በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣው ያለ ደም የሚሰጥ ሕክምና

ተፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣው ያለ ደም የሚሰጥ ሕክምና

ተፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣው ያለ ደም የሚሰጥ ሕክምና

“ከደም ጋር ግንኙነት ያለው ሥራ የሚሠሩና ቀዶ ሕክምና የሚያደርጉ ሁሉ ያለ ደም ስለሚሰጠው ቀዶ ሕክምና ማሰብ አለባቸው።”​—⁠በአኔስቲዚኦሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ዮአኪም ቦልት፣ ሉትቪግዝሃፈን፣ ጀርመን

ሳይንቲስቶችና ሐኪሞች ኤድስ ያስከተለው አሳዛኝ ሁኔታ የቀዶ ሕክምና ክፍል ለአደጋ የሚያጋልጥ እንዳይሆን ለማድረግ ተጨማሪ እርምጃዎች እንዲወስዱ አስገድዷቸዋል። ይህ ጥብቅ የሆነ የደም ምርመራ ማድረግ የሚጠይቅ እንደሆነ የታወቀ ነው። ሆኖም ይህም እንኳ ቢሆን በደም የሚሰጠውን ሕክምና ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ እንደማያደርገው ጠበብት ይናገራሉ። “ህብረተሰቡ የደም አቅርቦት ከምንጊዜውም በበለጠ አስተማማኝ እንዲሆን ለማድረግ ጥሪቱን በሙሉ እያዋለ ቢሆንም እንኳ” ይላል ትራንስፊውዥን የተባለው መጽሔት፣ “የደም አቅርቦቱ ምንጊዜም ቢሆን ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ሊሆን ስለማይችል ታካሚዎች ጀነቲካዊ ልዩነት የሚኖረውን [የሌላ ሰው ደም] ላለመውሰድ እንደሚጥሩ እናምናለን።”

ብዙ ዶክተሮች ደም በመስጠት የሚካሄደውን ሕክምና በጥርጣሬ ዓይን እያዩት መሆኑ ምንም አያስደንቅም። “ደም መስጠት በመሠረቱ ጥሩ አይደለም፤ ለየትኛውም ታካሚ ደም ያለመስጠት ጥብቅ አቋም አለን” ሲሉ በሳን ፍራንሲስኮ፣ ካሊፎርንያ የሚገኙት ዶክተር አሌክስ ዛፖላንስኪ ተናግረዋል።

ሕዝቡም ቢሆን ደም መውሰድ የሚያስከትላቸውን አደጋዎች በመገንዘብ ላይ ነው። እንዲያውም በ1996 የተካሄደ አንድ ጥናት 89 በመቶ የሚሆኑት ካናዳውያን ደም ከመውሰድ ይልቅ ሌላ አማራጭ ሕክምና ማግኘት እንደሚመርጡ አመልክቷል። “እንደ ይሖዋ ምሥክሮች ደም አንወስድም የሚሉት ሁሉም ታካሚዎች አይደሉም” ይላል ጆርናል ኦቭ ቫስኩላር ሰርጀሪ። “ሆኖም ደም መውሰድ በደም ለሚተላለፉ በሽታዎች የሚያጋልጥና ተፈጥሯዊ የሆነውን የሰውነትን በሽታ መከላከያ ሥርዓት ሊያዛባ የሚችል መሆኑ ለታካሚዎቻችን በሙሉ አማራጭ የሕክምና ዘዴዎችን እንድንፈልግ የሚያስገድድ ግልጽ ማስረጃ ነው።”

