በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 41

እውነተኛ ደስታ ማግኘት ትችላላችሁ

እውነተኛ ደስታ ማግኘት ትችላላችሁ

“ይሖዋን የሚፈሩ፣ በመንገዱም የሚሄዱ ሁሉ ደስተኞች ናቸው።”—መዝ. 128:1

መዝሙር 110 “የይሖዋ ደስታ”

ማስተዋወቂያ a

1. ‘መንፈሳዊ ፍላጎት’ ምንድን ነው? ከደስታ ጋር የሚያያዘውስ እንዴት ነው?

 እውነተኛ ደስታ የሚያመለክተው ጊዜያዊ የሆነን የደስታ ስሜት ብቻ አይደለም። በመላው ሕይወታችን እውነተኛ ደስታ ማግኘት እንችላለን። እንዴት? ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ማቴ. 5:3 ግርጌ) ኢየሱስ ሰዎች ሲፈጠሩ ጀምሮ ፈጣሪያቸውን ይሖዋ አምላክን የማወቅና የማምለክ ልባዊ ፍላጎት እንዳላቸው ያውቃል። ‘መንፈሳዊ ፍላጎት’ ማለት ይህ ነው። ደግሞም ይሖዋ ‘ደስተኛ አምላክ’ ስለሆነ እሱን የሚያመልኩ ሰዎችም ደስተኛ መሆን ይችላሉ።—1 ጢሞ. 1:11

“ለጽድቅ ሲሉ ስደት የሚደርስባቸው ደስተኞች ናቸው።”—ማቴ. 5:10 (ከአንቀጽ 2-3⁠ን ተመልከት) d

2-3. (ሀ) ኢየሱስ እነማን ደስተኞች እንደሆኑ ተናግሯል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን? ይህ አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

2 ደስተኛ መሆን የምንችለው ሕይወታችን አልጋ በአልጋ ከሆነልን ብቻ ነው? አይደለም። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ አስገራሚ ነገር ተናግሯል። “የሚያዝኑ ደስተኞች ናቸው” ብሏል፤ ምናልባትም ያዘኑት በሠሩት ኃጢአት ምክንያት በሚሰማቸው የጥፋተኝነት ስሜት አሊያም በሕይወታቸው ውስጥ ባጋጠማቸው አስጨናቂ ሁኔታ የተነሳ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ “ለጽድቅ ሲሉ ስደት የሚደርስባቸው” ወይም የክርስቶስ ተከታዮች በመሆናቸው ምክንያት ‘የሚነቀፉ’ ሰዎችም ደስተኞች እንደሆኑ ተናግሯል። (ማቴ. 5:4, 10, 11) ይሁንና እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እውነተኛ ደስታ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ ደስታ የሚያስገኝልን የተመቻቸ ሕይወት መምራታችን ሳይሆን መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማሟላታችንና ወደ አምላክ መቅረባችን መሆኑን ሊያስተምረን ፈልጓል። (ያዕ. 4:8) ታዲያ እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ልንወስዳቸው የሚገቡ ሦስት መሠረታዊ እርምጃዎችን በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።

መንፈሳዊ ምግብ ተመገቡ

4. እውነተኛ ደስታ ለማግኘት መውሰድ ያለብን የመጀመሪያ እርምጃ ምንድን ነው? (መዝሙር 1:1-3)

4 አንደኛ፣ እውነተኛ ደስታ ለማግኘት መንፈሳዊ ምግብ መመገብ አለብን። ሰዎችም ሆኑ እንስሳት በሕይወት ለመኖር ሥጋዊ ምግብ ያስፈልጋቸዋል። መንፈሳዊ ምግብ መመገብ የምንችለው ግን እኛ ሰዎች ብቻ ነን። ደግሞም መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልገናል። ኢየሱስ “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም” ያለው ለዚህ ነው። (ማቴ. 4:4) በመሆኑም የአምላክ ውድ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ምግብ ሳንመገብ አንድም ቀን እንዲያልፍብን መፍቀድ የለብንም። መዝሙራዊው ‘በይሖዋ ሕግ ደስ የሚለው እንዲሁም ሕጉን በቀንና በሌሊት የሚያነብ ሰው ደስተኛ እንደሆነ’ ተናግሯል።—መዝሙር 1:1-3ን አንብብ።

5-6. (ሀ) ከመጽሐፍ ቅዱስ ምን እንማራለን? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን የሚጠቅመን በየትኞቹ መንገዶች ነው?

