በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

“ፈጽሞ ብቻዬን ሆኜ አላውቅም”

“ፈጽሞ ብቻዬን ሆኜ አላውቅም”

በሕይወታችን ውስጥ ብቸኝነት እንዲሰማን የሚያደርጉ ብዙ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ፣ አዲስ አካባቢ ስንሄድ ወይም ከሌሎች ሰዎች ርቀን ስንኖር ብቸኝነት ሊሰማን ይችላል። እኔም እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች አጋጥመውኛል። ያም ቢሆን፣ ሕይወቴን መለስ ብዬ ሳስብ መቼም ቢሆን ብቻዬን ሆኜ እንደማላውቅ ይሰማኛል። እዚህ መደምደሚያ ላይ እንድደርስ ያደረገኝ ምን እንደሆነ ልንገራችሁ።

ወላጆቼ የተዉልኝ ምሳሌ

አባዬና እማዬ አጥባቂ ካቶሊኮች ነበሩ። ሆኖም የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሲማሩ ሁለቱም ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። አባዬ የኢየሱስን ምስሎች መቅረጹን አቆመ። ከዚህ ይልቅ የአናጺነት ሙያውን የቤታችንን ምድር ቤት የስብሰባ አዳራሽ ለማድረግ ተጠቀመበት። የፊሊፒንስ ዋና ከተማ በሆነችው በማኒላ አቅራቢያ በሚገኘው በሳን ኋን ዴል ሞንቴ የመጀመሪያው የስብሰባ አዳራሽ የተሠራው በዚህ መልኩ ነው።

ከወላጆቼና ከሌሎቹ የቤተሰቤ አባላት ጋር

ወላጆቼ ለአራት ታላላቅ ወንድሞቼና ለሦስት ታላላቅ እህቶቼ ግሩም መንፈሳዊ ትምህርት ይሰጧቸው ነበር። እኔም በ1952 ከተወለድኩ በኋላ ይህን መንፈሳዊ ትምህርት አስተምረውኛል። እያደግኩ ስሄድ አባቴ በየቀኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ አንድ ምዕራፍ እንዳነብ አበረታታኝ፤ በተጨማሪም የተለያዩ ቲኦክራሲያዊ ጽሑፎችን አስጠንቶኛል። አልፎ አልፎ ወላጆቼ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችንና የቅርንጫፍ ቢሮ ተወካዮችን ቤታችን ያሳርፉ ነበር። እነዚህ ወንድሞች የሚነግሩን ተሞክሮዎች ለቤተሰባችን የደስታና የብርታት ምንጭ ሆነውልናል፤ በሕይወታችን ውስጥ ለይሖዋ አገልግሎት ቅድሚያ እንድንሰጥም አነሳስተውናል።

ወላጆቼ ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ረገድ ግሩም አርዓያ ሆነውልኛል። ውዷ እናቴ ታማ ከሞተች በኋላ እኔና አባዬ በ1971 አብረን በአቅኚነት ማገልገል ጀመርን። ሆኖም በ1973 የ20 ዓመት ወጣት ሳለሁ አባቴ ሞተ። ሁለቱንም ወላጆቼን ማጣቴ የባዶነትና የብቸኝነት ስሜት እንዲሰማኝ አድርጓል። ያም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው “አስተማማኝና ጽኑ” ተስፋ እንደ መልሕቅ በመሆን ስሜታዊና መንፈሳዊ ሚዛኔን እንድጠብቅ ረድቶኛል። (ዕብ. 6:19) አባቴ ከሞተ ብዙም ሳይቆይ ልዩ አቅኚ ሆኜ ተሾምኩ። የአገልግሎት ምድቤ በፓላዋን ግዛት የሚገኝ ኮሮን የተባለ ገለልተኛ ደሴት ነበር።

