በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 3

በአምላክህ በይሖዋ ፊት ውድ ነህ!

በአምላክህ በይሖዋ ፊት ውድ ነህ!

“መንፈሳችን ተደቁሶ በነበረበት ጊዜ አስታወሰን።”—መዝ. 136:23

መዝሙር 33 ሸክማችሁን በይሖዋ ላይ ጣሉ

ማስተዋወቂያ *

1-2. ብዙ የይሖዋ አገልጋዮች ምን ዓይነት ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል? ይህስ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድርባቸው ይችላል?

እስቲ ከዚህ ቀጥሎ የተጠቀሱትን ሦስት ሁኔታዎች ለማሰብ ሞክር፦ አንድ ወጣት ወንድም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚሄድ ከባድ ሕመም እንዳለበት ተነገረው። በጉልምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ ታታሪ ወንድም ከሥራው የተባረረ ሲሆን ሌላ ሥራ ለማግኘት የሚያደርገው ጥረትም ሊሳካለት አልቻለም። አንዲት በዕድሜ የገፋች ታማኝ እህት፣ በይሖዋ አገልግሎት ማከናወን የምትችለው ነገር ውስን ሆኗል።

2 አንተም ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ ከዚህ በኋላ ምንም እንደማትጠቅም ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች ደስታህን ሊቀንሱብህ፣ ለራስህ አክብሮት እንድታጣ ሊያደርጉህ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያለህን ግንኙነት ሊያበላሹብህ ይችላሉ።

3. ሰይጣንም ሆነ በእሱ ቁጥጥር ሥር ያሉ ሰዎች ለሰው ሕይወት ምን አመለካከት አላቸው?

3 ይህ ዓለም ሰይጣን ለሰው ሕይወት ያለውን አመለካከት ያንጸባርቃል። ሰይጣን ለሰው ልጆች አክብሮት ኖሮት አያውቅም። ሰይጣን የአምላክን ትእዛዝ መጣስ ሞት እንደሚያስከትል በሚገባ እያወቀ ለሔዋን እንዲህ ብታደርግ ነፃነት እንደምታገኝ ነግሯታል፤ ይህ እንዴት ያለ ጭካኔ ነው! የዚህ ዓለም የንግድ፣ የፖለቲካና የሃይማኖት ሥርዓት ሁልጊዜም ቢሆን በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ነው። ከዚህ አንጻር በርካታ የንግድ ሰዎችና ፖለቲከኞች እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች ልክ እንደ ሰይጣን፣ በሚያዋርድና ክብርን ዝቅ በሚያደርግ መንገድ ሰዎችን የሚይዙ መሆናቸው የሚያስገርም አይደለም።

4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

4 ከዚህ በተቃራኒ ይሖዋ ለራሳችን አክብሮት እንዲኖረን ይፈልጋል፤ ዋጋ እንደሌለን እንዲሰማን የሚያደርጉ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም ይደግፈናል። (መዝ. 136:23፤ ሮም 12:3) ይህ ርዕስ ይሖዋ በሚከተሉት ሁኔታዎች ውስጥ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ያብራራል፦ (1) የጤና እክል ሲያጋጥመን፣ (2) የኢኮኖሚ ችግር ሲያጋጥመን እንዲሁም (3) በዕድሜ መግፋት የተነሳ በይሖዋ አገልግሎት ምንም ጠቃሚ ነገር ማከናወን እንደማንችል ሲሰማን። በመጀመሪያ ግን እያንዳንዳችን በይሖዋ ፊት ውድ መሆናችንን እንድንተማመን የሚያደርጉንን ምክንያቶች እስቲ እንመልከት።

በይሖዋ ፊት ውድ ነን

5. የሰው ልጆች በይሖዋ ፊት ውድ እንደሆኑ እንድትተማመን የሚያደርግህ ማስረጃ ምንድን ነው?

