በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥንቶቹ እስራኤላውያን በጦርነት ተካፍለዋል—እኛስ?

የጥንቶቹ እስራኤላውያን በጦርነት ተካፍለዋል—እኛስ?

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አንድ የናዚ ወታደር “ከመካከላችሁ አንዱም እንኳ ከፈረንሳይ ወይም ከእንግሊዝ ጋር አልዋጋም ካለ ሁላችሁም ትገደላላችሁ!” በማለት በተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ዛተባቸው። መሣሪያ የታጠቁ የናዚ ወታደሮች በአቅራቢያቸው ቢኖሩም እንኳ ከወንድሞቻችን መካከል አንዳቸውም አቋማቸውን አላላሉም። እንዴት ያለ የድፍረት አቋም ነው! ይህ ምሳሌ ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸውን አመለካከት ጎላ አድርጎ ያሳያል፤ በዚህ ዓለም ጦርነቶች ለመካፈል ፈቃደኞች አይደለንም። ከሞት ጋር ብንፋጠጥ እንኳ በዚህ ዓለም ግጭቶች አንዱን ወገን ከመደገፍ እንቆጠባለን።

ይሁንና ክርስቲያን ነን የሚሉ ሁሉ በዚህ አቋም ይስማማሉ ማለት አይደለም። ብዙዎች፣ ክርስቲያኖች ለአገራቸው መዋጋት እንደሚችሉ አልፎ ተርፎም እንዲህ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ይሰማቸዋል። እንዲህ ይሉ ይሆናል፦ ‘የጥንቶቹ እስራኤላውያን የአምላክ ሕዝቦች ነበሩ፤ ሆኖም በጦርነቶች ተካፍለዋል። ታዲያ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች በጦርነት መካፈል የለባቸውም የምትሉት ለምንድን ነው?’ አንድ ሰው እንዲህ ቢልህ ምን ብለህ ትመልሳለህ? የጥንቶቹ እስራኤላውያን የነበሩበት ሁኔታ በዛሬው ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች ካሉበት ሁኔታ በእጅጉ እንደሚለይ ማብራራት ትችላለህ። አምስት ልዩነቶችን እስቲ እንመልከት።

1. ሁሉም የአምላክ ሕዝቦች የአንድ ብሔር አባል ነበሩ

በጥንት ዘመን ይሖዋ ሕዝቡ እንዲሆን የመረጠው አንድን ብሔር ማለትም የእስራኤልን ብሔር ነበር። እስራኤላውያንን “ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተመረጣችሁ ልዩ ንብረቶቼ” በማለት ጠርቷቸዋል። (ዘፀ. 19:5) አምላክ ለእስራኤላውያን ተለይተው የሚኖሩበት ክልልም ሰጥቷቸዋል። በመሆኑም አምላክ እስራኤላውያንን ከሌሎች ብሔራት ጋር እንዲዋጉ ሲያዛቸው የሚወጉት ወይም የሚገድሉት የእምነት አጋሮቻቸውን አልነበረም። a

በዛሬው ጊዜ የአምላክ እውነተኛ አገልጋዮች “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ” ናቸው። (ራእይ 7:9) ከዚህ አንጻር፣ የአምላክ ሕዝቦች በጦርነት ቢካፈሉ የሚወጉት አልፎ ተርፎም የሚገድሉት የእምነት አጋሮቻቸውን ሊሆን ይችላል።

2. እስራኤላውያን ጦርነት እንዲወጡ የሚያዛቸው ይሖዋ ነበር

በጥንት ዘመን እስራኤላውያን መቼ ወይም ለምን መዋጋት እንዳለባቸው የሚወስነው ይሖዋ ነበር። ለምሳሌ አምላክ፣ እስራኤላውያን ከነአናውያንን በመውጋት ፍርዱን እንዲያስፈጽሙ አዟቸው ነበር። ይህንንም ያደረገው ከነአናውያን በአጋንንት አምልኮ፣ አስጸያፊ በሆነ የፆታ ብልግና እንዲሁም ልጆችን መሥዋዕት በማድረግ የሚታወቁ ጨካኝ ሰዎች ስለነበሩ ነው። ይሖዋ እስራኤላውያን እንዲህ ያለ መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን ከተስፋይቱ ምድር እንዲያጠፉ ያዘዛቸው እስራኤላውያንን ከመጥፎ ተጽዕኖ ሊጠብቃቸው ስለፈለገ ነው። (ዘሌ. 18:24, 25) እስራኤላውያን በተስፋይቱ ምድር ውስጥ መኖር ከጀመሩ በኋላም አምላክ እስራኤላውያንን ጨቋኝ ከሆኑ ጠላቶቻቸው ለመታደግ ሲል እንዲዋጉ የፈቀደላቸው ጊዜ አለ። (2 ሳሙ. 5:17-25) ሆኖም ይሖዋ፣ እስራኤላውያን በራሳቸው ተነሳሽነት ጦርነት እንዲወጡ ፈቅዶላቸው አያውቅም። እንዲህ ባደረጉበት ወቅትም አስከፊ መዘዝ አጋጥሟቸዋል።—ዘኁ. 14:41-45፤ 2 ዜና 35:20-24