ፈታኝ የአገልግሎት ምድቦች ላይ ብቻዬን ማገልገል

ኮሮን ስሄድ የ21 ዓመት ወጣት ነበርኩ። የከተማ ልጅ እንደመሆኔ መጠን በደሴቱ ላይ ኤሌክትሪክ፣ የቧንቧ ውኃ እንዲሁም መኪናና ሞተር ብስክሌት እምብዛም እንደሌለ ስመለከት በጣም ተገረምኩ። በዚያ የተወሰኑ ወንድሞች ቢኖሩም አብሮኝ የሚያገለግል አቅኚ ስላልነበረ አንዳንድ ጊዜ የምሰብከው ብቻዬን ነበር። በመጀመሪያው ወር ቤተሰቦቼና ጓደኞቼ በጣም ይናፍቁኝ ነበር። ምሽት ላይ በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ እያየሁ አለቅሳለሁ። የአገልግሎት ምድቤን ትቼ ወደ ቤት ለመመለስ ተፈትኜ ነበር።

ብቻዬን ባሳለፍኳቸው በእነዚያ ጊዜያት የልቤን አውጥቼ ወደ ይሖዋ እጸልይ ነበር። ከመጽሐፍ ቅዱስና ከጽሑፎቻችን ላይ ያነበብኳቸውን አበረታች ሐሳቦችም አስታውሳለሁ። መዝሙር 19:14 ብዙ ጊዜ ትዝ ይለኝ ነበር። ይሖዋ እሱን ስለሚያስደስቱት ነገሮች፣ ለምሳሌ ስለ ሥራዎቹና ስለ ባሕርያቱ ካሰላሰልኩ “ዓለቴና አዳኜ” እንደሚሆንልኝ ተገነዘብኩ። “ፈጽሞ ብቻህን አይደለህም” a የሚለው የመጠበቂያ ግንብ ርዕስም በእጅጉ ረድቶኛል። በተደጋጋሚ አንብቤዋለሁ። ይህ ሁኔታ ብቻዬን ከይሖዋ ጋር ጊዜ የማሳልፍበት አጋጣሚ ፈጥሮልኛል ሊባል ይችላል። የምጸልይበት፣ የማጠናበትና የማሰላስልበት ጊዜ አግኝቻለሁ።

ኮሮን ከሄድኩ ብዙም ሳይቆይ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኜ ተሾምኩ። በዚያ የነበርኩት ሽማግሌ እኔ ብቻ ስለሆንኩ ሳምንታዊውን ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት፣ የአገልግሎት ስብሰባ፣ የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት እንዲሁም የመጠበቂያ ግንብ ጥናት መምራት ጀመርኩ። የሕዝብ ንግግርም በየሳምንቱ አቀርባለሁ። ከዚያ ወዲህ በብቸኝነት ስሜት ለመዋጥ የሚያስችል ጊዜ እንኳ አልነበረኝም!

በኮሮን መስኩ ፍሬያማ ነበር። አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼ ውሎ አድሮ ተጠመቁ። ሆኖም አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎችም አጋጥመውኛል። አንዳንድ ጊዜ ወደ አገልግሎት ክልሌ ለመድረስ ግማሽ ቀን ያህል በእግሬ መጓዝ ያስፈልገኛል። እዚያ ከደረስኩ በኋላ ደግሞ የት እንደማድር አላውቅም። በተጨማሪም የጉባኤው ክልል ብዙ ትናንሽ ደሴቶችን ያካትት ነበር። ብዙ ጊዜ ወደ እነዚህ ደሴቶች ለመድረስ በማዕበል በሚናወጠው ባሕር ላይ በሞተር ጀልባ መጓዝ አስፈልጎኛል። ዋና ደግሞ አልችልም! እነዚህ ሁሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ይሖዋ ጠብቆኛል፤ እንዲሁም አጽንቶኛል። በኋላ እንዳስተዋልኩት፣ ለካ ይሖዋ በቀጣዩ የአገልግሎት ምድቤ ለሚያጋጥሙኝ ይበልጥ አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎች እያዘጋጀኝ ነበር።