5 የተሠራነው ከምድር አፈር ቢሆንም ከአፈር እጅግ የላቀ ዋጋ አለን። (ዘፍ. 2:7) በይሖዋ ፊት ውድ እንደሆንን እንድንተማመን የሚያደርጉንን አንዳንድ ምክንያቶች እስቲ እንመልከት። ይሖዋ የሰው ልጆችን የፈጠረው የእሱን ባሕርያት ማንጸባረቅ እንዲችሉ አድርጎ ነው። (ዘፍ. 1:27) ይህም በምድር ላይ ካሉት ሌሎች ፍጥረታቱ የበለጠ ቦታ እንደሰጠን የሚያሳይ ነው፤ ምድርንና እንስሳትን እንዲቆጣጠሩ ለሰው ልጆች ሥልጣን ሰጥቷቸዋል።—መዝ. 8:4-8

6. ይሖዋ ፍጹም ያልሆኑ የሰው ልጆችን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት የሚያሳየው ሌላው ማስረጃ ምንድን ነው?

6 አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላም ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለው አክብሮት አልቀነሰም። ይሖዋ እኛን በጣም ከፍ አድርጎ ከመመልከቱ የተነሳ፣ የሚወደውን ልጁን ኢየሱስን ለኃጢአታችን ቤዛ እንዲሆን ሰጥቶናል። (1 ዮሐ. 4:9, 10) ቤዛው ያስገኘውን ጥቅም መሠረት በማድረግ ይሖዋ በአዳም ኃጢአት ምክንያት የሞቱ ‘ጻድቃንንም ሆነ ዓመፀኞችን’ ወደፊት ያስነሳቸዋል። (ሥራ 24:15) የጤንነታችን ሁኔታ፣ የኢኮኖሚ አቅማችን ወይም ዕድሜያችን ምንም ይሁን ምን በእሱ ፊት ውድ እንደሆንን የአምላክ ቃል ያረጋግጥልናል።—ሥራ 10:34, 35

7. የይሖዋ አገልጋዮች በእሱ ፊት ውድ እንደሆኑ እንዲተማመኑ የሚያደርጓቸው ምን ተጨማሪ ምክንያቶች አሏቸው?

7 ይሖዋ ውድ አድርጎ እንደሚመለከተን የሚያሳዩ ሌሎች ማስረጃዎችም አሉ። ወደ ራሱ የሳበን ከመሆኑም ሌላ ምሥራቹን ስንሰማ የሰጠነውን ምላሽ በትኩረት ተመልክቷል። (ዮሐ. 6:44) ወደ እሱ መቅረብ ስንጀምር እሱም ወደ እኛ ይበልጥ ቀርቧል። (ያዕ. 4:8) ከዚህም ሌላ ይሖዋ ውድ እንደሆንን አድርጎ ስለሚመለከተን ጊዜ መድቦ ያስተምረናል። ይሖዋ አሁን ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆንን እንዲሁም ለውጥ አድርገን ምን ዓይነት ሰው መሆን እንደምንችል ያውቃል። ደግሞም ስለሚወደን ተግሣጽ ይሰጠናል። (ምሳሌ 3:11, 12) ይህ ሁሉ በይሖዋ ፊት ውድ እንደሆንን የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ነው!

8. በመዝሙር 18:27-29 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ስለሚያጋጥሙን ችግሮች ትክክለኛውን አመለካከት እንድንይዝ የሚረዳን እንዴት ነው?

