ለቤተሰብ | ትዳር
በችግሮች ላይ መወያየት የሚቻልበት መንገድ
ተፈታታኙ ነገር
ከትዳር ጓደኛህ ጋር በአንድ ችግር ላይ ተወያይታችሁ ስትጨርሱ በውይይቱ መጀመሪያ ላይ ከነበረው የበለጠ እንደምትበሳጩ ይሰማችኋል? ከሆነ ሁኔታውን ማሻሻል ትችላላችሁ። ይሁንና በመጀመሪያ ወንዶች ሐሳባቸውን በሚገልጹበት መንገድና ሴቶች ሐሳባቸውን በሚገልጹበት መንገድ መካከል ያለውን ልዩነት ማወቃችሁ ጠቃሚ ነው። *
ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር
ሴቶች የሚቀርብላቸውን መፍትሔ ከመስማታቸው በፊት ተናግረው መጨረስ ይመርጣሉ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ መናገራቸው በራሱ መፍትሔ ነው።
“የተሰማኝን ነገር ስገልጽና ባለቤቴ ስሜቴን እንደተረዳልኝ ሳውቅ ችግሩ ቀለል ይለኛል። ብዙውን ጊዜ ስሜቴን አውጥቼ ስናገር በአጭር ጊዜ ውስጥ እረጋጋለሁ።”—ሲርፓ *
“የተሰማኝን ነገር ለባለቤቴ የምገልጽበት አጋጣሚ ካላገኘሁ ችግሩን መርሳት ይከብደኛል። ችግሩን የምረሳው ተናግሬው ሲወጣልኝ ነው።”—ኤ ጂን
“ነገሩ ከወንጀል ምርመራ ጋር ይመሳሰላል። በምናገርበት ጊዜ ችግሩን ከሥረ መሠረቱ ለማስረዳት እሞክራለሁ፤ ይህ ደግሞ መንስኤውን እንዳውቅ ያስችለኛል።”—ሉርደስ
ወንዶች መፍትሔ መፈለግ ይቀናቸዋል። ወንዶች እንዲህ የሚሰማቸው መሆኑ አያስገርምም፤ ምክንያቱም ጠቃሚ ነገር እንዳደረጉ የሚሰማቸው ለአንድ ችግር መፍትሔ ሲያገኙ ነው። አንድ ባል መፍትሔ ማቅረቡ ሚስቱ ልትተማመንበት እንደምትችል የሚያሳይበት መንገድ ነው። በመሆኑም ያቀረበውን የመፍትሔ ሐሳብ ሚስቱ በደስታ ካልተቀበለች ግራ ይጋባል። ከርክ የተባለ አንድ ባለትዳር “አንድ ሰው መፍትሔ ካልፈለገ ስለ ችግሩ ለምን ያወራል!” ብሏል።
ይሁን እንጂ “ከምክር በፊት መቅደም ያለበት ችግሩን መረዳት ነው” በማለት ዘ ሰቨን ፕሪንሲፕልስ ፎር ሜኪንግ ሜሬጅ ዎርክ (ጋብቻ የተሳካ እንዲሆን የሚያስችሉ ሰባት መመሪያዎች) የተባለው መጽሐፍ ያስጠነቅቃል። “ለትዳር ጓደኛህ የመፍትሔ ሐሳብ ከማቅረብህ በፊት የገጠማትን ችግር እንዲሁም ስሜቷን እንደተረዳህላት እንድታውቅ ማድረግ አለብህ። አብዛኛውን ጊዜ የትዳር ጓደኛህ የምትፈልገው መፍትሔ እንድትሰጣት ሳይሆን በጥሞና እንድታዳምጣት ብቻ ነው።”
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
ለባሎች፦ የትዳር ጓደኛችሁ ስትናገር ስሜቷን ለመረዳት እየሞከራችሁ በጥሞና ማዳመጥን ተለማመዱ። ቶማስ የሚባል አንድ ባለትዳር እንዲህ ይላል፦ “አንዳንድ ጊዜ ካዳመጥኩ በኋላ ‘ማዳመጤ ምንም መፍትሔ አላመጣም’ ብዬ አስባለሁ። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ባለቤቴ የምትፈልገው ይህንኑ እንዳደርግላት ማለትም እንዳዳምጣት ብቻ ነው።” ስቴፈንም በዚህ ይስማማል። እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴን ሳላቋርጣት ስሜቷን እንድትገልጽ ማድረግ ከሁሉ የተሻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። አብዛኛውን ጊዜ ተናግራ ከጨረሰች በኋላ በጣም አንደቀለላት ትነግረኛለች።”
