በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሕይወት አክብሮት ማሳየት ቀረ እንዴ?

ለሕይወት አክብሮት ማሳየት ቀረ እንዴ?

ለሕይወት አክብሮት ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ሰዎች ለሕይወት አክብሮት እንደሌላቸው የሚያሳዩ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ በማኅበረሰቡ ጤንነትም ሆነ ደህንነት ላይ ከባድ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ።

  • ሲጋራ ማጨስ የካንሰር መንስኤ ከመሆኑም ሌላ ሰውነታችን ካንሰርን ለመዋጋት ያለውን አቅም ያዳክመዋል። በሳንባ ካንሰር ከሚሞቱት ሰዎች መካከል 90 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ወይ ሲጋራ ያጨሱ ነበር አሊያም ለሲጋራ ጭስ ተጋላጭ ነበሩ።

  • የጅምላ ተኩስ ጥቃቶች በየዓመቱ በብዙዎች ላይ ከባድ የስሜት ቀውስ ያስከትላሉ። በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀ አንድ ሪፖርት እንደሚገልጸው በትምህርት ቤቶች ከሚፈጸሙ የተኩስ ጥቃቶች “ምንም አካላዊ ጉዳት ሳይደርስባቸው የተረፉ ሰዎችም እንኳ ለበርካታ ዓመታት በሚዘልቅ የስሜት ጠባሳ እንደሚሠቃዩ ጥናቶች ያሳያሉ።”

  • በአልኮል ወይም በዕፅ ተጽዕኖ ሥር ሆነው የሚያሽከረክሩ ሰዎች በመኪና መጓዝ አልፎ ተርፎም በእግረኛ መንገድ ላይ መራመድ አደገኛ እንዲሆን ያደርጋሉ። ሰዎች ለሕይወት አክብሮት የማያሳዩ ከሆነ ንጹሐን የማኅበረሰቡ ክፍሎች ለአደጋ ይጋለጣሉ።

ምን ማድረግ ትችላለህ?

ጤንነትህን ተንከባከብ። ትንባሆ ወይም ኤሌክትሮኒክ ሲጋራ እንደማጨስ፣ ከመጠን በላይ እንደመጠጣት ወይም ዕፅ እንደመውሰድ ያሉ ጎጂ ልማዶችን አስወግድ። እንዲህ ያሉት ልማዶች ሕይወትህን አደጋ ላይ ይጥላሉ፤ እንዲሁም የቤተሰብህን አባላት ጨምሮ ለሌሎች ሕይወት አክብሮት እንደሌለህ ያሳያሉ።

“ሥጋን . . . ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።”—2 ቆሮንቶስ 7:1

ለደህንነት ትልቅ ቦታ ስጥ። በቤትህ ውስጥ ለአደጋ የሚያጋልጡ ነገሮች እንዳይኖሩ አድርግ። በጥንቃቄ አሽከርክር፤ እንዲሁም መኪናህ አደጋ እንዳያደርስ ተገቢውን ክትትል አድርግለት። በሌሎች ተጽዕኖ ተሸንፈህ ለከባድ የአካል ጉዳት ወይም ለሞት ሊዳርጉ በሚችሉ እንቅስቃሴዎች አትካፈል።

“አዲስ ቤት በምትሠራበት ጊዜ አንድ ሰው ከጣሪያህ ላይ ወድቆ በቤትህ ላይ የደም ዕዳ እንዳታመጣ በጣሪያህ ዙሪያ መከታ ሥራ።”—ዘዳግም 22:8 a

ለሌሎች ደግነት አሳይ። ለሕይወት አክብሮት ማሳየት ከእኛ የተለየ ዘር፣ ብሔርና የኑሮ ደረጃ ላላቸው ሰዎች ያለንን አመለካከትም ይነካል። ደግሞም በዓለም ላይ ላለው ዓመፅና ጦርነት ዋነኛው መንስኤ መድልዎና ጥላቻ ነው።

“የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ እንዲሁም ክፋት ሁሉ ከእናንተ መካከል ይወገድ። ይልቁንም አንዳችሁ ለሌላው ደጎች . . . ሁኑ።”—ኤፌሶን 4:31, 32

ምን ጥረት እያደረግን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ሚዛናዊና ጤናማ አኗኗርን ያበረታታሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራማችን ሰዎች ከሱስና ከጎጂ ልማዶች እንዲላቀቁ ረድቷል።

በግንባታ ፕሮጀክቶቻችን ላይ ጥብቅ የሆነ የደህንነት መመሪያ እንከተላለን። በስብሰባ አዳራሾቻችን እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራችንን ለመደገፍ በሚውሉ ሌሎች ሕንፃዎች ግንባታ ላይ የሚሳተፉ ፈቃደኛ ሠራተኞች ለአደጋ በማያጋልጥ መልኩ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ሥልጠና ያገኛሉ። ሕንፃዎቻችን የመንግሥትን የደህንነት መሥፈርት የሚያሟሉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በየጊዜው ክትትል ይደረግላቸዋል።

ሰብዓዊ እርዳታ እናበረክታለን። በቅርቡ በ12 ወራት ውስጥ በዓለም ዙሪያ በተከሰቱ 200 ገደማ የሚሆኑ ከባድ አደጋዎች ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ አበርክተናል፤ 12 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የሚሆን በመዋጮ የተገኘ ገንዘብ ለእርዳታ ሥራው ውሏል።

በምዕራብ አፍሪካ (2014) እንዲሁም በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ (2018) የኢቦላ ወረርሽኝ በተቀሰቀሰበት ወቅት የዚህን ገዳይ በሽታ ስርጭት መግታት የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ለሰዎች ትምህርት ሰጥተናል። “ታዛዥነት ሕይወትን ያድናል” በሚል ርዕስ ንግግር የሚያቀርቡ ተወካዮችን ልከናል። በእያንዳንዱ የስብሰባ አዳራሻችን መግቢያ ላይ እጅ መታጠቢያ ቦታ አዘጋጅተናል። እንዲሁም እጅ የመታጠብንና ሌሎች የጥንቃቄ እርምጃዎችን የመውሰድን አስፈላጊነት ጎላ አድርገን ገልጸናል።

ሴራሊዮን ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢያቸው ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮችም ሆነ ሌሎች ሰዎችን ከኢቦላ ቫይረስ ለመታደግ ላደረጉት ጥረት ምስጋና የሚያቀርብ አንድ የሬዲዮ ማስታወቂያ ተነግሮ ነበር።

በ2014 በላይቤሪያ በተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሽኝ ወቅት የተዘጋጀ የስብሰባ አዳራሽ የእጅ መታጠቢያ

a በጥንት ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ የነበሩት ቤቶች ጣሪያቸው ጠፍጣፋ ስለነበር ይህ ጥበብ የሚንጸባረቅበት መመሪያ የቤተሰቡ አባላትም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ለአደጋ እንዳይጋለጡ ያደርጋል።