በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 43

መዝሙር 90 እርስ በርስ እንበረታታ

ጥርጣሬን ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?

ጥርጣሬን ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?

“ሁሉንም ነገር መርምሩ።”1 ተሰ. 5:21

ዓላማ

ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ ሊነኩ የሚችሉ ጥርጣሬዎችን ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?

1-2. (ሀ) የይሖዋ አገልጋዮች ስለ የትኞቹ ጉዳዮች ሊጠራጠሩ ይችላሉ? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

 በማንኛውም ዕድሜ ያሉ ሰዎች አልፎ አልፎ ጥርጣሬ a ያጋጥማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወጣት አስፋፊ ይሖዋ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ሊጠራጠር ይችላል። በዚህም የተነሳ ለመጠመቅ ያመነታ ይሆናል። ወይም ደግሞ በወጣትነት ዕድሜው ሀብት ከማሳደድ ይልቅ ለመንግሥቱ ጉዳዮች ቅድሚያ ለመስጠት የወሰነን አንድ ጎልማሳ ወንድም ለማሰብ ሞክር። ቤተሰቡን ማስተዳደር እየከበደው ሲመጣ ጥርጣሬ ሊገባው ይችላል። አቅመ ደካማ የሆነችን አንዲት አረጋዊት እህትም ለማሰብ ሞክር። የቀድሞውን ያህል ማገልገል ባለመቻሏ በሐዘን ትዋጥ ይሆናል። አንተም እንዲህ የሚል ጥርጣሬ ተፈጥሮብህ ያውቅ ይሆናል፦ ‘ይሖዋ በእርግጥ ትኩረት ይሰጠኛል? ለይሖዋ ስል መሥዋዕት መክፈሌ በእርግጥ የጥበብ ውሳኔ ነበር? አሁንም ይሖዋ ሊጠቀምብኝ ይችላል?’

2 እንዲህ ላሉት ጥያቄዎች መልስ ካላገኘንላቸው በአምልኳችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። (1) ይሖዋ ትኩረት የሚሰጠን መሆኑን፣ (2) ያደረግነው ውሳኔ ትክክል መሆኑን ወይም (3) ይሖዋ አሁንም ሊጠቀምብን የሚችል መሆኑን ከተጠራጠርን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ማተኮራችን የሚረዳን እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን።

ጥርጣሬህን ማሸነፍ የምትችለው እንዴት ነው?

3. ጥርጣሬያችንን ማሸነፍ የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

3 ጥርጣሬያችንን ማሸነፍ የምንችልበት አንዱ መንገድ የአምላክን ቃል ተጠቅመን ለጥያቄዎቻችን መልስ መፈለግ ነው። እንዲህ ካደረግን እንጠናከራለን፤ በመንፈሳዊ እናድጋለን፤ እንዲሁም ‘በእምነት ጸንተን ለመቆም’ ይበልጥ ዝግጁ እንሆናለን።—1 ቆሮ. 16:13

4. ‘ሁሉንም ነገር መመርመር’ የምንችለው እንዴት ነው? (1 ተሰሎንቄ 5:21)

4 1 ተሰሎንቄ 5:21ን አንብብ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉንም ነገር መርምሩ” እንደሚል ልብ በል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ስለ አንድ ነገር ጥርጣሬ ካደረብን መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚያ ጉዳይ ምን እንደሚል ለማወቅ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ለምሳሌ በአምላክ ዓይን ምንም ዋጋ እንደሌለው የተሰማውን ወጣት መለስ ብለን እናስብ። ይህ ሐሳብ እውነት ነው ብሎ መደምደም ይኖርበታል? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ፣ ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ለማወቅ ጥረት በማድረግ ‘ሁሉንም ነገር መመርመር’ ይኖርበታል።

5. ይሖዋ ጥያቄያችንን ሲመልስልን “ማዳመጥ” የምንችለው እንዴት ነው?

