በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 41

መዝሙር 13 ምሳሌያችን የሆነው ክርስቶስ

ኢየሱስ በምድር ላይ ካሳለፋቸው የመጨረሻ 40 ቀናት የምናገኘው ትምህርት

ኢየሱስ በምድር ላይ ካሳለፋቸው የመጨረሻ 40 ቀናት የምናገኘው ትምህርት

“እነሱም ለ40 ቀናት ያዩት ሲሆን እሱም ስለ አምላክ መንግሥት ይነግራቸው ነበር።”ሥራ 1:3

ዓላማ

ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፋቸው የመጨረሻ 40 ቀናት የተወውን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

1-2. ሁለቱ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ወደ ኤማሁስ እየተጓዙ ሳሉ ምን አጋጠማቸው?

 ዕለቱ ኒሳን 16, 33 ዓ.ም. ነው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሐዘንና በፍርሃት ተውጠዋል። ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሁለቱ ከኢየሩሳሌም ወጥተው 11 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ ኤማሁስ መጓዝ ጀመሩ። እነዚህ ሰዎች፣ ሲከተሉት የነበረው ኢየሱስ በመገደሉ ቅስማቸው ተሰብሯል። ከመሲሑ ጋር በተያያዘ የነበራቸው ተስፋ እንደ ጉም በኖ ጠፍቷል። ሆኖም ያልጠበቁት ነገር አጋጠማቸው።

2 አንድ ሰው ወደ እነሱ ጠጋ ብሎ አብሯቸው መጓዝ ጀመረ። ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ባጋጠመው ነገር የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ለሰውየው ነገሩት። ከዚያም ሰውየው ሕይወታቸውን የሚቀይር ማብራሪያ ሰጣቸው። መሲሑ መሠቃየትና መሞት ያለበት ለምን እንደሆነ “ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ” አብራራላቸው። ሦስቱ ሰዎች ኤማሁስ ሲደርሱ ደቀ መዛሙርቱ የሰውየውን ማንነት አወቁ። ለካስ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ነው! ደቀ መዛሙርቱ መሲሑ ሕያው መሆኑን ሲያውቁ ምን ያህል ተደስተው ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስበው!—ሉቃስ 24:13-35

3-4. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን ዓይነት ለውጥ አድርገዋል? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን? (የሐዋርያት ሥራ 1:3)

3 ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፋቸው የመጨረሻ 40 ቀናት ለደቀ መዛሙርቱ በተደጋጋሚ ተገልጦላቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 1:3ን አንብብ።) በሐዘንና በፍርሃት ተውጠው የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በዚያ ጊዜ ውስጥ ተለውጠው በደስታ፣ በልበ ሙሉነትና በድፍረት ስለ መንግሥቱ መስበክና ማስተማር ጀመሩ። a

4 ኢየሱስ በእነዚያ ቀናት ውስጥ ስላከናወነው ነገር ማጥናታችን ይጠቅመናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ኢየሱስ ይህን ጊዜ (1) ደቀ መዛሙርቱን ለማበረታታት፣ (2) ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ እንዲሁም (3) ተጨማሪ ኃላፊነቶችን እንዲቀበሉ ለማሠልጠን የተጠቀመበት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። ከእያንዳንዱ ነጥብ ጋር በተያያዘ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት እንደሆነም እናያለን።

ሌሎችን አበረታቱ

5. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ማበረታቻ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው?

5 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ማበረታቻ ያስፈልጋቸው ነበር። ለምን? አንዳንዶቹ ሙሉ ጊዜያቸውን ተጠቅመው ኢየሱስን ለመከተል ሲሉ ቤታቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሥራቸውን ትተዋል። (ማቴ. 19:27) ሌሎቹ ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆናቸው የተነሳ ከማኅበረሰቡ ተገልለዋል። (ዮሐ. 9:22) እነዚህን መሥዋዕቶች የከፈሉት ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ መሆኑን ስላመኑ ነው። (ማቴ. 16:16) ሆኖም ኢየሱስ ሲገደል ተስፋቸው ጨለመ፤ በሐዘንም ተዋጡ።

6. ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ምን አደረገ?

