በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውርጃ የሚያስከትለው አሳዛኝ ጥፋት

ውርጃ የሚያስከትለው አሳዛኝ ጥፋት

በየዓመቱ ከ50 እስከ 60 ሚልዮን የሚያክሉ ገና ያልተወለዱ ሕጻናት በውርጃ ይገደላሉ። ይህ ምን ያህል ብዙ ቁጥር እንደሆነ ልትገምት ትችላለህን? በየሳምንቱ በሐዋይ ደሴት የሚኖሩትን ሕዝቦች የሚያክሉ ሰዎችን እንደ መፍጀት ያህል ነው።

አብዛኞቹ መንግሥታት የሚፈጸሙትን ውርጃዎች በጥንቃቄ ስለማይመዘግቡ ትክክለኛውን ቁጥር ማግኘት ያስቸግራል። ውርጃ በሚከለከልባቸው ወይም ሕጋዊ ባልሆነባቸው አገሮች ስለሚፈጸሙት ውርጃዎች ተመራማሪዎች ሊሰጡ የሚችሉት ቁጥር በግምት ላይ የተመሠረተ ነው። ቢሆንም በመላው ዓለም የሚፈጸመው ውርጃ የሚከተለውን ይመስላል:-

በዩናይትድ ስቴትስ ውርጃ ቶንሲል ከማስወጣት ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ በብዛት የሚፈጸም ቀዶ ጥገና ሆኗል። በየዓመቱ 1.5 ሚልዮን የሚያክሉ ውርጃዎች ይፈጸማሉ። ውርጃ ከሚፈጸምላቸው ሴቶች አብዛኞቹ ማለትም ከ5ቱ መሐል 4ቱ ያላገቡ ናቸው። ያላገቡ ሴቶች የሚያስወርዱበት ጊዜ ከሚወልዱበት ጊዜ በሁለት እጥፍ ሲበልጥ ያገቡ ሴቶች ግን የወለዱበት ጊዜ ካስወረዱበት ጊዜ በአማካይ በአሥር እጥፍ ይበልጣል።

ከመላው ዓለም በጣም ጥብቅ የሆነ ውርጃ የሚከለክል ሕግ ያለው በአብዛኛው የካቶሊክ አገሮች በሆኑት በመካከለኛውና በደቡብ አሜሪካ አገሮች ነው። ይሁን እንጂ በሕገ ወጥ መንገዶች የሚፈጸሙት ውርጃዎች በጣም ብዙ በመሆናቸው ምክንያት በሴቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ የጤንነት አደጋ ይደርሳል። ለምሳሌ ያህል በ1992 ብራዚላውያን ሴቶች አራት ሚልዮን የሚያክል ውርጃ ፈጽመዋል። ከእነዚህ መካከል ከ400,000 በላይ የሚሆኑት በደረሰባቸው የጤንነት ቀውስ ምክንያት የሕክምና እርዳታ ለመፈለግ ተገድደዋል። በላቲን አሜሪካ አንድ አራተኛ የሚያክሉ እርግዝናዎች በውርጃ ያከትማሉ።

ከአትላንቲክ ማዶ በሚገኘው የአፍሪካ አህጉርም ቢሆን ሕጉ ጥብቅ ነው። በተለይ የሕገ ወጥ አስወራጆችን እርዳታ በሚፈልጉ ድሃ ሴቶች ላይ ጉዳትና ሞት መድረሱ የተለመደ ሆኗል።

በመካከለኛው ምሥራቅ ብዙ አገሮች በሕግ መጽሐፎቻቸው ላይ ብቻ የሠፈረ ጥብቅ ሕግ ቢኖራቸውም የሚጠየቀውን ከፍተኛ ገንዘብ ለመክፈል የሚችሉ ሴቶች ለማስወረድ መፈለጋቸውና ማስወረዳቸው አልቀረም።

በምዕራብ አውሮፓ በአብዛኞቹ አገሮች በሕግ የሚፈቀዱ ውርጃዎች አሉ። በተለይ የስካንዲኔቪያ አገሮች በጣም ልል የሆነ ሕግ አላቸው። የእንግሊዝ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ውርጃ ሕጋዊ ከሆነበት ከ1967 ወዲህ በአገሪቱ የሚፈጸሙትን ውርጃዎች ይከታተላል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የውርጃዎች ቁጥር በእጥፍ እንዳደገ ተገንዝቧል። ከዚሁ ጋር አብሮ ዲቃላ የሆኑ ልጆች ብዛት፣ በሩካቤ ሥጋ የሚተላለፉ በሽታዎች፣ ዝሙት አዳሪነትና በርካታ የመዋለድ ችግሮች በእጥፍ ጨምረዋል።