ተመራጭ ዘዴ

ደስ የሚለው ነገር አማራጭ ዘዴ መኖሩ ነው። ያለ ደም የሚሰጥ ሕክምና አለ። ብዙዎቹ ታካሚዎች ይህን ዘዴ አማራጭ ሲጠፋ የሚወሰድ እርምጃ እንደሆነ አድርገው ሳይሆን ተመራጭ ሕክምና እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ደግሞም እውነት አላቸው። ብሪታንያዊው የቀዶ ሕክምና ስፔሽያሊስት ስቲቨን ጄፍሪ ፖላርድ ያለ ደም ቀዶ ሕክምና ከሚደረግላቸው ሰዎች መካከል ለበሽታ የሚጋለጡትና የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር “ደም ከሚወስዱት ታካሚዎች እኩል ይሆን እንደሆን እንጂ አይበልጥም። በተጨማሪም አብዛኛውን ጊዜ ያለ ደም ቀዶ ሕክምና የሚደረግላቸው ታካሚዎች ብዙውን ጊዜ ከደም ጋር ዝምድና ከሚኖራቸው ከቀዶ ሕክምና በኋላ ከሚከሰቱ ኢንፌክሽኖችና ውስብስብ ችግሮች ይጠበቃሉ” ብለዋል።

ያለ ደም የሚሰጠው ሕክምና ሊያድግ የቻለው እንዴት ነው? በአንድ በኩል ሲታይ ጥያቄው አስገራሚ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ያለ ደም የሚሰጠው ሕክምና በደም ከሚሰጠው ሕክምና በፊት የነበረ ነው። እንዲያውም በደም የሚሰጠው ሕክምና እስከ 20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ድረስ በቋሚነት ጥቅም ላይ መዋል የሚችልበት ደረጃ ላይ አልደረሰም ነበር። የሆነ ሆኖ ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ አንዳንዶች ያለ ደም የሚሰጠውን ሕክምና በስፋት ሲያስተዋውቁ ቆይተዋል። ለምሳሌ ያህል በ1960ዎቹ ዓመታት የታወቁት ቀዶ ሐኪም ዴንተን ኩሊ ልብ ሥራው ለተወሰነ ጊዜ እንዲያቆም በማድረግ ከተከናወኑት የመጀመሪያ ቀዶ ሕክምናዎች መካከል አንዳንዶቹን ያለ ደም አከናውነዋል።

በ1970ዎቹ ዓመታት ደም ከወሰዱ ታካሚዎች መካከል በሄፐታይተስ የተለከፉት ሰዎች ቁጥር እያደገ በመሄዱ ብዙ ዶክተሮች የደም አማራጮች መፈለግ ጀመሩ። በ1980ዎቹ ዓመታት በርከት ያሉ ትልልቅ የሕክምና ቡድኖች ያለ ደም ቀዶ ሕክምና ያካሂዱ ነበር። ከዚያም የኤድስ ወረርሽኝ ሲስፋፋ ይህንኑ ዘዴ የመጠቀም ፍላጎት ያደረባቸው ሌሎች ወገኖች እነዚህን የሕክምና ቡድኖች በተደጋጋሚ ያማክሩ ነበር። በ1990ዎቹ ዓመታት ብዙ ሆስፒታሎች ታካሚዎቻቸው ያለ ደም የሚሰጠውን ሕክምና መምረጥ የሚችሉባቸው ፕሮግራሞች አዘጋጅተዋል።

በአሁኑ ጊዜ ዶክተሮች በዘልማድ ደም በመስጠት ይከናወኑ የነበሩ ቀዶ ሕክምናዎችንና በድንገተኛ ሁኔታዎች የሚከናወኑ ሕክምናዎችን ያለ ደም በተሳካ ሁኔታ ማካሄድ ችለዋል። “የልብ፣ የሰውነት ፈሳሽ ማስተላለፊያ ሥሮች፣ የማኅፀንና የፅንስ፣ የአጥንት፣ እንዲሁም የፊኛ ከባድ ቀዶ ሕክምናዎችን ያለ ደም ወይም ያለ ደም ተዋጽኦዎች በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ይቻላል” ሲሉ ዲ ኤች ደብሊው ዎንግ በካኔዲያን ጆርናል ኦቭ አኔስቲዢያ ላይ ገልጸዋል።

