አንዳንዶች ምን ብለው ያምናሉ?
ሂንዱዎች
ሂንዱዎች አንድ ሰው መከራ የሚደርስበት በአሁኑ ሕይወቱ ወይም በቀድሞ ሕይወቱ በፈጸመው ድርጊት የተነሳ እንደሆነ ያምናሉ። አንድ ሰው አእምሮውን ከዓለማዊ ምኞቶች ሙሉ በሙሉ ማላቀቅ ከቻለ ሞክሻ የሚባል ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ማለትም ሌላ ፍጥረት ሆኖ ዳግመኛ መወለዱን እንደሚያቆም ያስተምራሉ።
ሙስሊሞች
ሙስሊሞች መከራ የሚደርሰው ሰዎችን ለመቅጣት ወይም እምነታቸውን ለመፈተን እንደሆነ ያምናሉ። የሰሜን አሜሪካ እስላማዊ ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር ሳይድ ሰኢድ “መከራ ላገኘናቸው በረከቶች አምላክን ምንጊዜም ማመስገንና የተቸገሩትን መርዳት እንዳለብን” እንደሚያስታውሰን ገልጸዋል።
የአይሁድ እምነት
የአይሁድ እምነት ሰዎች መከራ የሚደርስባቸው በራሳቸው ጥፋት እንደሆነ ያስተምራል። አንዳንድ አይሁዳውያን፣ ምንም ሳያጠፉ መከራ የደረሰባቸው ሰዎች ከትንሣኤ በኋላ ፍትሕ እንደሚያገኙ ያምናሉ። የካባላ አይሁድ እምነት ደግሞ ሪኢንካርኔሽንን ያስተምራል፤ በዚህ ትምህርት መሠረት አንድ ሰው ለኃጢአቱ ስርየት ማግኘት የሚችልበት ተደጋጋሚ አጋጣሚ ያገኛል።
ቡድሂስቶች
ቡድሂስቶች አንድ ሰው አሉታዊ ድርጊቶቹን፣ ስሜቶቹንና ምኞቶቹን ማስወገድ እስኪችል ድረስ በተደጋጋሚ እየተወለደ መከራ እንደሚደርስበት ያምናሉ። አንድ ሰው ጥበብ በማዳበር፣ የጽድቅ ሥራ በማከናወንና አእምሮውን በመገሠጽ ኒርቫና ላይ እንደሚደርስ ማለትም ከየትኛውም ዓይነት መከራ ነፃ እንደሚሆን ያስተምራሉ።
የኮንፊሽየስ ተከታዮች
የኮንፊሽየስ ተከታዮች መከራ በአብዛኛው የሚደርሰው “በሰዎች ድክመትና ስህተት የተነሳ ነው” ብለው እንደሚያምኑ ኤ ዲክሽነሪ ኦቭ ኮምፓራቲቭ ሪሊጅን ገልጿል። በኮንፊሽየስ ትምህርት መሠረት፣ መልካም አኗኗር በመከተል መከራን መቀነስ ቢቻልም ‘መከራ ከሰው የሚበልጥ አቅም ባላቸው መንፈሳዊ ኃይሎች ምክንያትም ሊመጣ ይችላል። በዚህ ወቅት ሰዎች ዕጣ ፈንታቸውን ከመቀበል ውጭ ምንም ማድረግ አይችሉም።’
የተለያዩ ባዕድ አምልኮዎች
የተለያዩ ባዕድ አምልኮዎች መከራ የሚደርሰው በመናፍስት ምክንያት እንደሆነ ያስተምራሉ። እንዲህ ያሉ እምነቶች፣ መናፍስት መልካም ዕድል ሊያመጡ ወይም ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ እንዲሁም አንዳንድ የአምልኮ ሥርዓቶችን በመፈጸም ጉዳቱን መከላከል እንደሚቻል ይገልጻሉ። በመሆኑም አንድ ሰው በሚታመምበት ጊዜ “አዋቂዎች” የሚሰጡት መድኃኒትና የሚፈጽሙት የአምልኮ ሥርዓት የመናፍስቱን ሥራ ለማፍረስ እንደሚያስችል ይታመናል።
ክርስቲያኖች
ክርስቲያኖች የዘፍጥረት መጽሐፍ በሚገልጸው መሠረት መከራ የመጣው የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በሠሩት ኃጢአት ምክንያት እንደሆነ ያምናሉ። ሆኖም በርካታ የክርስትና ሃይማኖቶች ይህን ትምህርት በርዘውታል። ለምሳሌ አንዳንድ ካቶሊኮች አንድ ሰው መከራ ሲደርስበት መከራውን ‘ለአምላክ እንደ መባ አድርጎ በማቅረብ’ አምላክ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንዲባርክ ወይም የእሱ መከራ ለሌላ ሰው መዳን እንዲያስገኝ መጠየቅ እንደሚችል ያስተምራሉ።
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት
jw.org ላይ የሚገኘውን አምላክ ሁሉንም ሃይማኖቶች ይቀበላል? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።