በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለብዙሃኑ ባሕል ሊኖረን የሚገባው ሚዛናዊ አመለካከት

ለብዙሃኑ ባሕል ሊኖረን የሚገባው ሚዛናዊ አመለካከት

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ለብዙሃኑ ባሕል ሊኖረን የሚገባው ሚዛናዊ አመለካከት

“በአንድ ወቅትና ቦታ እንደ ግዴታ ሲታይ ቆይቶ ከጊዜ በኋላ በሌላ ወቅትና ቦታ ያልተተቸ ልማድ የለም።”

አየርላንዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ዊልያም ሌኪ የሰዎችን ተለዋዋጭ ጠባይ ጠቅለል አድርገው የገለጹት በዚህ መንገድ ነበር። ይህ አስተያየት ባለፉት ዘመናት ለነበሩት ባሕሎችና ልማዶችም ሊሠራ ይችላል። በእርግጥም፣ በአንድ ወቅት በዕለታዊ ሕይወት ውስጥ የግድ አስፈላጊ እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ የነበሩና በሌላ ጊዜ የውግዘት መዓት የወረደባቸው በርካታ ልማዶች ነበሩ። ይህ የሚያስደንቅ አይደለም፤ ምክንያቱም ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ “የዚህ ዓለም መልክ ተለዋዋጭ ነው” በማለት ተናግሯል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 7:​31 NW

አዎን፣ ሰብዓዊው ኅብረተሰብ የማያቋርጥ ለውጥ ያደርጋል። ይህም ብዙውን ጊዜ በአመለካከትና በማኅበራዊ ልማዶች ላይ በሰፊው ሲንጸባረቅ ይታያል። ክርስቲያኖች “የዓለም ክፍል አይደሉም።” ይህም ማለት ከአምላክ ርቆ ከሚገኘው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ይርቃሉ ማለት ነው። ያም ሆኖ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ‘በዓለም ውስጥ’ እንደሚኖሩ ይገልጻል። ይህም ራሳቸውን ከሰዎች አግልለው መኖር እንዳለባቸው አያዝም ማለት ነው። ስለዚህ ባሕሎችን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት መያዙ እጅግ አስፈላጊ ነው።​—⁠ዮሐንስ 17:​11, 14-16፤ 2 ቆሮንቶስ 6:​14-17፤ ኤፌሶን 4:​17-19፤ 2 ጴጥሮስ 2:​20

ባሕል ምንድን ነው?

ባሕል በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ የሚገኝ ልማድ ሲሆን በተለይ ደግሞ በአንድ በተወሰነ ቦታ ወይም የሰዎች መደብ ውስጥ በእጅጉ የተስፋፋ ልማድ ነው። እንደ ገበታ ሥርዓት ያሉ አንዳንድ ባሕሎች ሰዎች በቡድን በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጥሩ ጠባይ እንዲያሳዩና እርስ በርሳቸው መከባበር እንዲችሉ ባሕርያቸውን ለመግራት ከማሰብ የመነጩ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ባለው ወቅት በኅብረተሰብ ውስጥ የሚኖረው መልካም ባሕርይ ከዘይት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ምክንያቱም በሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት ሸካራ እንዳይሆን ይረዳል።

ባሕሎች ሃይማኖታዊ መንፈስ በእጅጉ ይንጸባረቅባቸዋል። እንዲያውም ብዙዎቹ ባሕሎች በጥንት ጊዜ ከነበሩ አጉል እምነቶችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካልሆኑ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች የመነጩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል የሚወዱት ሰው በሞት ለተለያቸው ሰዎች አበባ የመስጠት ልማድ ከአጉል ሃይማኖታዊ እምነት የመነጨ ሊሆን ይችላል። * በተጨማሪም ብዙውን ጊዜ ተባዕታይ ፆታ ካለው ሕፃን ጋር ተያይዞ የሚጠቀሰው ሰማያዊ ቀለም አጋንንትን ያርቃል ተብሎ ይታመን ነበር። ሽፋሽፍትንና ቅንድብን ቀለም መቀባት ከቡዳ እንደሚከላከል፣ የከንፈር ቀለም ደግሞ አጋንንት በአንዲት ሴት አፍ ውስጥ ገብተው እንዳይዟት ለመከላከል እንደሚረዳ ይታመን ነበር። ሌላው ቀርቶ አንድ ሰው ሲያዛጋ አፉን በእጁ መክደኑ እንኳ ነፍሱ በሰፊው በተከፈተው አፉ ሾልኮ ሊወጣ ይችላል ከሚለው ሐሳብ የመነጨ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ከሃይማኖት ጋር የነበራቸው ቁርኝት እየተመናመነ በመሄዱ ዛሬ እነዚህ ልማዶችና ባሕሎች ሃይማኖታዊ ትርጉም የሌላቸው ድርጊቶች ሆነዋል።