5 ይሖዋ ስለሚወደን ደስተኛ ሕይወት መምራት የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወሳኝ መረጃ ሰጥቶናል። የሕይወታችን ዓላማ ምን እንደሆነ እንማራለን። ወደ አምላክ መቅረብና ለኃጢአታችን ይቅርታ ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን። በተጨማሪም የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ ስለሰጠን ግሩም ተስፋ እንማራለን። (ኤር. 29:11) ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የምንማራቸው እነዚህ እውነቶች ልባችን በደስታ እንዲሞላ ያደርጋሉ።

6 እንደምናውቀው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚጠቅሙ ምክሮችንም ይዟል። እነዚህን ምክሮች በሥራ ላይ ስናውል ደስታ እናገኛለን። ባጋጠሟችሁ ችግሮች ምክንያት ተስፋ በምትቆርጡበት ጊዜ የይሖዋን ቃል ለማንበብና ለማሰላሰል ተጨማሪ ጊዜ መድቡ። ኢየሱስ “ደስተኞችስ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው” ብሏል።—ሉቃስ 11:28

7. ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችሁ ይበልጥ ጥቅም ለማግኘት ምን ይረዳችኋል?

7 የአምላክን ቃል ስታነቡ ጊዜ ወስዳችሁ የምታነቡትን ነገር ለማጣጣም ጥረት አድርጉ። አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ሰው የምትወዱትን ምግብ ሠራላችሁ እንበል። ሆኖም በመቸኮላችሁ ወይም አእምሯችሁ በሌላ ሐሳብ በመወጠሩ የተነሳ ምግቡን ምንም ሳታጣጥሙት በልታችሁ ጨረሳችሁ። በልታችሁ ከጨረሳችሁ በኋላ በጣም በጥድፊያ እንደበላችሁ ትገነዘባላችሁ፤ ‘ምን አለ ቀስ ብዬ እያንዳንዱን ጉርሻ ባጣጣምኩት ኖሮ’ ብላችሁ ታስባላችሁ። መጽሐፍ ቅዱስን በምታነቡበት ጊዜም በጣም በችኮላ ከማንበባችሁ የተነሳ መልእክቱን ሳታጣጥሙ ቀርታችሁ ታውቃላችሁ? ጊዜ ወስዳችሁ የአምላክን ቃል በማንበብ ተደሰቱ፤ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናችሁ ሣሉ፤ የሚሰማውን ድምፅ ለመስማት ሞክሩ፤ እንዲሁም ስለምታነቡት ነገር ቆም ብላችሁ አስቡ። በዚህ መልኩ ማንበባችሁ ደስታችሁን ይጨምርላችኋል።

8. “ታማኝና ልባም ባሪያ” የተሰጠውን ኃላፊነት እየተወጣ ያለው እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

8 ኢየሱስ በተገቢው ጊዜ ምግብ እንዲያቀርብ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ ሾሞታል፤ ደግሞም የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እያቀረበልን ነው። b (ማቴ. 24:45) ታማኙ ባሪያ የሚያዘጋጃቸው ነገሮች በሙሉ በዋነኝነት የተመሠረቱት በመንፈስ መሪነት በተጻፈው በአምላክ ቃል ላይ ነው። (1 ተሰ. 2:13) በመሆኑም ይህ መንፈሳዊ ምግብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን የይሖዋን አስተሳሰብ ለማወቅ ይረዳናል። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን እንዲሁም jw.org ላይ የሚወጡ ርዕሶችን የምናነበው ለዚህ ነው። በሳምንቱ መሃልና በሳምንቱ መጨረሻ ለምናደርጋቸው የጉባኤ ስብሰባዎች እንዘጋጃለን። በተጨማሪም በቋንቋችን የሚገኙ ከሆነ በየወሩ የሚወጡትን የJW ብሮድካስቲንግ ፕሮግራሞች እንመለከታለን። የሚቀርብልንን መንፈሳዊ ምግብ በደንብ መመገባችን እውነተኛ ደስታ የሚያስገኘውን ሁለተኛውን እርምጃ ለመውሰድ ይረዳናል።

በይሖዋ መሥፈርቶች ተመሩ

9. እውነተኛ ደስታ ለማግኘት መውሰድ ያለብን ሁለተኛው እርምጃ ምንድን ነው?