ፓፑዋ ኒው ጊኒ

በ1978 ከአውስትራሊያ በስተ ሰሜን በምትገኘው በፓፑዋ ኒው ጊኒ እንዳገለግል ተመደብኩ። ፓፑዋ ኒው ጊኒ ከስፔን ጋር ተቀራራቢ ስፋት ያላት በተራሮች የተሞላች አገር ነች። የአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር ሦስት ሚሊዮን ገደማ ቢሆንም ከ800 በላይ ቋንቋዎች እንደሚነገሩ ሳውቅ በጣም ተደነቅኩ። ደግነቱ አብዛኞቹ ሰዎች በተለምዶ ቶክ ፒሲን ተብሎ የሚታወቀውን ሜላኔዥያን ፒጅን መናገር ይችላሉ።

መጀመሪያ ላይ በዋና ከተማዋ በፖርት ሞርዝቢ በሚገኝ እንግሊዝኛ ጉባኤ ውስጥ ለጊዜው እንዳገለግል ተመደብኩ። በኋላ ግን በቶክ ፒሲን ወደሚመራ ጉባኤ ተዛውሬ ቋንቋውን መማር ጀመርኩ። ክፍል ውስጥ የምማረውን ነገር አገልግሎት ላይ እጠቀምበታለሁ። ይህም ቋንቋውን በፍጥነት እንድማር ረድቶኛል። ብዙም ሳይቆይ በቶክ ፒሲን ቋንቋ የሕዝብ ንግግር ማቅረብ ቻልኩ። ፓፑዋ ኒው ጊኒ ከደረስኩ አንድ ዓመት እንኳ ሳይሞላኝ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ሰፊ በሆኑ የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙትን በቶክ ፒሲን የሚመሩ ጉባኤዎች እንድጎበኝ ስጠየቅ ምን ያህል ደንግጬ እንደሚሆን መገመት ትችላላችሁ።

ጉባኤዎቹ የሚገኙት ተራርቀው ስለሆነ ብዙ የወረዳ ስብሰባዎችን ማደራጀትና ረጅም ርቀት መጓዝ ነበረብኝ። መጀመሪያ ላይ አገሩም፣ ቋንቋውም፣ ባሕሉም አዲስ ስለሆነብኝ ብቸኝነት ተሰምቶኝ ነበር። አገሩ ተራራማ ስለሆነ ከአንዱ ጉባኤ ወደ ሌላው ጉባኤ ስሄድ በመኪና መጓዝ አልችልም። ስለዚህ በየሳምንቱ ማለት ይቻላል በአውሮፕላን እጓዝ ነበር። አሮጌ በሆኑት ትናንሽ አውሮፕላኖች ውስጥ ብቸኛ ተሳፋሪ የምሆንበት ጊዜ አለ። እነዚህ ጉዞዎች በጀልባ የመጓዝን ያህል ያስፈሩኝ ነበር!

ስልክ ያላቸው ብዙ ሰዎች ስላልነበሩ ለጉባኤዎቹ መልእክት የምልከው በደብዳቤ ነበር። ብዙውን ጊዜ ደብዳቤው ከመድረሱ በፊት እኔ ቀድሜ ስለምደርስ አስፋፊዎቹን ፈልጌ የማገኘው የአካባቢውን ሰዎች ጠይቄ ነበር። ሆኖም ወንድሞችን ባገኘኋቸው ቁጥር በከፍተኛ አድናቆት ስለሚቀበሉኝ ይህን ሁሉ መሥዋዕት የምከፍለው ለምን እንደሆነ አስታውሳለሁ። የይሖዋን ድጋፍ በብዙ መንገዶች ማየቴ ከእሱ ጋር ያለኝን ወዳጅነት በእጅጉ አጠናክሮታል።

ቡገንቨል የተባለን አንድ ደሴት ለመጀመሪያ ጊዜ ስጎበኝ አንድ ባልና ሚስት ፈገግ ብለው ወደ እኔ መጡና “ታስታውሰናለህ?” አሉኝ። ፖርት ሞርዝቢ እንደመጣሁ ለእነዚህ ባልና ሚስት መሥክሬላቸው እንደነበር አስታወስኩ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ካስጀመርኳቸው በኋላ የአካባቢው ተወላጅ ለሆነ አንድ ወንድም አስረከብኳቸው። በዚህ ወቅት ሁለቱም ተጠምቀው ነበር! በፓፑዋ ኒው ጊኒ ባሳለፍኳቸው ሦስት ዓመታት ውስጥ ካገኘኋቸው በርካታ በረከቶች አንዱ ይህ ነው።

