ስሜታዊ ጤንነት
መጽሐፍ ቅዱስ ጎጂ የሆኑ ስሜቶችን እንድናስወግድና ጥሩ የሆኑ ስሜቶችን እንድናዳብር ያበረታታናል።
ቁጣ
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ቶሎ የማይቆጣ ሰው ከኃያል ሰው . . . ይሻላል።”—ምሳሌ 16:32
ምን ማለት ነው? ስሜታችንን የመቆጣጠር ችሎታ ካዳበርን በእጅጉ እንጠቀማለን። ሁላችንም አንዳንድ ጊዜ እንደምንቆጣ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ቁጣችንን ካልተቆጣጠርነው የከፋ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። አብዛኞቹ ሰዎች በተበሳጩበት ሰዓት በተናገሩት ወይም ባደረጉት ነገር የተነሳ በኋላ ላይ እንደሚቆጩ ተመራማሪዎች ገልጸዋል።
ምን ማድረግ ትችላለህ? በስሜት ተገፋፍተህ እርምጃ ከመውሰድህ በፊት ቁጣህን ተቆጣጠር። አንዳንድ ሰዎች በቁጣ መገንፈል የጥንካሬ ምልክት እንደሆነ ይሰማቸዋል፤ ሆኖም ቁጣን አለመቆጣጠር የድክመት ምልክት እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ስሜቱን መቆጣጠር የማይችል ሰው ቅጥር እንደሌላት የፈረሰች ከተማ ነው” ይላል። (ምሳሌ 25:28) ቁጣችንን ለመቆጣጠር የሚረዳን አንዱ ዘዴ እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት የተሟላ መረጃ ለማግኘት መሞከር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ጥልቅ ማስተዋል ሰውን ቶሎ እንዳይቆጣ ያደርገዋል” ይላል። (ምሳሌ 19:11) ስለ ጉዳዩ የተሟላ መረጃ ለማግኘት መሞከራችን ጥልቅ ማስተዋል እንድናገኝ ይረዳናል፤ ይህም ስሜታችንን ሊያረጋጋልን ይችላል።
አመስጋኝነት
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ።”—ቆላስይስ 3:15
ምን ማለት ነው? ሰዎች አመስጋኝነት ለደስታ ቁልፍ እንደሆነ ሲናገሩ ይሰማል። ከባድ መከራ ወይም ኪሳራ የደረሰባቸው ሰዎች እንኳ የዚህን ሐሳብ እውነተኝነት ይመሠክራሉ። እነዚህ ሰዎች ስሜታዊ ጤንነታቸውን ለመጠበቅ የረዳቸው፣ ባጡት ነገር ላይ ከማተኮር ይልቅ ላላቸው ነገር አመስጋኝ መሆናቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
ምን ማድረግ ትችላለህ? አመስጋኝ ለመሆን የሚያነሳሱህን ነገሮች በየቀኑ ለማሰብ ሞክር። የግድ ትላልቅ ነገሮች መሆን አያስፈልጋቸውም። ትናንሽ የሚመስሉ ነገሮችንም ማሰብ ትችላለህ፤ ለምሳሌ ፀሐይ ስትወጣ ያላትን ውበት በማየትህ ወይም ከወዳጆችህ ጋር አስደሳች ጭውውት በማድረግህ አመስጋኝ መሆን ትችላለህ። በሕይወት መኖርህ በራሱ አመስጋኝ እንድትሆን የሚያነሳሳ አንድ ምክንያት ነው። እንዲህ ያሉ ነገሮችን ጊዜ
ወስደህ ካሰብክባቸውና አመስጋኝ ከሆንክ ስሜታዊ ጤንነትህ በእጅጉ ይሻሻላል።በተለይም ቤተሰቦችህ ወይም ጓደኞችህ ስላደረጉልህ ነገር ማሰብህ በጣም ጠቃሚ ነው። ሌሎችን ለማመስገን የሚያነሳሳ ምክንያት ስታገኝ በአካል አሊያም በደብዳቤ፣ በኢ-ሜይል ወይም በጽሑፍ መልእክት አማካኝነት አድናቆትህን ግለጽላቸው። ይህም ከእነሱ ጋር ያለህን ወዳጅነት ያጠናክረዋል፤ በተጨማሪም በመስጠት የሚገኘውን ደስታ ለማጣጣም ያስችልሃል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35
ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች
ጭቅጭቅ ውስጥ አትግባ።
“ጠብ መጫር ግድብን ከመሸንቆር ተለይቶ አይታይም፤ ስለዚህ ጥል ከመነሳቱ በፊት ከአካባቢው ራቅ።”—ምሳሌ 17:14
ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከልክ በላይ አትጨነቅ።
“ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት። እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው።”—ማቴዎስ 6:34
በስሜት ተገፋፍተህ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ነገሮችን በእርጋታ አስብ።
“የማመዛዘን ችሎታ ምንጊዜም ይጠብቅሃል፤ ጥልቅ ግንዛቤም ይጋርድሃል።”—ምሳሌ 2:11