የውርጃ ክፉ አማራጭ—መፍትሔው 60 ሚልዮን ነፍሳትን መግደል ነው?
የአሥራ አምስት ዓመቷ ወጣት ወንድ ጓደኛዋ በጥላቻ ጥሏት ሲሄድ ዓይኖችዋ እንባ አቅርረው፣ በፍርሃትና ግራ በመጋባት ስሜት ተውጣ ትመለከተዋለች። ስላረገዘች ‘ደደብ ነሽ’ ብሎ ሰድቧት መውጣቱ ነበር። በፍቅር የተሳሰሩ መስሏት ነበር።
ሌላዋ ሴት ደግሞ ስድስተኛ ልጅ እንዳረገዘች በማወቋ በጣም ተጨንቃለች። ባልዋ ከሥራ ተባርሯል። ሕፃናት ልጆችዋ ባዶ ሆዳቸውን ማደር ከጀመሩ ውሎ አድሯል። የሚወለደውን ተጨማሪ ልጅ እንዴት ሊያሳድጉ ነው?
አንድ ጥሩ አለባበስ ያላት ሴት ደግሞ ለሐኪሟ “ያረገዝኩት በጣም መጥፎ ጊዜ ላይ ነው” ትለዋለች። የመሐንዲስነት ዲግሪዋን አግኝታ አዲሱን ሥራዋን ለመጀመር በመዘጋጀት ላይ ነበረች። ባሏ የሕግ ባለ ሙያ በመሆኑ በሚሠራቸው ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ስለተጠመደ ምንም ጊዜ የለውም። ሕፃኑን የሚያሳድጉበት ጊዜ ከየት ሊያገኙ ይችላሉ?
የእነዚህ ሰዎች የኑሮ ሁኔታና በፊታቸው የተደቀነው አማራጭ በጣም የተለያየ ነው። ይሁን እንጂ ሁሉም የመረጡት መፍትሔ አንድ ዓይነት ነው። — ውርጃ
ውርጃ በዚህ በዘመናችን በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ኑሮ፣ በሕክምናና በሃይማኖታዊ መስኮች የተጧጧፈ ክርክር ከሚደረግባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አፍቃሬ ሕይወት ቡድኖች ላልተወለዱ ሕጻናት ሕይወት ሽንጣቸውን ገትረው ይሟገታሉ። በአፍቃሬ ምርጫ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ማንኛዋም ሴት ነጻነትና የመወሰን መብት ሊኖራት ይገባል ብለው ይከራከራሉ። የነጻነት ተሟጋቾቹን በምርጫዎች፣ በፍርድ ቤቶች፣ በአብያተ ክርስቲያናትና በጎዳናዎች ላይ ጭምር የሚታገሏቸው ሰዎች በርካታ ናቸው።
በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሁለቱ ጎራዎች መካከል በሚደረገው የተጧጧፈ ክርክር ተስበው ከሁለቱ ወገኖች በአንዱ ለመሰለፍ ተገድደዋል። “አፍቃሬ ምርጫ” እና “አፍቃሬ ሕይወት” የሚሉት ቃላት እንኳን ሚናቸውን ያልለዩ ሰዎችን ለመሳብ ታስበው በጥንቃቄ የተመረጡ ቃላት ናቸው። ነፃነት እንደ ጣዖት በሚመለክበት በዚህ ዘመን ከነጻነት ጎን የማይሰለፍ ሰው ሊኖር ይችላልን? በሌላው በኩል ደግሞ ለሕይወት የማይቆም ማን ሰው ይኖራል? አፍቃሬ ምርጫ ቡድኖች የኮት መስቀያዎቻቸውን በማወዛወዝ አደገኛና ሕገወጥ በሆነ መንገድ የሚያስወርዱ ጭቁን ሴቶች የሚደርስባቸውን አሟሟት ያሳያሉ። አፍቃሬ ሕይወት የሆኑ ተሟጋቾች ደግሞ ከመወለዳቸው በፊት የሚገደሉትን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕጻናት አሳዛኝ ዕጣ ለማስታወስ በውርጃ የወጡ ፅንሶችን በጠርሙስ ይዘው ለሕዝብ ያሳያሉ።
