የጥናት ርዕስ 6
መዝሙር 18 ለቤዛው አመስጋኝ መሆን
ለይሖዋ ይቅርታ አድናቆት ያለን ለምንድን ነው?
“አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ . . . አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”—ዮሐ. 3:16
ዓላማ
ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር የሚለው ምንን መሠረት አድርጎ እንደሆነ በመመርመር ለይሖዋ ይቅርታ ያለንን አድናቆት ማሳደግ።
1-2. የሰው ልጆች ያሉበት ሁኔታ በአንቀጽ 1 ላይ ከተጠቀሰው ወጣት ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
በሀብታም ቤተሰብ ውስጥ ያደገን አንድ ወጣት በምናብህ ለመሣል ሞክር። አንድ ቀን ወላጆቹ በድንገተኛ አደጋ ሕይወታቸው አለፈ። ወጣቱ ይህን ሲሰማ በሐዘን ተዋጠ። ሆኖም ሌላ አስደንጋጭ ዜናም ሰማ። ወላጆቹ የቤተሰባቸውን ንብረት እንዳባከኑና በከፍተኛ ዕዳ ውስጥ እንደተዘፈቁ ተገነዘበ። ወጣቱ ሀብታቸውን ከመውረስ ይልቅ ዕዳቸውን ወረሰ። አበዳሪዎቻቸው ደግሞ ገንዘባቸውን ለመቀበል ወደ እሱ ይመጡ ጀመር። ዕዳው ዕድሜ ልኩን ሠርቶ ሊከፍለው ከሚችለው በላይ ነው።
2 የእኛም ሁኔታ ከዚህ ወጣት ሁኔታ ጋር በአንዳንድ መንገዶች ይመሳሰላል። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን ፍጹማን የነበሩ ከመሆኑም ሌላ ውብ በሆነች ገነት ውስጥ ይኖሩ ነበር። (ዘፍ. 1:27፤ 2:7-9) አስደሳችና ዘላለማዊ የሆነ ሕይወት የመምራት አጋጣሚ ነበራቸው። በኋላ ግን ሁሉም ነገር ተቀየረ። መኖሪያቸው የሆነችውን ገነት እንዲሁም ለዘላለም የመኖር አጋጣሚያቸውን አጡ። ታዲያ ለልጆቻቸው ያወረሱት ምን ዓይነት ውርስ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት መልሱን ይነግረናል፦ “በአንድ ሰው [በአዳም] አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) አዳም ያወረሰን ውርስ ኃጢአት ነው፤ ኃጢአት ደግሞ ሞት ያስከትላል። በዘር የወረስነው ኃጢአት እንደ ትልቅ ዕዳ ሊቆጠር ይችላል፤ ማናችንም ብንሆን ይህን ዕዳ መክፈል አንችልም።—መዝ. 49:8
3. ኃጢአት ከዕዳ ጋር የሚመሳሰለው በምን መንገድ ነው?
