በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ—ትክክለኛ መረጃ የያዘ መጽሐፍ

መጽሐፍ ቅዱስ—ትክክለኛ መረጃ የያዘ መጽሐፍ

ከሳይንስ አንጻር ትክክለኛ መረጃ ይዟል

መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ መማሪያ መጽሐፍ ባይሆንም ተፈጥሮን በተመለከተ የያዛቸው መረጃዎች ትክክለኛ ናቸው። ከሜትሮሎጂና ከጄኔቲክስ ጋር በተያያዘ የሚናገረውን ነገር እንደ ምሳሌ ተመልከት።

ሜትሮሎጂ—ዝናብ የሚፈጠርበት መንገድ

ሜትሮሎጂ

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “[አምላክ] የውኃ ጠብታዎችን ወደ ላይ ይስባል፤ ጭጋጉም ወደ ዝናብነት ይለወጣል፤ ከዚያም ደመናት ያዘንባሉ።”—ኢዮብ 36:27, 28

እዚህ ጥቅስ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ በውኃ ዑደት ውስጥ የሚገኙትን ሦስት ዋና ዋና ሂደቶች ይገልጻል። የፀሐይ ብርሃን ምንጭ የሆነው አምላክ (1) በትነት አማካኝነት “የውኃ ጠብታዎችን ወደ ላይ ይስባል።” ከዚያም የተነነው ውኃ (2) በጥዜት አማካኝነት ደመና ይፈጥርና በዝናብ ወይም በበረዶ መልክ (3) ወደ መሬት ይወርዳል። የሜትሮሎጂ ባለሙያዎች አሁንም ድረስ ከዝናብ ጋር በተያያዘ ብዙ ያልተረዷቸው ነገሮች አሉ። የሚገርመው ነገር መጽሐፍ ቅዱስም “የደመናትን ንብርብር . . . ማን ሊያስተውል ይችላል?” በማለት ይናገራል። (ኢዮብ 36:29) ፈጣሪ ግን ስለ ዝናብ ዑደት ሙሉ በሙሉ የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ይህን መረጃ በቃሉ ውስጥ በትክክል እንዲያሰፍር አድርጓል። ይህን ያደረገው ሰዎች የዝናብን ዑደት በተመለከተ ሳይንሳዊ ትንታኔ መስጠት ከመቻላቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ነው።

ጄኔቲክስ—ፅንስ የሚያድግበት መንገድ

ጄኔቲክስ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ንጉሥ ዳዊት ለአምላክ እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር፦ “ፅንስ እያለሁ እንኳ ዓይኖችህ አዩኝ፤ የአካሌ ክፍሎች በሙሉ በመጽሐፍህ ተጻፉ።” (መዝሙር 139:16) ዳዊት ቅኔያዊ አነጋገር በመጠቀም፣ ፅንስ የሚያድገው አስቀድሞ በተጻፈ “መጽሐፍ” ወይም ንድፍ ውስጥ በሚገኝ መመሪያ መሠረት እንደሆነ ተናግሯል። የሚያስደንቀው ነገር፣ ይህ ሐሳብ የተጻፈው ከ3,000 ዓመታት ገደማ በፊት ነው!