6 ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን ሐዘን እንደ መንፈሳዊ ድክመት አልቆጠረውም፤ ከዚህ ይልቅ በእሱ ሞት ማዘናቸው የሚጠበቅ ነገር እንደሆነ ተሰምቶታል። በመሆኑም ከሞት በተነሳበት በዚያው ቀን ወዳጆቹን ማበረታታት ጀመረ። ለምሳሌ መግደላዊቷ ማርያም መቃብሩ ጋ ቆማ እያለቀሰች ሳለ ተገልጦላታል። (ዮሐ. 20:11, 16) በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ ለተጠቀሱት ሁለት ደቀ መዛሙርትም ተገልጦላቸዋል። በተጨማሪም ለሐዋርያው ጴጥሮስ ተገልጦለታል። (ሉቃስ 24:34) ከኢየሱስ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? ለመግደላዊቷ ማርያም በተገለጠበት ወቅት ምን እንደተፈጠረ እንመልከት።

7. በዮሐንስ 20:11-16 መሠረት ኢየሱስ ኒሳን 16 ጠዋት ላይ ማርያም ምን ስታደርግ ተመለከተ? ይህስ ምን እንዲያደርግ አነሳሳው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

7 ዮሐንስ 20:11-16ን አንብብ። ኒሳን 16 ማለዳ ላይ የተወሰኑ ታማኝ ሴቶች ኢየሱስ ወደተቀበረበት ቦታ ሄዱ። (ሉቃስ 24:1, 10) ከእነሱ መካከል አንዷ መግደላዊቷ ማርያም ነች። ማርያም ወደ መቃብሩ ስትደርስ መቃብሩ ባዶ ነበር። ይህን ለጴጥሮስና ለዮሐንስ ለመናገር እየሮጠች ሄደች። ከዚያም እነሱን ተከትላ ወደ መቃብሩ ተመለሰች። ጴጥሮስና ዮሐንስ መቃብሩ ባዶ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ማርያም ግን አልተመለሰችም። እያለቀሰች እዚያው ቆየች። ኢየሱስ እያያት እንደሆነ አላወቀችም ነበር። ኢየሱስ የዚህችን ታማኝ ሴት እንባ ሲመለከት በጣም አዘነላት። በመሆኑም ለማርያም ተገለጠላት። ቀጥሎ ያደረገው ነገር ማርያምን በእጅጉ አበረታቷታል። አነጋገራት፤ እንዲሁም ወሳኝ ኃላፊነት ሰጣት። መነሳቱን ለወንድሞቹ እንድታበስር ነገራት።—ዮሐ. 20:17, 18

ሌሎች ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በማስተዋል እንዲሁም ስሜታቸውን በመረዳት የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ (አንቀጽ 7ን ተመልከት)


8. የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

8 የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? እኛም እንደ ኢየሱስ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ለማስተዋል ጥረት ካደረግን፣ ስሜታቸውን ከተረዳንላቸው እንዲሁም ካበረታታናቸው ይሖዋን ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ በእጅጉ ልንረዳቸው እንችላለን። ጆሰሊን የተባለች እህት ምን እንዳጋጠማት እንመልከት። እህቷ በአሰቃቂ አደጋ ከሞተች በኋላ ጆሰሊን “ለበርካታ ወራት በጥልቅ ሐዘን ተውጬ ነበር” ብላለች። ይሁንና አንድ ወንድምና ባለቤቱ ቤታቸው ጋበዟት፤ በጥሞና አዳመጧት፤ ስሜቷን ተረዱላት፤ እንዲሁም ይሖዋ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታት አስታወሷት። ጆሰሊን እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ እነሱን በመጠቀም በማዕበል ከሚናወጥ ጨለማ ባሕር ውስጥ አውጥቶ ሕይወት አድን ጀልባ ላይ እንዳስቀመጠኝ ተሰማኝ። ይሖዋን ለማገልገል ያለኝ ፍላጎት በድጋሚ እንዲነሳሳ ረድተውኛል።” እኛም ሌሎች ስሜታቸውን አውጥተው ሲናገሩ በጥሞና በማዳመጥ እንዲሁም የሚያጽናኑ ቃላትን በመናገር በይሖዋ አገልግሎት እንዲጸኑ ልንረዳቸው እንችላለን።—ሮም 12:15

