የጥናት ርዕስ 42
በይሖዋ ፊት ያላቸውን ‘ንጹሕ አቋም የሚጠብቁ’ ደስተኞች ናቸው
“ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ፣ በይሖዋ ሕግ የሚመላለሱ ሰዎች ደስተኞች ናቸው።”—መዝ. 119:1 ግርጌ
መዝሙር 124 ምንጊዜም ታማኝ መሆን
ማስተዋወቂያ a
1-2. (ሀ) አንዳንድ መንግሥታት በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ምን እርምጃ ወስደዋል? ሆኖም የይሖዋ ሕዝቦች ምን ምላሽ ሰጥተዋል? (ለ) የይሖዋ ሕዝቦች ስደት ቢደርስባቸውም ደስተኛ ሊሆኑ የቻሉት ለምንድን ነው? (በሽፋኑ ሥዕል ላይም ሐሳብ ስጥ።)
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከ30 በሚበልጡ አገራት በሥራችን ላይ እገዳ ወይም ገደብ ተጥሏል። ከእነዚህ አገራት መካከል በአንዳንዶቹ፣ ባለሥልጣናት ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን አስረዋቸዋል። ምን አጥፍተው ይሆን? በይሖዋ ዓይን ምንም ያጠፉት ጥፋት የለም። የታሰሩት መጽሐፍ ቅዱስን በማንበባቸውና በማጥናታቸው፣ እምነታቸውን ለሌሎች በማካፈላቸው እንዲሁም ከእምነት አጋሮቻቸው ጋር በመሰብሰባቸው ብቻ ነው። በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ አንዱን ወገን ለመደገፍም ፈቃደኞች አይደሉም። እነዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ከባድ ተቃውሞ ቢደርስባቸውም ንጹሕ አቋማቸውን b ጠብቀዋል፤ ለይሖዋ የማይናወጥ ታማኝነት አሳይተዋል። ይህን በማድረጋቸውም ደስተኞች ናቸው!
2 የእነዚህን ደፋር የይሖዋ ምሥክሮች ፎቶግራፍ ስትመለከት ፊታቸው ላይ ፈገግታ እንደማይጠፋ አስተውለህ ይሆናል። ደስተኛ የሆኑት፣ በይሖዋ ፊት ያላቸውን ንጹሕ አቋም በመጠበቃቸው እሱ እንደሚደሰትባቸው ስለሚያውቁ ነው። (1 ዜና 29:17ሀ) ኢየሱስ “ለጽድቅ ሲሉ ስደት የሚደርስባቸው ደስተኞች ናቸው፤ . . . የሚጠብቃችሁ ሽልማት ታላቅ ስለሆነ ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ” ብሏል።—ማቴ. 5:10-12
ግሩም ምሳሌ
3. በሐዋርያት ሥራ 4:19, 20 መሠረት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ሐዋርያት ስደት ሲደርስባቸው ምን አደረጉ? ለምንስ?
3 በአሁኑ ጊዜ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እያጋጠማቸው ያለው ነገር በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያት ካጋጠማቸው ነገር ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ሐዋርያት ስለ ኢየሱስ በመስበካቸው ተሰደው ነበር። የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ሐዋርያቱ “በኢየሱስ ስም መናገራቸውን እንዲያቆሙ” በተደጋጋሚ አዘዋቸው ነበር። (ሥራ 4:18፤ 5:27, 28, 40) ታዲያ ሐዋርያቱ ምን አደረጉ? (የሐዋርያት ሥራ 4:19, 20ን አንብብ።) ‘ለሰዎች እንዲሰብኩና ስለ ክርስቶስ በተሟላ ሁኔታ እንዲመሠክሩ’ ያዘዛቸው ከዳኞቹ የሚበልጥ ሥልጣን ያለው አካል እንደሆነ ያውቁ ነበር። (ሥራ 10:42) በመሆኑም ሐዋርያቱን ወክለው የሚናገሩት ጴጥሮስና ዮሐንስ፣ ከዳኞቹ ይልቅ አምላክን እንደሚታዘዙ በድፍረት ተናገሩ፤ እንዲሁም ስለ ኢየሱስ መናገራቸውን እንደማያቆሙ ገለጹ። በሌላ አባባል ባለሥልጣናቱን እንዲህ ያሏቸው ያህል ነበር፦ ‘የእኛ ትእዛዝ ከአምላክ ትእዛዝ ይበልጣል የምትሉት እናንተ ማን ሆናችሁ ነው?’