5 የአምላክን ቃል ስናነብ ይሖዋ ሲያነጋግረን እያዳመጥን ነው ሊባል ይችላል። ይሁንና ከአንድ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያለውን አመለካከት ለማወቅ ከፈለግን የተለየ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን ጥያቄ በፈጠረብን ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሊሆን ይገባል። የይሖዋ ድርጅት ባዘጋጃቸው በርካታ የምርምር መሣሪያዎች ተጠቅመን በዚያ ጉዳይ ላይ ምርምር ልናደርግ እንችላለን። (ምሳሌ 2:3-6) ይሖዋ ምርምር ስናደርግ እንዲመራንና ከዚያ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያለውን አመለካከት ለማወቅ እንዲያግዘን በጸሎት ልንጠይቀው እንችላለን። ከዚያም ለእኛ ሁኔታ የሚሠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችንና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምክሮችን መፈለግ እንችላለን። ከእኛ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ስላጋጠማቸው ሰዎች የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን መመርመራችንም ሊጠቅመን ይችላል።

6. ስብሰባዎች ጥርጣሬያችንን ለማሸነፍ የሚረዱን እንዴት ነው?

6 በስብሰባዎቻችን ላይም ይሖዋ ሲያነጋግረን “ማዳመጥ” እንችላለን። በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን የምንገኝ ከሆነ ጥርጣሬያችንን ለማሸነፍ የሚረዳንን ሐሳብ ከመድረክ ላይ ከሚቀርቡ ንግግሮች ወይም ተሳታፊዎች ከሚሰጧቸው መልሶች ማግኘት እንችላለን። (ምሳሌ 27:17) ከዚህ በመቀጠል አንዳንድ ጥርጣሬዎችን ማሸነፍ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

ይሖዋ ትኩረት የሚሰጥህ መሆኑን ስትጠራጠር

7. አንዳንዶች ምን ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ?

7 ‘ይሖዋ በእርግጥ ትኩረት ይሰጠኛል?’ ብለህ ጠይቀህ ታውቃለህ? ከቁብ የማትቆጠር እንደሆንክ የሚሰማህ ከሆነ ከጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ጋር ወዳጅ መሆን የማይታሰብ ነገር እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል። ንጉሥ ዳዊትም እንዲህ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ይሖዋ የሰው ልጆችን ማየቱ እንኳ በጣም አስገራሚ እንደሆነ ስለተሰማው እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ታስተውለው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ቦታ ትሰጠውስ ዘንድ ሟች የሆነው የሰው ልጅ ምንድን ነው?” (መዝ. 144:3) ታዲያ የጥያቄህን መልስ ማግኘት የምትችለው ከየት ነው?

8. በ1 ሳሙኤል 16:6, 7, 10-12 መሠረት ይሖዋ ከሰዎች ጋር በተያያዘ ምን ያስተውላል?

8 መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ይሖዋ ሌሎች ትኩረት ለማይሰጧቸው ሰዎች ትኩረት እንደሚሰጥ እንማራለን። ለምሳሌ ይሖዋ ከእሴይ ልጆች መካከል አንዱን የእስራኤል ንጉሥ አድርጎ እንዲቀባ ሳሙኤልን ልኮት ነበር። እሴይ ከስምንት ልጆቹ መካከል ሰባቱን ወደ ሳሙኤል አመጣቸው። ይሁንና የመጨረሻውን ልጁን ዳዊትን አላመጣውም። b ያም ቢሆን ይሖዋ የመረጠው ዳዊትን ነበር። (1 ሳሙኤል 16:6, 7, 10-12ን አንብብ።) ይሖዋ የዳዊትን ውስጣዊ ማንነት ተመልክቷል፤ ዳዊት ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት ያለው ወጣት ነበር።