ሌሎች በአምላክ ቃል ላይ እንዲያመዛዝኑ እርዷቸው

9. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል? ኢየሱስ የረዳቸውስ እንዴት ነው?

9 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በአምላክ ቃል ያምኑ እንዲሁም ቃሉን በሕይወታቸው ውስጥ በሥራ ላይ ለማዋል ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር። (ዮሐ. 17:6) ያም ቢሆን ኢየሱስ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ በመከራ እንጨት ላይ መገደሉ ግራ አጋብቷቸዋል። ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱ ጥርጣሬ የመነጨው ከክፉ ልብ ሳይሆን ከግንዛቤ ጉድለት እንደሆነ አስተውሎ ነበር። (ሉቃስ 9:44, 45፤ ዮሐ. 20:9) በመሆኑም ቅዱሳን መጻሕፍትን ተጠቅመው እንዲያመዛዝኑ ረዳቸው። ወደ ኤማሁስ እየተጓዙ ለነበሩት ሁለት ደቀ መዛሙርት በተገለጠበት ወቅት ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

10. ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ደቀ መዛሙርቱ እንዲያምኑ የረዳቸው እንዴት ነው? (ሉቃስ 24:18-27)

10 ሉቃስ 24:18-27ን አንብብ። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ማንነቱን ወዲያውኑ እንዳልነገራቸው ልብ በሉ። ከዚህ ይልቅ ጥያቄዎችን ጠየቃቸው። ለምን? በአእምሯቸውና በልባቸው ውስጥ ያለውን ነገር እንዲነግሩት ስለፈለገ ሊሆን ይችላል። ደግሞም ሐሳባቸውን ገልጸውለታል። ኢየሱስ እስራኤልን ከሮማውያን ጭቆና ነፃ ያወጣል ብለው ጠብቀው እንደነበር ነገሩት። ስሜታቸውን በግልጽ ከነገሩት በኋላ ኢየሱስ ክንውኖቹ ያላቸውን ትርጉም ቅዱሳን መጻሕፍትን በመጠቀም አብራራላቸው። b በዚያው ምሽት ኢየሱስ እነዚህኑ እውነቶች ለሌሎቹ ደቀ መዛሙርቱም ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 24:33-48) ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?

11-12. (ሀ) ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ካስተማረበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።) (ለ) ኖርቴን አስጠኚው የረዳው እንዴት ነው?

11 የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁን በምታስተምሩበት ወቅት በአእምሯቸውና በልባቸው ውስጥ ያለውን ነገር ቀድታችሁ ለማውጣት ጥያቄዎችን በዘዴ ጠይቋቸው። (ምሳሌ 20:5) ስሜታቸውን ከተረዳችሁ በኋላ ካሉበት ሁኔታ ጋር የሚያያዙ ጥቅሶችን ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አሳዩአቸው። ከዚያ ግን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከመንገር ተቆጠቡ። ከዚህ ይልቅ በጥቅሶቹ ላይ እንዲያመዛዝኑ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንዲያስተውሉ እርዷቸው። በጋና የሚኖር ኖርቴ የተባለ ወንድም ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት።

