በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

1924—የዛሬ መቶ ዓመት

1924—የዛሬ መቶ ዓመት

የጥር 1924 ቡለቲን a እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ወጥቶ ነበር፦ “በዓመቱ መጀመሪያ ላይ እያንዳንዱ የጌታ ልጅ አገልግሎቱን ማስፋት የሚችልባቸውን አጋጣሚዎች መፈለጉ ጠቃሚ ነው።” በዚያ ዓመት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሁለት መንገዶች ማለትም ደፋሮች በመሆንና አዳዲስ የስብከት ዘዴዎችን በመሞከር ይህን ምክር በሥራ ላይ አውለዋል።

በሬዲዮ ተጠቅሞ መስበክ

በቤቴል የሚያገለግሉት ወንድሞች በስታትን ደሴት፣ ኒው ዮርክ ሲቲ የ​WBBR የሬዲዮ ጣቢያን ለመገንባት ከአንድ ዓመት በላይ ሲሠሩ ቆይተዋል። መሬቱን ከመነጠሩ በኋላ ለሠራተኞቹ የሚሆን ትልቅ ቤትና ለመሣሪያዎቹ የሚሆን ሌላ ሕንፃ ገነቡ። ይህ ሥራ ሲጠናቀቅ ወንድሞች ስርጭቱን ለመጀመር የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን ማሟላት ጀመሩ። ሆኖም የተለያዩ እንቅፋቶችን መወጣት አስፈልጓቸዋል።

ወንድሞች የሬዲዮ ጣቢያውን ዋነኛ አንቴና መስቀል አስቸግሯቸው ነበር። ዘጠና አንድ ሜትር ርዝመት ያለው አንቴና 61 ሜትር ቁመት ባላቸው ሁለት እንጨቶች መካከል መሰቀል ነበረበት። የመጀመሪያ ሙከራቸው ሳይሳካ ቀረ። ወንድሞች በይሖዋ እርዳታ በመተማመን በስተ መጨረሻ ተሳካላቸው። በፕሮጀክቱ ላይ የተካፈለው ካልቪን ፕሮሰር እንዲህ ብሏል፦ “የመጀመሪያው ሙከራችን ቢሳካልን ኖሮ በራሳችን ባከናወንነው ሥራ እንኩራራ ነበር።” ሆኖም ወንድሞች፣ የተሳካላቸው በይሖዋ እርዳታ እንደሆነ ተገንዝበዋል። ያጋጠማቸው እንቅፋት ግን ይህ ብቻ አልነበረም።

የ​WBBR አንቴና ከተሰቀለባቸው እንጨቶች አንዱን ሲያቆሙ

የሬዲዮ ቴክኖሎጂ ገና መጀመሩ ስለነበር አስፈላጊዎቹን መሣሪያዎች ገበያ ላይ ማግኘት ቀላል አልነበረም። በመሆኑም ወንድሞች፣ ያገለገለ ባለ500 ዋት ማሰራጫ ገዙ። ማይክሮፎን ከመግዛት ይልቅ የስልክ ማይክሮፎን ተጠቀሙ። የካቲት ውስጥ አንድ ምሽት ላይ ወንድሞች እነዚህ ቀለል ያሉ መሣሪያዎች በትክክል የሚሠሩ መሆኑን ለመሞከር አሰቡ። ለሙከራ የሚሆን ፕሮግራም ማሰራጨት ስለነበረባቸው ወንድሞች የመንግሥቱን መዝሙሮች ዘመሩ። ኧርነስት ሎ በወቅቱ ያጋጠማቸውን አስቂኝ ሁኔታ ተናግሯል። ወንድም ራዘርፎርድ b 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በብሩክሊን በሚገኘው ቢሮው ውስጥ ሆኖ በሬዲዮ መዝሙራቸውን ካዳመጠ በኋላ ስልክ ደወለላቸው።