8 አንዳንድ ሰዎች ንጉሥ ዳዊትን የማይረባ ሰው አድርገው የቆጠሩት ቢሆንም ዳዊት፣ ይሖዋ እንደሚወደውና እንደሚደግፈው ያውቅ ነበር። ይህን ማወቁም ስላለበት ሁኔታ ትክክለኛ አመለካከት እንዲይዝ ረድቶታል። (2 ሳሙ. 16:5-7) እኛም መንፈሳችን ሲደቆስ ወይም ችግሮች ሲያጋጥሙን ያለንበትን ሁኔታ በተለየ መንገድ መመልከት እንዲሁም ማንኛውንም እንቅፋት መሻገር እንድንችል ይሖዋ ይረዳናል። (መዝሙር 18:27-29ን አንብብ።) የይሖዋ እርዳታ እስካልተለየን ድረስ እሱን በደስታ እንዳናገለግል እንቅፋት ሊሆንብን የሚችል ነገር የለም። (ሮም 8:31) ይሖዋ እንደሚወደንና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተን ማስታወሳችን በጣም አስፈላጊ የሆነባቸውን ሦስት ሁኔታዎች እስቲ እንመልከት።

የጤና እክል ሲያጋጥመን

በመንፈስ መሪነት የተጻፉትን የይሖዋ ሐሳቦች ማንበባችን በሕመም ምክንያት የተፈጠረብንን አሉታዊ ስሜት ለማሸነፍ ይረዳናል (ከአንቀጽ 9-12⁠ን ተመልከት)

9. ሕመም ስለ ራሳችን ባለን ስሜት ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

9 ሕመም፣ ስሜታችንን ሊጎዳውና ለማንም እንደማንጠቅም እንዲሰማን ሊያደርገን ይችላል። ሰዎች አቅማችን ውስን መሆኑን መመልከታቸው አሊያም የሌሎች እርዳታ የሚያስፈልገን መሆኑ ያሸማቅቀን ይሆናል። ሌሎች ስለ ሕመማችን ባያውቁ እንኳ የቀድሟችንን ያህል ማድረግ እንደማንችል ማወቃችን ስለ ራሳችን መጥፎ እንዲሰማን ሊያደርግ ይችላል። እንዲህ ባለው አስጨናቂ ጊዜ ይሖዋ መንፈሳችንን ያነቃቃዋል። እንዴት?

10. በምሳሌ 12:25 መሠረት በምንታመምበት ወቅት ምን ይረዳናል?

10 በምንታመምበት ወቅት፣ “መልካም ቃል” መንፈሳችንን ሊያድስልን ይችላል። (ምሳሌ 12:25ን አንብብ።) ይሖዋ ብንታመምም እንኳ በእሱ ፊት ውድ እንደሆንን የሚያስታውሱን በርካታ መልካም ቃሎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍሩልን አድርጓል። (መዝ. 31:19፤ 41:3) በመንፈስ መሪነት የተጻፉትን እነዚህን ሐሳቦች ደግመን ደጋግመን ስናነብ ይሖዋ በሕመማችን ምክንያት የሚሰማንን አሉታዊ ስሜት እንድናሸንፍ ይረዳናል።

11. ይሖዋ አንድን ወንድም የረዳው እንዴት ነው?

