በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኤድስ ተጠቂ የሆኑ እናቶች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል

የኤድስ ተጠቂ የሆኑ እናቶች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል

የኤድስ ተጠቂ የሆኑ እናቶች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል

በምዕራብ ኢንዲስ የምትኖር ሲንቲያ * የተባለች አንዲት ሴት ሕፃን ልጅዋን ጡት ከማጥባትና ጡጦ ከማጥባት የቱን እንደምትመርጥ ግራ ተጋብታ ነበር። የቱን መምረጥ እንዳለባት ግልጽ ሊመስል ይችላል። ደግሞም የሕክምና ባለሙያዎች ከብዙ አሥርተ ዓመታት በፊት ጀምረው የእናት ጡት ወተት ‘ምትክ የማይገኝለት የሕፃናት ምግብ’ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ኖረዋል። ከዚህም ባሻገር ድሀ በሆነው ኅብረተሰብ ዘንድ ጡት ከሚጠቡ ሕፃናት ይልቅ ጡጦ የሚጠቡ ሕፃናት በተቅማጥ በሽታ የመሞት አጋጣሚያቸው 15 ጊዜ እጥፍ ነው። እንዲያውም በእናት ጡት ወተት ምትክ በሚሰጡ ምግቦች ሳቢያ በሚከሰቱ ችግሮች በየቀኑ 4, 000 የሚያክሉ ሕፃናት እንደሚሞቱ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) ያወጣቸው ሪፖርቶች ያስረዳሉ።

ሆኖም ጡት ላጥባ ወይስ አላጥባ የሚለው የሲንቲያ ጭንቀት ሌላም አሳሳቢ ነገር ይጨምራል። ሲንቲያን የሰውነት የተፈጥሮ መከላከያ ቅስም ሰባሪ በሆነው በኤድስ አማጪው ኤች አይ ቪ ቫይረስ ያስለከፋት ባሏ ነው። ሲንቲያ ልጅዋን ከተገላገለች በኋላ ደግሞ አንዲት የቫይረሱ ተጠቂ የሆነች እናት ከሰባት አንድ እጅ በጡት ወተት አማካኝነት ለልጅዋ ቫይረሱን የማስተላለፍ አጋጣሚ እንዳላት ተገነዘበች። * በመሆኑም ልጅዋን ጡት በማጥባት አለዚያም ጡጦ በማጥባት ከሚመጣው ችግር አንዱን መምረጥ ነበረባት።

በከፍተኛ ደረጃ የኤድስ ተጠቂ በሆኑት የዓለማችን ክፍሎች ከ10 ነፍሰ ጡር ሴቶች ውስጥ 2 ወይም 3 የሚሆኑት በኤች አይ ቪ የተለከፉ ናቸው። በአንድ አገር ምርመራ ከተደረገላቸው ነፍሰ ጡር ሴቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በቫይረሱ ተለክፈዋል። “ይህ አስደንጋጭ አሃዝ ሳይንቲስቶች ለዚህ በሽታ መድኃኒት ለማግኘት እንዲሯሯጡ አድርጓቸዋል” ሲል የተመድ ራዲዮ ዘግቧል። ለዚህ አሳሳቢ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት ስድስት የተመድ ድርጅቶች ልምዳቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጥሪታቸውን በማስተባበር ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመዋጋት ዩ ኤን ኤድስ (UNAIDS) በመባል የሚታወቅ የተቀናጀ የተባበሩት መንግሥታት ፕሮግራም አቋቁመዋል። * ይሁን እንጂ ዩ ኤን ኤድስ የተገነዘበው ነገር ቢኖር ኤድስ ለፈጠረው ግራ መጋባት መፍትሄ ማግኘት ቀላል እንዳልሆነ ነው።

ቀላል ለሆነው መፍትሔ ጋሬጣ የሆኑ ውስብስብ ችግሮች

የእናት ጡት ወተትንና ኤች አይ ቪ ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፍበትን መንገድ በተመለከተ ስፔሻሊስት የሆኑት ኤድዝ ዋይት አንድ ሕፃን በቫይረሱ የመለከፍ አጋጣሚውን በእጥፍ ከፍ ስለሚያደርገው፣ በበለጸጉ አገሮች የሚገኙ የኤች አይ ቪ ተጠቂ የሆኑ እናቶች ልጆቻቸውን ጡት ማጥባት እንደሌለባቸው የጤና ባለሙያዎች እየመከሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። የተሻለው አማራጭ ሕፃኑ ምትክ የሆኑ ምግቦችን እንዲመገብ ማድረግ ይመስላል። ሆኖም አንዳንድ ቴዎሪዎች ተጨባጭ ማስረጃ እንዳለው ተደርገው በቀላሉ ተቀባይነት በሚያገኙባቸው ታዳጊ አገሮች ይህን ቀላል መፍትሄ ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ ነው።

ሌላው እንቅፋት ደግሞ ከማኅበራዊ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው። ጡት ማጥባት በሰፊው በተለመደባቸው አገሮች አንዲት ሴት ልጅዋን ጡጦ አጠባች ማለት በኤች አይ ቪ መለከፏን ይፋ አደረገች ማለት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አንዲት ሴት ከታወቀብኝ ነቀፋ ይደርስብኛል፣ ሰው ሁሉ ያገልለኛል አልፎ ተርፎም እደበደባለሁ ብላ ልትፈራ ትችላለች። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሴቶች በኤች አይ ቪ መለከፋቸው እንዳይታወቅባቸው ለማድረግ ያላቸው ምርጫ ልጃቸውን ጡት ማጥባት እንደሆነ ይሰማቸዋል።