ወንድም ራዘርፎርድ “ጩኸታችሁን አቁሙ። የድመት ጫጫታ ነው የሚመስለው” አላቸው። ወንድሞች ኀፍረት ተሰምቷቸው ማሰራጫውን ዘጉት፤ ሆኖም የመጀመሪያ ስርጭታቸውን ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑ ገባቸው።

የካቲት 24, 1924 የመጀመሪያው ስርጭት በተደረገበት ወቅት ወንድም ራዘርፎርድ የሬዲዮ ጣቢያው “ለመሲሑ መንግሥት ጉዳዮች” እንዲውል የውሰና ንግግር አቀረበ። የሬዲዮ ጣቢያው ዓላማ “ሰዎች ሃይማኖታቸው ምንም ይሁን ምን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም ስለምንኖርበት ዘመን ግንዛቤ እንዲያገኙ መርዳት” እንደሆነ ገለጸ።

በስተ ግራ፦ ወንድም ራዘርፎርድ በመጀመሪያው ስቱዲዮ ውስጥ

በስተ ቀኝ፦ የሬዲዮ ማሰራጫውና ሌሎቹ መሣሪያዎች

የመጀመሪያ ስርጭቱ የተሳካ ነበር። ለቀጣዮቹ 33 ዓመታት WBBR የድርጅቱ ዋነኛ የሬዲዮ ጣቢያ ሆኖ ቀጥሏል።

በቀሳውስት ላይ የተሰነዘረ ክስ

ሐምሌ 1924 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በኮለምበስ፣ ኦሃዮ በተካሄደ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኙ። ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ልዑካን በአረብኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛ፣ በግሪክኛ፣ በሃንጋሪያኛ፣ በጣሊያንኛ፣ በሊቱዋንያኛ፣ በፖላንድኛ፣ በሩሲያኛ፣ በስካንዲኔቪያ ቋንቋዎችና በዩክሬንኛ ንግግሮችን አዳመጡ። የስብሰባው የተወሰነ ክፍል በሬዲዮ ተሰራጨ፤ እንዲሁም ኦሃዮ ስቴት ጆርናል የተባለው ጋዜጣ ስለ ስብሰባው በየዕለቱ እንዲዘግብ ዝግጅት ተደረገ።

በ1924 በኮለምበስ፣ ኦሃዮ የተካሄደው ትልቅ ስብሰባ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 24 ከ5,000 የሚበልጡ ተሰብሳቢዎች በአገልግሎት ተካፈሉ። ወደ 30,000 የሚጠጉ መጻሕፍትን አበረከቱ፤ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን አስጀመሩ። መጠበቂያ ግንብ ይህን ዕለት “እጅግ አስደሳች የሆነው የስብሰባው ክፍል” በማለት ጠርቶታል።

የስብሰባው ሌላ ጉልህ ገጽታ ደግሞ ዓርብ፣ ሐምሌ 25 ወንድም ራዘርፎርድ ያነበበው በቀሳውስት ላይ የተሰነዘረ ክስ ነበር። በሕጋዊ ሰነድ መልክ የቀረበው ይህ መግለጫ የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የንግዱ ዓለም መሪዎች “ሕዝቡ አምላክ ለእነሱ ሕይወት ለመስጠት ስላደረገው ዝግጅት ሳያውቁ በድንቁርና እንዲቃትቱ” በማድረግ ወንጀል እንደተከሰሱ ይገልጻል። በተጨማሪም መግለጫው፣ እነዚህ ሰዎች ‘የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርን እንደደገፉ እንዲሁም የአምላክ መንግሥት ምድራዊ ወኪል እንደሆነ እንደተናገሩ’ ይገልጻል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ይህን መልእክት ለሕዝቡ ለማድረስ ድፍረት ጠይቆባቸዋል።