በሥራ የተጠመደው ትንሹ ቤተሰባችን

ከአደል ጋር

በ1978 ኮሮንን ለቅቄ ከመውጣቴ በፊት አደል ከተባለች ደስ የምትልና የራሷን ጥቅም መሥዋዕት የምታደርግ እህት ጋር ተዋውቄ ነበር። ሳሙኤልና ሸርሊ የተባሉ ሁለት ልጆቿን እያሳደገች በዘወትር አቅኚነት ታገለግል ነበር። አረጋዊት እናቷንም ትንከባከባለች። ግንቦት 1981 ወደ ፊሊፒንስ ተመልሼ ከአደል ጋር ተጋባን። ከተጋባን በኋላ በዘወትር አቅኚነት እያገለገልን ቤተሰባችንን አብረን መንከባከብ ጀመርን።

ከአደል እንዲሁም ከልጆቻችን ከሳሙኤልና ከሸርሊ ጋር በፓላዋን ስናገለግል

ቤተሰብ የመሠረትኩ ቢሆንም በ1983 በድጋሚ ልዩ አቅኚ ሆኜ ተሾምኩ። የአገልግሎት ምድቤ በፓላዋን ግዛት የሚገኘው ሊናፓካን ደሴት ነበር። መላው ቤተሰባችን ምንም የይሖዋ ምሥክር ወደሌለበት ወደዚህ ሩቅ ቦታ ተዛወረ። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ የአደል እናት አረፈች። ሆኖም በአገልግሎት መጠመዳችን ሐዘናችንን ለመቋቋም ረድቶናል። ሊናፓካን ውስጥ እድገት የሚያደርጉ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን አገኘን። በመሆኑም ብዙም ሳይቆይ የስብሰባ አዳራሽ ስላስፈለገን አነስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ገነባን። እዚያ በሄድን በሦስት ዓመት ውስጥ 110 ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ በመገኘታቸው በጣም ተደሰትን። ብዙዎቹ ያንን አካባቢ ለቀን ከሄድን በኋላ እድገት አድርገው ተጠምቀዋል።

በ1986 በኩሊዮን ደሴት እንዳገለግል ተመደብኩ። እዚያም ብዙ የሥጋ ደዌ በሽተኞች ይኖሩ ነበር። በኋላ ደግሞ አደልም ልዩ አቅኚ ሆና ተሾመች። መጀመሪያ ላይ በሥጋ ደዌ የተነሳ ሰውነታቸው የተጎዳ ሰዎችን ማነጋገር አስፈርቶን ነበር። ሆኖም በአካባቢው ያሉት አስፋፊዎች፣ ታማሚዎቹ ሕክምና ስለወሰዱ በሽታው የመተላለፉ አጋጣሚ ጠባብ እንደሆነ በመንገር አጽናኑን። ከሥጋ ደዌ ታማሚዎቹ መካከል አንዳንዶቹ በአንዲት እህት ቤት በምናደርገው ስብሰባ ላይ ይገኙ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ለእነሱ መስበክ እየቀለለን መጣ። በአምላክም ሆነ በሰዎች ዘንድ እንደማይፈለጉ ለሚሰማቸው ለእነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ተስፋ መንገር በጣም አስደሳች ሆኖ አግኝተነዋል። አሁን በከባድ ሕመም እየተሠቃዩ ቢሆንም ወደፊት ፍጹም ጤንነት እንደሚያገኙ ሲያውቁ የሚሰማቸውን ደስታ ማየት ልዩ ስሜት ይፈጥራል።—ሉቃስ 5:12, 13

ልጆቻችን በኩሊዮን የጀመርነውን አዲስ ሕይወት መልመድ የቻሉት እንዴት ነው? እኔና አደል ልጆቻችን ጥሩ ጓደኞች እንዲያገኙ ስንል በኮሮን የሚኖሩ ሁለት ወጣት እህቶችን አብረውን እንዲያገለግሉ ጋበዝናቸው። ሳሙኤል፣ ሸርሊና ሁለቱ ወጣት እህቶች ብዙ ልጆችን በማስጠናት አስደሳች የአገልግሎት ጊዜ አሳልፈዋል። እኔና አደል ደግሞ ወላጆችን እናስጠናለን። እንዲያውም በአንድ ወቅት 11 ቤተሰቦችን እናስጠና ነበር። ከአጭር ጊዜ በኋላ፣ እድገት የሚያደርጉ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ስላገኘን አዲስ ጉባኤ ማቋቋም ቻልን!