9. ይሖዋ ትኩረት እንደሚሰጥህ እርግጠኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

9 ይሖዋ ትኩረት እንደሚሰጥህ ያሳየባቸውን መንገዶች ለማሰብ ሞክር። ለአንተ ሁኔታ የሚስማማ ምክር እንደሚሰጥህ ቃል ገብቷል። (መዝ. 32:8) አንተን በደንብ የማያውቅህ ከሆነ እንዴት ይህን ሊያደርግ ይችላል? (መዝ. 139:1) የሚሰጥህን ምክር በሥራ ላይ ማዋልህ ምን ጥቅም እንዳስገኘልህ ስትመለከት ይሖዋ ትኩረት እንደሚሰጥህ እርግጠኛ ትሆናለህ። (1 ዜና 28:9፤ ሥራ 17:26, 27) ይሖዋ ጥረትህን ያስተውላል። መልካም ባሕርያትህን ይመለከታል፤ ሊረዳህም ይፈልጋል። (ኤር. 17:10) ወዳጁ እንድትሆን ላቀረበልህ ግብዣ ምላሽ እንድትሰጥ ይፈልጋል።—1 ዮሐ. 4:19

“[ይሖዋን] ብትፈልገው ይገኝልሃል።”—1 ዜና 28:9 (አንቀጽ 9ን ተመልከት) c


ያደረግካቸው ውሳኔዎች ትክክል መሆናቸውን ስትጠራጠር

10. ቀደም ሲል ስላደረግናቸው ውሳኔዎች ስናስብ የትኞቹ ጥያቄዎች ሊፈጠሩብን ይችላሉ?

10 አንዳንዶች ሕይወታቸውን መለስ ብለው ሲያስቡ፣ ያደረጓቸው ውሳኔዎች ትክክል መሆናቸውን ይጠራጠሩ ይሆናል። ምናልባትም ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ መንገድ ለማገልገል ሲሉ ጥሩ ሥራቸውን ወይም አትራፊ ንግዳቸውን ትተው ሊሆን ይችላል። ይህን ውሳኔ ካደረጉ ምናልባትም አሥርተ ዓመታት አልፈው ይሆናል። በወቅቱ ዓለማዊ ግቦችን የተከታተሉ ሰዎች አሁን የተደላደለ ሕይወት የሚመሩ ሊመስል ይችላል። ይህን ሲያዩ እንዲህ ብለው ያስቡ ይሆናል፦ ‘ይሖዋን ለማገልገል ስል መሥዋዕት መክፈሌ በእርግጥ ጠቅሞኛል? ወይስ ሌሎች አጋጣሚዎች እንዲያመልጡኝ አድርጓል?’

11. የመዝሙር 73 ጸሐፊ ምን አስጨንቆት ነበር?

11 እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች የሚፈጠሩብህ ከሆነ የመዝሙር 73 ጸሐፊ ምን እንደተሰማው አስብ። ይህ መዝሙራዊ ሌሎች ጤናማና ባለጸጋ እንደሆኑ እንዲሁም ከውጥረት ነፃ የሆነ ሕይወት እንደሚመሩ ተሰምቶት ነበር። (መዝ. 73:3-5, 12) ያገኙትን ስኬት ሲመለከት ይሖዋን ለማገልገል ያደረገው ጥረት ምንም ዋጋ እንደሌለው ተሰማው። ይህ ተስፋ አስቆራጭ ሐሳብ ‘ቀኑን ሙሉ አስጨነቀው።’ (መዝ. 73:13, 14) ታዲያ ጭንቀቱን ማሸነፍ የቻለው እንዴት ነው?

12. በመዝሙር 73:16-18 መሠረት መዝሙራዊው ጭንቀቱን ማሸነፍ የቻለው እንዴት ነው?

12 መዝሙር 73:16-18ን አንብብ። መዝሙራዊው ሰላማዊ ቦታ ወደሆነው ወደ ይሖዋ መቅደስ ሄደ። እዚያም ተረጋግቶ ማሰብ ቻለ። የአንዳንድ ሰዎች ሕይወት የተደላደለ ቢመስልም እንኳ የወደፊቱ ሕይወታቸው አስተማማኝ እንዳልሆነ አስተዋለ። መንፈሳዊ ነገሮችን መከታተል ከሁሉ የተሻለ ውሳኔ እንደሆነ በመገንዘቡ የአእምሮ ሰላም አገኘ። በዚህም የተነሳ፣ ይሖዋን ማገልገሉን ለመቀጠል ያለው ቁርጠኝነት በድጋሚ ተቀጣጠለ።—መዝ. 73:23-28

