ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና
ልጆች የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዲሠሩ ማድረግ ያለው ጥቅም
ተፈታታኙ ነገር
በአንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ ልጆች የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት እንዲያግዙ ይጠበቅባቸዋል፤ ልጆቹም ያለ ምንም ማጉረምረም የሚጠበቅባቸውን ሥራ ያከናውናሉ። በሌሎች ቤተሰቦች ውስጥ ደግሞ ወላጆች፣ ልጆቻቸው የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዲሠሩ አይጠብቁባቸውም፤ ልጆቹም ይህ የወላጆቻቸው አቋም ደስ ስለሚያሰኛቸው ምንም ሥራ ከመሥራት ይቆጠባሉ።
በተለይም በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ ልጆች፣ በቤት ውስጥ ሥራዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ከማበርከት ይልቅ ተገልጋዮች የመሆን አዝማምያ እየታየባቸው እንደመጣ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ስቲቨን የተባለ አንድ ወላጅ እንዲህ ብሏል፦ “በዛሬው ጊዜ ልጆች የቪዲዮ ጨዋታዎችን ከመጫወት፣ ኢንተርኔት ከመቃኘት ወይም ቴሌቪዥን ከመመልከት ውጭ ምንም ነገር እንዲያደርጉ አይጠበቅባቸውም።”
እናንተስ ምን ይመስላችኋል? ቤት ውስጥ ለልጆቻችሁ ሥራ መስጠታችሁ ቤቱ በጥሩ ሁኔታ የተያዘ እንዲሆን ከማድረግ በተጨማሪ ለልጆቹ እድገት የሚያስገኘው ጥቅም እንዳለ ይሰማችኋል?
ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር
አንዳንድ ወላጆች በተለይ የልጆቻቸው ጊዜ ከትምህርት ቤት በሚሰጣቸው የቤት ሥራና ከትምህርት ሰዓት ውጭ በሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች የተጣበበ በሚሆንበት ጊዜ ለልጆቻቸው የቤት ውስጥ ሥራ ከመስጠት ወደኋላ ይላሉ። ሆኖም ልጆቻችሁ ቤት ውስጥ እንዲያግዙ ማድረጋችሁ ምን ጥቅም እንዳለው ተመልከቱ።
ልጆች የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራታቸው ለብስለታቸው አስተዋጽኦ ያበረክታል። የቤት ውስጥ ሥራዎችን የሚሠሩ ልጆች አብዛኛውን ጊዜ በትምህርት ቤት ስኬታማ ይሆናሉ፤ ይህ ደግሞ አያስገርምም። አንድ ልጅ የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራቱ ይበልጥ በራሱ እንዲተማመን፣ ራሱን የመግዛት ባሕርይ እንዲያዳብርና ውስጣዊ ጥንካሬው እንዲጎለብት ይረዳዋል፤ እነዚህ ባሕርያት ደግሞ በልጁ ትምህርት የመቀበል ችሎታ ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።
ልጆች የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራታቸው ሌሎችን የሚጠቅም ተግባር እንዲያከናውኑ ያሠለጥናቸዋል። የቤት ውስጥ ሥራዎችን የሚሠሩ ልጆች አዋቂ ከሆኑ በኋላ ማኅበረሰቡን የሚጠቅም ሥራ የማከናወን አጋጣሚያቸው ሰፊ እንደሚሆን ተስተውሏል። ይህ ደግሞ የሚያስገርም አይደለም፤ ምክንያቱም ልጆች የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራታቸው ከራሳቸው ፍላጎት ይልቅ ለሌሎች ፍላጎት ቅድሚያ እንዲሰጡ ያሠለጥናቸዋል። በተቃራኒው ደግሞ ቀደም ሲል የተጠቀሰው ስቲቨን እንደተናገረው “ልጆች ምንም ነገር እንዲያደርጉ የማይጠበቅባቸው ከሆነ ሌሎች ሁልጊዜ እነሱን ሊያገለግሏቸው እንደሚገባ አድርገው ያስባሉ፤ እንዲሁም ኃላፊነትን ከመወጣትና ጠንክሮ ከመሥራት ጋር በተያያዘ ከእነሱ ስለሚጠበቀው ነገር የተዛባ አመለካከት ይዘው ያድጋሉ።”
ልጆች የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራታቸው የቤተሰቡን አንድነት ያጠናክራል። ልጆች የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራታቸው በቤተሰቡ መካከል ጠቃሚ ድርሻ እንዳላቸው እንዲሰማቸው የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ለቤተሰቡ የጋራ ጥቅም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የማበርከት ኃላፊነት እንዳለባቸው እንዲገነዘቡ ያደርጋል። ወላጆች፣ ልጆቻቸው የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዲሠሩ ከማድረግ ይልቅ ከትምህርት ሰዓት ውጭ ለሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች ቅድሚያ እንዲሰጡ የሚያበረታቱ ከሆነ ግን ልጆቹ እንዲህ ያለው የኃላፊነት ስሜት አይሰማቸውም።
