በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መፍትሔ አግኝተዋል

የሪካርዶ እና የአንድሬስ ታሪክ

የሪካርዶ እና የአንድሬስ ታሪክ

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ከፍተኛ ኃይል አለው። የሪካርዶን እና የአንድሬስን ታሪክ እንደ ምሳሌ እንመልከት።

ሪካርዶ፦ ገና የ15 ዓመት ልጅ ሳለሁ የአንድ የወሮበሎች ቡድን አባል ሆንኩ። አዲሶቹ ጓደኞቼ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድረውብኛል። እንዲያውም ወህኒ ቤት ውስጥ አሥር ዓመት መታሰር እፈልግ ነበር! ይህ ሞኝነት ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ በሰፈራችን ያሉ ሰዎች ወህኒ ቤት ታስረው የወጡ ሰዎችን ያደንቋቸውና ያከብሯቸው ነበር። እኔም እንደ እነሱ መሆን እፈልግ ነበር።

አብዛኞቹ የወሮበሎች ቡድን አባላት እንደሚያደርጉት እኔም ዕፆችን እወስድ፣ የፆታ ብልግና እፈጽም እንዲሁም በተለያዩ የዓመፅ ድርጊቶች እካፈል ነበር። አንድ ምሽት ላይ ከሌላ የወሮበሎች ቡድን ጋር በተነሳ ጠብ ተኩስ መለዋወጥ ጀመርን። እገደላለሁ ብዬ አስቤ የነበረ ቢሆንም ምንም ጉዳት ሳይደርስብኝ አመለጥኩ። ይህም ስለ ሕይወቴና ስለ ግቦቼ በቁም ነገር እንዳስብ አደረገኝ፤ በመሆኑም በሕይወቴ ውስጥ ለውጥ ለማድረግ ወሰንኩ። ሆኖም መለወጥ የምችለው እንዴት ነው? እርዳታ ማግኘት የምችለውስ ከየት ነው?

አብዛኞቹ ዘመዶቼ በሕይወታቸው ደስተኛ አልነበሩም። በርካታ ችግሮች ነበሩባቸው። የአንደኛው አጎቴ ቤተሰብ ግን ከሌሎቹ የተለየ ነበር። የቤተሰቡ አባላት ጥሩ ሰዎች እንደሆኑና የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን እንደሚከተሉ አውቅ ነበር። እንዲያውም የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ በአንድ ወቅት ሲናገሩ ሰምቻለሁ። ስለዚህ ከተኩስ ልውውጡ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ ይሖዋ እንዲረዳኝ ስሙን እየጠራሁ ጸለይኩ። የሚገርመው ነገር በማግስቱ አንድ የይሖዋ ምሥክር በሬን አንኳኳ! እሱም መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረኝ ጀመር።

ብዙም ሳይቆይ አንድ ትልቅ ፈተና አጋጠመኝ። የቀድሞ ጓደኞቼ በተደጋጋሚ ስልክ እየደወሉ አብሬያቸው ጊዜ እንዳሳልፍ ይጠይቁኝ ነበር። ከእነሱ መለየቱ ቢከብደኝም ፈቃደኛ አለመሆኔን ነገርኳቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን ለመቀጠል ቆርጬ ነበር፤ እንዲህ በማድረጌም በጣም ደስተኛ ነኝ! ሕይወቴ በአስደናቂ ሁኔታ የተሻሻለ ሲሆን ይህም እውነተኛ ደስታ አስገኝቶልኛል።

የወሮበሎች ቡድን አባል በነበርኩበት ጊዜ፣ አክብሮት ለማትረፍ ወህኒ ቤት አሥር ዓመት ለመታሰር እመኝ እንደነበረ ለአምላክ በጸሎት እንደነገርኩት ትዝ ይለኛል። ስለዚህ እኔ እርዳታ እንደተደረገልኝ ሁሉ እኔም ሌሎችን መርዳት እንድችል የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆኜ ቢያንስ አሥር ዓመት እንዳገለግለው እንዲፈቅድልኝ ለመንኩት። አምላክ ጸሎቴን የመለሰልኝ ሲሆን የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆኜ 17 ዓመታት አሳልፌያለሁ! ደግሞም ለእስር ከመዳረግ ተርፌያለሁ።