ግሬጎር ሜንደል የተባሉት ኦስትሪያዊ የሥነ ዕፅዋት ተመራማሪ የጄኔቲክስን መሠረታዊ ሐሳብ በምርምር ያገኙት በ1800ዎቹ አጋማሽ ላይ ነው። እንዲሁም ተመራማሪዎች የሰው አካል የተገነባበትን መረጃ የያዘውን ዲ ኤን ኤ በቅደም ተከተል ደርድረው የጨረሱት ገና በሚያዝያ 2003 ነው። የሳይንስ ሊቃውንት፣ ፊደላትና ቃላት በመዝገበ ቃላት ውስጥ በቅደም ተከተል እንደሚቀመጡ ሁሉ በጂኖቻችን ውስጥ የሚገኘው መመሪያም ሥርዓት ባለው መልኩ የተደረደረ እንደሆነ ይናገራሉ። በእነዚህ መመሪያዎች መሠረት እንደ አንጎል፣ ልብ፣ ሳንባ፣ እጅና እግር ያሉ የአንድ ፅንስ የአካል ክፍሎች ትክክለኛውን ጊዜና ቅደም ተከተል ጠብቀው ይዳብራሉ። በእርግጥም ሳይንቲስቶች ዲ ኤን ኤን “የሕይወት መጽሐፍ” ብለው መጥራታቸው የተገባ ነው። ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ዳዊት እንዲህ ያለ ትክክለኛ መረጃ ሊጽፍ የቻለው እንዴት ነው? “የይሖዋ መንፈስ በእኔ ተናገረ፤ ቃሉ በአንደበቴ ላይ ነበረ” በማለት በትሕትና ተናግሯል። *2 ሳሙኤል 23:2

በውስጡ የሚገኙት ትንቢቶች በትክክል ተፈጽመዋል

የዓለም መንግሥታትና ከተሞች የሚነሱበትን እንዲሁም የሚወድቁበትን መንገድ፣ ጊዜና ሁኔታ አስቀድሞ ማወቅ በጣም አስቸጋሪ እንዲያውም ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን የኃያላን መንግሥታትንና ከተሞችን አወዳደቅ በተመለከተ ዝርዝር ነገሮችን አስቀድሞ ተናግሯል። እስቲ ሁለት ምሳሌዎችን ብቻ ተመልከት።

ባቢሎን እንደምትወድቅና ባድማ እንደምትሆን የተነገረው ትንቢት

የጥንቷ ባቢሎን ለበርካታ መቶ ዘመናት በምዕራብ እስያ ከፍተኛ ተጽዕኖ የነበረው ኃያል መንግሥት ዋና ማዕከል ነበረች። በአንድ ወቅት ይህች ከተማ በዓለም ላይ ካሉት ከተሞች ሁሉ ትልቋ ነበረች። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ኢሳይያስ በአምላክ መንፈስ በመመራት፣ ቂሮስ የተባለ ሰው ባቢሎንን ድል እንደሚያደርጋት እንዲሁም ለዘላለም ማንም ሰው እንደማይኖርባት አስቀድሞ ተናግሯል፤ የሚገርመው ነገር ኢሳይያስ ይህን ትንቢት የተናገረው ባቢሎን ከመጥፋቷ ከ200 ዓመታት ገደማ በፊት ነው። (ኢሳይያስ 13:17-20፤ 44:27, 28፤ 45:1, 2) ታዲያ ይህ ትንቢት በእርግጥ ተፈጽሟል?

ታሪክ

በ539 ዓ.ዓ. በጥቅምት ወር፣ ታላቁ ቂሮስ በአንድ ሌሊት ባቢሎንን ድል አደረጋት። በከተማዋ ዙሪያ የነበረውን ለም አካባቢ ያጠጡ የነበሩት ቦዮች ዞር ብሎ የሚያያቸው በማጣታቸው ምክንያት በጊዜ ሂደት ደረቁ። አንዳንድ ምንጮች እንደሚናገሩት በ200 ዓ.ም. የባቢሎን ከተማ በነበረችበት ቦታ ላይ ምንም ነዋሪ አልነበረም። እስከዛሬም ድረስ የፍርስራሽ ክምር እንደሆነች ትገኛለች። መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ባቢሎን “ሙሉ በሙሉ ባድማ” ሆናለች።—ኤርምያስ 50:13

ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ወደፊት ስለሚፈጸም ነገር እንዲህ በትክክል ሊናገር የቻለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህን በባቢሎን ላይ የተላለፈ ፍርድ “የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ በራእይ [እንዳየው]” ይናገራል።—ኢሳይያስ 13:1