መጠበቂያ ግንብ ስብሰባው ያስገኘውን ውጤት ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በኮለምበስ በተካሄደው ትልቅ ስብሰባ ላይ የተገኘው ይህ አነስተኛ የጌታ ሠራዊት . . . ጠላት የሚሰነዝርበትን ማንኛውንም እሳታማ ፍላጻ ለመመከት . . . እምነቱ ተጠናክሮ ተመልሷል።” በስብሰባው ላይ የተገኘው ሊዮ ክላውስ እንዲህ ብሏል፦ “ስብሰባውን ጨርሰን ስንወጣ ይህን መልእክት በክልላችን ውስጥ ለማሰራጨት ጓጉተን ነበር።”

ቀሳውስት ተከሰሱ የተባለው ትራክት

በጥቅምት ወር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ቀሳውስት ተከሰሱ በሚል ርዕስ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ቅጂዎች ታትሞ የወጣውን የወንድም ራዘርፎርድን መግለጫ የያዘውን ትራክት ማሰራጨት ጀመሩ። አነስተኛ ከተማ በሆነችው በክሊቭላንድ፣ ኦክላሆማ ወንድም ፍራንክ ጆንሰን ሌሎቹ አስፋፊዎች በመኪና እንዲወስዱት ከእነሱ ጋር ከተቀጣጠረበት ሰዓት 20 ደቂቃ አስቀድሞ ትራክቶቹን በክልሉ ውስጥ አሰራጭቶ ጨረሰ። በእሱ ስብከት የተበሳጩ የከተማው ሰዎች እየፈለጉት ስለነበር ግልጽ ቦታ ላይ ቆሞ ወንድሞችን ሊጠብቃቸው አልቻለም። ፍራንክ በአቅራቢያው በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለመደበቅ ወሰነ። ቤተ ክርስቲያኑ ባዶ ስለነበር ቀሳውስት ተከሰሱ የሚለውን ትራክት በሰባኪው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥና በእያንዳንዱ ወንበር ላይ አስቀመጠ። ከዚያም ቶሎ ብሎ ከቤተ ክርስቲያኑ ወጣ። አሁንም የተወሰነ ጊዜ ስለነበረው ሁለት ሌሎች ቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ በመግባት ይህንኑ ነገር አደረገ።

ከዚያም ፍራንክ ከወንድሞች ጋር ወደተቀጣጠረበት ቦታ በፍጥነት ሄደ። ከአንድ የነዳጅ ማደያ በስተ ጀርባ ተደብቆ የሚያሳድዱትን ሰዎች አጮልቆ ማየት ጀመረ። ሰዎቹ በአጠገቡ በመኪና ቢያልፉም አላዩትም። ልክ ሰዎቹ እንዳለፉ፣ በአቅራቢያው ባለ ከተማ ሲሰብኩ የነበሩት የፍራንክ የአገልግሎት ጓደኞች መጡና ይዘውት ሄዱ።

ከእነዚህ ወንድሞች መካከል አንዱ እንዲህ ብሏል፦ “ከተማዋን ለቀን በምንወጣበት ጊዜ በሦስቱ ቤተ ክርስቲያኖች በኩል አልፈናል። በእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት 50 ገደማ ሰዎች ቆመው ነበር። አንዳንዶቹ ሰዎች ትራክቱን እያነበቡ ነበር። አንዳንዶቹ ደግሞ ትራክቱን ከፍ አድርገው ይዘው ለሰባኪው ያሳዩታል። ያመለጥነው ለጥቂት ነው! ጥበቃ ስላደረገልን እንዲሁም ከእነዚህ የመንግሥቱ ጠላቶች ለማምለጥ የሚያስችል ጥበብ ስለሰጠን አምላካችንን ይሖዋን አመሰገንነው።”