3 ኢየሱስ ኃጢአትን ‘ከዕዳ’ ጋር አመሳስሎታል። (ማቴ. 6:12፤ ሉቃስ 11:4) ኃጢአት ስንሠራ የይሖዋ ባለዕዳዎች እንደሆንን ሊቆጠር ይችላል። ለሠራነው ኃጢአት የሚገባውን ቅጣት መክፈል ይኖርብናል። ይህ ዕዳ ካልተከፈለ ዕዳችን የሚሰረዝልን ስንሞት ብቻ ነው።—ሮም 6:7, 23
4. (ሀ) እርዳታ ካላገኙ፣ ሁሉም ኃጢአተኞች ምን ይጠብቃቸዋል? (መዝሙር 49:7-9) (ለ) “ኃጢአት” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ያመለክታል? (“ ኃጢአት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
4 አዳምና ሔዋን ያጡትን ነገር በሙሉ መልሰን ማግኘት እንችላለን? በራሳችን ጥረት አንችልም። (መዝሙር 49:7-9ን አንብብ።) እርዳታ ካላገኘን፣ ወደፊት በሕይወት የመኖርም ሆነ ከሞት የመነሳት ተስፋ አይኖረንም። ልክ እንደ እንስሳት ሞተን እንቀራለን ማለት ነው።—መክ. 3:19፤ 2 ጴጥ. 2:12
5. የሚወደን አባታችን የወረስነውን የኃጢአት ዕዳ ለመክፈል የረዳን እንዴት ነው? (ሥዕሉን ተመልከት።)
5 በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ወጣት፣ አንድ ሀብታም ሰው ዕዳውን በሙሉ እንደሚከፍልለት ቢነግረው ምን የሚሰማው ይመስልሃል? ይህን ልዩ ስጦታ በከፍተኛ አድናቆት እንደሚቀበል ምንም ጥያቄ የለውም። በተመሳሳይም የሚወደን አባታችን ይሖዋ ከአዳም የወረስነውን የኃጢአት ዕዳ ለመክፈል የሚያስችል ስጦታ ሰጥቶናል። ኢየሱስ ሁኔታውን ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” (ዮሐ. 3:16) በተጨማሪም ይህ ስጦታ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት የምንችልበት አጋጣሚ ይሰጠናል።
6. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጾች እንመረምራለን? ለምንስ?
6 ከዚህ ግሩም ስጦታ መጠቀምና ለኃጢአታችን ይቅርታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን እርቅ፣ ስርየት፣ ማስተሰረያ፣ ቤዛ፣ መዋጀት እና ጻድቅ ተደርጎ መቆጠር የሚሉትን አገላለጾች መመርመራችን ይህን ጥያቄ ለመመለስ ይረዳናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ የእነዚህን አገላለጾች ትርጉም እንመረምራለን። እነዚህ አገላለጾች ባላቸው ትርጉም ላይ ማሰላሰላችን ለይሖዋ ይቅርታ ያለንን አድናቆት ያሳድግልናል።
ዓላማው፦ እርቅ
7. (ሀ) አዳምና ሔዋን ሌላስ ምን አጥተዋል? (ለ) የአዳምና የሔዋን ዘሮች እንደመሆናችን መጠን ምን ያስፈልገናል? (ሮም 5:10, 11)
7 አዳምና ሔዋን ያጡት የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚያቸውን ብቻ ሳይሆን ከአባታቸው ከይሖዋ ጋር የነበራቸውን ውድ ዝምድናም ጭምር ነው። መጀመሪያ ላይ አዳምና ሔዋን የአምላክ ቤተሰብ አባላት ነበሩ። (ሉቃስ 3:38) በይሖዋ ላይ ካመፁ በኋላ ግን ከእሱ ቤተሰብ ተባረሩ፤ ይህ የሆነው ልጆች ከመውለዳቸው በፊት ነው። (ዘፍ. 3:23, 24፤ 4:1) እኛም የእነሱ ዘሮች እንደመሆናችን መጠን ከይሖዋ ጋር መታረቅ ያስፈልገናል። (ሮም 5:10, 11ን አንብብ።) በሌላ አባባል ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት ያስፈልገናል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው፣ ከላይ ያለው ጥቅስ ላይ “መታረቅ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ጠላትን ወዳጅ ማድረግ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል። የሚገርመው፣ ይህ እንዲሆን ቅድሚያውን ወስዶ ዝግጅት ያደረገው ይሖዋ ነው። እንዴት?
ዝግጅቱ፦ ስርየት
8. ስርየት ምንድን ነው?
8 ስርየት፣ ይሖዋ ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች ከእሱ ጋር መልሰው ጥሩ ዝምድና መመሥረት እንዲችሉ ሲል ያደረገው ዝግጅት ነው። ስርየት አንድን ነገር ተመጣጣኝ ዋጋ ባለው ሌላ ነገር መቀየርን ይጠይቃል። የጠፋን ወይም የተበላሸን ነገር በዚህ መንገድ መልሶ ማግኘት ወይም መተካት ይቻላል። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትም ስለዚህ ጉዳይ ይናገራሉ። (ሮም 3:25) ስርየት፣ አንድ ሰው ከአምላክ ጋር ሰላምና ጥሩ ዝምድና እንዲኖረው ያስችላል።
9. ይሖዋ እስራኤላውያን ለኃጢአታቸው ይቅርታ እንዲያገኙ ሲል የትኛውን ጊዜያዊ ዝግጅት አቋቁሞ ነበር?