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ በሚቀጥለው ጊዜ ከትዳር ጓደኛህ ጋር በአንድ ችግር ላይ ስትወያዩ እሷ ካልጠየቀችህ በስተቀር የመፍትሔ ሐሳብ የመስጠት ግፊትህን ተቆጣጠረው። ዓይን ዓይኗን እያየህ አዳምጣት፤ ትኩረትህ እሷ በምትናገረው ነገር ላይ ይሁን። ራስህን እየነቀነቅክ አዳምጣት። ማለት የፈለገችው እንደገባህ ለማሳየት የተናገረችውን ነገር ጠቅለል አድርገህ ድገምላት። “አንዳንድ ጊዜ ሚስቴ የሚያስፈልጋት ስሜቷን እንደተረዳሁላትና ምንጊዜም ከጎኗ እንደሆንኩ ማወቅ ብቻ ነው” በማለት ቻርልስ የተባለ አንድ ባለትዳር ተናግሯል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ያዕቆብ 1:19
ለሚስቶች፦ የትዳር ጓደኛችሁ እንዲያደርግላችሁ የምትፈልጉትን ነገር በግልጽ ንገሩት። ኢሌኒ የተባለች አንዲት ባለትዳር “የትዳር ጓደኛችን የሚያስፈልገንን ነገር እንዲያውቅ እንጠብቅበት ይሆናል፤ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ የምንፈልገውን ነገር በግልጽ መናገር ይኖርብናል” ብላለች። ኢኔስ ደግሞ የሚከተለውን ጠቃሚ ሐሳብ ተናግራለች፦ “ባለቤቴን እንዲህ ልለው እችላለሁ፦ ‘አንድ ነገር እያሳሰበኝ ስለሆነ ብታዳምጠኝ ደስ ይለኛል። የምፈልገው መፍትሔ እንድትሰጠኝ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ስሜቴን እንድትረዳልኝ ብቻ ነው።’”
እንዲህ ለማድረግ ሞክሪ፦ የትዳር ጓደኛሽ ተናግረሽ ሳትጨርሺ የመፍትሔ ሐሳብ ካቀረበ ለስሜቴ ግድ የለውም የሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አትቸኩዪ። ይህን ያደረገው አንቺን ለመርዳት ብሎ ነው። አስቴር የተባለች ባለትዳር እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ባደረገው ነገር ከመበሳጨት ይልቅ ለእኔ እንደሚያስብልኝና ሊያዳምጠኝ እንደሚፈልግ እንዲሁም የመፍትሔ ሐሳብ ያቀረበው ሊረዳኝ ብሎ እንደሆነ ለማሰብ እሞክራለሁ።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ሮም 12:10
ለሁለቱም፦ ሌሎች ለእኛ እንዲያደርጉልን የምንፈልገውን ነገር ለእነሱም ማድረግ ይቀናናል። ይሁን እንጂ በችግሮቻችሁ ላይ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመነጋገር የትዳር ጓደኛችሁ ምን እንዲደረግለት እንደሚፈልግ ማሰብ ያስፈልጋችኋል። (1 ቆሮንቶስ 10:24) ሚጌል የሚባል አንድ ባለትዳር ጉዳዩን እንደሚከተለው በማለት ይገልጸዋል፦ “ባል ከሆንክ፣ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ሁን። ሚስት ከሆንሽ፣ አንዳንዴ መፍትሔዎችን ለመስማት ፈቃደኛ ሁኚ። ሁለታችሁም ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ ከመሆናችሁ የምትጠቀሙት እናንተው ናችሁ።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ 1 ጴጥሮስ 3:8