ይህን የመሰለው ለብዙ ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነ አሳዛኝ ሁኔታ አቦርሽን፣ ዘ ክላሽ ኦቭ አብሶሉትስ በተባለው የሎረንስ ኤች ትራይብ መጽሐፍ ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ተገልጿል። “የአንድን ፅንስ ሰብአዊነት ሊያስተውሉና ሊገነዘቡ የሚችሉ፣ ሥዕሉን ከፍ አድርገው በመያዝ ለማልቀስ የሚችሉ ብዙ ሰዎች ፅንሱን የተሸከመችውን ሴትና ሰብዓዊ ችግርዋን ሊመለከቱላት አልቻሉም። . . . ሴቲቱንና ሰውነትዋን ሊመለከቱ ከቻሉትና የራሷን ዕጣ የመወሰን መብት ሊኖራት እንደሚገባ ከሚሟገቱላት ሰዎች መካከል ደግሞ ብዙዎቹ በዚችው ሴት ውስጥ የሚኖረውን ፅንስ አይመለከቱም። ፅንሱ እንዲኖር ሊፈቀድለት የሚገባውን ሕይወት እንደ እውነተኛ ሕይወት አይቆጥሩም።”
ይህ የሥነ ምግባር ጦርነት በመጧጧፍ ላይ እንዳለ በዚህ ዓመት ብቻ ከ50 እስከ 60 ሚልዮን የሚደርሱ ገና ያልተወለዱ ነፍሳት የመብት ውጊያ በሚደረግበት ጦር ሜዳ ላይ ይሠዋሉ።
በዚህ የብዙ ሰዎችን ስሜት በቀሰቀሰው ጥያቄ ላይ በየትኛው ወገን ትሰለፋለህ? ለሚከተሉት ቁልፍ ጥያቄዎች ምን መልስ ትሰጣለህ? በዚህ ጉዳይ ላይ ለመወሰን መቻል የሴቲቱ መሠረታዊ መብት ነውን? ውርጃ ሊፈቀድ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላልን? ሕይወት የሚጀምረው መቼ ነው? እንዲሁም እምብዛም
የማይጠየቅ ቢሆንም የሕይወትና የመዋለድ ፈጣሪ የሆነው አምላክስ ይህን እንዴት ይመለከተዋል? የሚልም ወሳኝ የሆነ ጥያቄ አለ።ፅንስ ማስወረድ ረዥም ታሪክ ያለው ድርጊት ነው። በጥንቷ ግሪክና ሮም ፅንስ ማስወረድ በጣም የተለመደ ነበር። በአውሮፓ በመካከለኛው ዘመንና ከ14ኛው መቶ ዘመን እስከ 17ኛው መቶ ዘመን እዘአ በነበሩት ዓመታት አንዲት እናት ፅንሱ በውስጧ ሲላወስ እስከሚሰማት ድረስ እንድታስወርድ ይፈቀድ ነበር። ወሲባዊ አብዮት ከተካሄደ በኋላ ደግሞ የዚህ አብዮት ውጤት ታየ። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አለውዴታቸው ማርገዝ ጀመሩ።
በ1960ዎቹ ዓመታት የሴቶች እንቅስቃሴ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ። የሴቶች እንቅስቃሴ የመሠረት ድንጋይ ደግሞ የመውለድ መብት ነው። አንዳንዶች ተገድዳ በመነወር ወይም ከቅርብ ዘመድ ጋር በተደረገ ሩካቤ ሥጋ ለፀነሰች ሴት ወይም የእናቲቱ ጤንነት አደገኛ ሁኔታ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ የማስወረድ መብት መሰጠት ይኖርበታል ብለው ይሟገታሉ። የሕክምና ቴክኖሎጂ ፅንሱ በሚወለድበት ጊዜ ሊኖረው የሚችለውን አካለ ስንኩልነትና ጾታ በማኅፀን ውስጥ እንዳለ ለማወቅ የሚያስችል ዘዴ አስገኝቷል። ሐኪሞች በሚሰጡት ተስፋ አስቆራጭ የምርመራ ውጤት ብቻ የብዙ እናቶች እርግዝና በውርጃ ያከትማል። ከ40 ዓመት የሚበልጥ ዕድሜ ያላቸው እናቶች አካለ ስንኩል የሆነ ሕፃን የመውለድ ስጋት ያጋጥማቸዋል።
የፅንስ መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን በቀላሉ ለማግኘት በማይቻልባቸው በድህነት የተጠቁ አገሮች የሚኖሩ ብዙ ሴቶች ሌላ ተጨማሪ ልጅ ቢወልዱ ሕፃኑን ማሳደግ ይከብዳቸዋል። አንዳንድ እርጉዝ ሴቶች ደግሞ ለአፍቃሬ ምርጫ ቡድን ከልክ በላይ የተጋነነ ትርጉም በመስጠት ያረገዙበት ጊዜ አመቺ ሆኖ ስላልተሰማቸው ወይም ወንድ ወይም ሴት ለመውለድ ባለመፈለጋቸው ብቻ ፅንሱን ለማስወረድ ይመርጣሉ።