11 ሆርሄ ያጋጠመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሆርሄ ወጣት ሳለ አቅም የሚያሳጣና በፍጥነት እየተባባሰ የሚሄድ ሕመም ያዘው፤ ይህም ዋጋ ቢስ እንደሆነ እንዲሰማው አድርጎት ነበር። ሆርሄ እንዲህ ብሏል፦ “ሕመሙ ፈጽሞ ያልጠበቅኩት ሥቃይ ያስከተለብኝ ከመሆኑም ሌላ የሰዎችን ትኩረት መሳቡ እንድሸማቀቅ አድርጎኝ ነበር። ሕመሙ እየተባባሰ ሲሄድ፣ በሕይወቴ ውስጥ ስለሚያስከትለው ለውጥ ማሰብ ጀመርኩ። ይህን ሳስብ ቅስሜ ተሰበረ፤ ስለዚህ እንዲረዳኝ ይሖዋን ተማጸንኩት።” ታዲያ ይሖዋ ሆርሄን የረዳው እንዴት ነው? እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ነገር ላይ ትኩረት ለማድረግ እቸገር ነበር፤ በመሆኑም በአንድ ጊዜ ረጅም ነገር ለማንበብ ከመሞከር ይልቅ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ያለውን አሳቢነት የሚገልጹ በመዝሙር መጽሐፍ ላይ የሚገኙ ጥቂት ቁጥሮችን እንዳነብ ማበረታቻ ተሰጠኝ። እነዚህን ጥቂት ቁጥሮች በየዕለቱ ደጋግሜ ማንበቤ እንድጽናና ረድቶኛል። ውሎ አድሮም ፊቴ እየፈካ እንደመጣ ሌሎች ሰዎች ማስተዋል ጀመሩ። እንዲያውም የእኔ አዎንታዊ መሆን እንዳበረታታቸው የሚናገሩ ነበሩ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ለጸሎቴ ምላሽ እንደሰጠኝ ተገነዘብኩ! ይሖዋ ለራሴ ባለኝ አመለካከት ላይ ለውጥ እንዳደርግ ረድቶኛል። ብታመምም እንኳ አምላክ ለእኔ ምን አመለካከት እንዳለው በሚገልጹ በቃሉ ውስጥ በሚገኙ ሐሳቦች ላይ ትኩረት ማድረግ ጀመርኩ።”

12. የጤና እክል አጋጥሞህ ከሆነ የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ምን ማድረግ ትችላለህ?

12 የጤና እክል አጋጥሞህ ከሆነ ይሖዋ ያለህበትን ሁኔታ እንደሚያውቅ አትጠራጠር። ስለ ሁኔታው ትክክለኛ አመለካከት ለማዳበር እንዲረዳህ ይሖዋን ለምነው። ከዚያም በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያስቀመጠልህን መልካም ቃላት ለማግኘት ጥረት አድርግ። ይሖዋ አገልጋዮቹን ምን ያህል ውድ አድርጎ እንደሚመለከታቸው በሚገልጹ ጥቅሶች ላይ ትኩረት አድርግ። ይህን ስታደርግ ይሖዋ በታማኝነት ለሚያገለግሉት ሁሉ መልካም እንደሆነ ማስተዋልህ አይቀርም።—መዝ. 84:11

የኢኮኖሚ ችግር ሲያጋጥመን

ይሖዋ የሚያስፈልገንን ለማሟላት ቃል እንደገባ ማስታወሳችን ሥራ አጥተን በምንቸገርበት ወቅት ይረዳናል (ከአንቀጽ 13-15⁠ን ተመልከት)

13. አንድ የቤተሰብ ራስ ሥራውን ማጣቱ ምን እንዲሰማው ሊያደርግ ይችላል?

13 ሁሉም የቤተሰብ ራሶች ቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ነገር ማሟላት ይፈልጋሉ። ይሁንና አንድ ወንድም ምንም ሳያጠፋ ከሥራው ተባረረ እንበል። ይህ ወንድም ሌላ ሥራ ለማግኘት ብዙ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካለትም። ይህ ሁኔታ የዋጋ ቢስነት ስሜት እንዲያድርበት ያደርግ ይሆናል። ታዲያ ይህ ወንድም፣ ይሖዋ በገባው ቃል ላይ ትኩረት ማድረጉ የሚረዳው እንዴት ነው?

14. ይሖዋ ቃሉን እንዲጠብቅ የሚያነሳሱት ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

14 ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን ቃሉን ይጠብቃል። (ኢያሱ 21:45፤ 23:14) እንዲህ ለማድረግ የሚያነሳሱት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። አንደኛ፣ ቃሉን መጠበቅ አለመጠበቁ ስሙን የሚነካ ጉዳይ ነው። ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደሚንከባከባቸው ቃል የገባ ሲሆን ይህን ቃሉን የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት ይሰማዋል። (መዝ. 31:1-3) በተጨማሪም ይሖዋ የቤተሰቡን አባላት ሳይንከባከብ ቢቀር ይህ በጣም ሊያሳዝነን እንደሚችል ያውቃል። ይሖዋ ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት ቃል ገብቷል፤ ደግሞም ይህን ቃሉን እንዳይፈጽም ሊያግደው የሚችል አንዳች ነገር የለም!—ማቴ. 6:30-33፤ 24:45

15. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ምን ችግር አጋጥሟቸው ነበር? (ለ) መዝሙር 37:18, 19 ምን ዋስትና ይሰጣል?

