በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 44

ክርስቲያናዊ ተስፋችሁን አጠናክሩ

ክርስቲያናዊ ተስፋችሁን አጠናክሩ

“ይሖዋን ተስፋ አድርግ።”—መዝ. 27:14

መዝሙር 144 ዓይንህ ሽልማቱ ላይ ያተኩር!

ማስተዋወቂያ a

1. ይሖዋ ምን ተስፋ ሰጥቶናል?

 ይሖዋ አስደናቂ የሆነውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ሰጥቶናል። አንዳንዶች የማይሞት መንፈሳዊ አካል ለብሰው በሰማይ ላይ ለመኖር ተስፋ ያደርጋሉ። (1 ቆሮ. 15:50, 53) አብዛኞቹ ሰዎች ደግሞ ፍጹም ጤንነትና ደስታ አግኝተው በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ያደርጋሉ። (ራእይ 21:3, 4) ተስፋችን ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ፣ ተስፋችንን ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን።

2. ተስፋችን በምን ላይ የተመሠረተ ነው? እንዲህ የምንለውስ ለምንድን ነው?

2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ተስፋ” የሚለው ቃል “ጥሩ ነገር እንደሚመጣ መጠበቅ” የሚል ፍቺ አለው። ስለ ወደፊቱ ጊዜ የተሰጠን ተስፋ እንደሚፈጸም እርግጠኞች ነን፤ ምክንያቱም የተስፋችን ምንጭ ይሖዋ ነው። (ሮም 15:13) ይሖዋ የገባልንን ቃል እናውቃለን፤ ቃሉን ምንጊዜም እንደሚፈጽምም እናውቃለን። (ዘኁ. 23:19) ይሖዋ ‘አደርገዋለሁ’ ያለውን ነገር ሁሉ ለመፈጸም ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ እንዳለው እርግጠኞች ነን። በመሆኑም ተስፋችን በምኞት ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በማስረጃና በእውነታ ላይ የተመሠረተ ነው።

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን? (መዝሙር 27:14)

3 የሰማዩ አባታችን ይወደናል፤ እንድንታመንበትም ይፈልጋል። (መዝሙር 27:14ን አንብብ።) በይሖዋ ላይ ያለን ተስፋ ጠንካራ ከሆነ ፈተናዎችን መወጣት እንዲሁም የወደፊቱን ጊዜ በድፍረትና በደስታ መጠባበቅ እንችላለን። ተስፋችን ጥበቃ የሚያደርግልን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። በመጀመሪያ ግን፣ ተስፋ ከመልሕቅና ከራስ ቁር ጋር የሚመሳሰለው እንዴት እንደሆነ እናያለን። ከዚያም ተስፋችንን ማጠናከር የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

ተስፋችን እንደ መልሕቅ ነው

4. ተስፋ እንደ መልሕቅ የሆነው እንዴት ነው? (ዕብራውያን 6:19)

4 ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ተስፋችንን ከመልሕቅ ጋር አመሳስሎታል። (ዕብራውያን 6:19ን አንብብ።) ጳውሎስ ብዙ ጊዜ በባሕር ላይ ይጓዝ ስለነበር መልሕቅ አንድን መርከብ ቀስ በቀስ እየራቀ እንዳይሄድ እንደሚያደርገው ያውቃል። በአንድ ወቅት ጳውሎስ በመርከብ እየተጓዘ ሳለ ኃይለኛ ማዕበል ተነሳ። በዚያ ወቅት መርከበኞቹ ከዓለት ጋር እንላተማለን ብለው ስለፈሩ መልሕቃቸውን ሲጥሉ ተመልክቷል። (ሥራ 27:29, 39-41) መልሕቅ አንድን መርከብ አጽንቶ እንደሚያቆም ሁሉ ተስፋችንም እንደ ማዕበል ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ከይሖዋ እየራቅን እንዳንሄድ ይረዳናል። ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ጽኑ ተስፋ ስላለን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መወጣት እንችላለን። ኢየሱስ ስደት እንደሚደርስብን እንዳስጠነቀቀን አትርሱ። (ዮሐ. 15:20) በመሆኑም ወደፊት በምናገኘው በረከት ላይ ማሰላሰላችን በክርስትና ጎዳና ላይ ጸንተን ለመመላለስ ይረዳናል።

5. ኢየሱስ ከሞት ጋር በተፋጠጠበት ወቅት ተስፋ የረዳው እንዴት ነው?