ክርስቲያኖችን የሚያሳስባቸው ጉዳይ

አንድ ክርስቲያን አንድን ባሕል ለመከተልም ሆነ ላለመከተል ውሳኔ ማድረግ እንዳለበት ሆኖ ሲሰማው በአንደኛ ደረጃ ሊያሳስበው የሚገባው ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው መሠረት አምላክ ያለው አመለካከት ምንድን ነው? የሚለው መሆን ይኖርበታል። ባለፉት ጊዜያት አንዳንድ ማኅበረሰቦች ምንም ጉዳት እንደሌላቸው አድርገው ይመለከቷቸው የነበሩትን አንዳንድ ልማዶች አምላክ አውግዟቸዋል። ከእነዚህም መካከል ልጆችን መሥዋዕት ማድረግ፣ ደምን አላግባብ መጠቀምና የተለያዩ የፆታ ብልግናዎች ይገኙበታል። (ዘሌዋውያን 17:​13, 14፤ 18:​1-30፤ ዘዳግም 18:​10) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ በሰፊው ከተለመዱት ባሕሎች መካከል አንዳንዶቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በቀጥታ የሚጋጩ ናቸው። ከእነዚህ መካከል እንደ ገና በዓልና በዓለ ትንሣኤ ካሉ ሃይማኖታዊ በዓላት ጋር ወይም ከመናፍስታዊ አምልኮ ጋር ግንኙነት ካላቸው በአጉል እምነት ላይ የተመሠረቱ ልማዶች ጋር ዝምድና ያላቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ባሕሎች ይገኙበታል።

ይሁን እንጂ በአንድ ወቅት አጠያያቂ ከሆኑ ልማዶች ጋር ዝምድና ስለነበራቸው በአሁኑ ጊዜ ግን በማኅበረሰቡ ውስጥ እንደ ጥሩ ምግባር ተደርገው ስለሚታዩ ባሕሎችስ ምን ለማለት ይቻላል? ለምሳሌ ያህል የቀለበት ሥርዓትንና ኬክ መቁረስን ጨምሮ በሠርግ ወቅት የሚከናወኑ በርካታ ልማዶች አረማዊ ምንጭ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ታዲያ ይህ ክርስቲያኖች እንደ እነዚህ ያሉትን ልማዶች መጠበቅ የለባቸውም ማለት ነውን? ክርስቲያኖች በአንድ አካባቢ ወይም በአንድ ወቅት ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ አንድምታ የነበረው መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኘውን እያንዳንዱን ልማድ በጥንቃቄ መመርመር ይኖርባቸዋል?

ጳውሎስ “የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ” በማለት ገልጿል። (2 ቆሮንቶስ 3:​17፤ ያዕቆብ 1:​25) አምላክ ይህን ነፃነት የራስ ወዳድ ፍላጎታችንን ለማሟላት እንደ ሰበብ አድርገን እንድንጠቀምበት ሳይሆን ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለይተን ማወቅ እንችል ዘንድ የማስተዋል ችሎታችንን ለማሰልጠን እንድንጠቀምበት ይፈልጋል። (ገላትያ 5:​13፤ ዕብራውያን 5:​14፤ 1 ጴጥሮስ 2:​16) በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንደተጣሱ የሚያሳይ ግልጽ የሆነ ማስረጃ እስከሌለ ድረስ የይሖዋ ምሥክሮች ድርቅ ያለ ሕግ ከማውጣት ይቆጠባሉ። ከዚያ ይልቅ እያንዳንዱ ክርስቲያን ጉዳዩን በመመዘን የራሱን የግል ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል።