በዚህ ጉዳይ ላይ በጣም አወዛጋቢ ከሆኑት ጥያቄዎች መካከል አንዱ ሕይወት የሚጀምረው መቼ ነው? የሚለው ጥያቄ ነው። በወንዴ ዘር የዳበረው የእንቁላል ሴል ሕይወት የለውም ብለው ለመከራከር ብዙም የሚደፍሩ ሰዎች የሉም። የሚነሣው ጥያቄ ሕያው የሆነው በምን መልክ ወይም በምን ደረጃ ነው በሚለው ላይ ነው። ፅንሱ እንደ ሰው ሊቆጠር ይችላልን? አንድ የሾላ ፍሬ የሾላ ዛፍ ነውን? ታዲያ አንድ ሽል ሰው ነው ሊባል ይቻላልን? በቃላት ላይ የሚደረገው ጭቅጭቅ ማቆሚያ ያለው አይመስልም። ሐኪሞች አለቀኑ የተወለደን ሕፃን ሕይወት ለማትረፍ ቀንና ሌሊት እየለፉ በዚያው ሆስፒታል ውስጥ በዚያው ዕድሜ የሚገኝ ሌላ ፅንስ መግደላቸው የሚያስገርም ነገር ነው። ሕፃኑ በማኅፀን ውስጥ እንዳለ እንዲገድሉት ሕጉ የሚፈቅድላቸው ሲሆን ከማኅፀን ከወጣ በኋላ ግን ቢገድሉት ነፍሰ ገዳይነት ይሆንባቸዋል።
ፅንስ ማስወረድ ሕጋዊ መሆን ይገባዋል በማለት አጥብቀው የሚጠይቁት አብዛኛውን ጊዜ ገና ከማርገዛቸው በፊት እርግዝናውን መከላከል የሚችሉበት የእርግዝና መከላከያ ማግኘት የማያስቸግራቸው “ነጻ የወጡ” ዘመናውያን ናቸው። ለመዋለድና ለመፀነስ ባላቸው ችሎታ ከተጠቀሙ በኋላ የመዋለድ መብታችን ሊጠበቅልን ይገባል በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ይሟገታሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሊከበርልን ይገባል ብለው የሚጠይቁት ይህ ያደረጉት የመዋለድ ምርጫ ተፈጻሚነት እንዳያገኝ የማድረግ መብት ነው። ለዚህ ጥያቄያቸው የሚያቀርቡት ምክንያት ምንድን ነው? “የራሴ አካል ነው” ይላሉ። ይሁን እንጂ በእርግጥ የራሳቸው አካል ነውን?
እናት:- “የራሴ አካል ነው!”
ሕፃን:- “የለም! የእኔ አካል ነው!”
አቦርሽን፣ ኤ ሲትዘንስ ጋይድ ቱ ዘ ኢሹስ የተባለው
መጽሐፍ በመጀመሪያዎቹ 12 የእርግዝና ሳምንታት “ልፋጭ የሚመስለውን ትንሽ ሽል ማውጣት በጣም ቀላል ነው” ይላል። ፅንስ ማስወረድ “እንደ ልፋጭ ያለ ሕዋስ እንደማስወገድ” ወይም “የመፀነስ ውጤት የሆነውን ነገር ዕድሜ እንደማሳጠር” መቆጠሩ ትክክል ነውን? ወይስ እነዚህ ቃላት መራራውን እውነት ለማስዋጥና የሕሊና ወቀሳን ለማስታገስ ታስበው በስኳር ተጠቅልለው የቀረቡ ናቸውን?ይህ ያልተፈለገ ሕዋስ የራሱ ክሮሞዞሞች ያሉት፣ የሚያድግና የሚዳብር ሕዋስ ነው። እንደ አንድ ትንቢታዊ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ በዓይነቱ ማንንም ስለማይመስለው ግለሰብ የሚገልጽ ሙሉ ታሪክ የያዘ ሕዋስ ነው። ኤ ደብልዩ ሊሌይ የተባሉት እውቅ የሥነ ፅንስ ተመራማሪ ፕሮፌሰር እንደሚከተለው በማለት አብራርተዋል:- “ከሥነ ሕይወት አንጻር በማንኛውም ጊዜ አንድ ሽል የእናቱ ተቀጽላ ነው የሚለውን አመለካከት ልንቀበል አንችልም። እናትና ሽል ከፅንስ ጀምሮ ሁለት የተለያዩ ግለሰቦች ናቸው።”
ኃላፊነት የጎደለው ባሕርይ
ሆኖም ብዙዎች በቀላሉ ሊያስወርዱ ስለሚችሉ ብቻ ያልተፈለገ እርግዝና እንዳያጋጥማቸው ጥረት ማድረግ የሚያስፈልጋቸው ሆኖ አይታያቸውም። በውርጃ ተጠቅሞ ከሚያጋጥማቸው “አደጋ” ማምለጥ የተሻለ ሆኖ አግኝተውታል።