4. በሐዋርያት ሥራ 5:27-29 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ሐዋርያት ለሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ምሳሌ ትተዋል? እኛስ የእነሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
4 ሐዋርያቱ ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትተዋል። ክርስቲያኖች ‘ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያቸው አድርገው ሊታዘዙ ይገባል።’ (የሐዋርያት ሥራ 5:27-29ን አንብብ።) ንጹሕ አቋማቸውን በመጠበቃቸው የተነሳ ከተገረፉ በኋላ ሐዋርያቱ “ስለ ስሙ ውርደት ለመቀበል ብቁ ሆነው በመቆጠራቸው ደስ እያላቸው” ከአይሁዳውያኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወጡ፤ መስበካቸውንም አላቆሙም!—ሥራ 5:40-42
5. የትኞቹን ጥያቄዎች መመለስ ይኖርብናል?
5 ሐዋርያት የተዉት ምሳሌ አንዳንድ ጥያቄዎችን ያስነሳል። ለምሳሌ ከሰው ይልቅ አምላክን እየታዘዙ “ሰው ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ መከተል የሚቻለው እንዴት ነው? (ሮም 13:1) እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው ‘ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት እየታዘዝን’ ዋነኛው ገዢያችን በሆነው በይሖዋ ፊት ያለንን ንጹሕ አቋም ጠብቀን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?—ቲቶ 3:1
‘የበላይ ባለሥልጣናት’
6. (ሀ) በሮም 13:1 ላይ የተጠቀሱት ‘የበላይ ባለሥልጣናት’ እነማን ናቸው? ከእነሱ ጋር በተያያዘ ምን ይጠበቅብናል? (ለ) ሁሉም መንግሥታት ስላላቸው ሥልጣን ምን ማለት ይቻላል?
6 ሮም 13:1ን አንብብ። በዚህ ጥቅስ ላይ ‘የበላይ ባለሥልጣናት’ የሚለው አገላለጽ በሌሎች ላይ ኃይልና ሥልጣን ያላቸውን ሰብዓዊ መሪዎች ያመለክታል። ክርስቲያኖች ለእነዚህ የመንግሥት ባለሥልጣናት መገዛት ይጠበቅባቸዋል። ባለሥልጣናት ሥርዓት ያስጠብቃሉ፤ ሕግ ያስከብራሉ፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ለይሖዋ ሕዝቦች ጥብቅና ይቆማሉ። (ራእይ 12:16) በመሆኑም እነሱ የሚጠይቁትን ቀረጥ፣ ግብር፣ ፍርሃትና ክብር እንድንሰጣቸው ታዘናል። (ሮም 13:7) ሆኖም እነዚህ መንግሥታት ሥልጣን ያላቸው ይሖዋ ስለፈቀደላቸው ብቻ ነው። ኢየሱስ በሮማዊው አገረ ገዢ በጳንጢዮስ ጲላጦስ ፊት በቀረበበት ወቅት ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ግልጽ አድርጓል። ጲላጦስ ኢየሱስን ለመፍታትም ሆነ ለመግደል ሥልጣን እንዳለው በተናገረበት ወቅት ኢየሱስ “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን አይኖርህም ነበር” ብሎታል። (ዮሐ. 19:11) እንደ ጲላጦስ ሁሉ በዘመናችን ያሉ መሪዎችና ፖለቲከኞች በሙሉ ሥልጣናቸው የተገደበ ነው።
7. መንግሥታትን መታዘዝ የማይኖርብን በየትኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ ነው? እነሱስ ምን መገንዘብ ይኖርባቸዋል?