9 ሁለተኛ፣ እውነተኛ ደስታ ለማግኘት በይሖዋ መሥፈርቶች መመራት ይኖርብናል። መዝሙራዊው “ይሖዋን የሚፈሩ፣ በመንገዱም የሚሄዱ ሁሉ ደስተኞች ናቸው” በማለት ጽፏል። (መዝ. 128:1) ይሖዋን እንፈራዋለን ሲባል እሱን በጣም ስለምናከብረው እሱን የሚያሳዝን ምንም ነገር ከማድረግ እንቆጠባለን ማለት ነው። (ምሳሌ 16:6) በመሆኑም አምላክ ትክክልና ስህተት የሆኑ ነገሮችን በተመለከተ ያወጣውን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ መሥፈርት ምንጊዜም ለመከተል ጥረት እናደርጋለን። (2 ቆሮ. 7:1) ይሖዋ የሚወዳቸውን ነገሮች ካደረግን፣ ከሚጠላቸው ነገሮች ደግሞ ከራቅን ደስተኛ እንሆናለን።—መዝ. 37:27፤ 97:10፤ ሮም 12:9

10. በሮም 12:2 መሠረት ምን ኃላፊነት አለብን?

10 ሮም 12:2ን አንብብ። አንድ ሰው ትክክልና ስህተት የሆኑ ነገሮችን በተመለከተ መሥፈርት የማውጣት መብት ያለው ይሖዋ እንደሆነ ያውቅ ይሆናል። ሆኖም በአምላክ መሥፈርቶች ለመመራት መወሰንም አለበት። ለምሳሌ አንድ ሰው፣ መንግሥት የተሽከርካሪዎችን የፍጥነት ወሰን የመደንገግ መብት እንዳለው ያውቅ ይሆናል። ሆኖም በዚህ ሕግ ለመመራት ላይፈልግ ይችላል። በመሆኑም ከፍጥነት ወሰን በላይ ያሽከረክራል። የይሖዋን መሥፈርቶች መከተል ከሁሉ የተሻለ የሕይወት ጎዳና እንደሆነ በእርግጥ እንደምናምን ማሳየት የምንችለው በምግባራችን ነው። (ምሳሌ 12:28) ዳዊት ስለ ይሖዋ የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ እንዲህ ያለ አመለካከት እንደነበረው ያሳያል፦ “የሕይወትን መንገድ አሳወቅከኝ። በፊትህ ብዙ ደስታ አለ፤ በቀኝህ ለዘላለም ደስታ አለ።”—መዝ. 16:11

11-12. (ሀ) የሚያስጨንቅ ወይም የሚያሳዝን ነገር ሲያጋጥመን ምን እንዳናደርግ መጠንቀቅ ይኖርብናል? (ለ) መዝናኛ በምንመርጥበት ጊዜ ፊልጵስዩስ 4:8 የሚረዳን እንዴት ነው?

11 የሚያስጨንቅ ወይም የሚያሳዝን ነገር ሲያጋጥመን ከችግራችን ለመሸሽ ትኩረታችንን የሚሰርቅልን ነገር እንፈልግ ይሆናል። እንዲህ ቢሰማን አያስገርምም። ሆኖም ይሖዋ የሚጠላውን ነገር እንዳናደርግ መጠንቀቅ ይኖርብናል።—ኤፌ. 5:10-12, 15-17

12 ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ክርስቲያኖች ‘ጽድቅ፣ ንጹሕ፣ ተወዳጅና በጎ’ የሆነውን ነገር ማሰባቸውን እንዳያቋርጡ አበረታቷቸዋል። (ፊልጵስዩስ 4:8ን አንብብ።) ጳውሎስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው ስለ መዝናኛ ባይሆንም የጻፈው ሐሳብ የመዝናኛ ምርጫችንንም ሊነካው ይገባል። እስቲ እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ጥቅሱ ላይ “ነገር” የሚለው ቃል በሚገኝበት ቦታ ሁሉ “ሙዚቃ፣” “ፊልም፣” “መጽሐፍ” ወይም “ቪዲዮ ጌም” የሚለውን ቃል ተኩ። እንዲህ ማድረጋችሁ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውና የሌላቸው መዝናኛዎች የትኞቹ እንደሆኑ ለመለየት ይረዳችኋል። ላቅ ያሉትን የይሖዋን መሥፈርቶች መከተል እንፈልጋለን። (መዝ. 119:1-3) እንዲህ ካደረግን እውነተኛ ደስታ የሚያስገኘውን ቀጣዩን እርምጃ በንጹሕ ሕሊና መውሰድ እንችላለን።—ሥራ 23:1