ያለ ደም የሚከናወን ቀዶ ሕክምና ያለው አንዱ ጥቅም የተሻለ ጥንቃቄ የተሞላበት ሕክምና የሚያስገኝ መሆኑ ነው። “ብዙ ደም እንዳይፈስ በማድረግ ረገድ የቀዶ ሐኪሙ ችሎታ ትልቅ ሚና ይጫወታል” ሲሉ በክሌቭላንድ ኦሃዮ የቀዶ ሕክምና ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ቤንጃሚን ጄ ራይክስታይን ተናግረዋል። አንድ የደቡብ አፍሪካ የሕግ መጽሔት አንዳንድ ጊዜ ያለ ደም የሚከናወን ቀዶ ሕክምና “ጊዜ የማይወስድ፣ ይበልጥ ከብክለት የጠራና ከፍተኛ ወጪ የማይጠይቅ” ሊሆን ይችላል ብሏል። በተጨማሪም “ብዙውን ጊዜ ከቀዶ ሕክምናው በኋላ እንክብካቤ ለማድረግ የሚወጣው ወጭ አነስተኛና ጊዜ ቆጣቢ ሆኖ ተገኝቷል” ሲል አክሎ ገልጿል። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ያለ ደም በሚሰጥ ሕክምና ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞች ያሏቸው 180 የሚያክሉ ሆስፒታሎች ሊኖሩ ከቻሉባቸው ምክንያቶች ጥቂቶቹ እነዚህ ናቸው።

ደምና የይሖዋ ምሥክሮች

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆኑ ምክንያቶች ደም አይወስዱም። * ሆኖም የደም ምትክ የሆኑ ሕክምናዎችን ይቀበላሉ፤ እንዲህ ዓይነቱን ሕክምና ለማግኘትም ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። “የይሖዋ ምሥክሮች የተሻለ ሕክምና የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው” ሲሉ ዶክተር ሪቻርድ ኬ ስፔንስ በአንድ የኒው ዮርክ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና ዲሬክተር በነበሩበት ጊዜ ተናግረዋል። “በቡድን ደረጃ ሲታዩ አንድ ቀዶ ሐኪም ከሚገጥሙት ታካሚዎች ሁሉ የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው ናቸው።”

ዶክተሮች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ያለ ደም ብዙ የቀዶ ሕክምና ዘዴዎች በመጠቀም ችሎታቸውን በሚገባ አዳብረዋል። የስርአተ ልብ ወቧንቧ ቀዶ ሐኪም የሆኑትን የዴንተን ኩሊ ተሞክሮ ተመልከት። የሕክምና ቡድናቸው ከ27 ዓመት በላይ በሚሆን ጊዜ ውስጥ በ663 የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ያለ ደም የልብ ቀዶ ሕክምና ማከናወን ችሏል። የተገኙት ውጤቶች የልብ ቀዶ ሕክምናዎች ያለ ደም በተሳካ ሁኔታ ሊከናወኑ እንደሚችሉ በግልጽ አሳይተዋል።

እርግጥ ነው፣ ብዙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን ደም አንወስድም በሚለው አቋማቸው ተችተዋቸዋል። ሆኖም በታላቋ ብሪታንያና በአየርላንድ ሰመመን ሰጪ ባለሙያዎች ማኅበር የታተመ አንድ መመሪያ መጽሐፍ የምሥክሮቹን አቋም “ለሕይወት ያላቸውን አክብሮት የሚያሳይ ምልክት” ሲል ጠርቶታል። እውነቱን ለመናገር ከሆነ የምሥክሮቹ ጥብቅ አቋም ሁሉም ሰው ይበልጥ አስተማማኝ የሆነ ሕክምና ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ እንዲመቻች በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። “ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው የይሖዋ ምሥክሮች በኖርዌይ የጤና አገልግሎት ትልቅ ዘርፍ ላይ ማሻሻያ የሚደረግበትን አቅጣጫ ከማመልከታቸውም በላይ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ጫና ፈጥረዋል” ሲሉ የኖርዌይ ናሽናል ሆስፒታል ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ስቴይን ኤ ኤቨንሰን ጽፈዋል።