7 ክርስቲያኖች የመንግሥታት ሕግ ከአምላክ ሕግ ጋር እስካልተጋጨ ድረስ ለመንግሥታት ይገዛሉ። ሆኖም አምላክ የሚከለክለውን ነገር እንድናደርግ ወይም እሱ የሚጠብቅብንን ነገር እንዳናደርግ ሲጠይቁን ሰዎችን አንታዘዝም። ለምሳሌ ወጣቶች ሠራዊቱን ተቀላቅለው በጦርነቶች እንዲካፈሉ ያዝዙ ይሆናል። c ወይም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳችንን እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን ሊያግዱ ይችላሉ፤ በተጨማሪም እንዳንሰብክና እንዳንሰበሰብ ይከለክሉን ይሆናል። መንግሥታት ሥልጣናቸውን አላግባብ ሲጠቀሙ፣ ለምሳሌ የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት ሲያሳድዱ በአምላክ ፊት ተጠያቂ ይሆናሉ። ይሖዋ ሁሉንም ነገር ይመለከታል!—መክ. 5:8
8. በይሖዋና በመንግሥታት መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ይህን ማወቅ ያለብንስ ለምንድን ነው?
8 “የበላይ” የሚለው ቃል “የተሻለ፣ የበለጠ ወይም የላቀ” የሚል ትርጉም ያስተላልፋል። “ከሁሉ የተሻለ፣ ከሁሉ የበለጠ ወይም ከሁሉ የላቀ” ማለት ግን አይደለም። መንግሥታት ‘የበላይ ባለሥልጣናት’ ተብለው ቢጠሩም ከእነሱ የበለጠ ሥልጣን ያለው አካል አለ። ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአራት ቦታዎች ላይ “ከሁሉ የላቀው አምላክ” ተብሎ ተጠርቷል።—ዳን. 7:18, 22, 25, 27
“ከሁሉ የላቀው አምላክ”
9. ነቢዩ ዳንኤል ምን ራእይ ተመለከተ?
9 ነቢዩ ዳንኤል፣ ይሖዋ ከሁሉም መንግሥታት የላቀ ሥልጣን እንዳለው የሚያሳይ ራእይ ተመልክቷል። በመጀመሪያ ዳንኤል ጥንትም ሆነ ዛሬ ያሉ የዓለም ኃያላን መንግሥታትን የሚወክሉ አራት ትላልቅ አውሬዎችን ተመለከተ፤ እነዚህ መንግሥታት ባቢሎን፣ ሜዶ ፋርስ፣ ግሪክ፣ ሮም እና በዘመናችን ሥልጣን ላይ ያለው አንግሎ አሜሪካ ናቸው። (ዳን. 7:1-3, 17) ከዚያም ዳንኤል፣ ይሖዋ አምላክ በሰማያዊ ችሎቱ በዙፋን ላይ ተቀምጦ ተመለከተ። (ዳን. 7:9, 10) ይህ ታማኝ ነቢይ ቀጥሎ የተመለከተው ነገር በዛሬው ጊዜ ላሉ መንግሥታት ማስጠንቀቂያ ይሆናል።
10. በዳንኤል 7:13, 14, 27 መሠረት ይሖዋ ምድርን እንዲገዙ ሥልጣን የሚሰጠው ለእነማን ነው? ይህስ ስለ እሱ ምን ያሳያል?