የይሖዋን አምልኮ አስቀድሙ

13. እውነተኛ ደስታ የሚያስገኘው ሦስተኛው እርምጃ ምንድን ነው? (ዮሐንስ 4:23, 24)

13 ሦስተኛ፣ በሕይወታችሁ ውስጥ የይሖዋን አምልኮ አስቀድሙ። ይሖዋ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን አምልኳችን ይገባዋል። (ራእይ 4:11፤ 14:6, 7) በመሆኑም እሱ በሚፈልገው መንገድ ማለትም “በመንፈስና በእውነት” እሱን ለማምለክ ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል። (ዮሐንስ 4:23, 24ን አንብብ።) በቃሉ ውስጥ ከሚገኙት እውነቶች ጋር በሚስማማ መንገድ አምልኮ ማቅረብ እንድንችል በአምላክ ቅዱስ መንፈስ መመራት ይኖርብናል። የምንኖረው በሥራችን ላይ እገዳ ወይም ገደብ በተጣለበት አገር ውስጥ ቢሆንም እንኳ ለአምልኳችን ቅድሚያ መስጠት አለብን። በአሁኑ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናቸው ምክንያት ብቻ የታሰሩ ከ100 በላይ ወንድሞችና እህቶች አሉ። c ያም ቢሆን ለመጸለይ፣ ለማጥናት እንዲሁም ስለ አምላካችንና ስለ መንግሥቱ ለሌሎች ለመናገር አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ በደስታ ያደርጋሉ። ነቀፋ ወይም ስደት ሲደርስብን ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደሆነና ወሮታ እንደሚከፍለን ማወቃችን ያስደስተናል።—ያዕ. 1:12፤ 1 ጴጥ. 4:14

እውነተኛ ታሪክ

14. በታጂኪስታን የሚኖር አንድ ወጣት ወንድም ምን ደርሶበታል? ለምንስ?

14 ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ አሁን የጠቀስናቸውን ሦስት እርምጃዎች መውሰዳችን እውነተኛ ደስታ እንደሚያስገኝልን የሚያረጋግጡ በርካታ ተሞክሮዎች አሉ። በታጂኪስታን የሚኖረው የ19 ዓመቱ ጆቪዶን ቦቦጆኖቭ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት የደረሰበትን ነገር እንደ ምሳሌ እንመልከት። ጥቅምት 4, 2019 ወታደሮች ከቤቱ አስገድደው ወሰዱት፤ ከዚያም ለወራት በእስር የቆየ ሲሆን እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ብዙ እንግልት ደርሶበታል። የደረሰበት ግፍ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት ስቧል። ወታደሮች፣ ጆቪዶን የውትድርና ቃለ መሐላ እንዲፈጽምና የወታደር የደንብ ልብስ እንዲለብስ ለማስገደድ ሲሉ እንደደበደቡት ሪፖርት ተደርጓል። ከዚያ በኋላ ጥፋተኛ ነው ተብሎ ተፈርዶበት ወደ ወህኒ ወረደ። በመጨረሻም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በምሕረት ከእስር አስፈቱት። ጆቪዶን ይህ ሁሉ መከራ ቢደርስበትም ንጹሕ አቋሙንና ደስታውን ጠብቋል። እንዴት? ምንጊዜም ለመንፈሳዊ ፍላጎቱ ንቁ በመሆን ነው።

ጆቪዶን መንፈሳዊ ምግብ ተመግቧል፤ በአምላክ መሥፈርቶች ተመርቷል፤ እንዲሁም የይሖዋን አምልኮ በሕይወቱ ውስጥ አስቀድሟል (ከአንቀጽ 15-17⁠ን ተመልከት)

15. ጆቪዶን እስር ቤት በነበረበት ወቅት መንፈሳዊ ምግብ የሚያገኘው እንዴት ነበር?

15 ጆቪዶን እስር ቤት በነበረበት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ሌላ ጽሑፍ ባይኖረውም መንፈሳዊ ምግብ ይመገብ ነበር። እንዴት? ወንድሞችና እህቶች ምግብ ሲወስዱለት ምግቡን በሚያመጡበት ፌስታል ላይ የዕለቱን ጥቅስ ይጽፉለት ነበር። በመሆኑም በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ማሰላሰል ችሏል። ከእስር ከተፈታ በኋላ፣ እስካሁን ከባድ ፈተና ላላጋጠማቸው ክርስቲያኖች እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል፦ “ነፃነታችሁን የአምላክን ቃልና ድርጅቱ ያዘጋጃቸውን ጽሑፎች በማንበብ ስለ ይሖዋ ያላችሁን እውቀት ለማሳደግ ልትጠቀሙበት ይገባል።”

16. ጆቪዶን በምን ላይ አተኩሯል?