በዚህ መቶ ዘመን ልጆች ለጉርምስና የሚደርሱበት ዕድሜ ዝቅ እንዳለ የስታትስቲክስ መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህም ምክንያት በዕድሜ አነስተኛ የሆኑ ልጆች እንኳን ልጅ የመውለድ ችሎታ ሊኖራቸው ችሏል። ይሁን እንጂ ልጅ ከመውለድ መብት ጋር የሚመጣ ከባድ ኃላፊነት እንዳለ የሚገልጽ ትምህርት ተሰጥቷቸዋልን? አሜሪካውያን በአማካይ በ16 ዓመታቸው፣ ከአምስት አሜሪካውያን አንዱ ደግሞ ከአሥራ ሦስት ዓመት ዕድሜ በፊት ድንግልናቸውን ያጣሉ። ካገቡ ወንዶችና ሴቶች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ከጋብቻቸው ውጭ ሩካቤ ሥጋ ፈጽመዋል ወይም በመፈጸም ላይ ይገኛሉ። ሕገወጥ ሩካቤ ሥጋ የሚፈጽሙ ሰዎች ለውርጃ የተዘጋጁ ደንበኞች ናቸው። የኤድስን መስፋፋት ለመግታት ዝሙት አዳሪነትን ሕጋዊ ማድረግ ያስፈልጋል ሲባል እንደሚሰማው ክርክር ሁሉ፣ ለውርጃ ሕጋዊ ፈቃድ መስጠት፣ ውርጃ የሚያስከትለውን የጤንነት አደጋ ሊቀንስ ቢችልም ከሥነ ምግባር ጉድለት የሚመጣ በሽታ እንዲስፋፋ ይበልጥ አመቺ የሆነ ሁኔታ እንዲኖር አድርጓል።
ጥቃት የደረሰባቸው በዓመፅ ምክንያት ነው ወይስ በሁኔታዎች አስገዳጅነት?
አስገድዶ በማስነወር ምክንያት የሚደርስ እርግዝና እጅግ በጣም ጥቂት መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ። በሚኒያፖሊስ ዩ ኤስ ኤ ተገድደው በተነወሩ 3,500 ሴቶች ላይ ጥናት ተደርጎ አንዳቸውም እንኳን እንዳላረገዙ ተረጋግጧል። በቀድሞዋ ቺኮዝሎቫኪያ ከተፈጸሙት 86,000 የሚያክሉ ውርጃዎች መካከል ተገድደው በመነወራቸው ምክንያት አርግዘው ያስወረዱት 22ቱ ብቻ ናቸው። ስለዚህ ተገድደው በመነወራቸው ምክንያት የሚያስወርዱ ሴቶች በጣም ጥቂት ናቸው።
ፈውስ የማይገኝለት አካለ ስንኩልነት ይደርስባቸዋል የሚል አስፈሪ ትንቢት የሚነገርላቸው ፅንሶችስ? አንዳንድ ዶክተሮች ችግር እንደሚኖር የሚጠቁም ምልክት እንደተመለከቱ ወዲያው ነፍሰጡሮቹ እንዲያስወርዱ አጥብቀው ያሳስባሉ። እነዚህ ሐኪሞች የምርመራ ውጤታቸው ትክክል እንደሚሆን ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ሊሆኑ ይችላሉን? ብዙ ወላጆች እንደነዚህ ያሉት አስደንጋጭ ትንቢቶች መሠረተ ቢስ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሊመሠክሩ ይችላሉ። ይህንንም የሚያረጋግጡላቸው ጤነኛና ደስተኛ ልጆች አሏቸው። አካለ ስንኩላን የሚባሉ ልጆች የወለዱ ወላጆችም ቢሆኑ የእነዚህ ሕፃናት ወላጆች ለመሆን በመቻላቸው ተደስተዋል። እንዲያውም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ፅንሱ አካለ ስንኩል እንደሚሆን ስለተነገራቸው ለማስወረድ የሚጠይቁት ነፍሰጡሮች ቁጥር ውርጃ እንዲፈጸምላቸው ከሚጠይቁ ሴቶች ጠቅላላ ቁጥር 1 በመቶ ብቻ ነው።
ይሁን እንጂ ይህን ጽሑፍ ስታነብ በቆየህበት ጊዜ ውስጥ ብቻ በመቶ የሚቆጠሩ ሕፃናት ከመወለዳቸው በፊት ተገድለዋል። ይህ ዓይነቱ ግድያ የሚፈጸመው የት ነው? በዚህስ ድርጊት የሚካፈሉ ሰዎች ሕይወታቸው በድርጊቱ እንዴት ተነክቷል?