10 ዳንኤል 7:13, 14, 27ን አንብብ። አምላክ የሁሉንም መንግሥታት ሥልጣን ወስዶ ብቃቱን ለሚያሟሉና ይበልጥ ኃያላን ለሆኑ አካላት ይሰጠዋል። እነሱ እነማን ናቸው? ‘የሰው ልጅ የሚመስለው’ ኢየሱስ ክርስቶስና ‘ከሁሉ የላቀው አምላክ ቅዱሳን የሆኑት ሰዎች’ ማለትም “ለዘላለም ዓለም” የሚነግሡት 144,000ዎች ናቸው። (ዳን. 7:18) በእርግጥም ይሖዋ ‘ከሁሉ የላቀ አምላክ’ ነው። ምክንያቱም እንዲህ ያለ እርምጃ ለመውሰድ ሥልጣን ያለው እሱ ብቻ ነው።
11. ዳንኤል፣ ይሖዋ በመንግሥታት ላይ ሥልጣን እንዳለው የሚያሳይ ሌላስ ምን ተናግሯል?
11 ዳንኤል ያየው ራእይ ከዚያ ቀደም ከተናገረው ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነው። ዳንኤል “[የሰማይ አምላክ] ነገሥታትን ያስወግዳል፤ ደግሞም ያስቀምጣል” ብሏል። በተጨማሪም “ልዑሉ አምላክ በሰው ልጆች መንግሥት ላይ እንደሚገዛ እንዲሁም መንግሥቱን ለወደደው እንደሚሰጥ” ጽፏል። (ዳን. 2:19-21፤ 4:17) ለመሆኑ ይሖዋ ነገሥታትን ያስወገደበት ወይም ያስቀመጠበት ጊዜ አለ? ምን ጥያቄ አለው!
12. ይሖዋ በጥንት ዘመን ነገሥታትን ከዙፋናቸው እንዳስወገደ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ። (ሥዕሉን ተመልከት።)
12 ይሖዋ ‘ከበላይ ባለሥልጣናት’ የበለጠ ሥልጣን እንዳለው በግልጽ አሳይቷል። እስቲ ሦስት ምሳሌዎችን እንመልከት። የግብፁ ፈርዖን የይሖዋን ሕዝቦች በባርነት የገዛ ሲሆን እነሱን ለመልቀቅ ፈቃደኛ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ገልጿል። ሆኖም አምላክ ሕዝቡን ነፃ አውጥቷቸዋል፤ ፈርዖንንም በቀይ ባሕር አስጥሞታል። (ዘፀ. 14:26-28፤ መዝ. 136:15) የባቢሎኑ ንጉሥ ቤልሻዛር ድግስ ባዘጋጀበት ምሽት ‘በሰማያት ጌታ ላይ ታበየ’፤ እንዲሁም ከይሖዋ ይልቅ ‘ከብርና ከወርቅ የተሠሩ አማልክትን አወደሰ።’ (ዳን. 5:22, 23) ይሁን እንጂ አምላክ ይህን ትዕቢተኛ ሰው አዋረደው። “በዚያኑ ሌሊት” ቤልሻዛር ተገደለ። መንግሥቱም ለሜዶናውያንና ለፋርሳውያን ተሰጠ። (ዳን. 5:28, 30, 31) የፓለስቲናው ንጉሥ ቀዳማዊ ሄሮድስ አግሪጳ፣ ሐዋርያው ያዕቆብን ካስገደለ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስንም ሊገድለው በማሰብ አሰረው። ሆኖም ይሖዋ ሄሮድስ ዕቅዱን እንዲያሳካ አልፈቀደለትም፤ ‘የይሖዋ መልአክ ቀሰፈውና’ ሞተ።—ሥራ 12:1-5, 21-23
13. ይሖዋ ጥምረት የፈጠሩ ነገሥታትን ድል እንዳደረገ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።
13 ይሖዋ ጥምረት ከፈጠሩ መንግሥታትም በላይ ኃይል እንዳለው አሳይቷል። ለእስራኤላውያን በመዋጋት፣ ጥምረት የፈጠሩ 31 ከነአናውያን ነገሥታትን እንዲደመስሱ ረድቷቸዋል፤ እንዲሁም የተስፋይቱን ምድር አብዛኛውን ክፍል እንዲቆጣጠሩ አስችሏቸዋል። (ኢያሱ 11:4-6, 20፤ 12:1, 7, 24) በተጨማሪም ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ንጉሥ ቤንሃዳድንና ሌሎች 32 የሶርያ ነገሥታትን ሙሉ በሙሉ ድል እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል።—1 ነገ. 20:1, 26-29
14-15. (ሀ) ንጉሥ ናቡከደነጾርና ንጉሥ ዳርዮስ ስለ ይሖዋ ሉዓላዊነት ምን ተናግረዋል? (ለ) መዝሙራዊው ስለ ይሖዋና ስለ ሕዝቡ ምን ብሏል?
