በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማናችንም ልንጠይቅ የምንችለው ቀላል ጥያቄ

ማናችንም ልንጠይቅ የምንችለው ቀላል ጥያቄ

ሜሪ እና ባለቤቷ ጆን a የሚኖሩት ለሥራ ከፊሊፒንስ የመጡ ብዙ ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ ነው፤ በመሆኑም ለእነዚህ ሰዎች ምሥራቹን ይሰብካሉ። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ሜሪ፣ በምትኖርበት አገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮችም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመር ችላ ነበር። ይህን ማድረግ የቻለችው እንዴት ነው?

ሜሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቿን “መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የሚፈልግ ሌላ ሰው ታውቃላችሁ?” ብላ ትጠይቃቸዋለች። “አዎ” ካሏት እንዲያስተዋውቋት ትጠይቃቸዋለች። ይህ ቀላል ጥያቄ ብዙ ጊዜ ጥሩ ውጤት ያስገኛል። ለምን? ምክንያቱም ለአምላክ ቃል አድናቆት ያላቸው ሰዎች የሚማሩትን ነገር ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መናገር ይፈልጋሉ። ሜሪ ይህን ጥያቄ በመጠየቋ ምን ውጤት አግኝታለች?

የሜሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጃስሚን አራት አዳዲስ ጥናቶችን አስተዋወቀቻት። ከእነሱ መካከል አንዷ የሆነችው ክርስቲን በጥናቷ በጣም ደስተኛ ከመሆኗ የተነሳ በሳምንት ሁለቴ እንድታስጠናት ሜሪን ጠየቀቻት። ሜሪ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የሚፈልጉ ሌሎች ሰዎችን ታውቅ እንደሆነ ስትጠይቃት ክሪስቲን “አዎ፣ ጓደኞቼን አስተዋውቅሻለሁ” አለቻት። በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ክርስቲን ለሜሪ ማጥናት የሚፈልጉ አራት ጓደኞቿን አስተዋወቀቻት። ከጊዜ በኋላ ሌሎች ጓደኞቿንም አስተዋወቀቻት፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ሌሎች ተጨማሪ ጓደኞቻቸውን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ጋበዙ።

ክርስቲን በፊሊፒንስ ያሉ ቤተሰቦቿም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማሩ ፈለገች። ስለዚህ ልጇን አንድሪያን አነጋገረቻት። መጀመሪያ ላይ አንድሪያ ‘የይሖዋ ምሥክሮች መናፍቃን እንደሆኑ፣ በኢየሱስ እንደማያምኑና ብሉይ ኪዳንን ብቻ እንደሚጠቀሙ’ አስባ ነበር። አንዴ ብቻ ካጠናች በኋላ ግን ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የነበራት አመለካከት የተሳሳተ እንደሆነ ተገነዘበች። በምታጠናበት ጊዜ “መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ካለማ ትክክል መሆን አለበት!” በማለት ትናገር ነበር።

ከጊዜ በኋላ አንድሪያ ሜሪን ማጥናት ከሚፈልጉ ሁለት ጓደኞቿና ከሥራ ባልደረባዋ ጋር አስተዋወቀቻት። በተጨማሪም ሜሪ በወቅቱ ባታውቅም ዓይነ ስውር የሆነችው የአንድሪያ አክስት አንጄላ ውይይታቸውን ታዳምጥ ነበር። አንድ ቀን አንጄላ እሷ ራሷ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስለምትፈልግ ከሜሪ ጋር እንድታስተዋውቃት አንድሪያን ጠየቀቻት። አንጄላ በምትማረው ነገር በጣም ተደሰተች። በአንድ ወር ውስጥ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃሏ የያዘች ከመሆኑም በላይ በሳምንት አራቴ ማጥናት እንደምትፈልግ ገለጸች! በአንድሪያ እገዛ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት በስብሰባዎች ላይ በቋሚነት መገኘት ጀመረች።

ሜሪ ክርስቲንን ስታስጠናት የክርስቲን ባለቤት ጆሹዋ ብዙ ጊዜ በአካባቢው እንደሚኖር አስተዋለች። በመሆኑም ሜሪ ጥናቱ ላይ መገኘት ይፈልግ እንደሆነ ጠየቀችው። በዚህ ጊዜ ጆሹዋ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ማዳመጥ አዳምጣለሁ፤ ግን ምንም ጥያቄ እንዳትጠይቂኝ፤ ጥያቄ ከጠየቅሽኝ ተነስቼ እወጣለሁ።” ሆኖም ጥናቱ በጀመረ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ከክርስቲን ይበልጥ ብዙ ጥያቄዎችን የጠየቀ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱን መቀጠል እንደሚፈልግ ተናገረ።

ሜሪ ያቀረበችው ቀላል ጥያቄ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለማስጀመር አስችሏታል። አንዳንዶቹ ጥናቶቿ ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ጥናት እንዲቀጥሉ ሁኔታዎችን አመቻቸች። ሜሪ በአጠቃላይ በአራት አገሮች የሚኖሩ 28 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን አስጀምራለች።

በተሞክሮው መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰችው ጃስሚን ሚያዝያ 2021 ተጠመቀች። ክርስቲን ደግሞ ግንቦት 2022 የተጠመቀች ሲሆን ከቤተሰቦቿ ጋር አብራ ለመሆን ስትል ወደ ፊሊፒንስ ተመልሳለች። ክርስቲን ከሜሪ ጋር ያስተዋወቀቻቸው ሌሎች ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም ተጠምቀዋል። አንጄላ ከጥቂት ወራት በኋላ የተጠመቀች ከመሆኑም ሌላ በአሁኑ ጊዜ በዘወትር አቅኚነት እያገለገለች ነው። የክርስቲን ባለቤት ጆሹዋ፣ ልጃቸው አንድሪያ እንዲሁም ሌሎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ጥሩ እድገት እያደረጉ ነው።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ምሥራቹ በቤተሰብ አባላትና በጓደኛሞች መካከል በፍጥነት ተስፋፍቶ ነበር። (ዮሐ. 1:41, 42ሀ፤ ሥራ 10:24, 27, 48፤ 16:25-33) ታዲያ እናንተስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁንና ፍላጎት ያሳዩ ሌሎች ሰዎችን “መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የሚፈልግ ሌላ ሰው ታውቃላችሁ?” ብላችሁ ለምን አትጠይቋቸውም? ማናችንም ልንጠይቅ በምንችለው በዚህ ቀላል ጥያቄ አማካኝነት ምን ያህል ሰዎች ጥናት ይጀምሩ እንደሆነ ማን ያውቃል?

a ስሞቹ ተቀይረዋል