በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ጭንቀት

ጭንቀት

ጭንቀት ሁለት ገጽታዎች አሉት። አንደኛው ጠቃሚ ሲሆን ሌላው ደግሞ ጎጂ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሁለቱንም ገጽታዎች ለይተን ማወቅ እንድንችል ይረዳናል።

መጨነቅ ተፈጥሯዊ ነው?

እውነታው፦

ጭንቀት ያለመረጋጋት፣ የመረበሽ ወይም የስጋት ስሜትን ያካትታል። የምንኖረው አስተማማኝ ባልሆነ ዓለም ውስጥ በመሆኑ አልፎ አልፎ ማናችንም በጭንቀት ስሜት ልንዋጥ እንችላለን።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ንጉሥ ዳዊት “ልቤ በየዕለቱ በሐዘን እየተደቆሰ፣ በጭንቀት ተውጬ የምኖረው እስከ መቼ ነው?” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 13:2) ዳዊት ይህን ሁኔታ እንዲቋቋም የረዳው ምንድን ነው? በጸሎት አማካኝነት የልቡን ለአምላክ ያፈሰሰ ከመሆኑም ሌላ በአምላክ ታማኝ ፍቅር ሙሉ በሙሉ ይተማመን ነበር። (መዝሙር 13:5፤ 62:8) አምላክም የከበደንን ነገር በእሱ ላይ እንድንጥል ጋብዞናልአንደኛ ጴጥሮስ 5:7 “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ [በአምላክ] ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል” ይላል።

ለምንወዳቸው ሰዎች መልካም ነገር ማድረጋችን ስለ እነሱ ብዙ እንዳንጨነቅ ይረዳናል

አብዛኛውን ጊዜ ግን የሚሰማንን ጭንቀት ለማስታገሥ ልናደርግ የምንችለው ነገር ይኖራል። ለምሳሌ ያህል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ጳውሎስ “የጉባኤዎች ሁሉ ሐሳብ [ባስጨነቀው]” ጊዜ በዚያ ያሉትን ወንድሞች ለማጽናናትና ለማበረታታት ጥረት አድርጓል። (2 ቆሮንቶስ 11:28) ከዚህ አንጻር ሲታይ የተሰማው ጭንቀት ጠቃሚ ነበር ማለት እንችላለን፤ ምክንያቱም አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠት አነሳስቶታል። የእኛም ሁኔታ ከዚህ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። የዚህ ተቃራኒ የሆነ አመለካከት መያዝ ይኸውም ግድየለሽ ወይም ቸልተኛ መሆን ለሌሎች ፍቅራዊ አሳቢነት እንደሚጎድለን ይጠቁማል።—ምሳሌ 17:17

“ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”ፊልጵስዩስ 2:4

ከልክ ያለፈ ጭንቀትን መቆጣጠር የምንችለው እንዴት ነው?

እውነታው፦

ሰዎች ከዚህ በፊት ስለሠሩት ስህተት፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ወይም ከገንዘብ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች በማሰብ ይጨነቁ ይሆናል። *

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ከዚህ በፊት በሠሩት ስህተት የተነሳ መጨነቅ፦ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት ሰካራሞች፣ ቀማኞች፣ ሴሰኞችና ሌቦች ነበሩ። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) እነዚህ ሰዎች ቀደም ሲል ባደረጉት ነገር የተነሳ አልተጨነቁም፤ ምክንያቱም አካሄዳቸውን ከለወጡ አምላክ ታላቅ ምሕረት እንደሚያሳያቸው እርግጠኞች ነበሩ። ደግሞም አምላክ በነፃ ምሕረት እንደሚያደርግ ያውቁ ነበር። መዝሙር 130:4 “በአንተ [በአምላክ] ዘንድ በእርግጥ ይቅርታ አለ” ይላል።

ስለ ወደፊቱ ጊዜ መጨነቅ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት” ብሏል። (ማቴዎስ 6:25, 34) ነጥቡ ምንድን ነው? ዛሬ ባጋጠሟችሁ ችግሮች ላይ ብቻ ትኩረት አድርጉ። የነገውን ጭንቀት በዛሬው ላይ ጨምራችሁ ጭንቀታችሁን አታባብሱት፤ እንዲህ ማድረጋችሁ የማመዛዘን ችሎታችሁን ሊያዛባባችሁና ቸኩላችሁ ውሳኔ ላይ እንድትደርሱ ሊያደርጋችሁ ይችላል። ጊዜ ካለፈ በኋላ ደግሞ፣ በሌለ ነገር ስትጨነቁ እንደነበር ትገነዘቡ ይሆናል።

ስለ ገንዘብ መጨነቅ፦ አንድ ጥበበኛ ሰው “ድሃም ሆነ ባለጸጋ አታድርገኝ” ሲል ጸልዮ ነበር። (ምሳሌ 30:8) ከዚህ ይልቅ ባለው ረክቶ መኖርን ተመኝቷል፤ ይህ ደግሞ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አመለካከት ነው። ዕብራውያን 13:5 እንዲህ ይላል፦ “አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ። እሱ [አምላክ] ‘ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም’ ብሏልና።” ችግር ላይ ስንወድቅ ሊከዳን ከሚችለው ከገንዘብ በተለየ አምላክ በእሱ ላይ የሚታመኑትንና በትንሽ ነገር ረክተው የሚኖሩትን አገልጋዮቹን ፈጽሞ አይከዳቸውም።

“ጻድቅ ሰው ሲጣል፣ ልጆቹም ምግብ ሲለምኑ አላየሁም።”መዝሙር 37:25

ሳንጨነቅ የምንኖርበት ጊዜ ይመጣል?

ሰዎች ምን ይላሉ?

ሃሬት ግሪን የተባለችው ጋዜጠኛ በ2008 ዘ ጋርዲያን ላይ ባወጣችው ርዕስ “ጭንቀት ወደነገሠበት አዲስ ዘመን ተሸጋግረናል” ብላለች። በ2014 ደግሞ ፓትሪክ ኦካነር ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ላይ “አሜሪካውያን ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ በጭንቀት እየተዋጡ ነው” ሲል ጽፏል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“በሰው ልብ ውስጥ ያለ ጭንቀት ልቡ እንዲዝል ያደርገዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።” (ምሳሌ 12:25) የአምላክ መንግሥት ምሥራች ልዩ የሆነ “መልካም ቃል” ይዟል። (ማቴዎስ 24:14) የአምላክ መንግሥት ወይም መስተዳድር፣ እኛ በራሳችን ፈጽሞ ማድረግ የማንችለውን ነገር በቅርቡ ያከናውናል። አዎ፣ በሽታንና ሞትን ጨምሮ ማንኛውንም አስጨናቂ ነገር ከሥረ መሠረቱ ያስወግዳል! አምላክ “እንባን ሁሉ [ከዓይናችን] ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።”—ራእይ 21:4

“በእሱ በመታመናችሁ የተነሳ . . . ተስፋ እንዲትረፈረፍላችሁ ተስፋ የሚሰጠው አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ።”ሮም 15:13

^ አን.10 በጭንቀት ምክንያት በሚመጣ ከባድ የስሜት ቀውስ የሚሠቃዩ ሰዎች የሕክምና ባለሙያ ማማከራቸው ጥሩ ሊሆን ይችላል። ንቁ! መጽሔት ለየትኛውም ዓይነት የሕክምና ዘዴ የድጋፍ ሐሳብ ከመስጠት ይቆጠባል።