ይሁን እንጂ ከቀድሞ ጓደኞቼ መካከል አብዛኞቹ የብዙ ዓመታት እስራት ተፈርዶባቸው ወህኒ ቤት ይገኛሉ። ሌሎቹ ደግሞ ሞተዋል። ሕይወቴን ወደ ኋላ መለስ ብዬ ስመለከተው፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑትን ዘመዶቼን ለማመስገን እነሳሳለሁ። ከሌሎች የተለየ አቋም በመውሰድ ሕይወታቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መንገድ ይመሩ ነበር። ይህም የወሮበሎቹ ቡድን ውስጥ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ እንዳከብራቸው አድርጎኛል። ከሁሉ በላይ ደግሞ አምላክ የተሻለውን የሕይወት መንገድ ስላስተማረኝ አመሰግነዋለሁ።

አንድሬስ፦ ተወልጄ ያደግሁት ዕፅ መውሰድ፣ ዝርፊያ፣ ግድያ እና ዝሙት አዳሪነት በተስፋፉበት የድሆች ሰፈር ነበር። አባቴ የአልኮል መጠጥና የኮኬይን ሱሰኛ ነበር። አባቴና እናቴ ሁልጊዜ ይሰዳደቡ እንዲሁም ይደባደቡ ነበር።

ገና በልጅነት ዕድሜዬ የአልኮል መጠጦች መጠጣትና ዕፅ መውሰድ ጀመርኩ። አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈው በመስረቅና የሰረቅሁትን ነገር በመሸጥ ነበር። ከፍ እያልኩ ስሄድ አባቴ ከእኔ ጋር ለመቀራረብ ጥረት ማድረግ ጀመረ፤ ሆኖም ይህን ለማድረግ የሞከረው በተሳሳተ መንገድ ነበር። ዕፆችንና ሌሎች ሕገ ወጥ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ በድብቅ ማስገባትና መሸጥ የምችልበትን መንገድ አስተማረኝ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ገንዘብ አገኘሁ። አንድ ቀን ፖሊሶች ወደ ቤቴ መጡና ይዘውኝ ሄዱ። ከዚያም በነፍስ ግድያ ሙከራ ተከስሼ የአምስት ዓመት እስራት ተፈረደብኝ።

አንድ ቀን ጠዋት፣ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ማድረግ የሚፈልጉ እስረኞችን የሚጋብዝ ማስታወቂያ በድምፅ ማጉያ ሲነገር ሰማሁ። እኔም በውይይቱ ላይ ለመገኘት ወሰንኩ። የሰማሁት ነገር ስላሳመነኝ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። የይሖዋ ምሥክሮች የጥቅሶቹን መልእክት ሳያድበሰብሱ የአምላክን የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ገለጹልኝ።

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ ያላስደሰታቸው አብረውኝ የታሰሩ ሰዎች ዛቻ ይሰነዝሩብኝ ጀመር፤ ይህም ያለአምላክ እርዳታ አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችን ማድረግ እንደማልችል አስገነዘበኝ። ስለዚህ ይሖዋ ብርታትና ጥበብ እንዲሰጠኝ ጸለይኩ፤ እሱም ያቀረብኩትን ጸሎት በመስማት ረድቶኛል። በመሆኑም ተቃዋሚዎቼ ለሚሰነዝሩት ዛቻ ከመንበርከክ ይልቅ ለሌሎች እስረኞች በድፍረት መመሥከር ችያለሁ።

ከእስር የምፈታበት ጊዜ ሲደርስ በጣም ከመጨነቄ የተነሳ እስር ቤቱ ውስጥ መቆየት ፈልጌ ነበር! ግቢውን ለቅቄ በምወጣበት ጊዜ በርካታ እስረኞች ተሰናበቱኝ። እንዲያውም አንዳንዶቹ በፍቅር “ትንሿ ሰባኪ፣ ደህና ሁኚ” አሉኝ።

መጽሐፍ ቅዱስ ባላጠና ኖሮ ሕይወቴ ወዴት ያመራ እንደነበረ ሳስበው ይዘገንነኛል። አምላክ ስለወደደኝና የመለወጥ ተስፋ የለውም ብሎ ስላልተወኝ እጅግ በጣም አመሰግነዋለሁ። *

^ መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንዳለው የሚያሳዩ ተጨማሪ ምሳሌዎችን jw.org ላይ ማግኘት ይቻላል። ላይብረሪ በሚለው ዓምድ ሥር ተከታታይ ርዕሶች ላይ “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል“ የሚለውን ፈልግ።