12 ኖርቴ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረው የ16 ዓመት ልጅ እያለ ነው። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ቤተሰቦቹ ተቃወሙት። ታዲያ እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? አስጠኚው እውነተኛ ክርስቲያኖች ስደት እንደሚደርስባቸው ማቴዎስ ምዕራፍ 10ን ተጠቅሞ አብራርቶለት ነበር። ኖርቴ “ስለዚህ ስደቱ ሲጀምር እውነትን እንዳገኘሁ እርግጠኛ ሆንኩ” ብሏል። በተጨማሪም አስጠኚው ማቴዎስ 10:16ን በመጠቀም ኖርቴ ከቤተሰቦቹ ጋር በጥንቃቄና በአክብሮት ስለ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች መወያየት የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንዲገነዘብ ረዳው። ኖርቴ ከተጠመቀ በኋላ አቅኚ ለመሆን አሰበ። አባቱ ግን ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገባ ፈልጎ ነበር። አስጠኚው ለኖርቴ ምን ማድረግ እንዳለበት ከመንገር ይልቅ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ስሜቱን አውጥቶ እንዲናገር አበረታታው፤ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ እንዲያመዛዝን ረዳው። ውጤቱስ ምን ሆነ? ኖርቴ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባት ወሰነ። በዚህ ጊዜ አባቱ ከቤት አባረረው። ኖርቴ ስላጋጠመው ነገር ምን ይሰማዋል? “ትክክለኛውን ውሳኔ እንዳደረግኩ እርግጠኛ ነኝ” ብሏል። እኛም ጊዜ ወስደን ሌሎችን በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ እንዲያመዛዝኑ የምንረዳቸው ከሆነ ጠንካራ ክርስቲያኖች ይሆናሉ።—ኤፌ. 3:16-19

ሌሎች በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ እንዲያመዛዝኑ በመርዳት የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ (አንቀጽ 11ን ተመልከት) e


“ስጦታ” እንዲሆኑ ወንድሞችን አሠልጥኗቸው

13. ኢየሱስ አባቱ የሰጠው ሥራ መከናወኑን እንዲቀጥል ያደረገው እንዴት ነው? (ኤፌሶን 4:8)

13 ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ አባቱ የሰጠውን ሥራ ፍጹም በሆነ መንገድ አከናውኗል። (ዮሐ. 17:4) ሆኖም ኢየሱስ ‘ሥራውን በትክክል መሥራት የምችለው እኔ ብቻ ነኝ’ የሚል አስተሳሰብ አልነበረውም። ለሦስት ዓመት ተኩል በዘለቀው የአገልግሎት ዘመኑ ሌሎችም ሥራውን እንዲያከናውኑ አሠልጥኗል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከመመለሱ በፊት የይሖዋን ውድ በጎች የመንከባከቡን እንዲሁም የስብከቱንና የማስተማሩን ሥራ የመምራቱን ኃላፊነት ለደቀ መዛሙርቱ በአደራ ሰጥቷቸዋል፤ ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ በወቅቱ ገና በ20ዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ሊሆኑ ይችላሉ። (ኤፌሶን 4:8ን አንብብ።) ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፋቸው የመጨረሻ 40 ቀናት እነዚህን ትጉ፣ ታማኝና ታታሪ ወንዶች “ስጦታ” እንዲሆኑ ያሠለጠናቸው እንዴት ነው?

14. ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፋቸው የመጨረሻ 40 ቀናት ደቀ መዛሙርቱን መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ የረዳቸው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ቀጥተኛ ሆኖም ፍቅር የሚንጸባረቅበት ምክር ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ አንዳንዶቹ የመጠራጠር ዝንባሌ እንዳላቸው ስላስተዋለ ምክር ሰጥቷቸዋል። (ሉቃስ 24:25-27፤ ዮሐ. 20:27) ከሰብዓዊ ሥራቸው ይልቅ ለእረኝነቱ ሥራ ትልቅ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥቶ ነግሯቸዋል። (ዮሐ. 21:15) ሌሎች በይሖዋ አገልግሎት ምንም ዓይነት መብት ቢያገኙ ይህ ጉዳይ ሊያሳስባቸው እንደማይገባ ነግሯቸዋል። (ዮሐ. 21:20-22) ከዚህም ሌላ፣ ስለ መንግሥቱ የነበራቸውን የተሳሳተ አመለካከት አርሞላቸዋል፤ እንዲሁም ምሥራቹን በመስበክ ላይ እንዲያተኩሩ ረድቷቸዋል። (ሥራ 1:6-8) ሽማግሌዎች ከኢየሱስ ምን ትምህርት ያገኛሉ?

