የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ
በሽታን መከላከል የሚቻለው እንዴት ነው?
ሰውነትህ በዓይን ከማይታዩና ድምፅ ከሌላቸው ሆኖም ሞት ሊያስከትሉ ከሚችሉ ጠላቶች ጋር በየዕለቱ ይዋጋል። እንደ ባክቴሪያ፣ ቫይረስና ጥገኛ ተውሳኮች ያሉ ወራሪዎች ጤንነትህን አደጋ ላይ ይጥሉታል። * ይሁንና ሰውነትህ እንዲህ ያለ ውጊያ እያደረገ እንዳለ እንኳ ላይታወቅህ ይችላል፤ ምክንያቱም የሰውነትህ በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት አብዛኞቹን ወራሪዎች የበሽታ ምልክቶች መታየት ከመጀመራቸው በፊት ያባርሯቸዋል ወይም ያጠፏቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ግን እነዚህ ጎጂ ጀርሞች ድል ሊያደርጉ ይችላሉ። በመሆኑም በዚህ ወቅት የሰውነትህን መከላከያ ለማጠናከር መድኃኒት መውሰድ አሊያም ሕክምና ማግኘት ሊያስፈልግህ ይችላል።
በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት፣ ሰዎች ረቂቅ ተሕዋስያንና ሌሎች ጎጂ ፍጥረታት ስለሚያስከትሉት ጉዳት የሚያውቁት ነገር አልነበረም። በ19ኛው መቶ ዘመን ግን የሳይንስ ሊቃውንት ጀርሞች በሽታ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አረጋገጡ፤ ይህ ደግሞ በተሻለ መልኩ በሽታን መከላከል እንድንችል አስታጥቆናል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የሕክምና ተመራማሪዎች፣ እንደ ፈንጣጣና ፖሊዮ ያሉ አንዳንድ በሽታዎች የሚያስከትሉትን ጉዳት በእጅጉ መቀነስ ወይም ከናካቴው ማጥፋት ችለዋል። ሆኖም ከጥቂት ጊዜ ወዲህ እንደ ቢጫ ወባና ዴንጊ ያሉት በሽታዎች በድጋሚ እያንሰራሩ ነው። ለምን? የሚከተሉትን ነጥቦች ተመልከት፦
-
በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች ጉዞ ያደርጋሉ፤ ከእነዚህ መካከል በሽታ አምጪ ጀርሞችን የተሸከሙ በርካታ ሰዎች ይኖራሉ። ክሊኒካል ኢንፌክሽየስ ዲዚዝስ በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንደገለጸው “ቀሳፊ የሆኑ ተላላፊ በሽታዎች በሙሉ” ከአገር አገር በሚጓዙ መንገደኞች አማካኝነት ሊዛመቱ ይችላሉ።
-
አንዳንድ ባክቴሪያዎች አንቲባዮቲኮችን (ፀረ ባክቴሪያ መድኃኒቶችን) መቋቋም ጀምረዋል። የዓለም የጤና ድርጅት እንዲህ ብሏል፦ “ዓለማችን ወደ ድህረ አንቲባዮቲክ ዘመን እያመራች ሲሆን ይህ ደግሞ በርካታ ተራ በሽታዎች መድኃኒት እንዲያጡ እንዲሁም የብዙዎች ሕይወት እንዲቀጠፍ ያደርጋል።”
-
አብዛኛውን ጊዜ ሕዝባዊ ዓመፅና ድህነት፣ መንግሥታት በሽታዎችን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ጥረት ያከሽፋል።
-
ብዙ ሰዎች በሽታን ለመከላከል ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው አያውቁም።
እንዲህ ያሉ አሳሳቢ ችግሮች ቢኖሩም ራስህንና ቤተሰብህን ከበሽታ ለመጠበቅ ብዙ ነገር ማድረግ ትችላለህ። ቀጣዩ ርዕስ፣ በታዳጊ አገሮች ውስጥም እንኳ ሊሠራባቸው የሚችሉ ቀላልና ውጤታማ የሆኑ የበሽታ መከላከያ ዘዴዎች እንዳሉ ይገልጻል።
^ አን.3 አብዛኞቹ ረቂቅ ተሕዋስያን በሽታ አያመጡም። እነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ትኩረት የሚያደርጉት፣ ጤንነትን አደጋ ላይ በሚጥሉ ረቂቅ ተሕዋስያንና በሽታ አምጪ በሆኑ ሌሎች ሕዋሳት ላይ ነው።