ዶክተሮች ያለ ደም ሕክምና እንዲሰጡ ለመርዳት የይሖዋ ምሥክሮች ጠቃሚ የሆነ የመረጃ አገልግሎት አቋቁመዋል። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከ1, 400 በላይ የሚሆኑ ሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ያለ ደም ከሚሰጥ ሕክምና ጋር ዝምድና ባላቸው ከ3, 000 በላይ በሚሆኑ ጽሑፎች አማካኝነት ለዶክተሮችና ለተመራማሪዎች የሕክምና መረጃ ለመስጠት ዝግጁ ናቸው። “በዛሬው ጊዜ የምሥክሮቹ ሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ባከናወኑት ሥራ የተነሳ ሳያስፈልግ በደም አማካኝነት ከሚሰጠው ሕክምና መጠበቅ የቻሉት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ሳይሆኑ ሕሙማን በጠቅላላ ናቸው” ሲሉ በቦስተን የሕግ ኮሌጅ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ቻርልስ ባረን ተናግረዋል። *

የይሖዋ ምሥክሮች ያለ ደም ስለሚሰጥ ሕክምና ያጠናቀሩት መረጃ በሕክምና መስክ ለተሰማሩ ለብዙዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ አስገኝቷል። ለምሳሌ ያህል አውቶትራንስፊውዥን:- ቴራፒዩቲክ ፕሪንስፕልስ ኤንድ ትሬንድስ የተባለው መጽሐፍ ደራሲዎች መረጃዎች ሲያጠናቅሩ በደም ምትክ ሊሰጡ ስለሚችሉ የሕክምና አማራጮች መረጃ ለማግኘት የይሖዋ ምሥክሮችን ጠይቀው ነበር። ምሥክሮቹ የጠየቁትን መረጃ በደስታ ሰጥተዋቸዋል። ከጊዜ በኋላ ደራሲዎቹ በአመስጋኝነት ስሜት እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ባደረግነው ጥናት ደም በደም ሥር በመስጠት የሚከናወነውን ሕክምና ማስወገድ የሚቻልባቸው እንዲህ ያሉ እጥር ምጥን ያሉና የተሟሉ ዝርዝር ስልቶች አላገኘንም።”

በሕክምና መስክ የታየው ዕድገት ብዙዎች ያለ ደም ስለሚሰጠው ሕክምና እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ይህ ወዴት ይመራን ይሆን? የኤድስ ቫይረስን ያገኙት ፕሮፌሰር ሉክ ሞንታንዬ “በዚህ መስክ ያለን ግንዛቤ እየተሻሻለ መሄዱ ደም በደም ስር በመስጠት የሚካሄደው ሕክምና አንድ ቀን መክሰም እንዳለበት ያመለክታል” ሲሉ ገልጸዋል። እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን የደም ምትክ የሆኑ ነገሮች የሰዎችን ሕይወት በመታደግ ላይ ይገኛሉ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.16 የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ግብዣ ሲቀርብላቸው ለሆስፒታል የሕክምና ባለሞያዎች ገለጻ ያደርጋሉ። ከዚህም በተጨማሪ እርዳታ እንዲሰጡ በሚጠየቁበት ጊዜ ታካሚዎች አስቀድመው ከሐኪሙ ጋር ግልጽና ቀጣይ የሆነ የሐሳብ ልውውጥ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

አንዳንድ ዶክተሮች ምን ይላሉ?

‘ያለ ደም የሚሰጠው ቀዶ ሕክምና ለይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ታካሚዎች አስፈላጊ ነው። እያንዳንዱ ዶክተር ይህን ማድረግ ያለበት ይመስለኛል።’​— በጀርመን፣ ሉትቪግዝሃፈን በአኔስቲዚኦሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ዮአኪም ቦልት