በሌሎች አገሮች በድፍረት መስበክ

ዮሴፍ ክሬት

በሌሎች አገሮች ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም በድፍረት ይሰብኩ ነበር። በሰሜናዊ ፈረንሳይ የሚኖረው ዮሴፍ ክሬት ከፖላንድ ለመጡ የማዕድን ቆፋሪዎች ይሰብክ ነበር። “በቅርቡ ሙታን ይነሳሉ” በሚል ርዕስ ንግግር እንዲያቀርብ ዝግጅት ተደረገ። ወንድሞችና እህቶች የከተማዋን ነዋሪዎች ሲጋብዙ በአካባቢው ያለው ቄስ ምዕመናኑን በንግግሩ ላይ እንዳይገኙ አስጠነቀቃቸው። ሆኖም ማስጠንቀቂያው ያስገኘው ውጤት ከተጠበቀው ተቃራኒ ነበር። ቄሱን ጨምሮ ከ5,000 የሚበልጡ ሰዎች በንግግሩ ላይ ተገኙ። ወንድም ክሬት፣ ቄሱ ለእምነቱ ጥብቅና እንዲቆም ግብዣ አቀረበለት። ቄሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም። ወንድም ክሬት፣ የመሠከረላቸው ሰዎች ለአምላክ ቃል ጥማት እንዳላቸው ስላስተዋለ ያሉትን ጽሑፎች በሙሉ አበረከተ።—አሞጽ 8:11

ክሎድ ብራውን

አፍሪካ ውስጥ በምትገኘው በጎልድ ኮስት (አሁን ጋና በመባል ትታወቃለች) እውነትን ያስተዋወቀው ክሎድ ብራውን ነበር። ያቀረባቸው ንግግሮችና ያበረከታቸው ጽሑፎች በዚያች አገር ውስጥ እውነት በፍጥነት እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የፋርማሲ ባለሙያ ለመሆን እየተማረ የነበረው ጆን ብላንክሰን ወንድም ብራውን ካቀረባቸው ንግግሮች አንዱን አዳመጠ። በዚህ ጊዜ እውነትን እንዳገኘ ወዲያውኑ ተገነዘበ። ጆን እንዲህ ብሏል፦ “የተማርኩት እውነት በጣም ስላስደሰተኝ ይህን እውነት በፋርማሲ ትምህርት ቤታችን ውስጥ በነፃነት እናገር ነበር።”

ጆን ብላንክሰን

ጆን የሥላሴ ትምህርት ቅዱስ ጽሑፋዊ እንዳልሆነ ሲገነዘብ ወደ አንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ቄሱን ስለ ሥላሴ ትምህርት ጠየቀው። ቄሱም “አንተ ክርስቲያን አይደለህም፤ የዲያብሎስ ወገን ነህ። ሂድ ከዚህ!” ብሎ አባረረው።

ጆን ቤቱ ከገባ በኋላ ለቄሱ ደብዳቤ በመጻፍ ሕዝብ በተሰበሰበበት ስለ ሥላሴ ትምህርት እንዲያብራራ ጠየቀው። በዚህ ጊዜ ቄሱ፣ የፋርማሲ ትምህርት ቤቱ ኃላፊ ጆንን ወደ ቢሮው እንዲጠራው አደረገ። ከዚያም ኃላፊው፣ በእርግጥ ለቄሱ ደብዳቤ ጽፎለት እንደሆነ ጆንን ጠየቀው።

ጆንም “አዎ፣ ጽፌለታለሁ” በማለት መለሰ።

ኃላፊው ጆንን ለቄሱ ደብዳቤ ጽፎ ይቅርታ እንዲጠይቀው አዘዘው። በመሆኑም ጆን እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፈ፦

“የትምህርት ቤታችን ኃላፊ ደብዳቤ ጽፌ ይቅርታ እንድጠይቅህ አዞኛል። የሐሰት ትምህርት እንደምታስተምር አምነህ ከተቀበልክ ይቅርታ ልጠይቅህ ዝግጁ ነኝ።”

የትምህርት ቤቱ ኃላፊ ደብዳቤውን ሲያይ ደንግጦ “ብላንክሰን፣ መጻፍ የምትፈልገው ደብዳቤ ይህ ነው?” አለው።

እሱም “አዎ፣ ሌላ የምጽፈው ነገር የለኝም” ብሎ መለሰ።

ኃላፊውም እንዲህ አለው፦ “ከትምህርት ቤት ትባረራለህ። መንግሥት የሚደግፈውን ቤተ ክርስቲያን ቄስ ተቃውመህ በመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ መማር የምትችል ይመስልሃል?”

