በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የራስህ መደምደሚያ ላይ መድረስ የምትችለው እንዴት ነው?

የራስህ መደምደሚያ ላይ መድረስ የምትችለው እንዴት ነው?

“ጽንፈ ዓለም ራሱን ከምንም ነገር መፍጠር ይችላል፤ የሆነውም ይህ ነው።”—ስቲቨን ሆኪንግ እና ሌናርድ መሎዲኖቭ፣ የፊዚክስ ሊቃውንት፣ 2010

“አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ።”—መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዘፍጥረት 1:1

ጽንፈ ዓለምን እና ሕይወት ያላቸውን ነገሮች የፈጠራቸው አምላክ ነው? ወይስ እንዲሁ በአጋጣሚ ነው የተገኙት? በዚህ ርዕስ ላይ የተጠቀሱት ሁለት የፊዚክስ ሊቃውንት የተናገሩት ሐሳብ እና በመጽሐፍ ቅዱስ መግቢያ ላይ የሚገኙት ቃላት ፈጽሞ የሚቃረኑ ናቸው። ሁለቱም ሐሳቦች በየፊናቸው አጥባቂ ደጋፊዎች አሏቸው። ብዙ ሰዎች ግን ስለዚህ ጉዳይ እርግጠኛ አይደሉም። ታዋቂ በሆኑ መጻሕፍት እና በሕዝባዊ የክርክር መድረኮች ላይ ጉዳዩ ብዙ ክርክር ተደርጎበታል።

አስተማሪዎችህ በእርግጠኝነት ጽንፈ ዓለም እና ሕይወት በራሳቸው እንደመጡ እንዲሁም ፈጣሪ የሚባል ነገር እንደሌለ ነግረውህ ይሆናል። ይሁንና ፈጣሪ እንደሌለ የሚያሳይ ማስረጃ አቅርበውልሃል? በሌላ በኩል ደግሞ የሃይማኖት መሪዎች ፈጣሪ አለ ብለው ሲሰብኩ ሰምተህ ይሆናል። ሆኖም ሐሳባቸውን በማስረጃ አስደግፈው ነግረውሃል? ወይስ የእምነት ጉዳይ ነው ብለህ በጭፍን እንድትቀበለው ይጠብቁብሃል?

አንተም ይህን ጉዳይ አስበህበት ታውቅ ይሆናል፤ ምናልባትም ፈጣሪ መኖር አለመኖሩን በእርግጠኝነት መናገር የሚችል ሰው እንደሌለ ይሰማህ ይሆናል። ግን ሌላም ጥያቄ ሊፈጠርብህ ይችላል፦ በእርግጥ የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ ለውጥ ያመጣል?

ይህ የንቁ! እትም፣ ብዙ ሰዎች በፈጣሪ መኖር እንዲያምኑ ያደረጓቸውን አንዳንድ ማስረጃዎች ያቀርባል። ከዚያም ሕይወት እንዴት ተገኘ? ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ትልቅ ለውጥ የሚያመጣው ለምን እንደሆነ ያብራራል።