“ደም በመስጠት የሚከናወነው ሕክምና ከቀድሞው በተሻለ ደረጃ ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ጊዜም እንኳ በሰውነት የተፈጥሮ መከላከያ ዘዴ ላይ እክል ሊፈጥር፣ ለሄፐታይተስ ወይም በፆታ ግንኙነት ለሚተላለፉ በሽታዎች ሊያጋልጥ፣ አልፎ ተርፎም ሌሎች ችግሮች ሊያስከትል ይችላል።”​— በሕክምና ረዳት ክሊኒካዊ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ቴሬንስ ጄ ሳኪ

“አብዛኞቹ ሐኪሞች ደም የመስጠት ልማድ አላቸው። ቀዶ ሕክምና ለሚያደርገው ታካሚ ሁሉ ደም ይሰጣሉ። እኔ ግን እንደዚያ አላደርግም።”​— በሳን ፍራንሲስኮ የልብ ተቋም ውስጥ የልብ ቀዶ ሕክምና ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር አሌክስ ዛፖላንስኪ

“ለሁሉም ታካሚ የግድ ደም መስጠትን የሚጠይቅ ሆድ ነክ ቀዶ ሕክምና አለ ብዬ አላምንም።”​— በጀርመን፣ ዬና በቀዶ ሕክምና ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ዮሐነስ ሼሌ

[ሥዕሎች]

ዶክተር ዮአኪም ቦልት

ዶክተር ቴሬንስ ጄ ሳኪ

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ያለ ደም የሚሰጥ ሕክምና

ከሚከናወንባቸው መንገዶች አንዳንዶቹ

ፈሳሾች:- ሪንገርስ ላክቴት ሶሉሽን፣ ዴክስትራን፣ ሃይድሮክሲኢቲል ስታርችና ሌሎችም የደም መጠን ተጠብቆ እንዲቆይ በማድረግ የደም መጠን ሲቀንስ የሚከሰተውን ክውታ (shock)) ለመከላከል ይረዳሉ። በአሁኑ ጊዜ ሙከራ እየተደረገባቸው ያሉት አንዳንድ ፈሳሾች ኦክስጅን ማጓጓዝ ይችላሉ።

መድኃኒቶች:- በጀነቲካዊ ምህንድስና የተፈበረኩ ፕሮቲኖች ቀይ የደም ሕዋሳት (ኢሪትሮፖይቲን)፣ እንክብሊተ ደም (ኢንተርሉኪን-11) እና የተለያዩ ነጭ የደም ሕዋሳት (ጂ ኤም- ሲ ኤስ ኤፍ፣ ጂ- ሲ ኤስ ኤፍ) እንዲባዙ ሊያደርጉ ይችላሉ። ሌሎች መድኃኒቶች ደግሞ በቀዶ ሕክምና ወቅት የሚፈሰውን ደም መጠን በእጅጉ ይቀንሳሉ (አፕሮቲኒን፣ አንቲፋይብረኖሊቲክስ) ወይም አጣዳፊ የደም መፍሰስ ችግርን ለመቀነስ ይረዳሉ (ዴስሞፕሬሲን)።

የደም መፍሰስን ለማቆም የሚያገለግሉ ባዮሎጂያዊ ነገሮች:- ከኮላጂንና ከሴሉሎስ የተሠሩ ደረቦችን (pads) ቁስሉ ላይ በማድረግ የሚፈሰውን ደም ማቆም ይቻላል። የዘህ (fibrin) ሙጫዎችና ማሸጊያዎች ቁስሉን ለመድፈን ወይም ስፋት ያለውን በመድማት ላይ ያለ ኅብረ ሕዋስ ለመሸፈን ሊያገለግሉ ይችላሉ።

ደምን መልሶ መጠቀም:- በቀዶ ሕክምና ወይም በከባድ ጉዳት ወቅት የሚፈስሰውን ደም በደም ማዘዋወሪያ መሣሪያዎች መልሶ መጠቀም ይቻላል። ደሙ ተጣርቶ ባልተቋረጠ የደም ዝውውር አማካኝነት ወደ ታካሚው ሰውነት ሊገባ ይችላል። ሁኔታው በጣም ከባድ በሚሆንበት ጊዜ በዚህ ዘዴ በመጠቀም በሊትሮች ሊለካ የሚችል ደም መልሶ ወደ ሰውነት ማስገባት ይቻላል።