9 ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት እንዲችሉ ሲል ኃጢአታቸውን ይቅር ለማለት የሚያስችል ጊዜያዊ ዝግጅት አቋቁሞ ነበር። እስራኤላውያን በየዓመቱ የስርየትን ቀን ያከብሩ ነበር። በዚያ ዕለት ሊቀ ካህናቱ ሕዝቡን ወክሎ የእንስሳት መሥዋዕቶችን ያቀርባል። እርግጥ ነው፣ የእንስሳት መሥዋዕቶች የማንንም ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ማስተሰረይ አይችሉም፤ ምክንያቱም እንስሳት ከሰዎች ያንሳሉ። ያም ቢሆን፣ ንስሐ የገቡ እስራኤላውያን ይሖዋ የሚጠብቀውን መሥዋዕት እስካቀረቡ ድረስ እሱ ኃጢአታቸውን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነበር። (ዕብ. 10:1-4) በተጨማሪም ይህ ዝግጅት እንዲሁም እስራኤላውያን በየጊዜው የሚያቀርቧቸው የኃጢአት መባዎች፣ ኃጢአተኛ መሆናቸውንና ዘላቂ መፍትሔ ማግኘታቸው አንገብጋቢ መሆኑን እንዲያስታውሱ ያደርጋቸዋል።
10. ይሖዋ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ለማለት የትኛውን ዘላቂ ዝግጅት አድርጓል?
10 ይሖዋ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ለማለት የሚያስችል ዘላቂ ዝግጅት አድርጓል። የሚወደው ልጁ “የብዙዎችን ኃጢአት ለመሸከም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖ” እንዲቀርብ አደረገ። (ዕብ. 9:28) ኢየሱስ “በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ” ሰጥቷል። (ማቴ. 20:28) ይሁንና ቤዛ ምንድን ነው?
ዋጋው፦ ቤዛው
11. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ቤዛ ምን ያመለክታል? (ለ) ቤዛውን መክፈል የሚችለው ምን ዓይነት ሰው ነው?
11 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ቤዛ የሚያመለክተው ስርየትንና እርቅን ለማስገኘት የተከፈለውን ዋጋ ነው። a ቤዛው፣ ይሖዋ የታጣውን ነገር መልሶ እንዲሰጠን የሚያስችል መሠረት ይሆናል። በምን መንገድ? አዳምና ሔዋን ፍጹም ሕይወታቸውን እንዲሁም ለዘላለም የመኖር አጋጣሚያቸውን እንዳጡ አስታውስ። ስለዚህ ቤዛው ከታጣው ነገር ጋር ተመጣጣኝ ዋጋ ሊኖረው ይገባል። (1 ጢሞ. 2:6) ቤዛውን መክፈል የሚችለው (1) ፍጹም የሆነ፣ (2) በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ያለው እንዲሁም (3) ይህን ሕይወቱን ለእኛ ሲል ለመተው ወይም መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነ ለአካለ መጠን የደረሰ ወንድ ብቻ ነው። የጠፋውን ሕይወት መተካት ወይም ማስተሰረይ የሚችለው የዚህ ሰው ሕይወት ብቻ ነው።
12. ኢየሱስ የቤዛውን ዋጋ ሊከፍል የቻለው ለምንድን ነው?