5 ኢየሱስ በአሰቃቂ ሁኔታ እንደሚገደል ቢያውቅም ተስፋው ጽኑ እንዲሆን የረዳው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ሐዋርያው ጴጥሮስ ከመዝሙር መጽሐፍ ላይ አንድ ትንቢት ጠቅሶ ነበር፤ ትንቢቱ ኢየሱስ የነበረውን የመተማመን ስሜት ግሩም አድርጎ የሚገልጽ ነው፤ እንዲህ ይላል፦ “በተስፋ እኖራለሁ፤ ምክንያቱም በመቃብር አትተወኝም፤ ታማኝ አገልጋይህም መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም። . . . በፊትህ በታላቅ ደስታ እንድሞላ ታደርገኛለህ።” (ሥራ 2:25-28፤ መዝ. 16:8-11) ኢየሱስ እንደሚሞት ቢያውቅም አምላክ ከሞት እንደሚያስነሳውና ወደ ሰማይ ተመልሶ ከአባቱ ጋር በደስታ እንደሚኖር ጠንካራ ተስፋ ነበረው።—ዕብ. 12:2, 3

6. አንድ ወንድም ስለ ተስፋ ምን ብሏል?

6 ብዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ክርስቲያናዊ ተስፋቸው እንዲጸኑ ረድቷቸዋል። በእንግሊዝ ይኖር የነበረውን ሌነርድ ቺን የተባለ ታማኝ ወንድማችንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሌነርድ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጦር ሠራዊቱን ለመቀላቀል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ታስሮ ነበር። ለሁለት ወራት ለብቻው ታሰረ፤ ከዚያም ከባድ የጉልበት ሥራ እንዲሠራ ተገደደ። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ያጋጠመኝ ነገር፣ ለመጽናት ተስፋ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አስገንዝቦኛል። ኢየሱስ፣ ሐዋርያትና ነቢያት ግሩም ምሳሌ ትተውልናል፤ በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ አስደናቂ ቃል ገብቶልናል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለወደፊቱ ጊዜ አስደሳች ተስፋ ይሰጡናል፤ እንድንጸናም ይረዱናል።” ተስፋ ለሌነርድ መልሕቅ ሆኖለታል፤ ለእኛም መልሕቅ ሊሆንልን ይችላል።

7. ፈተናዎች ተስፋችንን የሚያጠናክሩልን እንዴት ነው? (ሮም 5:3-5፤ ያዕቆብ 1:12)

7 ፈተናዎችን በጽናት ስንወጣ የይሖዋን እርዳታ ማየትና ሞገሱን ማግኘት እንችላለን፤ ይህ ደግሞ ተስፋችንን ያጠናክረዋል። (ሮም 5:3-5፤ ያዕቆብ 1:12ን አንብብ።) በዚህ ጊዜ፣ ምሥራቹን መጀመሪያ ስንሰማ ከነበረን ይበልጥ ጠንካራ የሆነ ተስፋ ይኖረናል። ሰይጣን የሚያጋጥሙን ፈተናዎች ተስፋ እንዲያስቆርጡን ይፈልጋል። ሆኖም በይሖዋ እርዳታ እያንዳንዱን ፈተና መወጣት እንችላለን።

ተስፋችን እንደ ራስ ቁር ነው

8. ተስፋ እንደ ራስ ቁር የሆነው እንዴት ነው? (1 ተሰሎንቄ 5:8)

8 መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋችንን ከራስ ቁር ጋርም ያመሳስለዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:8ን አንብብ።) ወታደሮች የራስ ቁር የሚያደርጉት ጭንቅላታቸውን ጠላት ከሚሰነዝረው ጥቃት ለመከላከል ነው። እኛም በምናደርገው መንፈሳዊ ውጊያ ላይ አእምሯችንን ከሰይጣን ጥቃቶች መከላከል ይጠበቅብናል። ሰይጣን አስተሳሰባችንን የሚመርዙ ሐሳቦችንና ፈተናዎችን ያዥጎደጉድብናል። የራስ ቁር የአንድን ወታደር ጭንቅላት እንደሚጠብቅለት ሁሉ ተስፋችን ለይሖዋ ታማኝ መሆን እንድንችል አስተሳሰባችንን ይጠብቅልናል።

9. ተስፋ የሌላቸው ሰዎች ሕይወታቸው ምን ይመስላል?