ወንድሞች ተጨማሪ ኃላፊነቶችን እንዲቀበሉ በማሠልጠን የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ (አንቀጽ 14ን ተመልከት)


15-16. (ሀ) ሽማግሌዎች የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? አብራራ። (ለ) ፓትሪክ ከተሰጠው ምክር የተጠቀመው እንዴት ነው?

15 ሽማግሌዎች የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? ወጣቶችን ጨምሮ ወንድሞች ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ለመቀበል ብቃቱን እንዲያሟሉ ሊያሠለጥኗቸውና ሊረዷቸው ይገባል። c ሽማግሌዎች ከሚያሠለጥኗቸው ወንድሞች ፍጽምና አይጠብቁም። እነዚህ ወጣት ወንድሞች ተሞክሮ እንዲያገኙ እንዲሁም ትሑት፣ ታማኝና ሌሎችን ለማገልገል ፈቃደኛ መሆን ያለውን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ ለመርዳት ፍቅራዊ ምክር ሊሰጧቸው ይገባል።—1 ጢሞ. 3:1፤ 2 ጢሞ. 2:2፤ 1 ጴጥ. 5:5

16 ፓትሪክ የተባለ ወንድም ከተሰጠው ምክር የተጠቀመው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ፓትሪክ ወጣት ሳለ እህቶችን ጨምሮ ሌሎችን የሚያነጋግርበትም ሆነ የሚይዝበት መንገድ ደግነት የጎደለው ነበር። አንድ የጎለመሰ የጉባኤ ሽማግሌ የፓትሪክን ድክመት ስላስተዋለ ደግነት የሚንጸባረቅበት ሆኖም ቀጥተኛ ምክር ሰጠው። ፓትሪክ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ምክር ስለሰጠኝ አመስጋኝ ነኝ። ሌሎች ወንድሞች እኔ የምፈልጋቸውን የአገልግሎት መብቶች ሲያገኙ አዝን ነበር። ሆኖም ሽማግሌው የሰጠኝ ምክር በጉባኤ ውስጥ መብት በማግኘት ላይ ከማተኮር ይልቅ ወንድሞቼንና እህቶቼን በትሕትና በማገልገል ላይ ማተኮር እንዳለብኝ እንዳስተውል ረዳኝ።” በውጤቱም ፓትሪክ በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ እያለ ሽማግሌ ሆኖ ተሹሟል።—ምሳሌ 27:9

17. ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ እንደሚተማመን ያሳየው እንዴት ነው?

17 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የመስበክ ብቻ ሳይሆን የማስተማርም ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 28:20) ደቀ መዛሙርቱ ይህን ኃላፊነት ለመቀበል ብቁ እንዳልሆኑ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ ይህን ሥራ ማከናወን እንደሚችሉ አልተጠራጠረም፤ ደግሞም እንደሚተማመንባቸው ነግሯቸዋል። “አብ እኔን እንደላከኝ፣ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” ማለቱ ሙሉ በሙሉ እንደሚተማመንባቸው ያሳያል።—ዮሐ. 20:21

