በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለራስ አክብሮት ማሳየት ቀረ እንዴ?

ለራስ አክብሮት ማሳየት ቀረ እንዴ?

ለራስ አክብሮት ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ለራሳቸው አክብሮት ያላቸው ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በልበ ሙሉነት መጋፈጥ ይችላሉ። በቀላሉ ተስፋ አይቆርጡም።

  • አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ለራሳቸው ጥሩ አመለካከት የሌላቸው ሰዎች ለጭንቀት፣ ለድባቴና ለአመጋገብ መዛባት የመጋለጣቸው አጋጣሚ ሰፊ ነው። በተጨማሪም የመጠጥና የዕፅ ሱሰኛ የመሆናቸው አጋጣሚ ይጨምራል።

  • ለራሳቸው አክብሮት ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን ከሌሎች ጋር አያወዳድሩም፤ ይህም በዙሪያቸው ካሉት ሰዎች ጋር ተስማምቶ መኖርና ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረት ቀላል እንዲሆንላቸው ያደርጋል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለራሳቸው አክብሮት የሌላቸው ሰዎች ተቺ የመሆን ዝንባሌ አላቸው፤ ይህም ከሌሎች ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ሊያበላሸው ይችላል።

  • ለራሳቸው አክብሮት ያላቸው ሰዎች የሚያጋጥማቸውን ተፈታታኝ ሁኔታ በጽናት መቋቋም ይችላሉ፤ ያጋጠማቸው እንቅፋት ግባቸው ላይ ከመድረስ እንዲያግዳቸው አይፈቅዱም። በአንጻሩ ግን፣ ለራሳቸው አክብሮት የሌላቸው ሰዎች ያጋጠሟቸውን ትናንሽ እንቅፋቶች አግዝፈው የማየት ዝንባሌ አላቸው። ይህ ደግሞ በቀላሉ ተስፋ እንዲቆርጡ ሊያደርጋቸው ይችላል።

ምን ማድረግ ትችላለህ?

የሚያበረታቱ ጓደኞችን ምረጥ። አክብሮት ከሚያሳዩህ፣ ደህንነትህ ከልብ ከሚያሳስባቸው እንዲሁም ከሚያበረታቱህ ሰዎች ጋር ተቀራረብ።

“እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።”—ምሳሌ 17:17

ሌሎችን እርዳ። ለሌሎች ደግነት ስታሳይ እንዲሁም ውለታ ሊመልሱልህ የማይችሉ ሰዎችን ጨምሮ ለሌሎች መልካም ነገር ስታደርግ በመስጠት የሚገኘውን እውነተኛ ደስታ ታጣጥማለህ። ላከናወንከው መልካም ሥራ ባትመሰገንም እንኳ ሌሎችን መርዳትህ አንተን ይጠቅምሃል።

“ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35

ልጆችህ ለራሳቸው አክብሮት እንዲያዳብሩ እርዳቸው። ይህን ማድረግ የምትችልበት አንዱ መንገድ ያጋጠሟቸውን ችግሮች አቅማቸው በፈቀደ መጠን በራሳቸው እንዲፈቱ ማድረግ ነው። እንዲህ ማድረግህ፣ ልጆችህ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መቋቋምና ማሸነፍ የሚቻልበትን መንገድ እንዲማሩ ይረዳቸዋል። ልጆችህ ይህን ትምህርት ማግኘታቸው ለራሳቸው አክብሮት እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል፤ አዋቂ ከሆኑ በኋላም ይጠቅማቸዋል።

“ልጅን ሊሄድበት በሚገባው መንገድ አሠልጥነው፤ በሚያረጅበት ጊዜም እንኳ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።”—ምሳሌ 22:6

ምን ጥረት እያደረግን ነው?

ስብሰባዎቻችንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራማችን ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ ብሎም ለራሳቸው ያላቸውን አክብሮት እንዲያሳድጉ ይረዷቸዋል።

ሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን

በሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ንግግሮችን እናዳምጣለን። በእነዚህ ንግግሮች አማካኝነት፣ ለራሳችን አክብሮት ማዳበር የምንችልበትን መንገድ እንማራለን። በስብሰባዎቻችን ላይ ማንም ሰው መገኘት ይችላል፤ እንዲሁም መግቢያ በነፃ ነው። በስብሰባዎቻችን ላይ እንደሚከተሉት ያሉ ትምህርቶችን ታገኛለህ፦

  • አምላክ በግለሰብ ደረጃ ከቁም ነገር ይቆጥርሃል?

  • የሕይወትን ዓላማ ማወቅ የሚቻለው እንዴት ነው?

  • ጠንካራና ዘላቂ ጓደኝነት መመሥረት የሚቻለው እንዴት ነው?

‘እርስ በርስ የሚተሳሰቡ’ እውነተኛ ጓደኞችም ታገኛለህ።—1 ቆሮንቶስ 12:25, 26

ስለ ስብሰባዎቻችን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በስብሰባ አዳራሻችን ውስጥ ምን ይከናወናል? የሚለውን አጭር ቪዲዮ jw.org ላይ ፈልግ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራማችን

ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅመን አሳታፊ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በነፃ እንሰጣለን። ይህ መጽሐፍ ቁልፍ ጥቅሶችን፣ ግልጽ ማብራሪያዎችን፣ ውጤታማ ጥያቄዎችን፣ ልብ የሚነኩ ቪዲዮዎችንና ማራኪ ሥዕሎችን ይዟል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራማችን ሰዎች ለራሳቸው አክብሮት እንዲያዳብሩና ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ ይረዳቸዋል።

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ የሚጠቅምህ እንዴት እንደሆነ ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? የሚለውን አጭር ቪዲዮ jw.org ላይ ፈልግ።