9 የዘላለም ሕይወት ተስፋችን በጥበብና በማስተዋል እንድንመላለስ ይረዳናል። በሌላ በኩል ግን ተስፋችን ከደበዘዘና ሥጋዊ አስተሳሰብ አእምሯችንን እንዲቆጣጠረው ከፈቀድን የዘላለም ሕይወት ተስፋችንን ልንረሳው እንችላለን። በጥንቷ ቆሮንቶስ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ወሳኝ በሆነው የትንሣኤ ተስፋ ላይ እምነት አጥተው ነበር። (1 ቆሮ. 15:12) ጳውሎስ፣ ለወደፊቱ ጊዜ ተስፋ የሌላቸው ሰዎች የሚኖሩት ለዛሬ ብቻ እንደሆነ ተናግሯል። (1 ቆሮ. 15:32) በዛሬው ጊዜም አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት የሌላቸው ብዙ ሰዎች የሚኖሩት ለዕለቱ ብቻ ነው፤ የሚያሳስባቸው የአሁኑን ሕይወታቸውን አስደሳች የማድረጉ ጉዳይ ብቻ ነው። እኛ ግን አምላክ በሰጠን የወደፊት ተስፋ ላይ እምነት አለን። ተስፋችን እንደ ራስ ቁር በመሆን አስተሳሰባችንን ይጠብቅልናል፤ በተጨማሪም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና የሚያበላሽ የራስ ወዳድነት ሕይወት እንዳንመራ ይረዳናል።—1 ቆሮ. 15:33, 34

10. ተስፋ ከውሸት አስተሳሰብ የሚጠብቀን እንዴት ነው?

10 እንደ ራስ ቁር የሆነው ተስፋችን ‘ይሖዋን ለማስደሰት መሞከር ዋጋ የለውም’ ከሚለው አስተሳሰብ እንድንጠበቅ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች እንዲህ ይሉ ይሆናል፦ ‘እኔ በፍጹም የዘላለም ሕይወት ላገኝ አልችልም። ብቁ አይደለሁም። የአምላክን መሥፈርቶች ላሟላ አልችልም።’ የኢዮብ የውሸት አጽናኝ የሆነው ኤሊፋዝም ተመሳሳይ ሐሳብ እንደተናገረ አስታውሱ። ኤሊፋዝ “ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሟች የሆነ ሰው ምንድን ነው?” ብሏል። አክሎም ስለ አምላክ ሲናገር “እነሆ፣ በቅዱሳኑ ላይ እምነት የለውም፤ ሰማያትም እንኳ በፊቱ ንጹሐን አይደሉም” ብሏል። (ኢዮብ 15:14, 15) ይህ ዓይን ያወጣ ውሸት ነው! እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የሚመነጨው ከሰይጣን ነው። ሰይጣን እንዲህ ባሉ ሐሳቦች ላይ ካውጠነጠናችሁ ተስፋችሁ እንደሚደበዝዝ ያውቃል። በመሆኑም እንዲህ ያሉ ውሸቶችን ከአእምሯችሁ በማውጣት በይሖዋ ተስፋዎች ላይ አተኩሩ። ይሖዋ ለዘላለም እንድትኖሩ እንደሚፈልግና እዚያ ግብ ላይ እንድትደርሱ እንደሚረዳችሁ አትጠራጠሩ።—1 ጢሞ. 2:3, 4

ተስፋችሁ እንዳይደበዝዝ ተጠንቀቁ

11. ተስፋችን እስኪፈጸም በምንጠባበቅበት ጊዜ መታገሥ ያለብን ለምንድን ነው?