13. ቀደም ሲል ያደረግካቸውን ውሳኔዎች በተመለከተ ጥርጣሬ ከተሰማህ የአእምሮ ሰላም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

13 አንተም በተመሳሳይ በአምላክ ቃል እርዳታ የአእምሮ ሰላም ማግኘት ትችላለህ። እንዴት? በሰማይ የምታከማቸውን ሀብት ጨምሮ ያገኘሃቸው ነገሮች ያላቸውን ዋጋ አስብ፤ ከዚያም ያገኘኸውን ነገር ሀብት የሚያሳድዱ ሰዎች ካላቸው ነገር ጋር አወዳድር። እነሱ ያላቸው ዓለም የሚሰጣቸው ነገር ብቻ ነው። ለወደፊት ተስፋ የሚያደርጉት ምንም ነገር ስለሌለ የሚታመኑት በዚህ ዓለም በሚያገኙት ስኬት ላይ ብቻ ነው። ለአንተ ግን ይሖዋ ልታስበው ከምትችለው በላይ በረከት እንደሚሰጥህ ቃል ገብቶልሃል። (መዝ. 145:16) ልናስብበት የሚገባው ሌላም ነገር አለ፦ የተለየ ውሳኔ አድርገን ቢሆን ኖሮ ሕይወታችን ምን ይመስል እንደነበር በእርግጥ ማወቅ እንችላለን? ሆኖም ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች ነን። ለአምላክና ለሰዎች ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው ውሳኔ የሚያደርጉ ሰዎች መልካም ነገር አይጎድልባቸውም።

ይሖዋ ቃል የገባልህን በረከት አሻግረህ ተመልከት (አንቀጽ 13ን ተመልከት) d


ይሖዋ ሊጠቀምብህ የሚችል መሆኑን ስትጠራጠር

14. አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ናቸው? ምን ጥያቄ ሊፈጠርባቸውስ ይችላል?

14 አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች በዕድሜ መግፋት፣ በጤና መቃወስ ወይም በአካል ጉዳት የተነሳ አቅማቸው ተገድቧል። በዚህም ምክንያት በይሖዋ ዘንድ ስላላቸው ዋጋ ጥርጣሬ ሊገባቸው ይችላል። ‘ይሖዋ አሁንም ሊጠቀምብኝ ይችላል?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል።

15. የመዝሙር 71 ጸሐፊ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበር?

15 የመዝሙር 71 ጸሐፊ እንዲህ ያለ ስሜት ተሰምቶት ነበር። “ጉልበቴ በሚያልቅበት ጊዜም አትተወኝ” በማለት ጸልዮአል። (መዝ. 71:9, 18) ያም ቢሆን ይህ መዝሙራዊ ይሖዋን በታማኝነት እስካገለገለ ድረስ እሱ እንደሚመራውና እንደሚደግፈው እርግጠኛ ነበር። መዝሙራዊው እንደተገነዘበው፣ ይሖዋ የአቅም ገደብ ቢኖርባቸውም እሱን ለማገልገል ልባዊ ጥረት በሚያደርጉ ሰዎች ይደሰታል።—መዝ. 37:23-25

16. ይሖዋ አረጋውያንን የሚጠቀምባቸው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (መዝሙር 92:12-15)

16 አረጋውያን፣ ያላችሁበትን ሁኔታ በተመለከተ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ይኑራችሁ። አካላችሁ ቢደክምም እንኳ ይሖዋ በመንፈሳዊ እንድታብቡ ሊረዳችሁ ይችላል። (መዝሙር 92:12-15ን አንብብ።) አሁን ማድረግ በማትችሉት ነገር ላይ ከማተኮር ይልቅ ማድረግ በምትችሉት ነገር ላይ አተኩሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ለሌሎች ምሳሌ በመሆን እንዲሁም ልባዊ አሳቢነት በማሳየት ወንድሞቻችሁን ማጠናከር ትችላላችሁ። ይሖዋ ባለፉት ዓመታት የረዳችሁ እንዴት እንደሆነ ለሌሎች መናገር ትችላላችሁ፤ እንዲሁም እሱ የሰጣቸው ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ያላችሁን ጠንካራ እምነት መግለጽ ትችላላችሁ። ከዚህም ሌላ ሌሎች ሰዎችን አስመልክቶ የምታቀርቡት ልባዊ ጸሎት ያለውን ኃይል አቅልላችሁ አትመልከቱ። (1 ጴጥ. 3:12) ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ሁላችንም ለይሖዋም ሆነ ለወንድሞቻችን መስጠት የምንችለው ነገር አለ።

17. ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደር የሌለብን ለምንድን ነው?