የቀዶ ሕክምና መገልገያዎች:- አንዳንድ መሣሪያዎች የደም ስሮችን የመቁረጡንና መልሶ የማሸጉን ሥራ በአንድነት ያከናውናሉ። ሌሎች መሣሪያዎች በአንድ ሕብረ ሕዋስ ላይ የተከሰተን ሰፋ ያለ ቦታን የሚሸፍን የመድማት ችግር ሊያስወግዱ ይችላሉ። ላፐረስኮፕና ሰውነትን ብዙም የማይቀድዱ መሣሪያዎች ትልልቅ ብጣቶች በሚኖሩበት ጊዜ የሚከሰተው ዓይነት ከፍተኛ የደም መፍሰስ ችግር ሳይኖር ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ያስችላሉ።

የቀዶ ሕክምና ዘዴዎች:- የቀዶ ሕክምናው ቡድን ልምድ ካካበቱ ሐኪሞች ጋር መማከርን ጨምሮ ጥንቃቄ የተሞላበት ዝግጅት ማድረጉ ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና እክሎችን ለማስወገድ ይረዳል። የሚፈሰውን ደም ለማቆም ፈጣን እርምጃ መውሰዱ በጣም አስፈላጊ ነው። ምንም እርምጃ ሳይወሰድ ከ24 ሰዓት በላይ ካለፈ የታካሚው የመሞት ዕድል በእጅጉ ሊጨምር ይችላል። ትልልቅ ቀዶ ሕክምናዎችን በርከት ወዳሉ ትንንሽ ቀዶ ሕክምናዎች መለወጡ የሚፈስሰው ደም ጠቅላላ መጠን እንዲቀንስ ለማድረግ ይረዳል።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ያለ ደም የሚሰጥ ሕክምና አዲሱ “መደበኛ የሕክምና ዘዴ”?

ንቁ! ዘጋቢ ያለ ደም የሚሰጥ ሕክምና የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች በተመለከተ ከአራት የሙያው ጠበብት ጋር ውይይት አድርጓል።

በሃይማኖታዊ እምነቶቻቸው ምክንያት ደም ከማይወስዱት ታካሚዎች በተጨማሪ ያለ ደም ሕክምና እንዲደረግላቸው ፍላጎት እያሳዩ ያሉት እነማን ናቸው?

ዶክተር ሽፓን:- ብዙውን ጊዜ በሕክምና ማዕከላችን ያለ ደም ሕክምና እንዲደረግላቸው ጥያቄ የሚያቀርቡት ጥሩ ግንዛቤ ያላቸው ታካሚዎች ናቸው።

ዶክተር ሻንደር :- በ1998 በግል ምክንያቶች ሳቢያ ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ ያልሆኑት ታካሚዎች በሃይማኖታዊ እምነቶቻቸው የተነሳ ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ ካልሆኑት ታካሚዎች ቁጥር በልጦ ተገኝቷል።

ዶክተር ቦይድ :- ለምሳሌ ያህል የካንሰር ሕሙማንን መጥቀስ ይቻላል። ደም ካልወሰዱ ይበልጥ ማገገም እንደሚችሉና በሽታውም እምብዛም እንደማይመላለስባቸው በተደጋጋሚ ጊዜያት ታይቷል።

ዶክተር ሽፓን :- ብዙውን ጊዜ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮችንና ቤተሰቦቻቸውን የምናክመው ያለ ደም ነው። ቀዶ ሐኪሞች እንኳ ሳይቀሩ ደም እንዳንሰጥ ይጠይቁናል! ለምሳሌ ያህል አንድ ቀዶ ሐኪም ቀዶ ሕክምና ታደርግ ስለነበረችው ሚስቱ ሊያነጋግረን መጥቶ “አደራችሁን ደም እንዳትሰጧት” ብሎን ነበር።

