግሞ በሰላም እንለያያለን።” የሆነው ግን ይህ አልነበረም። ወንድም ሆስከን እንዲህ ብሏል፦ “ገና ጥቂት ደቂቃዎች እንደተነጋገርን [ሰባኪው] በሩን በኃይል መታው፤ የበሩ መስታወት የሚረግፍ መስሎኝ ነበር።”

ሰባኪው “ወደ አሕዛብ ሄደህ እነሱን አታናግርም?” ብሎ ጮኸበት። ወንድም ሆስከን ምላሽ አልሰጠውም፤ ሆኖም እየሄደ ሳለ በልቡ “አንተስ ከእነሱ መች ተለየህ?” ብሎ አሰበ።

ሰባኪው በቀጣዩ ቀን በቤተ ክርስቲያን ሲያስተምርም ስለ ወንድም ሆስከን መጥፎ ነገር መናገሩን ቀጠለ። ወንድም ሆስከን እንዲህ ብሏል፦ “በከተማው ውስጥ እንደ እኔ ዓይነት አጭበርባሪ ታይቶ እንደማይታወቅ ምዕመናኑን ያስጠነቀቃቸው ሲሆን ልገደል እንደሚገባ ተናገረ።” ወንድም ሆስከን ግን በዚህ ሳይበገር በስብከቱ ሥራ ቀጠለ፤ ደግሞም ጥሩ ውጤት አገኘ። እንዲህ ብሏል፦ “በስብከቱ ሥራ በጣም አስደሳች ጊዜ አሳልፌያለሁ። አንዳንዶቹ ሰዎች ‘የአምላክ ሰው እንደሆንክ እናውቃለን!’ ይሉኝ ነበር፤ በተጨማሪም የሚያስፈልገኝ ነገር ካለ ሊሰጡኝ እንደሚፈልጉ ይነግሩኝ ነበር።”

የግልና የቤተሰብ ጥናት

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ፣ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት ሲሉ ወርቃማው ዘመን * በተባለው መጽሔት ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ዓምዶችን ያወጡ ነበር። “የልጆች የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ” የተባለው ዓምድ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ሊወያዩባቸው የሚችሉ አንዳንድ ጥያቄዎችን ይዞ ይወጣ ነበር። ወላጆች “ለልጆቻቸው እነዚህን ጥያቄዎች ካቀረቡላቸው በኋላ መልሱን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲያገኙ ይረዷቸዋል።” “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስንት መጻሕፍት አሉ?” እንደሚሉት ያሉ አንዳንድ ጥያቄዎች መሠረታዊ እውቀት የሚያስጨብጡ ነበሩ። “ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ስደት እንደሚደርስባቸው መጠበቅ ይኖርባቸዋል?” እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች ደግሞ ልጆች ደፋር ሰባኪዎች እንዲሆኑ ያዘጋጇቸው ነበር።

ለጎለመሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ደግሞ “የመለኮታዊው የዘመናት ዕቅድ ጥልቅ ጥናት” የተባለ ዓምድ ይዘጋጅ ነበር፤ ይህ ዓምድ የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍ የመጀመሪያ ጥራዝ ላይ የተመሠረቱ የሚያመራምሩ ጥያቄዎችን የያዘ ነበር። እነዚህ ዓምዶች በሺዎች የሚቆጠሩ አንባቢዎችን ጠቅመዋል፤ ሆኖም የታኅሣሥ 21, 1921 ወርቃማው ዘመን መጽሔት ሁለቱም ዓምዶች መውጣት እንደሚያቆሙ አስታወቀ። እንዲህ ያለ ድንገተኛ ለውጥ የተደረገው ለምንድን ነው?

አዲስ መጽሐፍ!

የአምላክ በገና የተባለው መጽሐፍ

የሚነበበውን ክፍል የሚጠቁም ካርድ

ጥያቄዎችን የያዘ ካርድ

አመራር የሚሰጡት ወንድሞች፣ አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መሠረታዊ እውነቶችን በተደራጀ መንገድ መማር እንደሚያስፈልጋቸው ተገነዘቡ። ለዚህም ሲባል ኅዳር 1921 የአምላክ በገና (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ወጣ። መጽሐፉን የወሰዱ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች “የአምላክ በገና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም” የተባለውን ኮርስም ይወስዱ ነበር። በዚህ ኮርስ ላይ ተማሪዎቹ ራሳቸውን የሚያስተምሩ ሲሆን “አምላክ ለሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ለመስጠት ስላለው ዓላማ” ይማሩ ነበር። ትምህርቱ የሚካሄደው እንዴት ነበር?

አንድ ሰው መጽሐፉን ሲወስድ፣ ከመጽሐፉ ላይ የሚያነብባቸውን ገጾች የሚገልጽ ትንሽ ካርድ ይሰጠዋል። በቀጣዩ ሳምንት ደግሞ ባነበባቸው ገጾች ላይ የተመሠረቱ ጥያቄዎችን የያዘ ሌላ ካርድ ይላክለታል። በዚህኛው ካርድ መጨረሻ ላይ፣ ለቀጣዩ ሳምንት እንዲያነብ የሚጠበቅበት ገጽ ይነገረዋል።

ለ12 ሳምንታት ያህል ተማሪው በአቅራቢያው ካለ ጉባኤ አዲስ ካርድ ይላክለታል። አብዛኛውን ጊዜ ካርዶቹን የሚልኩት በዕድሜ የገፉ ወይም የአቅም ገደብ ያለባቸው ወንድሞችና እህቶች ናቸው። ለምሳሌ በሚልቬል፣ ፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው አና ካትሪን ጋርድነር እንዲህ ብላ ነበር፦ “ታማሚ የነበረችው እህቴ ቴል የአምላክ በገና የተባለው መጽሐፍ ሲወጣ በአገልግሎቷ ተጨማሪ ተሳትፎ ማድረግ ቻለች፤ ጥያቄዎች የያዙ ካርዶችን በየሳምንቱ ለሰዎች ትልክ ነበር።” ተማሪው ኮርሱን ሲያጠናቅቅ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማግኘት እንዲችል አንድ ክርስቲያን በአካል ሄዶ ያነጋግረዋል።

ቴል ጋርድነር በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ሆና

የሚጠብቃቸው ሥራ

በዓመቱ መጨረሻ ላይ ወንድም ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ ለሁሉም ጉባኤዎች ደብዳቤ ላከ። በደብዳቤው ላይ እንዲህ ብሏል፦ “የመከሩ ወቅት ከጀመረ ወዲህ፣ የዚህን ዓመት ያህል የመንግሥቱ ምሥራች ስብከት ሥራ በስፋትና ውጤታማ በሆነ መንገድ ተከናውኖ አያውቅም።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ገና የሚቀረን ብዙ ሥራ አለ። ሌሎችም በዚህ የተባረከ ሥራ እንዲካፈሉ አበረታቷቸው።” የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ይህን ምክር በተግባር እንዳዋሉት በግልጽ ማየት ይቻላል። በ1922 ከዚያ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መንገድ ስለ መንግሥቱ በድፍረት አውጀዋል።

^ አን.9 ወርቃማው ዘመን (እንግሊዝኛ) በ1937 መጽናኛ (እንግሊዝኛ) የተባለ ሲሆን በ1946 ደግሞ ንቁ! ተብሏል።