ንድፍ አውጪ አለው?
የጉንዳን አንገት
የሜካኒካል ምሕንድስና ባለሙያዎች፣ ጉንዳኖች ባላቸው ከአካላቸው ብዙ እጥፍ የሚበልጥ ክብደት የመሸከም ችሎታ ይደነቃሉ። በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉ መሐንዲሶች፣ ጉንዳኖች ያላቸውን ይህን ችሎታ ለመረዳት ሲሉ የኮምፒዩተር ሞዴሎችን አዘጋጅተዋል፤ ሞዴሎቹ የጉንዳኖቹን አካል አወቃቀርና ባሕርይ እንዲሁም እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ናቸው። ሞዴሎቹ የተሠሩት የጉንዳኖቹን ውስጣዊ የአካል ክፍል የሚያሳይ የራጅ ምስል (ረቂቅ ሲቲ ስካን) እና ጉንዳኖች ከባድ ሸክም ሲሸከሙ ኃይላቸውን የሚጠቀሙበትን መንገድ የሚያሳዩ ምስሎችን በመጠቀም ነው።
የጉንዳኖች አንገት ትልቅ ሚና አለው፤ ምክንያቱም አንድ ጉንዳን በአፉ የሚይዘው ከባድ ሸክም ሙሉ ክብደት የሚያርፈው አንገቱ ላይ ነው። በጉንዳኑ አንገት ውስጥ የሚገኙ ለስላሳ ሕብረ ሕዋሳት በደረቱ አካባቢ (ሰውነቱ) እና በጭንቅላቱ ላይ ካሉት ጠንካራ ድጋፍ ሰጪ አጥንቶች ጋር የተቆላለፉ ናቸው፤ ይህም በታጠፉ እጆች ላይ ጣቶች ከሚቆላለፉበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነው። “ይህ መቆላለፍ ያለው ንድፍና አወቃቀር፣ የአንገቱ መገጣጠሚያ ለሚያከናውነው ተግባር ወሳኝ ነው” በማለት ከተመራማሪዎቹ አንዱ ይናገራል። “የአንገቱ መገጣጠሚያ ይበልጥ ጥንካሬ እንዲኖረው ያደረገው ነገር ጠንካራና ለስላሳ የአካል ክፍሎቹ የተያያዙበት መንገድ ሳይሆን አይቀርም፤ ምናልባትም መገጣጠሚያው ከባድ ሸክም እንዲሸከም የሚያስችለው ይህ ንድፍ ሊሆን ይችላል።” የጉንዳን አንገት እንዴት እንደሚሠራ በግልጽ መታወቁ ለሰው ሠራሽ ሮቦቶች ንድፍ መሻሻል አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል ተመራማሪዎች ተስፋ ያደርጋሉ።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ውስብስብ በሆነ መንገድ የተቆላለፈው ጠንካራ የጉንዳን አንገት በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?