መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ጦርነት
በጥንት ዘመን እስራኤላውያን፣ በአምላካቸው በይሖዋ ስም ጦርነት ያካሂዱ ነበር። ታዲያ አምላክ በዘመናችን ጦርነት መካሄዱን ይደግፋል ማለት ነው?
የጥንት እስራኤላውያን ጦርነት ያካሄዱት ለምንድን ነው?
አንዳንዶች ምን ይላሉ?
እስራኤላውያን የሚያመልኩት ደም የተጠማ “የጦርነት አምላክ” ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
እስራኤላውያን ድል ያደረጓቸው ብሔራት፣ ዓመፀኞች እንዲሁም ከእንስሳት ጋርና በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸም የፆታ ግንኙነትን ብሎም ልጆችን መሥዋዕት ማድረግን በመሳሰሉ ወራዳ ድርጊቶች የተጨማለቁ ነበሩ። አምላክ አካሄዳቸውን እንዲለውጡ ለብዙ ዘመናት ከታገሣቸው በኋላ እነዚህን ብሔራት ለማጥፋት የተነሳበትን ምክንያት ለእስራኤላውያን ሲገልጽ “ከእናንተ ፊት አባርሬ የማስወጣቸው ብሔራት ራሳቸውን በእነዚህ ነገሮች አርክሰዋል” ብሏል።—ዘሌዋውያን 18:21-25፤ ኤርምያስ 7:31
“አምላክህ ይሖዋ እነዚህን ብሔራት ከፊትህ የሚያባርራቸው ከራሳቸው ክፋት የተነሳ ነው።”—ዘዳግም 9:5
አምላክ በዘመናችን በሚደረጉ ጦርነቶች አንደኛውን ወገን ይደግፋል?
አንተ ምን አስተውለሃል?
በብዙ ጦርነቶች ላይ በተቃራኒ ወገኖች ያሉት ሃይማኖታዊ መሪዎች አምላክ ከጎናቸው እንደሆነ ይናገራሉ። የጦርነት መንስኤዎች (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ “እስከ ዛሬ በተደረጉት ጦርነቶች ሁሉ ላይ የሃይማኖት እጅ አለበት” ይላል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ክርስቲያኖች ከጠላቶቻቸው ጋር እንዲዋጉ አልተፈቀደላቸውም። ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ ሲጽፍ “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ። . . . ራሳችሁ አትበቀሉ” ብሏል።—ሮም 12:18, 19
ኢየሱስ ተከታዮቹን ወደ ውጊያ ከመላክ ይልቅ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ፤ ይህን ብታደርጉ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 5:44, 45) ክርስቲያኖች የሚኖሩበት አገር ጦርነት በሚያካሂድበት ጊዜም እንኳ ገለልተኞች መሆን ይገባቸዋል፤ ምክንያቱም ‘የዓለም ክፍል አይደሉም።’ (ዮሐንስ 15:19) አምላክ በሁሉም ብሔራት የሚኖሩ አምላኪዎቹ ጠላቶቻቸውን እንዲወዱና ከዓለም የተለዩ እንዲሆኑ የሚፈልግባቸው ከሆነ በዘመናችን በሚካሄዱት ጦርነቶች ላይ እንዴት የአንዱ ወገን ደጋፊ ሊሆን ይችላል?
“መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም። መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል ቢሆን ኖሮ በአይሁዳውያን እጅ እንዳልወድቅ አገልጋዮቼ ይዋጉልኝ ነበር። አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም።”—ዮሐንስ 18:36
ጦርነት የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?
አንዳንዶች ምን ይላሉ?
ጦርነት የማይቀር ነገር ነው። ጦርነትና ሥልጣን በ21ኛው መቶ ዘመን (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ “ጦርነት ሁልጊዜም ይቀጥላል። በዚህ ምዕተ ዓመት ዘላቂ የሆነ ዓለም አቀፍ ሰላም ይመጣል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው” ይላል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የመዋጋት ፍላጎት ያለው ሰው ከሌለ ጦርነት አይኖርም። ከሰማይ ሆኖ የሚገዛው የአምላክ መንግሥት፣ በቅርቡ የጦር መሣሪያዎችን ከምድር ገጽ የሚያስወግድ ከመሆኑም ሌላ የሰው ልጆችን በሙሉ ሰላም ፈጣሪ እንዲሆኑ ያስተምራል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ስለሚወስደው እርምጃ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “በሩቅ ካሉ ኃያላን ብሔራት ጋር [በተያያዘ] ሁሉንም ነገር ያቀናል። እነሱ ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ። አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ሰይፍ አያነሳም፤ ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም።”—ሚክያስ 4:3
በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር፣ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሯሯጡ መንግሥታት፣ ዜጎች ለዓመፅ እንዲነሳሱ የሚያደርጉ ፍትሐዊ ያልሆኑ ፖሊሲዎች ወይም በተለያዩ ጎሳዎች መካከል መከፋፈል እንዲኖር የሚያደርገው ጭፍን ጥላቻ እንደማይኖር መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። በመሆኑም ጦርነት ሙሉ በሙሉ ይወገዳል። አምላክ እንዲህ በማለት ቃል ገብቷል፦ “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም፤ ምክንያቱም ውኃ ባሕርን እንደሚሸፍን ምድርም በይሖዋ እውቀት ትሞላለች።”—ኢሳይያስ 11:9
“ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል። ቀስትን ይሰባብራል፤ ጦርንም ያነክታል፤ የጦር ሠረገሎችን በእሳት ያቃጥላል።”—መዝሙር 46:9