15 ይሖዋ ቃሉን የሚጠብቀው ለምን እንደሆነ ማስታወሳችን፣ የኢኮኖሚ ችግር ሲያጋጥመን እሱ እንደሚረዳን እንድንተማመን ያደርገናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች እንደ ምሳሌ እንመልከት። በኢየሩሳሌም በሚገኘው ጉባኤ ላይ ከባድ ስደት በተነሳበት ወቅት “ከሐዋርያት በስተቀር ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ . . . ተበተኑ።” (ሥራ 8:1) ይህ ምን ሊያስከትልባቸው እንደሚችል እስቲ አስበው፤ እነዚህ ክርስቲያኖች በኢኮኖሚ መቸገራቸው አይቀርም። ቤታቸውንና መተዳደሪያቸውን አጥተው ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን ይሖዋ አልተዋቸውም፤ እነሱም ቢሆን ደስታቸውን አላጡም። (ሥራ 8:4፤ ዕብ. 13:5, 6፤ ያዕ. 1:2, 3) ይሖዋ እነዚያን ታማኝ ክርስቲያኖች ደግፏቸዋል፤ እኛንም ቢሆን ይደግፈናል።መዝሙር 37:18, 19ን አንብብ።

የዕድሜ መግፋት አቅማችንን ሲገድበው

ማድረግ በምንችለው ነገር ላይ ማተኮራችን ዕድሜያችን ቢገፋም ይሖዋ እኛንም ሆነ የምናከናውነውን አገልግሎት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እንድንተማመን ያደርገናል (ከአንቀጽ 16-18⁠ን ተመልከት)

16. ይሖዋ ለእሱ የምናቀርበውን አምልኮ ከፍ አድርጎ ይመለከተው እንደሆነ እንድንጠራጠር የሚያደርገን አንዱ ሁኔታ ምንድን ነው?

16 ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ ለይሖዋ መስጠት የምንችለው ነገር በጣም ጥቂት እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ንጉሥ ዳዊትም ዕድሜው እየገፋ ሲሄድ እንዲህ ዓይነት ስሜት ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። (መዝ. 71:9) ታዲያ ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው?

17. ጄሪ የተባለች እህት ካጋጠማት ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን?

17 ጄሪ የተባለችን እህት ተሞክሮ እስቲ እንመልከት። ጄሪ በስብሰባ አዳራሽ በሚካሄድ የጥገና ሥልጠና ላይ እንድትገኝ ተጋበዘች፤ እሷ ግን መሄድ አልፈለገችም። “አርጅቻለሁ፣ መበለት ነኝ፤ በዚያ ላይ ደግሞ ለይሖዋ አገልግሎት የማውለው ምንም ችሎታ የለኝም። ስለዚህ ምንም አልጠቅምም” ብላ ነበር። ጄሪ ሥልጠናው ከሚሰጥበት ቀን በፊት በነበረው ምሽት ላይ የልቧን አውጥታ ለይሖዋ በጸሎት ነገረችው። በቀጣዩ ቀን ወደ ስብሰባ አዳራሽ የሄደችው በሥልጠናው ላይ መገኘቷ ይጠቅም እንደሆነ እየተጠራጠረች ነበር። በሥልጠናው ላይ አንደኛው ተናጋሪ፣ ከሁሉ የበለጠ አስፈላጊ የሆነው ብቃት ከይሖዋ ለመማር ፈቃደኛ መሆን እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገለጸ። ጄሪ እንዲህ ስትል ታስታውሳለች፦ “‘ይሄማ እኔም ያለኝ ብቃት ነው!’ ብዬ አሰብኩ። ይሖዋ ጸሎቴን እየመለሰልኝ እንደሆነ ስለተገነዘብኩ ማልቀስ ጀመርኩ። ለእሱ ልሰጠው የምችለው ጠቃሚ ነገር እንዳለኝና ሊያስተምረኝ ፈቃደኛ መሆኑን እንዳረጋገጠልኝ ተሰማኝ።” አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ወደ ሥልጠናው የገባሁት ፍርሃት ፍርሃት እያለኝ እንዲሁም የተስፋ መቁረጥና የዋጋ ቢስነት ስሜት እየተሰማኝ ነበር። ከሥልጠናው የወጣሁት ግን ጥርጣሬዬ ተወግዶ፣ ተበረታትቼና ዋጋ እንዳለኝ ተሰምቶኝ ነው!”