18. ሽማግሌዎች የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

18 ሽማግሌዎች የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? ተሞክሮ ያላቸው ሽማግሌዎች ለሌሎች ኃላፊነት ይሰጣሉ። (ፊልጵ. 2:19-22) ለምሳሌ ሽማግሌዎች በስብሰባ አዳራሽ ጽዳትና ጥገና ሥራ ወጣቶችን ማሳተፍ ይችላሉ። አንድን ሥራ ለተወሰኑ ሰዎች ከሰጡ በኋላ እነሱን በማሠልጠን ከዚያም ሥራውን ለእነሱ በመተው እንደሚተማመኑባቸው ማሳየት ይችላሉ። ማቲው የተባለ አዲስ የጉባኤ ሽማግሌ ተሞክሮ ያላቸው ሽማግሌዎች የተሟላ ሥልጠና ስለሰጡት እንዲሁም ኃላፊነቱን በራሱ እንዲወጣ ስለሚተማመኑበት አመስጋኝ እንደሆነ ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “የምሠራቸውን ስህተቶች የሥልጠናው ክፍል አድርገው ስለሚመለከቱ እንዲሁም እንዳሻሽል ስለሚረዱኝ በጣም ተጠቅሜያለሁ።” d

19. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?

19 ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፋቸውን የመጨረሻ 40 ቀናት ሌሎችን ለማበረታታት፣ ለማስተማርና ለማሠልጠን ተጠቅሞባቸዋል። እኛም የእሱን ምሳሌ በጥብቅ ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (1 ጴጥ. 2:21) እሱም እንዲህ እንድናደርግ ይረዳናል። ደግሞም እንዲህ በማለት ቃል ገብቶልናል፦ “እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”—ማቴ. 28:20

መዝሙር 15 የይሖዋን በኩር አወድሱ!

a ወንጌሎችና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ የተገለጠባቸውን የተለያዩ ወቅቶች ይዘግባሉ፤ ለምሳሌ ለመግደላዊቷ ማርያም (ዮሐ. 20:11-18)፣ ለሌሎች ሴቶች (ማቴ. 28:8-10፤ ሉቃስ 24:8-11)፣ ለሁለት ደቀ መዛሙርት (ሉቃስ 24:13-15)፣ ለጴጥሮስ (ሉቃስ 24:34)፣ ቶማስን ሳይጨምር ለሐዋርያቱ (ዮሐ. 20:19-24)፣ ቶማስን ጨምሮ ለሐዋርያቱ (ዮሐ. 20:26)፣ ለሰባት ደቀ መዛሙርት (ዮሐ. 21:1, 2)፣ ከ500 ለሚበልጡ ደቀ መዛሙርት (ማቴ. 28:16፤ 1 ቆሮ. 15:6)፣ ለወንድሙ ለያዕቆብ (1 ቆሮ. 15:7)፣ ለሁሉም ሐዋርያት (ሥራ 1:4) እንዲሁም በቢታንያ አቅራቢያ ለሐዋርያቱ (ሉቃስ 24:50-52) ተገልጧል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተዘገቡ ኢየሱስ የተገለጠባቸው ሌሎች ወቅቶችም ሊኖሩ ይችላሉ።—ዮሐ. 21:25

b የመሲሐዊ ትንቢቶችን ዝርዝር ለማግኘት “ስለ መሲሑ የተነገሩት ትንቢቶች ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ ያረጋግጣሉ?” የሚለውን ርዕስ jw.org ላይ አንብብ።

c አንዳንድ ጊዜ ከ20ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ እስከ 20ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ የሚገኙ ወንድሞች የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ሆነው ሊሾሙ ይችላሉ። ሆኖም እነዚህ ወንድሞች በመጀመሪያ የጉባኤ ሽማግሌዎች ሆነው በማገልገል ልምድ ማካበት አለባቸው።

d ወጣት ወንድሞች ኃላፊነቶችን ለመቀበል ብቁ እንዲሆኑ መርዳት ስለሚቻልባቸው መንገዶች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የነሐሴ 2018 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 11-12 ከአን. 15-17ን እና የሚያዝያ 15, 2015 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 3-13ን ተመልከት

e የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ አስጠኚው ቅዱሳን መጻሕፍትን ተጠቅሞ እንዲያመዛዝን ከረዳው በኋላ የገና ጌጣጌጦቹን ለመጣል ይወስናል።