17 በይሖዋ አገልግሎት ማከናወን የምትችለው ነገር በመገደቡ የተነሳ ሐዘን የሚሰማህ ከሆነ ይሖዋ የምታከናውነውን ማንኛውንም ነገር ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት አስታውስ። የምታከናውነውን ነገር ከሌሎች ጋር ለማወዳደር ትፈተን ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ልታደርግ አይገባም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ ሰዎችን በዚህ መልኩ አያወዳድርም። (ገላ. 6:4) ለምሳሌ ማርያም ለኢየሱስ እጅግ ውድ የሆነና ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ሰጥታው ነበር። (ዮሐ. 12:3-5) ድሃዋ መበለት ደግሞ በቤተ መቅደሱ መዋጮ ያደረገችው በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸውን ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች ነው። (ሉቃስ 21:1-4) ሆኖም ኢየሱስ እነዚህን ሴቶች አላወዳደራቸውም። ከዚህ ይልቅ ያተኮረው ሁለቱም ባሳዩት እምነት ላይ ነው። ኢየሱስ የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ ነው። የምታከናውነው ነገር ለአንተ በጣም ትንሽ ቢመስልህም እንኳ ለይሖዋ ባለህ ፍቅርና ታማኝነት ተነሳስተህ እስካደረግከው ድረስ በእሱ ዘንድ ትልቅ ዋጋ አለው።

18. ጥርጣሬያችንን ለማሸነፍ ምን ይረዳናል? (“ የይሖዋ ቃል ጥርጣሬህን ለማሸነፍ ይረዳሃል” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

18 ሁላችንም አልፎ አልፎ ጥርጣሬ ያድርብናል። ይሁንና እስካሁን እንደተመለከትነው፣ አስተማማኝና እውነተኛ የሆነው የአምላክ ቃል ጥርጣሬያችንን ለማሸነፍ ይረዳናል። እንግዲያው ጥርጣሬህን በእምነት ለመተካት ጥረት አድርግ። ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ይሰጥሃል። የከፈልካቸውን መሥዋዕቶች ያደንቃል፤ ወሮታ እንደሚከፍልህም ቃል ገብቷል። ይሖዋ ሁሉንም ታማኝ አገልጋዮቹን እንደሚወዳቸውና ትኩረት እንደሚሰጣቸው እርግጠኛ ሁን።

መዝሙር 111 ለደስታችን ምክንያት የሆኑ ነገሮች

a ተጨማሪ ማብራሪያ፦ በዚህ ርዕስ ውስጥ የምንመለከተው በይሖዋ ዘንድ ያለንን ዋጋ ወይም ያደረግናቸውን ውሳኔዎች በተመለከተ ስለሚሰማን ጥርጣሬ ነው። እንዲህ ያለው ጥርጣሬ መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋና እሱ በገባው ቃል ላይ እምነት ከማጣት ጋር አያይዞ ከሚጠቅሰው ጥርጣሬ የተለየ ነው።

b መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ዳዊትን ሲመርጠው ዕድሜው ስንት እንደነበር በቀጥታ ባይነግረንም በወቅቱ ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ያለ ወጣት ሳይሆን አይቀርም።—የመስከረም 1, 2011 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 29 አን. 2ን ተመልከት።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት ወጣት እህት ከቅዱሳን መጻሕፍት ምክር ለማግኘት ጥረት በማድረግ ይሖዋን ትፈልጋለች።

d የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም ቤተሰቡን ለማስተዳደር የጽዳት ሥራ ይሠራል፤ አእምሮው ያተኮረው ግን ወደፊት በሚመጣው ገነት ላይ ነው።