በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጽንፈ ዓለም ምን ይነግረናል?

ጽንፈ ዓለም ምን ይነግረናል?

ጽንፈ ዓለም አሁንም የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎችን እንዳስደመመ ነው። ምርምር ለማድረግ የሚጠቀሙባቸው መሣሪያዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የተራቀቁ ሆነዋል። ታዲያ በምርምራቸው ምን አግኝተዋል?

ጽንፈ ዓለም የተደራጀ ነው። አስትሮኖሚ በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንዲህ ይላል፦ “ጋላክሲዎች ዝም ብለው ሰማይ ላይ የተበተኑ ነገሮች አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ እንደ ድር እርስ በርስ ተሳስረው የተቀመጡ ናቸው።” እንዲህ እንዲደራጁ ያስቻላቸው ምንድን ነው? ሳይንቲስቶች ለዚህ ሚስጥሩ ዳርክ ማተር (ጽልመታዊ ቁስ አካል) የተባለ በዓይን የማይታይ ቁስ አካል ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ። ይህ ዳርክ ማተር የተባለው ነገር እንዲህ ተብሎለታል፦ “ጋላክሲዎች፣ የጋላክሲ ክላስተሮችና የጋላክሲ ሱፐር ክላስተሮች ቦታ ቦታቸውን ይዘው የሚደረደሩበትና የሚንጠለጠሉበት በዓይን የማይታይ እንደ ፍሬም ያለ ነገር [ነው]።”

ታዲያ ጽንፈ ዓለም እንዲህ የተደራጀ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? እንዲሁ በአጋጣሚ በተፈጠረ ክስተት አማካኝነት ነው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው? አላን ሰንዴጅ በአንድ ወቅት የሰጡትን ሐሳብ እንመልከት፤ እኚህ ሰው በ20ኛው መቶ ዘመን ከተነሱ ታላላቅና ተጽዕኖ ፈጣሪ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች አንዱ ተደርገው የሚቆጠሩ ሲሆን በአምላክ ያምኑ ነበር።

እንዲህ ብለዋል፦ “በሥርዓት የተደራጀው [አጽናፈ ዓለም] የተገኘው በፍንዳታ ነው ብሎ መቀበል በጣም ይከብደኛል። ሥርዓትና መልክ እንዲኖረው ያደረገ አንድ ነገር መኖር አለበት።”

ጽንፈ ዓለም ለሕይወት ምቹ እንዲሆን ተደርጎ ተስተካክሏል። ሳይንቲስቶች ዊክ ፎርስ (ደካማ ኃይል) ብለው የሚጠሩትን ነገር እንደ ምሳሌ እንመልከት። ፀሐይ ወጥነት ባለው መጠን መንደዷን እንድትቀጥል የሚያደርጋት ይህ ኃይል ነው። ይህ ኃይል አሁን ካለው ደከም ያለ ቢሆን ኖሮ ፀሐይ የምትባል ነገር አትኖርም ነበር። ትንሽ ጠንከር ቢል ኖሮ ደግሞ ፀሐይ ገና ድሮ ነድዳ ታልቅ ነበር።

ዊክ ፎርስ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ካሉ ለሕይወት የግድ አስፈላጊ የሆኑ ኃይሎች አንዱ ብቻ ነው። አኒል አናንታስዋሚ የተባለ የሳይንስ ፀሐፊ እንደተናገረው ከእነዚህ ኃይሎች አንዱም እንኳ አሁን ካለው የተለየ ቢሆን ኖሮ “ከዋክብት፣ ፕላኔቶችና ጋላክሲዎች አይኖሩም ነበር። ሕይወት ሊኖር የሚችልበት ምንም መንገድ አልነበረም።”

ጽንፈ ዓለም ለሰው ልጆች ተስማሚ መኖሪያ ይዟል። ምድር ለሕይወት ተስማሚ የሆነ ከባቢ አየርና የውኃ መጠን አላት፤ ጨረቃም ብትሆን ምድር ካለችበት እንዳትናወጥ ለማድረግ የሚያስችል ትክክለኛ መጠን አላት። ናሽናል ጂኦግራፊክ እንዲህ ይላል፦ “የምድር አካባቢያዊ ሁኔታ፣ ሥነ ምህዳርና ሥነ ሕይወት ይህችን እንግዳ ዓለት [ምድርን] ልዩ ያደርጋታል፤ ለሰው ልጆች እንዲህ ዓይነት ተስማሚ ቦታ እስከ አሁን ሊገኝ አልቻለም።” *

አንድ ጸሐፊ እንደተናገሩት የእኛ ሥርዓት ፀሐይ በጋላክሲያችን ውስጥ “ለብቻው ገንጠል ብሎ የተቀመጠ” ነው። ይሁንና በምድር ላይ ሕይወት እንዲኖር ያስቻለው እንዲህ ገለል ብሎ መቀመጡ ነው። ሥርዓተ ፀሐያችን የሚገኘው ወደ ሌሎች ከዋክብት ቀረብ ብሎ ማለትም በጋላክሲው መሃል ወይም ጫፍና ጫፍ ላይ ቢሆን ኖሮ አካባቢው ላይ የሚኖረው ጨረር ለሕይወት አደገኛ ይሆን ነበር። አንዳንድ ሳይንቲስቶች አሁን ያለንበትን ቦታ “ጋላክሲያዊ የመኖሪያ ክልል” ብለው የሚጠሩት ለዚህ ነው።

ፖል ዴቪስ የተባሉት የፊዚክስ ሊቅ ስለ ጽንፈ ዓለምና ስለ ሕግጋቱ ባላቸው እውቀት ላይ ተመሥርተው የሚከተለው መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል፦ “እኛ እዚህ ጽንፈ ዓለም ውስጥ የተገኘነው እንዲሁ በዕድል፣ በአጋጣሚ እና በድንገት ነው ብዬ ማሰብ ይከብደኛል። . . . እዚህ ያለነው በዓላማ መሆኑ አያጠራጥርም።” እርግጥ ነው፣ እኚህ የፊዚክስ ሊቅ ‘ጽንፈ ዓለምን እና የሰው ልጆችን የፈጠረው አምላክ ነው’ ብለው አያስተምሩም። አንተ ግን ምን ትላለህ? ጽንፈ ዓለምም ሆነ ምድር፣ ሕይወት በውስጣቸው እንዲኖር ለማስቻል የታሰበበት ንድፍ ያላቸው ይመስላል። ታዲያ ይህ የሆነው ምናልባት ንድፍ አውጪ ስላላቸው ይሆን?

^ አን.8 ናሽናል ጂኦግራፊክ ላይ የወጣው ይህ ርዕስ ‘አምላክ ምድርን እና የሰው ልጆችን ፈጥሯል’ የሚለውን ሐሳብ ለማራመድ የተጻፈ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የጽሑፉ ዓላማ ምድር ለሰው ልጆች መኖሪያነት በጣም ተስማሚ መሆኗን ማብራራት ነው።