በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከውጥረት እፎይታ ማግኘት

ውጥረት ምንድን ነው?

ውጥረት ምንድን ነው?

አስቸጋሪ ወይም አደገኛ ሁኔታ ሲያጋጥመን ሰውነታችን ውጥረት ውስጥ ይገባል። በዚህ ወቅት አንጎላችን ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ሆርሞኖች ይረጫል። እነዚህ ሆርሞኖች ደግሞ የልብ ምትን ይጨምራሉ፤ የደም ግፊትን ይቆጣጠራሉ፤ ብሎም ሳንባችን እንዲሰፋ ወይም እንዲጠብብ እንዲሁም ጡንቻዎቻችን እንዲገታተሩ ያደርጋሉ። እኛ ሳይታወቀን ሰውነታችን በራሱ እርምጃ ለመውሰድ ይዘጋጃል። ውጥረት የፈጠረብን ነገር ካለፈ በኋላ ግን ሰውነታችን ይረጋጋና ወደ ቀድሞ ሁኔታው ይመለሳል።

ውጥረት ጠቃሚ ወይም ጎጂ ሊሆን ይችላል

ውጥረት ተፈጥሯዊ ነገር ነው፤ ሰውነትህ ውጥረት ውስጥ መግባቱ አስቸጋሪ ወይም አደገኛ ሁኔታዎችን ለማለፍ ይረዳሃል። ውጥረት የሚጀምረው ከአንጎል ነው። ጠቃሚ የሆነ ውጥረት ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ ያስችልሃል። በተወሰነ መጠን ውጥረት ውስጥ መሆንህ ግብህ ላይ ለመድረስ እንዲሁም በፈተና፣ በሥራ ቃለ መጠይቅ ወይም በስፖርታዊ ውድድር ላይ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ሊረዳህ ይችላል።

ይሁንና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ፣ ከልክ ያለፈ ወይም ሥር የሰደደ ውጥረት ጎጂ ነው። ሰውነትህ ሁልጊዜ ውጥረት ውስጥ ከሆነ አካላዊ፣ ስሜታዊ እና አእምሯዊ ጉዳት ሊደርስብህ ይችላል። ባሕርይህ እንዲሁም ሌሎችን የምትይዝበት መንገድ ይቀየር ይሆናል። ከዚህም ሌላ አንዳንዶች ሥር የሰደደ ውጥረትን ለመቋቋም ሲሉ ለሱሶች ወይም ለሌሎች መጥፎ ልማዶች ይጋለጣሉ። አልፎ ተርፎም ውጥረት በመንፈስ ጭንቀት እንድትዋጥ፣ ሁሉ ነገር እንዲታክትህ እንዲሁም ራስህን ለማጥፋት እንድታስብ ሊያደርግህ ይችላል።

ውጥረት በተለያዩ ሰዎች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ሊለያይ ይችላል፤ ያም ቢሆን በጥቅሉ ሲታይ ውጥረት ለብዙ ዓይነት በሽታዎች መንስኤ ይሆናል። አብዛኞቹን የሰውነት ክፍሎችም ይነካል።