14 ይሖዋ ከሁሉ የላቀ አምላክ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል። የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነጾር፣ ውዳሴ የሚገባው ይሖዋ እንደሆነ በትሕትና ከመቀበል ይልቅ ‘ስለ ግርማው ክብር እንዲሁም ስለ ገዛ ብርታቱና ኃይሉ’ ጉራ በነዛበት ጊዜ አምላክ አእምሮውን እንዲስት አድርጎታል። ናቡከደነጾር አእምሮው ከተመለሰለት በኋላ ‘ልዑሉን አምላክ አመሰገነ’፤ እንዲሁም ‘የይሖዋ የመግዛት ሥልጣን ዘላለማዊ እንደሆነ’ አምኖ ተቀበለ። አክሎም “[እሱን] ሊያግደው . . . የሚችል ማንም የለም” ብሏል። (ዳን. 4:30, 33-35) ዳንኤል በአምላክ ፊት ያለው ንጹሕ አቋም ከተፈተነና ይሖዋ ከአንበሶች ጉድጓድ ካዳነው በኋላ ንጉሥ ዳርዮስ እንዲህ በማለት አውጇል፦ “ሰዎች የዳንኤልን አምላክ ፈርተው እንዲንቀጠቀጡ ትእዛዝ አስተላልፌአለሁ። እሱ ለዘላለም የሚኖር ሕያው አምላክ ነውና። መንግሥቱ ፈጽሞ አይጠፋም፤ ሉዓላዊነቱም ዘላለማዊ ነው።”—ዳን. 6:7-10, 19-22, 26, 27 ግርጌ
15 መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ የብሔራትን ሴራ አክሽፏል፤ የሕዝቦችን ዕቅድ አጨናግፏል።” አክሎም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ አምላኩ የሆነ ብሔር፣ የራሱ ንብረት አድርጎ የመረጠው ሕዝብ ደስተኛ ነው።” (መዝ. 33:10, 12) በእርግጥም በይሖዋ ፊት ያለንን ንጹሕ አቋም የምንጠብቅበት በቂ ምክንያት አለን።
የመጨረሻው ጦርነት
16. ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ምን እንደሚሆን መተማመን እንችላለን? ለምንስ? (ሥዕሉን ተመልከት።)
16 ይሖዋ በጥንት ዘመን ምን እንዳደረገ አንብበናል። በቅርቡስ ምን እንደሚሆን መጠበቅ እንችላለን? ይሖዋ በመጪው “ታላቅ መከራ” ወቅት ታማኝ አገልጋዮቹን እንደሚያድናቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ማቴ. 24:21፤ ዳን. 12:1) ይህን የሚያደርገው፣ የማጎጉ ጎግ ማለትም ግንባር የፈጠሩ ብሔራት በዓለም ዙሪያ ባሉ ታማኝ የይሖዋ ሕዝቦች ላይ በጭካኔ ጥቃት በሚሰነዝሩበት ወቅት ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል የሆኑት 193 አገራት በሙሉ ግንባር ቢፈጥሩ እንኳ ከሁሉ ከላቀው አምላክና ከሰማያዊ ሠራዊቱ ጋር ሊተካከሉ አይችሉም። ይሖዋ እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል፦ “ራሴን ገናና አደርጋለሁ፤ እንዲሁም ራሴን እቀድሳለሁ፤ በብዙ ብሔራትም ፊት ማንነቴ እንዲታወቅ አደርጋለሁ፤ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።”—ሕዝ. 38:14-16, 23፤ መዝ. 46:10
17. መጽሐፍ ቅዱስ የምድር ነገሥታትና በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ሰዎች ምን እንደሚጠብቃቸው ይናገራል?