11 ተስፋችን እንዳይደበዝዝ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። አምላክ ቃሉን የሚፈጽምበትን ጊዜ ስንጠባበቅ ትዕግሥት ልናጣ እንችላለን። ሆኖም ይሖዋ ዘላለማዊ አምላክ ነው፤ በመሆኑም እሱ ለጊዜ ያለው አመለካከት ከእኛ የተለየ ነው። (2 ጴጥ. 3:8, 9) ዓላማውን የሚፈጽመው ከሁሉ በተሻለው መንገድ ነው፤ ሆኖም እርምጃ የሚወስደው እኛ በጠበቅነው ጊዜ ላይሆን ይችላል። ታዲያ አምላካችን ቃሉን እስኪፈጽም በትዕግሥት በምንጠባበቅበት ጊዜ ተስፋችን እንዳይደበዝዝ ምን ይረዳናል?—ያዕ. 5:7, 8

12. በዕብራውያን 11:1, 6 መሠረት ተስፋና እምነት የሚያያዙት እንዴት ነው?

12 ለተስፋችን ዋስትና የሰጠንን ይሖዋን የሙጥኝ ካልን ተስፋችን አይደበዝዝብንም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋን ይሖዋ ስለመኖሩ እንዲሁም ‘ከልብ ለሚፈልጉት ወሮታ ከፋይ ስለመሆኑ’ ካለን እምነት ጋር ያያይዘዋል። (ዕብራውያን 11:1, 6ን አንብብ።) ይሖዋ ይበልጥ እውን በሆነልን መጠን ቃል የገባውን ነገር ሁሉ እንደሚፈጽም ይበልጥ እንተማመናለን። ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና በማጠናከር ተስፋችን እንዳይደበዝዝ ማድረግ የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት።

ጸሎትና ማሰላሰል ተስፋችን እንዳይደበዝዝ ይረዳናል (ከአንቀጽ 13-15⁠ን ተመልከት) b

13. ወደ አምላክ መቅረብ የምንችለው እንዴት ነው?

13 ወደ ይሖዋ ጸልዩ፤ ቃሉንም አንብቡ። ይሖዋን ማየት ባንችልም ወደ እሱ መቅረብ እንችላለን። እንደሚሰማን እርግጠኞች ሆነን በጸሎት ልናነጋግረው እንችላለን። (ኤር. 29:11, 12) ቃሉን በማንበብና በማሰላሰል ደግሞ አምላክን ማዳመጥ እንችላለን። ይሖዋ የጥንት ታማኞቹን እንዴት እንደተንከባከበ ስናነብ ተስፋችን ይበልጥ ይጠናከራል። “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ [በአምላክ ቃል ውስጥ] የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏልና።”—ሮም 15:4

14. ይሖዋ ለሌሎች ባደረገላቸው ነገር ላይ ማሰላሰል ያለብን ለምንድን ነው?

14 ይሖዋ ቃሉን እንደጠበቀ በሚገልጹ ዘገባዎች ላይ አሰላስሉ። አምላክ ለአብርሃምና ለሣራ ያደረገላቸውን ነገር እንደ ምሳሌ እንመልከት። ልጅ መውለድ የማይችሉበት ዕድሜ ላይ ደርሰው ነበር። ሆኖም አምላክ ልጅ እንደሚወልዱ ቃል ገባላቸው። (ዘፍ. 18:10) ታዲያ አብርሃም ምን አደረገ? መጽሐፍ ቅዱስ “የብዙ ብሔራት አባት እንደሚሆን በተሰጠው ተስፋ አምኗል” ይላል። (ሮም 4:18) ከሰዎች አመለካከት አንጻር ሁኔታው ተስፋ የሌለው ቢመስልም አብርሃም ይሖዋ ቃሉን እንደሚፈጽም እርግጠኛ ነበር። ይሖዋ ይህን ታማኝ ሰው አላሳፈረውም። (ሮም 4:19-21) እንዲህ ያሉ ዘገባዎች፣ ሁኔታው ጨርሶ የማይቻል ቢመስልም እንኳ ይሖዋ ምንጊዜም ቃሉን እንደሚጠብቅ ያረጋግጡልናል።

15. አምላክ ባደረገልን ነገር ላይ ማሰላሰል ያለብን ለምንድን ነው?