ምሥራቅ አውሮፓ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ለውጥ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን በዚህች አህጉር የነበረውም ማስወረድን የሚመለከት ሕግ በመለወጥ ላይ ነው። በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ውስጥ በየዓመቱ 11 ሚልዮን የሚያክሉ ውርጃዎች እንደሚፈጸሙ የሚገመት ሲሆን ይህም አገሪቷን በዓለም ከፍተኛ ደረጃ ከሚሰጣቸው አገሮች አንዷ ያደርጋታል። በዚህ አካባቢ የእርግዝና መከላከያዎች እንደልብ የማይገኙ በመሆናቸውና የኢኮኖሚው ሁኔታ በጣም የከፋ በመሆኑ አንዲት ሴት በዕድሜዋ ውስጥ በአማካይ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ጊዜ ታስወርዳለች።

በምሥራቅ አውሮፓ በሙሉ ልል የመሆን አዝማሚያ ይታያል። በዚህ ረገድ ሩማኒያ ዋነኛዋ ናት። በዚህች አገር የቀድሞው መንግሥት የሕዝብ ቁጥር እንዲጨምር ለማበረታት ሲል ማስወረድ ይከለክልና የእርግዝና መከላከያዎችን በሕግ ያግድ ነበር። ሴቶች ቢያንስ አራት ልጅ በመውለድ ኮታቸውን እንዲያሟሉ ይገደዱ ነበር። በዚህም ምክንያት በ1988 በሩማንያ የሚገኙ ወላጅ የሌላቸው ሕጻናት ማሳደጊያ ቤቶች ወላጆቻቸው በጣሏቸው ሕፃናት ተጣብበው ነበር። በ1989 የተቋቋመው አብዮታዊ መንግሥት ይህን በውርጃ ላይ የተጣለውን እገዳ ካነሣ በኋላ ግን ከ4 ፅንሶች መካከል 3ቱ በውርጃ ይገደላሉ። ይህም ከአውሮፓ ከፍተኛውን ደረጃ የያዘ ቁጥር ነው።

በጣም ከፍተኛ ውርጃ የሚፈጸመው በእስያ ነው። በአንደኛነት ደረጃ የምትገኘው “አንድ ልጅ ብቻ” የሚል መርሕ ያላትና ውርጃ የሚያስገድድ ሕግ ያላት የቻይና ሕዝባዊት ሪፑብሊክ ነች። በዚህች አገር በየዓመቱ 14 ሚልዮን የሚያክሉ ውርጃዎች ስለሚፈጸሙ የመሪነቱን ቦታ ይዛለች። በጃፓን አገር ሴቶች ላስወረዱአቸው ሕጻናት ማስታወሻ የሚሆን ትንሽ ሐውልት ሠርተው በሚያምር ልብስና አሻንጉሊት ያስጌጣሉ። ሕዝቡ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎችን ለመውሰድ ስለሚፈራ ዋነኛው የቤተሰብ ብዛት መመጠኛ ዘዴ ውርጃ ሆኗል።

በእስያ በተለይም በሕንድ አገር የሕክምና ቴክኖሎጂ የሴት መብት ተሟጋቾችን አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የጣለ ነገር ፈጥሯል። እንደ አምኒዮሰንተሲስ እና አልትራ ሳውንድ የመሰሉትን ቴክኒኮች በመጠቀም ፅንሱ ወንድ ወይም ሴት መሆኑን በተረገዘ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ማወቅ ተችሏል። በሩቅ ምሥራቅ አገሮች ባሕል ወንዶች ልጆች ከሴት ልጆች ይበልጥ ይወደዳሉ። ስለዚህ የጾታ መለያ ቴክኒኮችና ማስወረጃዎች በቀላሉ በሚገኙባቸው አገሮች በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴት ፅንሶች በውርጃ እንዲወጡ ይደረጋል። በዚህም ምክንያት የወንዶችና የሴቶች ሕጻናት የወሊድ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ የማይመጣጠን ሆኗል። ከዚህ የተነሣ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ፅንሶቻቸውን የማስወረድ መብት ለሴቶች ይሰጣቸው ብለው እንዲከራከሩ በሚያስገድዳቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወድቀዋል።

ወንድ ልጆች ይበልጥ ተወዳጅ በሆኑበት በእስያ አህጉር ዶክተሮች በሺህ የሚቆጠሩ ሴት ሽሎችን ያስወርዳሉ

የምታስወርደው እናት ምን ይሰማታል?