17 የጎግ ጥቃት ይሖዋ የመጨረሻውን ጦርነት እንዲያካሂድ ያነሳሳዋል። ይሖዋ ‘የዓለምን ነገሥታት ሁሉ’ በአርማጌዶን ያጠፋቸዋል። (ራእይ 16:14, 16፤ 19:19-21) በአንጻሩ “በምድር ላይ የሚኖሩት ቅኖች ብቻ [ይሆናሉ]፤ በእሷም ላይ የሚቀሩት ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ናቸው።”—ምሳሌ 2:21 ግርጌ
ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ አለብን
18. ብዙ እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ለማድረግ ፈቃደኞች ሆነዋል? ለምንስ? (ዳንኤል 3:28)
18 ባለፉት ዘመናት በርካታ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሉዓላዊ ገዢያቸው ለሆነው ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር የተነሳ ነፃነታቸውን አልፎ ተርፎም ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለዋል። እነዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች በይሖዋ ፊት ያላቸውን ንጹሕ አቋም ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። አቋማቸው ከሁሉ ለላቀው አምላክ ታማኝነታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ወደ እቶን እሳት ቢጣሉም በሕይወት ከተረፉት ሦስት ዕብራውያን ጋር ተመሳሳይ ነው።—ዳንኤል 3:28ን አንብብ።
19. ይሖዋ በሕዝቡ ላይ የሚፈርደው ምንን መሠረት አድርጎ ነው? ይህስ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?
19 መዝሙራዊው ዳዊት በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋምን መጠበቅ ያለውን አስፈላጊነት ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ በሕዝቦች ላይ ፍርድ ያስተላልፋል። ይሖዋ ሆይ፣ እንደ ጽድቄ፣ እንደ ንጹሕ አቋሜም ፍረድልኝ።” (መዝ. 7:8) በሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ዳዊት “ንጹሕ አቋሜና ቅንነቴ ይጠብቁኝ” በማለት ጽፏል። (መዝ. 25:21) ከሁሉ የተሻለው የሕይወት ጎዳና፣ ምንም ነገር ቢመጣ ምንጊዜም ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት መጠበቅ ነው። እንዲህ ካደረግን እንደ መዝሙራዊው ዓይነት ስሜት ይኖረናል፤ መዝሙራዊው “ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ፣ በይሖዋ ሕግ የሚመላለሱ ሰዎች ደስተኞች ናቸው” ብሏል።—መዝ. 119:1 ግርጌ
መዝሙር 122 ጸንታችሁ ቁሙ፣ አትነቃነቁ!
a መጽሐፍ ቅዱስ፣ ክርስቲያኖች ለበላይ ባለሥልጣናት ማለትም በዚህ ዓለም ውስጥ ላሉ መንግሥታት መታዘዝ እንዳለባቸው ይናገራል። ይሁንና አንዳንድ መንግሥታት ይሖዋንና አገልጋዮቹን በግልጽ ይቃወማሉ። ታዲያ በአንድ በኩል ባለሥልጣናትን እየታዘዝን በሌላ በኩል ደግሞ በይሖዋ ፊት ያለንን ንጹሕ አቋም ጠብቀን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?
b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ በይሖዋ ፊት ያለንን ንጹሕ አቋም እንጠብቃለን ሲባል ፈተና ቢደርስብንም እንኳ ለእሱና ለሉዓላዊነቱ ያለንን ታማኝነት ፈጽሞ አናላላም ማለት ነው።
c በዚህ እትም ውስጥ የሚገኘውን “የጥንቶቹ እስራኤላውያን በጦርነት ተካፍለዋል—እኛስ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።