በመሆኑም ወላጆች ‘ልጄ ከትምህርት ሰዓት ውጭ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በመጠመዱ ምክንያት ከቤተሰቡ ጋር ቢራራቅ ምን ጥቅም አለው?’ ብለው ራሳቸውን መጠየቃቸው ተገቢ ነው።ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
ከትንሽነታቸው ጀምሩ። ወላጆች ልጆቻቸው ሦስት ዓመት ከሞላቸው ጊዜ ጀምሮ አንዳንድ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ሊሰጧቸው እንደሚገባ የሚናገሩ ሰዎች አሉ። ሌሎች ደግሞ ልጆቹ ሁለት ዓመት ወይም ከዚያ በታች ሆነውም እንኳ የቤት ውስጥ ሥራ ቢሰጣቸው ጥሩ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ዞሮ ዞሮ ትናንሽ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር አብረው መሥራትና ወላጆቻቸውን መምሰል እንደሚያስደስታቸው መገንዘብ ያስፈልጋል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 22:6
ለዕድሜያቸው የሚመጥን ሥራ ስጧቸው። ለምሳሌ ያህል፣ የሦስት ዓመት ልጅ አሻንጉሊቶቹን ሊያነሳሳ፣ የፈሰሰ ነገር ሊያጸዳ ወይም ልብስ ሊያጣጥፍ ይችላል። ከፍ ያሉ ልጆች ደግሞ ቤት ሊያጸዱ፣ መኪና ሊያጥቡ ወይም ምግብ ሊሠሩ ይችላሉ። የልጃችሁን አቅም ግምት ውስጥ አስገቡ። ልጃችሁ የተሰጠውን ሥራ በደስታ ሲያከናውን ስታዩ ትገረሙ ይሆናል።
ለቤት ውስጥ ሥራ ቅድሚያ ስጡ። እርግጥ ልጆቻችሁ በየቀኑ ከትምህርት ቤት ብዙ የቤት ሥራ ይዘው የሚመጡ ከሆነ ይህን ማድረግ ይከብዳችሁ ይሆናል። ይሁንና ልጆች በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት እንዲያገኙ ሲባል የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዳይሠሩ ማድረግ “ቅድሚያ ለሚሰጠው ነገር ቅድሚያ አለመስጠት” እንደሆነ ዘ ፕራይስ ኦቭ ፕሪቭሌጅ የተባለው መጽሐፍ ገልጿል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ ልጆች የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራታቸው ጎበዝ ተማሪዎች እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። በተጨማሪም ይህን ማድረጋቸው ወደፊት የራሳቸው ቤተሰብ ለሚመሠርቱበት ጊዜ ጥሩ ሥልጠና ይሰጣቸዋል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ፊልጵስዩስ 1:10
ውጤቱ ላይ ሳይሆን ዓላማው ላይ አተኩሩ። ልጃችሁ አንድን ሥራ እናንተ በምትፈልጉት ፍጥነት ሠርቶ ላያጠናቅቅ ይችላል። በተጨማሪም ሥራው እምብዛም ጥራት እንደሌለው ይሰማችሁ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ሥራውን ከልጁ ተቀብላችሁ እናንተ ራሳችሁ ለመሥራት ብትፈተኑም እንኳ እንዲህ ከማድረግ ተቆጠቡ። ዓላማችሁ ሥራው አንድ አዋቂ በሚሠራበት መንገድ ጥርት ብሎ እንዲሠራ ማድረግ ሳይሆን ልጃችሁ ኃላፊነት መቀበል እንዲችልና ከሥራ የሚገኘውን ደስታ እንዲያጣጥም መርዳት ነው።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ መክብብ 3:22
ልጆቻችሁ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ብለው እንዲሠሩ አታድርጉ። አንዳንዶች፣ ልጆች ለሚሠሩት የቤት ውስጥ ሥራ ገንዘብ መክፈል ልጆቹ ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ ለማሠልጠን እንደሚረዳ ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ እንዲህ ማድረግ ልጆች ለቤተሰቡ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ከማሰብ ይልቅ ከቤተሰቡ በሚያገኙት ጥቅም ላይ እንዲያተኩሩ እንደሚያደርጋቸው ይናገራሉ። እንዲሁም ልጁ በቂ ገንዘብ ሲኖረው የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለመሥራት ፈቃደኛ እንዳይሆን ሊያደርገው ይችላል ብለው ይሰጋሉ፤ ምክንያቱም በቂ ገንዘብ ካለው ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልገው አይሰማውም። ከዚህ ምን እንማራለን? ወላጆች ለልጆቻቸው የኪስ ገንዘብ ሊሰጧቸው ቢችሉም ይህን የሚያደርጉት ለሚያከናውኑት ሥራ እንደ ክፍያ አድርገው መሆን የለበትም።