በዚህ ጊዜ ጆን እንዲህ አለ፦ “ግን አንተ ስታስተምረን ያልገባንን ነገር መጠየቅ እንችላለን አይደል?”

ኃላፊውም “አዎ፣ ትችላላችሁ” ሲል መለሰ።

ከዚያም ጆን እንዲህ አለ፦ “እኔም ያደረግኩት ይህንኑ ነው። ቄሱ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያስተምረኝ ጥያቄ ጠየቅኩት። እሱ ጥያቄውን መመለስ ስላቃተው እኔ ይቅርታ መጠየቅ ያለብኝ ለምንድን ነው?”

ጆን ብላንክሰን ደብዳቤ ጽፎ ይቅርታ ባይጠይቅም ከትምህርት ቤቱ አልተባረረም።

የወደፊቱን ጊዜ በጉጉት መጠበቅ

መጠበቂያ ግንብ የዓመቱን እንቅስቃሴ ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በእርግጥም እንደ ዳዊት ‘ለውጊያው ብርታት ታስታጥቀኛለህ’ ማለት እንችላለን። (መዝሙር 18:39) በዚህ ዓመት በእጅጉ ተበረታተናል፤ ምክንያቱም የጌታን እጅ ተመልክተናል። . . . ታማኝ አገልጋዮቹ . . . በደስታ ምሥክርነት ሲሰጡ ነበር።”

በዓመቱ መገባደጃ አካባቢ ወንድሞች የሬዲዮ ስርጭቱን ለማስፋፋት ዝግጅት አደረጉ። በቺካጎ አቅራቢያ አዲስ የሬዲዮ ጣቢያ መገንባት ጀመሩ። ይህ አዲስ የሬዲዮ ጣቢያ ወርድ (WORD) ማለትም “ቃል” ተብሎ ይጠራ ነበር፤ በሬዲዮ አማካኝነት የሚሰብኩት የአምላክን ቃል እንደመሆኑ መጠን እንዲህ ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው። ወርድ የተባለው የሬዲዮ ጣቢያ ባለ5,000 ዋት ማሰራጫ በመጠቀም የመንግሥቱን መልእክት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ እስከ ካናዳ ሰሜናዊ ክፍል ድረስ አሰራጭቷል።

ቀጣዩ ዓመት ማለትም 1925 አስደናቂ መንፈሳዊ ብርሃን የፈነጠቀበት ዓመት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ስለ ራእይ ምዕራፍ 12 አዲስ ግንዛቤ አገኙ። ይህ አዲስ ግንዛቤ አንዳንዶች እንዲሰናከሉ ምክንያት ሆኗል። ሌሎች በርካታ ሰዎች ግን በሰማይ ስለተከናወነው ነገር እንዲሁም ይህ ክንውን በምድር ላይ ባሉ የአምላክ ሕዝቦች ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ አዲስ ግንዛቤ በማግኘታቸው በእጅጉ ተደስተዋል።

a አሁን ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን—የስብሰባው አስተዋጽኦ ተብሎ ይጠራል።

b በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን እንቅስቃሴ ይመራ የነበረው ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ “ዳኛ” ራዘርፎርድ ተብሎ ይጠራ ነበር። ምክንያቱም በቤቴል ማገልገል ከመጀመሩ በፊት አልፎ አልፎ በሚዙሪ ስምንተኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ልዩ ዳኛ ሆኖ ይሠራ ነበር።