በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሳይንቲስቶች ምን ሊነግሩን አይችሉም?

ሳይንቲስቶች ምን ሊነግሩን አይችሉም?

ሳይንቲስቶች በሳይንስ የተደረሰበትን ያህል ስለ ጽንፈ ዓለም ብዙ ነገር አውቀዋል። ያም ቢሆን በጣም አስፈላጊ ለሆኑ በርካታ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አልቻሉም።

ሳይንስ ጽንፈ ዓለም እና ሕይወት እንዴት እንደጀመረ ሊነግረን ይችላል? በአጭሩ አይችልም። አንዳንዶች ኮስሞሎጂ የተባለው የሳይንስ ዘርፍ ጽንፈ ዓለም እንዴት እንደተገኘ ማብራራት እንደሚችል ይሰማቸዋል። ማርሴሎ ግሌይዜር የተባሉት የዳርትማውዝ ኮሌጅ የሥነ ፈለክ ፕሮፌሰር አግኖስቲክ (የአምላክን መኖር በእርግጠኝነት መናገር እንደማይቻል የሚያምኑ) ናቸው፤ ሆኖም እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፦ “‘ጽንፈ ዓለም እንዴት ተገኘ?’ ለሚለው ጥያቄ ማብራሪያ ማግኘት አልቻልንም።”

በተመሳሳይም ‘ሕይወት እንዴት ተገኘ?’ የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ሳይንስ ኒውስ በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንዲህ ይላል፦ “‘ምድር ላይ ሕይወት እንዴት ጀመረ?’ የሚለውን ጉዳይ በትክክል ማወቅ ጨርሶ የማይቻል ይመስላል፤ መጀመሪያ አካባቢ ምድር ላይ ስለተከናወኑት ነገሮች የሚጠቁሙት አብዛኞቹ ጂኦሎጂያዊ መረጃዎች ከጠፉ ዘመን የላቸውም።” እነዚህ ሐሳቦች እንደሚጠቁሙት ሳይንስ ‘ጽንፈ ዓለም እና ሕይወት እንዴት ጀመረ?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት አልቻለም።

ይሁንና ‘ምድር ላይ ያሉት ሕይወት ያላቸው ነገሮች የታሰበበት ንድፍ ካላቸው ንድፋቸውን ያወጣው ማን ነው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። የሚከተሉት ጥያቄዎችም ይፈጠሩብህ ይሆናል፦ ‘ጥበበኛና አፍቃሪ የሆነ ፈጣሪ ካለ ፍጥረታቱ የሆኑት የሰው ልጆች ሲሠቃዩ ዝም የሚለው ለምንድን ነው? እርስ በርስ የሚቃረኑ ብዙ ሃይማኖቶችን እያየ ዝም የሚለው ለምንድን ነው? እሱን እናመልካለን የሚሉ ብዙ ሰዎች በርካታ መጥፎ ነገሮችን ሲፈጽሙ ዝም ብሎ የሚያየው ለምንድን ነው?’

የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ከሳይንስ ማግኘት አይቻልም። ይህ ሲባል ግን እነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ የላቸውም ማለት አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ ብዙ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ አርኪ መልስ አግኝተዋል።

ጊዜ ወስደው መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ አንዳንድ ሳይንቲስቶች በፈጣሪ መኖር እንዲያምኑ ያደረጓቸውን ምክንያቶች ማወቅ የምትፈልግ ከሆነ jw.org​ን ጎብኝ። “ስለ ሕይወት አመጣጥ የተሰጡ አስተያየቶች” ብለህ በመጻፍ ፈልግ።