12 ኢየሱስ የቤዛውን ዋጋ መክፈል የቻለባቸውን ሦስት ምክንያቶች እንመልከት። (1) ፍጹም ነበር፤ “ምንም ኃጢአት አልሠራም።” (1 ጴጥ. 2:22) (2) በዚህም የተነሳ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ነበረው። (3) ለእኛ ሲል ለመሞትና ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኗል። (ዕብ. 10:9, 10) ኢየሱስ የመጀመሪያው ሰው አዳም ኃጢአት ከመሥራቱ በፊት እንደነበረው ፍጹም ሰው ነበር። (1 ቆሮ. 15:45) በመሆኑም የኢየሱስ ሞት የአዳምን ኃጢአት ማስተሰረይ ማለትም አዳም ያጣውን ነገር መተካት ይችላል። (ሮም 5:19) በዚህም የተነሳ ኢየሱስ “የኋለኛው አዳም” ተብሎ ሊጠራ ችሏል። ሌላ ፍጹም ሰው መጥቶ አዳም ላጣው ነገር ዋጋ መክፈል አያስፈልገውም። ኢየሱስ “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” ሞቷል።—ዕብ. 7:27፤ 10:12
13. በስርየትና በቤዛው መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
13 ታዲያ በስርየትና በቤዛው መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ስርየት፣ አምላክ በእሱና በሰው ልጆች መካከል ያለውን ዝምድና ለማደስ የወሰደውን እርምጃ ያመለክታል። ቤዛው ደግሞ ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች ስርየት እንዲያገኙ የተከፈለውን ዋጋ ያመለክታል። ይህ ዋጋ ለእኛ ሲባል የፈሰሰው የኢየሱስ ውድ ደም ነው።—ኤፌ. 1:7፤ ዕብ. 9:14
ውጤቱ፦ መዋጀት እና ጻድቅ ተደርጎ መቆጠር
14. ከዚህ በመቀጠል ምን እንመረምራለን? ለምንስ?
14 የስርየት ዝግጅት የትኞቹን ውጤቶች ያስገኛል? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስርየት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ለመግለጽ የተለያዩ ቃላትን ይጠቀማል። የእነዚህ ቃላት ትርጉም የጋራ ነጥብ ቢኖረውም እያንዳንዱ ቃል፣ ለይሖዋ ይቅርታ መንገድ ከፋች የሆነው የስርየት ዝግጅት ያሉትን የተለያዩ ገጽታዎች ያጎላል። እነዚህን ቃላት መመርመራችን ከይሖዋ ይቅርታ በግለሰብ ደረጃ ጥቅም ማግኘት የምንችልባቸውን መንገዶች ለማስተዋልም ይረዳናል።
15-16. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መዋጀት” የሚለው ቃል ምን ያመለክታል? (ለ) መዋጀታችን የሚጠቅመንስ እንዴት ነው?
15 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መዋጀት የሚለው ቃል፣ ቤዛው በመከፈሉ ምክንያት ነፃ መውጣታችንን ያመለክታል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ጉዳዩን ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከንቱ አኗኗር ነፃ የወጣችሁት ሊበላሹ በሚችሉ ነገሮች ይኸውም በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁና። ከዚህ ይልቅ ነፃ የወጣችሁት [ቃል በቃል “የተዋጃችሁት”] ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም ባለ ውድ ደም ይኸውም በክርስቶስ ደም ነው።”—1 ጴጥ. 1:18, 19 ግርጌ
16 በቤዛዊ መሥዋዕቱ የተነሳ ከኃጢአትና ከሞት ጭቆና ነፃ መውጣት እንችላለን። (ሮም 5:21) በእርግጥም፣ ውድ በሆነው የኢየሱስ ደም ወይም ሕይወት በመዋጀታችን ይሖዋንና ኢየሱስን የምናመሰግንበት በቂ ምክንያት አለን።—1 ቆሮ. 15:22
17-18. (ሀ) ጻድቅ ተደርጎ መቆጠር ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) ይህ እኛን የሚጠቅመንስ እንዴት ነው?