ዶክተር ሻንደር :- እኔ ያለሁበት የሰመመን መስጫ ክፍል አባላት ‘ደም የማይወስዱት ታካሚዎችም ምንም ችግር አልገጠማቸውም፣ እንዲያውም በተሻለ ሁኔታ ላይ ያሉ ይመስላሉ። ሁለት ዓይነት መስፈርት የምንከተለው ለምንድን ነው? ይሄኛው የተሻለ የሕክምና ዘዴ ከሆነ ለሁሉም ልንጠቀምበት ይገባል’ ብለዋል። ስለዚህ አሁን ያለ ደም የሚደረገውን ሕክምና መደበኛ የሕክምና ዘዴ አድርገን እንደምንከተል ተስፋ እናደርጋለን።

ሚስተር ኧርንሾው :- ያለ ደም የሚከናወነው ቀዶ ሕክምና በተለይ ለይሖዋ ምሥክሮች ተስማሚ እንደሆነ እሙን ነው። ሆኖም ሁሉንም ሰው ማከም የምንፈልገው በዚህ መንገድ ነው።

ያለ ደም የሚከናወነው ሕክምና ወጪው ከፍተኛ ነው ወይስ አነስተኛ?

ሚስተር ኧርንሾው :- ወጪ ይቀንሳል እንጂ የበለጠ ወጪ አይጠይቅም።

ዶክተር ሻንደር :- ያለ ደም የሚሰጠው ሕክምና የሚጠይቀው ወጪ በ25 በመቶ ዝቅ ያለ ነው።

ዶክተር ቦይድ :- ያለው ጥቅም ይሄ ብቻ ቢሆን እንኳ ልንጠቀምበት ይገባል።

ያለ ደም በሚሰጠው ሕክምና ረገድ ምን ያህል ዕድገት አድርገናል?

ዶክተር ቦይድ :- ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ ያለ ይመስለኛል። አሁን ባለበት የሚያቆም አይሆንም። በየጊዜው ደም እንዳንጠቀም የሚገፋፉ አሳማኝ የሆኑ አዳዲስ ምክንያቶች እያገኘን ነው።

[ሥዕሎች]

ዶክተር ዶናት አር ሽፓን በአኔስቲዚኦሎጂ ፕሮፌሰር፣ ዙሪክ፣ ስዊዘርላንድ

ዶክተር አርዬ ሻንደር በአኔስቲዚኦሎጂ ክሊኒካዊ ረዳት ፕሮፌሰር፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ሚስተር ፒተር ኧርንሾው፣ ኤፍ አር ሲ ኤስ በአጥንት ቀዶ ሕክምና ስፔሽያሊስትና አማካሪ፣ ለንደን፣ እንግሊዝ

ዶክተር ማርክ ኢ ቦይድ በፅንስና የማኅፀን ሕክምና ፕሮፌሰር፣ ካናዳ

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የታካሚው ድርሻ

▪ ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልግበት ሁኔታ ከመፈጠሩ በፊት የደም ምትክ ሊሆኑ ስለሚችሉ አማራጮች ከሐኪምህ ጋር ተነጋገር። በተለይ ነፍሰ ጡር የሆኑ ሴቶች፣ ትንንሽ ልጆች ያሏቸው ወላጆችና አረጋውያን እንዲህ ማድረጋቸው በጣም አስፈላጊ ነው።

▪ በተለይ ለእንዲህ ዓይነቱ ዓላማ የሚያገለግል ሕጋዊ ሰነድ ካለ እንዲደረግልህ የምትፈልጋቸውን ነገሮች በጽሑፍ አስፍር።

▪ ሐኪምህ ያለ ደም ሊያክምህ ፈቃደኛ ካልሆነ ፍላጎትህን ሊያሟላልህ የሚችል ሌላ ሐኪም ፈልግ።

▪ አንዳንዶቹ በደም ምትክ የሚሰጡ አማራጮች ውጤት እስኪያስገኙ ድረስ የተወሰነ ጊዜ ስለሚወስዱ ቀዶ ሕክምና እንደሚያስፈልግህ ካወቅክ ሕክምናውን የምትወስድበትን ጊዜ አታራዝም።