ውርጃ እንደ ማንኛውም ሌላ ሕክምና የሚያስከትለው አደጋና ሕመም አለ። አንዲት ሴት በምትፀንስበት ጊዜ ሰርቪክስ የሚባለው የማኅፀን አፍ በፅንሱ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በጥብቅ ይዘጋል። ይህን የማኅፀን አፍ ለማስፋትና ለማስወረድ የሚያገለግለውን መሣሪያ ለማስገባት የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ሥቃይና ሕመም ያስከትላል። በመምጠጫ መሣሪያ አማካኝነት የሚፈጸመው ውርጃ 30 ደቂቃ ያህል ወይም ከዚያም በላይ ሊፈጅ የሚችል ሲሆን በዚህ ጊዜ አንዳንድ ሴቶች ከመካከለኛ እስከ ከባድ የሚደርስ ሕመምና ቁርጠት ይሰማቸዋል። ጨው በተበጠበጠበት ውሃ አማካኝነት በሚፈጸመው ውርጃ ደግሞ ነፍሰ ጡሯ ሴት ፕሮስቶግላንዲን በሚባለው የሚያስምጥ መድኃኒት ረዳትነት ከመውለጃዋ ጊዜ በፊት ምጥ እንዲይዛት ይደረጋል። ምጡ ለበርካታ ሰዓታት እንዲያውም በቀናት ለሚቆጠር ጊዜ ሊቆይ ስለሚችል ከፍተኛ የሆነ ሕመምና የስሜት ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።

ውርጃው እንደተከናወነ ሊከሰቱ ከሚችሉት የጤና እክሎች መካከል በርካታ ደም መፍሰስ፣ የማኅፀን አፍ ‘የሰርቪክስ’ መቀደድ ወይም መጎዳት፣ የማኅፀን መቀደድ፣ የደም መርጋት፣ የማደንዘዣ መድኃኒት የሚያስከትለው ሕመም፣ መንቀጥቀጥ፣ ትኩሳት፣ ብርድና ማስመለስ ይገኙበታል። በተለይ የሕፃኑ የሰውነት ክፍሎች ወይም እንግዴ ልጁ ተቆርጦ በማኅፀን ውስጥ ከቀረ ከፍተኛ የሆነ የኢንፌክሽን አደጋ ይኖራል። በውርጃ ጊዜ በማኅፀን ውስጥ ተቆርጦ የሚቀር ነገር መኖሩ ያልተለመደ ነገር አይደለም። እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ኦፕራሲዮን በማድረግ በመበስበስ ላይ የሚገኘውን ሕዋስ ወይም ማኅፀኑን ራሱን ማውጣት አስፈላጊ ይሆናል። በዩናይትድ ስቴትስ፣ በብሪታንያና በቀድሞዋ ቺኮዝሎቫኪያ የተደረጉ መንግሥታዊ ጥናቶች እንዳመለከቱት ማስወረድ መካን የመሆን፣ ከማኅፀን ውጭ የማርገዝን፣ ከቀኑ በፊትና አካለ ጎደሎ የሆነ ሕፃን የመውለድን ዕድል በእጅጉ ይጨምራል።

የዩናይትድ ስቴትስ የጤና ጥበቃ ኃላፊ የነበሩት ሲ ኤቨረት ኩፕ እንደተናገሩት “ፅንሷን ያስወረደችና አሁን ከፍተኛ የሆነ ልጅ የመውለድ ፍላጎት እያላት ማርገዝ ያልቻለች ሴት በሚሰማት የስሜት ቀውስና የበደለኛነት ስሜት ላይ ጥናት ያደረገ ሰው የለም።”

በውርጃ ላይ በሚደረጉ ጥናቶች ውስጥ ለሕይወትና ለአምላክ ሕግጋት ባላቸው አክብሮት የተነሳ ድንግልናቸውን ጠብቀው የሚኖሩ ንጹሕ ክርስቲያኖች መጨመር ይገባቸው ነበር። እንዲህ ያለ ጥናት ቢደረግ ኖሮ እነዚህ ወጣቶች ከሌሎች የበለጠ ጤናማ ዝምድና ለመመሥረት እንደሚችሉ፣ ለራሳቸው ጥሩ አመለካከትና ዘላቂ የሆነ የአእምሮ ሰላም እንዳላቸው ማረጋገጥ ይቻል ነበር።

ያልተወለደው ሕፃን ምን ይሰማዋል?