15 ይሖዋ ለእናንተ ያደረገላችሁን ነገር አስቡ። አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የገባልን ቃል በመፈጸሙ በግለሰብ ደረጃ የተጠቀማችሁት እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክሩ። ለምሳሌ ይሖዋ መሠረታዊ ነገሮችን እንደሚሰጠን ኢየሱስ ቃል ገብቶልናል። (ማቴ. 6:32, 33) በተጨማሪም ይሖዋ ስንጠይቀው መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጠን ኢየሱስ ዋስትና ሰጥቶናል። (ሉቃስ 11:13) ይሖዋ የገባውን ቃል ፈጽሟል። ይሖዋ ከእናንተ ጋር በተያያዘ ቃሉን የጠበቀባቸውን ሌሎች መንገዶችም ታስታውሱ ይሆናል። ለምሳሌ ይቅር እንደሚለን፣ እንደሚያጽናናን እንዲሁም በመንፈሳዊ እንደሚመግበን ቃል ገብቶልናል። (ማቴ. 6:14፤ 24:45፤ 2 ቆሮ. 1:3) አምላክ እስካሁን ባደረገላችሁ ነገር ላይ ካሰላሰላችሁ ለወደፊቱ ጊዜ በሰጣችሁ ተስፋ ላይ ያላችሁ እምነት ይጠናከራል።

በተስፋው ደስ ይበላችሁ

16. ተስፋ ውድ ስጦታ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

16 የዘላለም ሕይወት ተስፋችን ከአምላክ ያገኘነው ውድ ስጦታ ነው። ወደፊት ግሩም ሕይወት ይጠብቀናል፤ እንደምናገኘውም እርግጠኞች ነን። ተስፋችን እንደ መልሕቅ በመሆን ፈተናዎችን እንድንወጣ፣ ስደትን እንድንቋቋም አልፎ ተርፎም ሞትን እንድንጋፈጥ ይረዳናል። እንደ ራስ ቁር በመሆን አስተሳሰባችንን ይጠብቅልናል፤ ይህም መጥፎ የሆነውን ለመጸየፍና ጥሩ የሆነውን አጥብቀን ለመያዝ ይረዳናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ተስፋችን ወደ አምላክ እንድንቀርብ የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ እሱ ምን ያህል እንደሚወደን ያሳየናል። ተስፋችን ጠንካራ ከሆነ በእጅጉ እንጠቀማለን።

17. ተስፋችን ደስታ የሚያስገኝልን እንዴት ነው?

17 ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “በተስፋው ደስ ይበላችሁ” የሚል ማበረታቻ ሰጥቷል። (ሮም 12:12) ጳውሎስ ታማኝነቱን ከጠበቀ በሰማይ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኝ እርግጠኛ ስለነበር ሊደሰት ችሏል። እኛም ይሖዋ ምንጊዜም ቃሉን እንደሚጠብቅ እርግጠኞች ስለሆንን በተስፋችን ልንደሰት እንችላለን። መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአምላኩ በይሖዋ ተስፋ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው፤ እሱ . . . ለዘላለም ታማኝ ነው።”—መዝ. 146:5, 6

መዝሙር 139 በአዲሱ ዓለም ስትኖር ይታይህ

a ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስደናቂ ተስፋ ሰጥቶናል። ይህ ተስፋ ሕይወታችንን ብሩሕ የሚያደርግልን ከመሆኑም ሌላ በአሁኑ ጊዜ ከሚያጋጥሙን ፈተናዎች አሻግረን እንድንመለከት ይረዳናል። ምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥመን ታማኝነታችንን ለመጠበቅ የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል። እንዲሁም አስተሳሰባችንን ሊመርዙ በሚችሉ ሐሳቦች ከመሸነፍ ይጠብቀናል። እነዚህ ምክንያቶች ክርስቲያናዊ ተስፋችንን እንድናጠናክር ያነሳሱናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ እንመለከታለን።

b የሥዕሉ መግለጫ፦ የራስ ቁር የአንድን ወታደር ጭንቅላት ይጠብቃል፤ መልሕቅ ደግሞ አንድ መርከብ እንዳይናወጥ አጽንቶ ያቆማል፤ በተመሳሳይም ተስፋችን አስተሳሰባችንን ይጠብቅልናል፤ እንዲሁም ፈተና ሲያጋጥመን አጽንቶ ያቆመናል። አንዲት እህት በልበ ሙሉነት ወደ ይሖዋ ስትጸልይ። አንድ ወንድም፣ አምላክ ለአብርሃም የገባውን ቃል የፈጸመው እንዴት እንደሆነ ሲያሰላስል። ሌላ ወንድም ደግሞ እሱ እንዴት እንደተባረከ ሲያሰላስል።