ነነዌ “እንደ በረሃ ደረቅ” እንደምትሆን የተነገረው ትንቢት

የአሦር ግዛት ዋና ከተማ የነበረችው ነነዌ ድንቅ የሥነ ሕንፃ ጥበብ የሚታይባት ከተማ ነበረች። ከተማይቱ ሰፋፊ መንገዶች፣ የመናፈሻ ቦታዎች፣ ቤተ መቅደሶችና ግዙፍ ቤተ መንግሥቶች ነበሯት። ይሁንና ነቢዩ ሶፎንያስ ይህች ታላቅ ከተማ “ባድማና እንደ በረሃ ደረቅ” እንደምትሆን ትንቢት ተናግሯል።—ሶፎንያስ 2:13-15

ነነዌ በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በባቢሎናውያንና በሜዶናውያን ጥምር ኃይል ሙሉ በሙሉ ጠፋች። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ከተማይቱ ድል ከተመታች በኋላ “ለ2500 ዓመታት ያህል ጨርሶ ተረስታ ቆይታለች።” እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ሰዎች ነነዌ በእርግጥ በታሪክ የነበረች ከተማ መሆኗን እንኳ ይጠራጠሩ ነበር! የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች የነነዌን ፍርስራሽ በቁፋሮ ያገኙት በ19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ነው። በዛሬው ጊዜ፣ ሰዎች በነነዌ ፍርስራሽ ላይ ጉዳት እያደረሱ ከመሆኑም ሌላ ፍርስራሹ በመበስበስ ላይ ይገኛል፤ በዚህም ምክንያት ግሎባል ሄሪቴጅ ፈንድ የተባለው ድርጅት “የጥንቷ ነነዌ ፍርስራሾች ዳግመኛ ተቀብረው ሊጠፉ ይችላሉ” በማለት ያለውን ስጋት ገልጿል።

ሶፎንያስ ወደፊት ስለሚከሰተው ነገር አስቀድሞ ሊያውቅ የቻለው እንዴት ነው? ‘የይሖዋ ቃል ወደ እሱ እንደመጣ’ በሐቀኝነት ተናግሯል።—ሶፎንያስ 1:1

መጽሐፍ ቅዱስ በአእምሯችን ለሚጉላሉ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል

መጽሐፍ ቅዱስ በአእምሯችን ለሚጉላሉ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጣል። የሚከተሉትን ምሳሌዎች ተመልከት።

በዓለም ላይ ይህን ያህል መከራና ሥቃይ የበዛው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች መከራና ሥቃይ እየደረሰባቸው ያለው ለምን እንደሆነ ግልጽ ማብራሪያ ይሰጣል። እንዲህ ይላል፦

  1. “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።”መክብብ 8:9

    ብልሹ የሆነውና ውስን አቅም ያለው የሰዎች አገዛዝ፣ ዓለም በመከራ የተሞላ እንዲሆን አድርጓል።

  2. “ሁሉም መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል።”መክብብ 9:11

    ከባድ በሽታዎችን፣ ሰው ሠራሽ አደጋዎችንና የተፈጥሮ አደጋዎችን ጨምሮ የተለያዩ ያልተጠበቁ ክስተቶች ማንኛውንም ሰው፣ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሊያጋጥሙት ይችላሉ።

  3. “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ።”ሮም 5:12

    የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት በተፈጠሩበት ወቅት ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ነበሩ። ‘ኃጢአት ወደ ዓለም የገባው’ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ሆን ብለው በፈጣሪያቸው ላይ ባመፁበት ጊዜ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ በሰው ልጆች ላይ መከራ የሚደርሰው ለምን እንደሆነ በመናገር ብቻ አይወሰንም። አምላክ ክፋትን ሁሉ ጠራርጎ እንደሚያጠፋም ይናገራል፤ በተጨማሪም “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም” የሚል ተስፋ ይሰጣል።—ራእይ 21:3, 4

ስንሞት ምን እንሆናለን?

መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ሲሞት ሙሉ በሙሉ በድን እንደሚሆን ይገልጻል። መክብብ 9:5 “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም” በማለት ይናገራል። አንድ ሰው ሲሞት “ሐሳቡ ሁሉ ይጠፋል።” (መዝሙር 146:4) በመሆኑም ስንሞት አንጎላችን እንዲሁም የስሜት ሕዋሶቻችን መሥራት ያቆማሉ። ስለሆነም ከሞትን በኋላ ምንም ስሜት አይኖረንም፤ እንዲሁም ማሰብም ሆነ ምንም ነገር ማድረግ አንችልም።

ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ በመናገር ብቻ አይወሰንም። በሞት ያንቀላፉ ሰዎች በትንሣኤ አማካኝነት ከሞት የመነሳት አስደሳች ተስፋ እንዳላቸውም ይናገራል።—ሆሴዕ 13:14፤ ዮሐንስ 11:11-14

የተፈጠርንበት ዓላማ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት የፈጠራቸው ይሖዋ አምላክ ነው። (ዘፍጥረት 1:27) በመሆኑም የመጀመሪያው ሰው አዳም “የአምላክ ልጅ” ተብሎ ተጠርቷል። (ሉቃስ 3:38) አምላክ ሰውን የፈጠረበት ዓላማ አለው፤ ሰው የተፈጠረው በሰማይ ካለው አባቱ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርት እንዲሁም አርኪ ሥራ እየሠራ ደስተኛ ሆኖ በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖር ነው። አምላክ፣ ሁሉንም ሰዎች መንፈሳዊ ዝንባሌ ማለትም ስለ እሱ የማወቅ ተፈጥሯዊ ፍላጎት እንዲኖራቸው አድርጎ የፈጠራቸው ለዚህ ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው” በማለት ይናገራል።—ማቴዎስ 5:3

ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ “ደስተኞችስ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው!” በማለት ይናገራል። (ሉቃስ 11:28) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ እንድናውቅ የሚያስችለን ከመሆኑም ሌላ በአሁኑ ጊዜ አስደሳች ሕይወት እንድንመራ እንዲሁም የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ብሩሕ ተስፋ እንዲኖረን ይረዳናል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ወደ እሱ እንድትቀርብ ጋብዞሃል

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተለያዩ ማስረጃዎችን ከመረመሩ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ አንድ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ብቻ የሚታይ መጽሐፍ እንዳልሆነ ተገንዝበዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነና አምላክ ለሰው ልጆች ሐሳቡን የገለጸበት መጽሐፍ እንደሆነ ሙሉ እምነት አላቸው! መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ እሱን እንድታውቀውና ወዳጁ እንድትሆን ያቀረበልህን ግብዣ ይዟል። “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” በማለት ይናገራል።​—ያዕቆብ 4:8

መጽሐፍ ቅዱስን መመርመርህ አንድ ግሩም አጋጣሚ ይከፍትልሃል። ይህ ግሩም አጋጣሚ ምንድን ነው? አንድን መጽሐፍ ስታነብ ስለ ደራሲው አስተሳሰብ ማወቅ እንደምትችል ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብም የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ስለሆነው አምላክ አስተሳሰብና ስሜት ማወቅ ትችላለህ። ይህ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ ለማሰብ ሞክር። የፈጣሪህን አመለካከትና ስሜት ማወቅ ትችላለህ ማለት ነው! ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተሉትን ነገሮች እንድታውቅ ይረዳሃል፦

ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ምንም ክፍያ እንድትማር ሊረዱህ ይችላሉ። ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ወደሆነው ወደ ይሖዋ አምላክ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እንድትቀርብ ያስችልሃል።

በዚህ ርዕስ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ የሚያሳዩ አንዳንድ ማስረጃዎችን ተመልክተናል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ተመልከት። መጽሐፉን www.pr418.com/am ላይ ማግኘት ትችላለህ፤ ወይም ይህን ኮድ አስነብብ

በተጨማሪም www.pr418.com/am ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ማን ነው? የሚለውን ቪዲዮ መመልከት ትችላለህ

የሕትመት ውጤቶች > ቪዲዮዎች በሚለው ሥር ተመልከት

^ አን.10 መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ ይናገራል።—መዝሙር 83:18