ሞቆትና ተመችቶት ከሚኖርበት ከእናቱ ማኅፀን በድንገት የመግደያ መሣሪያ የሚሰነዘርበት ያልተወለደስ ሕፃን ምን ይሰማዋል? ሥቃዩን የሚቀበለው ሕፃን የሚሰማውን ሊነግረን የሚችልበት መንገድ ስለማይኖር ስለሚሰማው ሥቃይ የሚኖረን እውቀት ከግምት ሊያልፍ አይችልም።

አብዛኞቹ ውርጃዎች የሚፈፀሙት ሕፃኑ ከተፀነሰ በኋላ ባሉት 12 ሳምንቶች ውስጥ ነው። በዚህ ጊዜ ላይ ሽሉ መተንፈስና መዋጥ ይጀምራል። ልቡም ይመታል። ትናንሽ ጣቶቹን መቆልመም፣ እጁን መጨበጥ፣ በዙሪያው የከበበውን ፈሳሽ መቅዘፍ ይችላል። ሕመምም ይሰማዋል።

ብዙዎቹ ሽሎች በመቆንጠጫ ከተያዙ በኋላ በአየር ግፊት በሚስብና ሹል ጫፍ ባለው መሣሪያ ተጎትተው ከነበሩበት ማኅፀን ወጥተው በዕቃ ውስጥ ይከተታሉ። ይህ ዓይነቱ የውርጃ ዘዴ ቫኪዩም አስፒሬሽን ይባላል። ይህ መሣሪያ ከፍተኛ የመሳብ ኃይል ስላለው (ከቤት የምንጣፍ መጥረጊያ መሣሪያ 29 ጊዜ የሚበልጥ ኃይል አለው) የሽሉን ትናንሽ ብልቶች ይሰባብራቸዋል። በሌሎች ሕፃናት ላይ ደግሞ ውርጃ የሚፈጸመው ማኅፀኑን በመለጠጥና ክብ ቅርጽ ያለው ቢላዋ አስገብቶ የማኅፀኑን ግድግዳ በመቧጠጥና ሕፃኑን በመቆራረጥ ነው።

ከ16 ሳምንት የሚበልጥ ዕድሜ ያላቸው ሽሎች ጨው በተበጠበጠበት ውሃ እንዲመረዙ በማድረግ በሚፈጸመው የውርጃ ዘዴ ሊሞቱ ይችላሉ። ሽሉ የሚኖርበት ውሃ በረዥም መርፌ ከተቀዳ በኋላ ብዙ ጨው የተበጠበጠበት ውሃ ይጨመርበታል። ሕፃኑ በሚተነፍስበትና በሚውጥበት ጊዜ ገና ያልጠነከረው ሳንባው በዚህ መርዛማ ፈሳሽ ስለሚሞላ መታገልና መንዘፍዘፍ ይጀምራል። የጨዋማ ውሃው ኃይል የቆዳውን ላይኛ ክፍል ስለሚያቃጥለው ቆዳው በሙሉ ቆሳስሎ ይተጣጠፋል። በአንጎሉ ደም መፍሰስ ሊጀምር ይችላል። እናቲቱ አንድ ቀን ከሚያክል ጊዜ በኋላ ምጥ ሲጀምራት ሊሞት የሚያጣጥር ሕፃን የሚወለድበት ጊዜ ቢኖርም አብዛኛውን ጊዜ ሕፃኑ በሰዓቶች በሚቆጠር ጊዜ ውስጥ ይሞታል።

ሕፃኑ ብዙ ያደገ ሆኖ እነዚህን ወይም እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ዘዴዎችን መጠቀም የማይቻል በሚሆንበት ጊዜ የሚኖረው አማራጭ አንድ ብቻ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ሕይወት ለማትረፍ ሳይሆን ሕይወት ለማጥፋት የእናቲቱ ማኅፀን በቀዶ ሕክምና ይከፈታል። የእናቲቱ ሆድ ከተከፈተ በኋላ ገና በሕይወት ያለ ሕፃን ተጎትቶ ይወጣል። እንዲያውም ሕፃኑ ሊያለቅስ ይችላል። ቢሆንም መሞት ስላለበት ይጣላል። አንዳንዶቹን በማነቅ፣ ውኃ ውስጥ በማስመጥና በሌሎች ዘዴዎች እንዲሞቱ ይደረጋል።

ሐኪሙስ ምን ይሰማዋል?