18. ዕድሜያችን እየገፋ ቢሄድም ይሖዋ ለእሱ የምናቀርብለትን አምልኮ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያሳየው እንዴት ነው?

18 ዕድሜያችን እየገፋ ቢሄድም ይሖዋ ሊጠቀምብን እንደሚችል እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝ. 92:12-15) ያን ያህል ችሎታ እንደሌለን ወይም የምናከናውነው ሥራ በጣም ውስን እንደሆነ ቢሰማንም እንኳ ይሖዋ በእሱ አገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ኢየሱስ አስተምሮናል። (ሉቃስ 21:2-4) ስለዚህ ማከናወን በምትችለው ነገር ላይ ትኩረት አድርግ። ለምሳሌ ስለ ይሖዋ ለሰዎች መናገር፣ ለወንድሞችህ መጸለይ እንዲሁም በታማኝነት እንዲጸኑ ሌሎችን ማበረታታት ትችላለህ። ይሖዋ የሥራ አጋሩ አድርጎ የሚመለከትህ ብዙ ነገር ማከናወን ስለቻልክ ሳይሆን በደስታ ስለምትታዘዘው ነው።—1 ቆሮ. 3:5-9

19. ሮም 8:38, 39 ምን ዋስትና ይሰጠናል?

19 በእርግጥም አገልጋዮቹን ከፍ አድርጎ የሚመለከት እንደ ይሖዋ ያለ አምላክ ስላለን አመስጋኞች ነን! ይሖዋ የፈጠረን የእሱን ፈቃድ እንድናደርግ ነው፤ ደግሞም ሕይወታችን ትርጉም የሚኖረው በእውነተኛው አምልኮ ስንካፈል ነው። (ራእይ 4:11) ዓለም ዋጋ እንደሌለን አድርጎ ቢመለከተንም ይሖዋ ፈጽሞ በእኛ አያፍርም። (ዕብ. 11:16, 38) በሕመም፣ በኢኮኖሚ ችግር ወይም በዕድሜ መግፋት የተነሳ መንፈሳችን ሲደቆስ፣ ከሰማያዊው አባታችን ፍቅር ሊለየን የሚችል አንዳች ነገር እንደሌለ እናስታውስ።ሮም 8:38, 39ን አንብብ።

^ አን.5 ዋጋ እንደሌለህ እንዲሰማህ ከሚያደርግ ሁኔታ ጋር እየታገልክ ነው? ይህ ርዕስ በይሖዋ ፊት ምን ያህል ውድ እንደሆንክ እንድታስታውስ ይረዳሃል። በተጨማሪም በሕይወትህ ውስጥ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ፣ ለራስህ ጥሩ አመለካከት ይዘህ መቀጠል የምትችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

መዝሙር 30 አባቴ፣ አምላኬና ወዳጄ