17 ጻድቅ ተደርገን ተቆጥረናል ሲባል ክሳችን ተሰርዞልናል፤ እንዲሁም የኃጢአት መዝገባችን ተደምስሷል ማለት ነው። ይሖዋ ይህን የሚያደርገው የራሱን የፍትሕ መሥፈርት ጥሶ አይደለም። ይሖዋ ጻድቅ አድርጎ የሚቆጥረን በራሳችን ጥረት አይደለም፤ ወይም ደግሞ ኃጢአታችንን በቸልታ ያልፋል ማለት አይደለም። ሆኖም በስርየት ዝግጅቱ እንዲሁም በተከፈለልን የቤዛ ዋጋ ላይ እምነት ስላለን ይሖዋ ዕዳችንን የሚሰርዝበት መሠረት አለው።—ሮም 3:24፤ ገላ. 2:16
18 ይህ ለእያንዳንዳችን ምን ትርጉም አለው? በሰማይ ላይ ከኢየሱስ ጋር እንዲገዙ የተመረጡት ሰዎች የአምላክ ልጆች በመሆን ጻድቃን ተደርገው ተቆጥረዋል። (ቲቶ 3:7፤ 1 ዮሐ. 3:1) ኃጢአታቸው ይቅር ተብሎላቸዋል። በሌላ አባባል፣ የወንጀል መዝገባቸው ተሰርዞላቸዋል ሊባል ይችላል። በመሆኑም ወደ መንግሥቱ ለመግባት ብቁ ናቸው። (ሮም 8:1, 2, 30) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ደግሞ የአምላክ ወዳጆች በመሆን ጻድቃን ተደርገው ተቆጥረዋል፤ ኃጢአታቸውም ይቅር ተብሎላቸዋል። (ያዕ. 2:21-23) ከታላቁ መከራ የሚተርፉት እጅግ ብዙ ሕዝብ ጨርሶ ያለመሞት አጋጣሚ አላቸው። (ዮሐ. 11:26) በሞት ያንቀላፉት “ጻድቃን” እና “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” የትንሣኤ ተስፋ ይጠብቃቸዋል። (ሥራ 24:15፤ ዮሐ. 5:28, 29) በመጨረሻም፣ በምድር ላይ ያሉ ታዛዥ የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ “የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት” ያገኛሉ። (ሮም 8:21) በእርግጥም የስርየት ዝግጅት ግሩም በረከት ያስገኛል፤ ከአባታችን ከይሖዋ ጋር ሙሉ በሙሉ እንታረቃለን።
19. ሁኔታችን የተቀየረው እንዴት ነው? (“ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
19 ቀደም ሲል ሁኔታችን ያለውን ነገር ሁሉ ካጣውና ፈጽሞ ሊከፍለው የማይችለው ዕዳ ከወረሰው ወጣት ጋር ይመሳሰል ነበር። ሆኖም ይሖዋ ረድቶናል። የስርየት ዝግጅት በመደረጉ እንዲሁም ቤዛው በመከፈሉ ሁኔታችን ተቀይሯል። በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን እምነት ከኃጢአትና ከሞት እንድንዋጅ ወይም ነፃ እንድንወጣ ያስችለናል። ኃጢአታችን ሊሰረዝልን፣ የወንጀል መዝገባችንም ሊደመሰስልን ይችላል። ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ከሚወደን አባታችን ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት ችለናል።
20. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?
20 ይሖዋና ኢየሱስ ባደረጉልን ነገር ላይ ስናሰላስል ልባችን በአድናቆት ይሞላል። (2 ቆሮ. 5:15) የእነሱን እርዳታ ባናገኝ ኖሮ ምንም ተስፋ አይኖረንም ነበር! ይሁንና የይሖዋ ይቅርታ ለእያንዳንዳችን ምን ትርጉም አለው? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የዚህን ጥያቄ መልስ እንመረምራለን።
መዝሙር 10 ይሖዋ አምላካችንን አወድሱ!
a በአንዳንድ ቋንቋዎች “ቤዛ” የሚለው ቃል “የሕይወት ዋጋ” ወይም “የተከፈለው ዋጋ” ተብሎ ይተረጎማል።