በዛሬው ጊዜ ሰዎች ጦርነት እንዲወጡ የሚያዛቸው ይሖዋ አይደለም። ብሔራት የሚዋጉት የአምላክን ፈቃድ ለማስፈጸም ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም ለማራመድ ነው። ውጊያ የሚወጡት ግዛታቸውን ለማስፋት፣ የኢኮኖሚ ጥቅም ለማግኘት ወይም ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ለማሳካት ሊሆን ይችላል። ይሁንና የአምልኮ መብታቸውን ለማስከበር ወይም የአምላክን ጠላቶች ለማጥፋት ሲሉ በአምላክ ስም እንደሚዋጉ ስለሚናገሩ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ ወደፊት በሚካሄደው የአርማጌዶን ጦርነት አማካኝነት እውነተኛ አገልጋዮቹን ይታደጋቸዋል፤ እንዲሁም ጠላቶቹን ያጠፋል። (ራእይ 16:14, 16) በዚያ ጦርነት ወቅት አምላክ የሚጠቀመው ምድራዊ አገልጋዮቹን ሳይሆን ሰማያዊ ፍጥረታትን ያቀፈውን ሠራዊቱን ነው።—ራእይ 19:11-15

3. እስራኤላውያን በይሖዋ ላይ እምነት ያሳዩ ሰዎችን አይገድሉም ነበር

ይሖዋ ኢያሪኮን ባጠፋበት ወቅት ረዓብንና ቤተሰቧን አድኗቸዋል፤ በዛሬው ጊዜ ያሉ ተዋጊዎችስ ለይሖዋ ታማኝ የሆኑ ሰዎችን ይምራሉ?

በጥንት ዘመን ብዙውን ጊዜ እስራኤላውያን ተዋጊዎች በአምላክ ላይ እምነት ላሳደሩ ሰዎች ምሕረት ያሳዩ ነበር፤ የሚያጠፉት አምላክ እንዲገደሉ የፈረደባቸውን ሰዎች ብቻ ነበር። ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት። ይሖዋ ኢያሪኮ እንድትጠፋ ቢያዝም ረዓብ እምነት በማሳየቷ እስራኤላውያን እሷንና ቤተሰቦቿን አላጠፏቸውም። (ኢያሱ 2:9-16፤ 6:16, 17) ከጊዜ በኋላም ገባኦናውያን ፈሪሃ አምላክ እንዳላቸው በማሳየታቸው መላዋ የገባኦን ከተማ ሳትጠፋ ቀርታለች።—ኢያሱ 9:3-9, 17-19

በዛሬው ጊዜ ብሔራት ጦርነት በሚያካሂዱበት ወቅት በአምላክ ላይ እምነት ያሳዩ ሰዎችን አይምሩም። አንዳንድ ጊዜም ብሔራት በሚያካሂዱት ጦርነት ምክንያት ንጹሐን ዜጎች ሕይወታቸውን ያጣሉ።

4. እስራኤላውያን አምላክ ከጦርነት ጋር በተያያዘ ያወጣቸውን ሕጎች መታዘዝ ይጠበቅባቸው ነበር

በጥንት ዘመን ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ወታደሮች በሚዋጉበት ወቅት የእሱን መመሪያዎች እንዲከተሉ ይጠብቅባቸው ነበር። ለምሳሌ አንዲትን ከተማ ከመውጋታቸው በፊት “የሰላም ጥሪ” እንዲያስተላልፉ ያዘዛቸው ጊዜ ነበር። (ዘዳ. 20:10) በተጨማሪም ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ወታደሮች የጦር ሰፈራቸውን ንጽሕና እንዲጠብቁና የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹን እንዲያከብሩ ይጠብቅባቸው ነበር። (ዘዳ. 23:9-14) በዙሪያቸው ያሉ ብሔራት፣ ድል ባደረጉባቸው አካባቢዎች ያሉ ሴቶችን ይደፍሩ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ እስራኤላውያን እንዲህ እንዳያደርጉ ከልክሏቸዋል። አንዲትን ምርኮኛ ሴት ማግባት ቢፈልጉ እንኳ ይህን ማድረግ የሚችሉት ከተማዋን ድል ካደረጉ ከአንድ ወር በኋላ ነበር።—ዘዳ. 21:10-13

በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ አገሮች ከጦርነት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን ፈርመዋል። የእነዚህ ስምምነቶች ዓላማ ንጹሐን ዜጎችን ከጉዳት ለመታደግ ቢሆንም የሚያሳዝነው ግን እነዚህ ስምምነቶች ብዙ ጊዜ ይጣሳሉ።

5. አምላክ ለሕዝቡ ይዋጋላቸው ነበር

አምላክ በኢያሪኮ ለእስራኤላውያን ተዋግቶላቸው ነበር፤ በዛሬው ጊዜስ ለአንድ ብሔር ይዋጋል?