ሐኪሞች ለበርካታ መቶ ዓመታት ታላቅ ክብር በሚሰጠው የሂፖክራተስ መሐላ የተገለጸውን የሥነ ምግባር ሕግ ተቀብለዋል። ይህ መሐላ በከፊል እንዲህ ይላል:- “ለማንም ቢሆን፣ ብጠየቅ እንኳን የሚገድል መድኃኒት ወይም ለመግደል የሚያስችል ምክር አልሰጥም። ሙያዬን በቅድስናና ነውር በሌለበት መንገድ እይዛለሁ እንጂ ለማንም ሴት የሚጎዳና ‘ፅንስ የሚያስወርድ’ መድኃኒት አልሰጥም።”

በማኅፀን ውስጥ የሚኖር ሕይወት የሚገድሉ ዶክተሮች ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር ውጊያ ይደርስባቸዋል። ዶክተር ጆርጅ ፍሌሽ ይህን የሥነ ምግባር ውጊያ እንደሚከተለው በማለት ገልጸዋል:- “ተለማማጅ ሐኪም በነበርኩባቸው ጊዜያት ያከናወንኳቸው የመጀመሪያዎቹ ውርጃዎች የስሜት መረበሽ አላስከተሉብኝም። . . . መረበሽ የጀመርኩት በመቶ የሚቆጠሩ ውርጃዎችን ከፈጸምኩ በኋላ ነው። . . . ምን ለወጠኝ ? ገና ሥራ በጀመርኩበት ጊዜ አንድ ባልና ሚስት መጥተው ውርጃ እንዲፈጸምላቸው ጠየቁኝ። የሴትየዋ ማኅፀን አንገት በጣም የጠበቀ ስለነበረ ልከፍተውና ሽሉን ላወጣው ሳልችል ቀረሁ። ስለዚህ ከሳምንት በኋላ የማኅፀንዋ አፍ ላላ ሲል እንድትመጣ ነገርኳት። ባልና ሚስቱ ተመልሰው ሐሳባቸውን እንደለወጡ ነገሩኝ። ከሰባት ወር በኋላ ልጃቸውን አዋለድኩ።

“ከዓመታት በኋላ እኔና የሕፃኑ ወላጆች አባል በሆንበት የቴኒስ ክበብ በሚገኝ መዋኛ ውስጥ ከሕፃኑ ጀፍሪ ጋር ተጫወትኩ። በጣም ደስተኛና የሚያምር ሕፃን ነበር። የጀፍሪን ሕይወት ከማጥፋት ያገደኝ ያጋጠመኝ የቴክኒክ ችግር ብቻ እንደነበረ ሳስብ በጣም ተሰቀቅኩ። . . . እናቲቱ ስለፈለገች ብቻ አንድን የዳበረ ሽል መገነጣጠል ማኅበረሰቡ ሊፈቅደው የማይገባ ወራዳ ተግባር እንደሆነ አምናለሁ።”

ውርጃ በሚፈጸምበት ክሊኒክ ውስጥ በረዳትነት ትሠራ የነበረችና አሁን ግን ይህን ሥራ ያቆመች አንዲት ነርስ ስለ ሥራዋ እንዲህ ብላለች:- “ከምንሠራቸው ሥራዎች አንዱ የሽሉን ብልቶች መቁጠር ነው። . . . ባስወረደችው ሴት ማኅፀን ውስጥ የቀረ የሽል ክፍል ቢኖር በሴትዬዋ ላይ ከፍተኛ ችግር ሊደርስ ይችላል። የሽሉን ብልቶች አንድ ላይ ካደረግኩ በኋላ ሁለት እጆች፣ ሁለት እግሮች፣ ወገብ፣ ራስ ወዘተ መኖራቸውን አንድ በአንድ እቆጥራለሁ። . . . አራት ልጆች አሉኝ። . . . በሥራዬና በግል ሕይወቴ መካከል ላስታርቅ የማልችለው ትልቅ ግጭት አለ። . . . ውርጃ በጣም ከባድ ሥራ ነው።”

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ጋዜጠኛ ውርጃን በመቃወም በተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በሕጋዊ ፈቃድ ውርጃ የተፈጸመበትን የ20 ሣምንት ፅንስ ፎቶ ግራፍ ሲያነሳ

[ምንጭ]

ፎቶ:- Nina Berman/Sipa Press

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዋሽንግተን ዲሲ ውርጃን በመደገፍ የተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ

[ምንጭ]

ፎቶ:- Rose Marston/Sipa Press

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዩናይትድ ስቴትስ ለማስወረድ ከሚጠይቁ 5 ሴቶች መካከል 4ቱ ያላገቡ ናቸው