16 ወንድማችን በይሖዋ መሥፈርቶች ይመራ ነበር። በተሳሳቱ ሐሳቦች ላይ ከማውጠንጠን ወይም መጥፎ ድርጊት ከመፈጸም ይልቅ በይሖዋና እሱ ከፍ አድርጎ በሚመለከታቸው ነገሮች ላይ አተኩሯል። ጆቪዶን የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች በአድናቆት ይመለከት ነበር። ሁልጊዜ ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነሳ የወፎችን ዝማሬ ይሰማል። ምሽት ላይ ደግሞ ጨረቃንና ከዋክብትን ይመለከታል። እንዲህ ብሏል፦ “ከይሖዋ ያገኘኋቸው እነዚህ ስጦታዎች ደስተኛ እንድሆንና እንድበረታ ረድተውኛል።” ይሖዋ ለሰጠን ሥጋዊና መንፈሳዊ ነገሮች አመስጋኞች ከሆንን ደስተኛ ልብ ይኖረናል። ይህ ደስታ ደግሞ መጽናት እንድንችል ብርታት ይሰጠናል።

17. አንደኛ ጴጥሮስ 1:6, 7 እንደ ጆቪዶን ዓይነት ሁኔታ ላጋጠማቸው ክርስቲያኖች የሚሠራው እንዴት ነው?

17 በተጨማሪም ጆቪዶን የይሖዋን አምልኮ አስቀድሟል። ለእውነተኛው አምላክ ያለውን ታማኝነት መጠበቁ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ኢየሱስ “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ” ብሏል። (ሉቃስ 4:8) የጦር አዛዦችና ወታደሮች ጆቪዶን ሃይማኖቱን እንዲክድ ለማድረግ ፈልገው ነበር። እሱ ግን እጅ ላለመስጠትና አቋሙን ላለማላላት እንዲረዳው በየዕለቱ፣ ቀንም ሆነ ማታ ወደ ይሖዋ አጥብቆ ይጸልይ ነበር። ጆቪዶን ብዙ ግፍ ቢደርስበትም አቋሙን አላላላም። በውጤቱም ከመያዙ፣ ከመደብደቡና ከመታሰሩ በፊት ያልነበረውን ነገር ይኸውም ተፈትኖ የተረጋገጠ እምነት ማግኘት ችሏል፤ በዚህም በጣም ደስተኛ ነው።—1 ጴጥሮስ 1:6, 7ን አንብብ።

18. ደስታችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

18 እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ምን እንደሚያስፈልገን ይሖዋ ያውቃል። እውነተኛ ደስታ የሚያስገኙትን ሦስቱን እርምጃዎች ከወሰዳችሁ ከባድ ችግሮች ቢያጋጥሟችሁም ደስታችሁን መጠበቅ ትችላላችሁ። እንዲህ ካደረጋችሁ እናንተም “አምላኩ ይሖዋ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው” ማለት ትችላላችሁ!—መዝ. 144:15

መዝሙር 89 ስማ፣ ታዘዝ፤ ትባረካለህ

a ብዙ ሰዎች እውነተኛ ደስታ ማግኘት ከባድ ሆኖባቸዋል፤ ምክንያቱም ደስታ ለማግኘት የሚሞክሩት በተሳሳተ መንገድ ይኸውም ተድላን፣ ሀብትን፣ ዝናን ወይም ሥልጣንን በማሳደድ ነው። ይሁንና ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት እውነተኛ ደስታ ማግኘት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ አስተምሯል። እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ልንወስዳቸው የሚገቡ ሦስት እርምጃዎችን በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።

b በነሐሴ 15, 2014 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “‘በተገቢው ጊዜ ምግብ’ እያገኘህ ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

c ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት jw.org ላይ “በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ” ብለህ ፈልግ።

d የሥዕሉ መግለጫ፦ በትወና መልክ በቀረበው ፎቶግራፍ ላይ አንድ ወንድም ተይዞ ወደ ፍርድ ቤት ሲወሰድ የእምነት ባልንጀሮቹ ድጋፍ ሲያሳዩት።