በጥንት ዘመን ይሖዋ ለእስራኤላውያን ይዋጋላቸው ነበር። እንዲያውም ብዙ ጊዜ በተአምራዊ መንገድ ድል አጎናጽፏቸዋል። ለምሳሌ ይሖዋ እስራኤላውያን የኢያሪኮ ከተማን ድል እንዲያደርጉ የረዳቸው እንዴት ነው? እስራኤላውያን የይሖዋን መመሪያ ተከትለው ‘ታላቅ የጦርነት ጩኸት ሲያሰሙ ቅጥሩ ፈረሰ’፤ በመሆኑም በቀላሉ ከተማዋን መቆጣጠር ቻሉ። (ኢያሱ 6:20) ከአሞራውያን ጋር በተዋጉበት ጊዜስ ድል የተቀዳጁት እንዴት ነው? “ይሖዋ ከሰማይ ትላልቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸው። . . . እንዲያውም በእስራኤላውያን ሰይፍ ከሞቱት ይልቅ በበረዶ ድንጋይ የሞቱት ይበልጣሉ።”—ኢያሱ 10:6-11

በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ለየትኛውም ብሔር አይዋጋም። በኢየሱስ የሚተዳደረው መንግሥቱ “የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም።” (ዮሐ. 18:36) ከዚህ ይልቅ በሁሉም መንግሥታት ላይ ሥልጣን ያለው ሰይጣን ነው። በዓለም ላይ የሚካሄዱት አሰቃቂ ጦርነቶች የእሱን ክፋት ያንጸባርቃሉ።—ሉቃስ 4:5, 6፤ 1 ዮሐ. 5:19

እውነተኛ ክርስቲያኖች ሰላም ፈጣሪዎች ናቸው

እስካሁን እንደተመለከትነው፣ በዛሬው ጊዜ ያለንበት ሁኔታ የጥንቶቹ እስራኤላውያን ከነበሩበት ሁኔታ በእጅጉ የተለየ ነው። ይሁንና በጦርነት የማንካፈለው በእነዚህ ልዩነቶች የተነሳ ብቻ አይደለም። ሌሎች ምክንያቶችም አሉን። ለምሳሌ አምላክ በመጨረሻዎቹ ቀኖች ከእሱ የተማሩ ሰዎች በጦርነት መካፈል ይቅርና ‘ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነትን እንደማይማሩ’ ተናግሯል። (ኢሳ. 2:2-4) በተጨማሪም ክርስቶስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ‘የዓለም ክፍል እንደማይሆኑ’ ተናግሯል፤ ከዚህ ዓለም ግጭቶች ጋር በተያያዘ አንዱን ወገን ከመደገፍ ይቆጠባሉ።—ዮሐ. 15:19

ክርስቶስ ተከታዮቹ ከዚህ ያለፈ ነገር እንዲያደርጉም ይጠብቅባቸዋል። ወደ ጥላቻ፣ ቁጣና ጦርነት የሚያመሩ ዝንባሌዎችን እንዲያስወግዱ አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 5:21, 22) በተጨማሪም ተከታዮቹ “ሰላም ፈጣሪዎች” እንዲሆኑና ጠላቶቻቸውን እንዲወዱ ነግሯቸዋል።—ማቴ. 5:9, 44

ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርብናል? በጦርነት መካፈል እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ይሁንና በጉባኤ ውስጥ ግጭት ወይም ክፍፍል ሊፈጥር የሚችል የጥላቻ ርዝራዥ በልባችን ውስጥ ይኖር ይሆን? እንዲህ ያሉ ስሜቶችን ከውስጣችን ነቅለን ለማስወገድ ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥል።—ያዕ. 4:1, 11

በብሔራት መካከል ባሉ ግጭቶች ከመካፈል ይልቅ በመካከላችን ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍን ጥረት እናደርጋለን። (ዮሐ. 13:34, 35) ይሖዋ ጦርነትን ሁሉ ለዘላለም የሚያስወግድበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን፤ እስከዚያው ድረስ ግን የገለልተኝነት አቋማችንን ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—መዝ. 46:9

a እርግጥ የእስራኤል ነገዶች እርስ በርስ የተዋጉበት ጊዜ አለ፤ ሆኖም እነዚህ የእርስ በርስ ጦርነቶች ይሖዋን አሳዝነውታል። (1 ነገ. 12:24) አንዳንድ ጊዜ ግን እንዲህ ያሉ ጦርነቶችን ይፈቅድ ነበር፤ ይህ የሆነው አንዳንዶቹ ነገዶች በእሱ ላይ በማመፃቸው ወይም ሌላ አስከፊ ኃጢአት በመፈጸማቸው የተነሳ ነው።—መሳ. 20:3-35፤ 2 ዜና 13:3-18፤ 25:14-22፤ 28:1-8