መጀመሪያ ላይ በአካባቢው ያለሁት ብቸኛው የጉባኤ ሽማግሌ እኔ ነበርኩ። ስለዚህ ቅርንጫፍ ቢሮው በኩሊዮን ላሉት ስምንት አስፋፊዎች እንዲሁም ማሪሊ በተባለችው መንደር ለሚኖሩት ዘጠኝ አስፋፊዎች ሳምንታዊ ስብሰባዎችን እንድመራ ጠየቀኝ። ማሪሊ ለመድረስ በጀልባ ለሦስት ሰዓት ያህል መጓዝ ይጠይቃል። እዚያ ስብሰባ ካደረግን በኋላ በቤተሰብ አንድ ላይ ለብዙ ሰዓታት ተራራማውን አካባቢ አቋርጠን በመሄድ ሃልሲ በተባለ መንደር ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እንመራለን።

ውሎ አድሮ በማሪሊና በሃልሲ ከፍተኛ እድገት ስለተገኘ በሁለቱም ቦታዎች የስብሰባ አዳራሾችን ገነባን። እንደ ሊናፓካን ሁሉ እዚህም አብዛኛውን የግንባታ ቁሳቁስ ያዘጋጁትም ሆነ የግንባታ ሥራውን ያከናወኑት ወንድሞችና ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ናቸው። በማሪሊ የገነባነው የስብሰባ አዳራሽ 200 ሰዎችን መያዝ የሚችል ከመሆኑም ሌላ እንደ አስፈላጊነቱ መስፋት የሚችል ስለሆነ ትላልቅ ስብሰባዎችንም እዚያ ማካሄድ ችለናል።

ሐዘንና ብቸኝነት ከዚያም ደስታን መልሶ ማግኘት

ልጆቻችን ካደጉ በኋላ በ1993 እኔና አደል ፊሊፒንስ ውስጥ በወረዳ ሥራ መካፈል ጀመርን። ከዚያም በ2000 በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት በመካፈል ለአስተማሪነት ሠለጠንኩ። ይህን ሥራ ለማከናወን ብቃቱ እንዳለኝ አልተሰማኝም ነበር። ሆኖም አደል ምንጊዜም ታበረታታኛለች። ይሖዋ ይህን አዲስ ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስፈልገኝን ብርታት እንደሚሰጠኝ አስታወሰችኝ። (ፊልጵ. 4:13) አደል ይህን ያለችኝ ከራሷ ተሞክሮ በመነሳት ነው። ምክንያቱም ከጤና ችግሮች ጋር ብትታገልም አገልግሎቷን እያከናወነች ነበር።

በ2006 አስተማሪ ሆኜ እያገለገልኩ ሳለሁ አደል ፓርኪንሰንስ የሚባል የነርቭ በሽታ እንዳለባት አወቅን። በዚህ ጊዜ በጣም ደነገጥን! የአገልግሎት ምድቤን አቁሜ እሷን ብንከባከብ እንደሚሻል ስነግራት አደል እንዲህ አለችኝ፦ “እባክህ ሊረዳኝ የሚችል ሐኪም ፈልግልኝ። ይሖዋ በአገልግሎታችን እንድንቀጥል እንደሚረዳን እርግጠኛ ነኝ።” አደል ለቀጣዮቹ ስድስት ዓመታት ምንም ሳታጉረመርም አገልግሎቷን ማከናወኗን ቀጥላለች። መራመድ ሲያቅታት ዊልቼሯ ላይ ቁጭ ብላ ታገለግል ነበር። መናገር ሲያቅታት ደግሞ በስብሰባዎች ላይ አንድ ወይም ሁለት ቃል ብቻ በመናገር ሐሳብ ትሰጣለች። አደል በ2013 ሕይወቷ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በጽናት ረገድ ለተወችው ግሩም ምሳሌ የአድናቆት መልእክቶች ይደርሷት ነበር። ታማኝና አፍቃሪ ከሆነችው ባለቤቴ ከአደል ጋር ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት ከኖርኩ በኋላ እሷን ሳጣ የሐዘንና የብቸኝነት ስሜት እንደ አዲስ አገረሸብኝ።