ለሌሎች ጥቅም ማሰብ

ታዲያ ይህ ማለት የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በቀጥታ የሚቃረን እስካልሆነ ድረስ በማንኛውም ባሕል ውስጥ መካፈል ምንም ስህተት የለውም ማለት ነውን? በፍጹም። (ገላትያ 5:​13) አንድ ክርስቲያን የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን ‘የብዙዎችንም ጥቅም’ ማሰብ እንዳለበት ጳውሎስ አመልክቷል። “ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር” ማድረግ ይኖርበታል፤ እንዲሁም በእርሱ ምክንያት ሌሎች እንዲደናቀፉ መፍቀድ አይኖርበትም። (1 ቆሮንቶስ 10:​31-33) ስለዚህ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልግ አንድ ሰው ራሱን እንዲህ ብሎ መጠየቅ ይኖርበታል:- ‘ሌሎች ለዚህ ባሕል ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው? በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉት ሰዎች ባሕሉን የሚያያይዙት ተገቢ ያልሆነ ትርጉም ከሚያሰጥ ነገር ጋር ነው? በአንድ ባሕል ውስጥ መካፈሌ አምላክን ደስ የማያሰኙ ልማዶችን ወይም አስተሳሰቦችን እንደምደግፍ አድርጎ ያስቆጥረኛል?’​—⁠1 ቆሮንቶስ 9:​19, 23፤ 10:​23, 24

አንዳንድ ባሕሎች በጥቅሉ ሲታዩ ምንም ክፋት የሌለባቸው ሊመስሉ ቢችሉም እንኳ የአካባቢው ነዋሪዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚጋጭ መንገድ ይጠቀሙባቸው ይሆናል። ለምሳሌ ያህል አንድን ወቅት ጠብቆ አበባ መስጠት ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር የሚጋጭ ትርጉም ሊያሰጠው ይችላል። ታዲያ አንድን ክርስቲያን በአንደኛ ደረጃ ሊያሳስበው የሚገባው ነገር ምን መሆን ይኖርበታል? አንድን ባሕል አመጣጡን ለመመርመር የሚያበቃ ምክንያት ሊኖር ቢችልም አንዳንድ ጊዜ ባሕሉ ግለሰቡ አሁን በሚኖርበት ቦታና ወቅት በሚኖሩ ሰዎች ዘንድ ምን ትርጉም አለው ብሎ ማሰቡ ይበልጥ የተሻለ ይሆናል። አንድ ባሕል በዓመቱ ውስጥ በአንድ በተወሰነ ወቅት ወይም በአንድ በተወሰነ ሁኔታ ሥር ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ወይም አሉታዊ አንድምታ ያለው ከሆነ ክርስቲያኖች በዚያን ወቅት በባሕሉ ተካፋይ ላለመሆን በጥበብ ሊወስኑ ይችላሉ።

ጳውሎስ ክርስቲያኖች በትክክለኛ እውቀትና በተሟላ ማስተዋል ፍቅራቸው እንዲበዛ ጸልዮአል። ክርስቲያኖች ለብዙሃኑ ባሕል ሚዛናዊ አመለካከት በመያዝ ‘ነውር የሌለባቸው መሆን እንዲችሉና ለሌሎች እንቅፋት እንዳይሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትነው ይይዛሉ።’ (ፊልጵስዩስ 1:​9, 10) እንደዚሁም ‘ምክንያታዊነታቸው ለሰው ሁሉ’ ግልጽ ሆኖ እንዲታይ ያደርጋሉ።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​5

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 ስለ ሰው ዘር አመጣጥ የሚያጠኑ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ሙታን በሕይወት ያሉትን እንዳይተናኮሉ ለመከላከል አንዳንድ ጊዜ የአበባ እቅፍ እንደ ስጦታ ተደርጎ ለሙታን ይሰጥ ነበር።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አንድ ሰው ሲያዛጋ አፉን በእጁ መክደንና የሚወዱት ሰው በሞት ለተለያቸው ሰዎች አበባ መስጠትን የመሳሰሉ አንዳንድ ጥንታዊ ባሕሎች መጀመሪያ ላይ የነበራቸውን ትርጉም አጥተዋል