አደል በአገልግሎት ምድቤ እንድቀጥል ትፈልግ ስለነበር በአገልግሎቴ ቀጠልኩ። ራሴን በሥራ ማስጠመዴ የብቸኝነት ስሜትን ለመቋቋም ረድቶኛል። ከ2014 እስከ 2017 ባሉት ዓመታት፣ በሥራችን ላይ ገደብ ተጥሎ በነበረባቸው አገሮች ውስጥ የሚገኙ በታጋሎግ ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎችን እንድጎበኝ ተመደብኩ። ከዚያ በኋላ ደግሞ በታይዋን፣ በዩናይትድ ስቴትስና በካናዳ የሚገኙ በታጋሎግ ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎችን ጎብኝቻለሁ። በ2019 ሕንድና ታይላንድ ውስጥ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በተካሄዱ የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤቶች ላይ አስተምሬያለሁ። እነዚህ የአገልግሎት ምድቦች ታላቅ ደስታ አስገኝተውልኛል። በሕይወቴ ውስጥ ከሁሉ በላይ ደስተኛ የምሆነው በይሖዋ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ስጠመድ ነው።

የሚያስፈልገኝን እርዳታ አጥቼ አላውቅም

በሁሉም ምድቦቼ ላይ ከማገኛቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር በጣም እቀራረባለሁ። ስለዚህ ከእነሱ ተለይቶ መሄድ ቀላል አይደለም። እንዲህ ባሉት ጊዜያት ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መታመን እንዳለብኝ ተምሬያለሁ። የይሖዋን ድጋፍ በተደጋጋሚ አይቻለሁ። ይህም የሚያጋጥመኝን ማንኛውንም ለውጥ በሙሉ ልቤ እንድቀበል ረድቶኛል። በአሁኑ ወቅት ፊሊፒንስ ውስጥ ልዩ አቅኚ ሆኜ እያገለገልኩ ነው። ከአዲሱ ጉባኤዬ ጋር በደንብ ተላምጃለሁ፤ ጉባኤው የሚያስብልኝና የሚንከባከበኝ ቤተሰብ ሆኖልኛል። ሳሙኤልና ሸርሊ የእናታቸውን የእምነት ምሳሌ እየተከተሉ እንደሆነ ማየቴም በጣም ያስደስተኛል።—3 ዮሐ. 4

ጉባኤው አሳቢ ቤተሰብ ሆኖልኛል

አዎ፣ ውዷ ባለቤቴ በከባድ ሕመም ተሠቃይታ ስትሞት ማየትን ጨምሮ በሕይወቴ ውስጥ ብዙ መከራዎችን አሳልፌያለሁ። ከተለያዩ አዳዲስ ሁኔታዎች ጋር መላመድም አስፈልጎኛል። ያም ቢሆን ይሖዋ “ከእያንዳንዳችን የራቀ” እንዳልሆነ ተመልክቻለሁ። (ሥራ 17:27) የይሖዋ እጅ ‘አጭር አይደለም’፤ በገለልተኛ አካባቢ የሚኖሩትን ጨምሮ አገልጋዮቹን ምንጊዜም መደገፍና ማበረታታት ይችላል። (ኢሳ. 59:1) ዓለቴ ይሖዋ በሕይወቴ ሁሉ ከጎኔ አልተለየም፤ ለዚህም በጣም አመስጋኝ ነኝ። ፈጽሞ ብቻዬን ሆኜ አላውቅም።

a የመስከረም 1, 1972 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 521-527⁠ን ተመልከት።