ሌሎች መሰናክሎችም አሉ። ለምሳሌ ያህል የ20 ዓመቷን የማርገሬትን ሁኔታ ተመልከት። ቢያንስ 95 ከመቶ እንደሚሆኑት እንደሌሎቹ የኡጋንዳ የገጠር ሴቶች ሁሉ እሷም የኤች አይ ቪ ምርመራ አድርጋ አታውቅም። ሆኖም ማርገሬት የተጨነቀችበት ምክንያት አላት። የመጀመሪያ ልጅዋ የሞተባት ሲሆን ሁለተኛ ልጅዋ ደግሞ መንምኖ ሊሞት ደርሷል። ማርገሬት ኤች አይ ቪ ሊኖርባት ቢችልም ሦስተኛ ልጅዋን በቀን አሥር ጊዜ ጡት ታጠባዋለች። “ምንጊዜም ቢሆን ልጄን የእናት ጡት ወተት ምትክ የሆኑ ምግቦች መመገብ አልችልም” ትላለች። ለምን? ማርገሬት ለእናት ጡት ወተት ምትክ እንዲሆኑ ተብለው የሚዘጋጁት ምግቦች ዋጋ በመንደሯ ከሚገኝ ከአንድ ቤተሰብ ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢ አንድ ነጥብ አምስት ጊዜ እንደሚበልጥ ተናግራለች። ይህ ምግብ ያለ ምንም ክፍያ በነፃ የሚገኝ ቢሆን እንኳ ለመበጥበጫ የሚሆን ለሕፃኑ ጤንነት ምንም የማያሰጋ ንጹህ ውኃ ማግኘት ሌላው ችግር ነው። *

በኤች አይ ቪ የተለከፉ እናቶች ተገቢ የሆነ የንጽህና አጠባበቅ የሚያደርጉበት፣ የእናት ጡት ወተት ምትክ የሚሆኑ ምግቦችን በበቂ መጠን የሚያገኙበትና በአስተማማኝ ሁኔታ የተጣራ ውኃ የሚያገኙበት መንገድ ቢፈጠር ከእነዚህ ችግሮች መካከል አንዳንዶቹን መቅረፍ ይቻል ነበር። ይህን ማድረግ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነውን? ሊሆን ይችላል። ሆኖም በጣም የሚያስገርመው እነዚህን ዝግጅቶች ለማድረግ ከገንዘብም በላይ የሚያስፈልገው ነገር ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያ የመስጠት ጉዳይ ነው። በዓለማችን ላይ የመጨረሻ ድሀ የሚባሉት አንዳንዶቹ ታዳጊ አገሮች ወታደራዊ ወጪያቸው ለጤናና ለትምህርት ከሚያወጡት ወጪ ሁለት እጥፍ ገደማ እንደሚበልጥ የተመድ ሪፖርት ያስረዳል።

ስለ ፀረ ኤድስ መድኃኒቶችስ ምን ለማለት ይቻላል?

ኤች አይ ቪ ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፍበትን ሁኔታ በእጅጉ ሊቀንስ ይችላል የሚባል በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ዋጋው ብዙም ውድ ያልሆነ ኤ ዜድ ቲ የተባለ ቀላል መድኃኒት መገኘቱን የተመድ ሳይንቲስቶች ሪፖርት አድርገዋል። በዩ ኤን ኤድስ ድጎማ የዚህ መድኃኒት ዋጋ ወደ 50 ዶላር ዝቅ እንዲል ተደርጓል። ከዚህም በላይ ደግሞ 3 ዶላር ብቻ በሚያስወጣው ኔቫይረፔን በተባለው መድኃኒት አማካኝነት የኤች አይ ቪ ተጠቂ የሆኑ እናቶችንና የወለዱትን ሕፃን ማከም ኤች አይ ቪ እንዳይተላለፍ በመግታት ረገድ ከኤ ዜድ ቲ ይበልጥ ውጤታማ መሆኑን ሐምሌ 1999 የኤድስ ተመራማሪዎች አስታውቀው ነበር። ኔቫይረፔን የተባለው መድኃኒት በዓመት 400, 000 ሕፃናትን በኤች አይ ቪ እንዳይለከፉ ሊከላከል እንደሚችል የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ሆኖም አንዳንዶች ይህ ሕክምና ኤች አይ ቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በመከላከል ብቻ የተወሰነ ስለሆነ የኋላ ኋላ እናትዬዋ የኤድስ ተጠቂ በምትሆንበትና በምትሞትበት ጊዜ ልጁ የሙት ልጅ ሆኖ ይቀራል በማለት ትችት ይሰነዝራሉ። ተመድ ግን ከዚህ ውጭ ያለው አማራጭ እነዚህ ምንም የማያውቁ እምቦቀቅላዎች በቫይረሱ ተለክፈው አዝጋሚና አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ እንዲሞቱ መፍቀድ ይሆናል ሲል ምላሽ ሰጥቷል። በተጨማሪም በኤች አይ ቪ የተለከፉ እናቶች ለበርካታ ዓመታት በሕይወት ሊኖሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ለምሳሌ ያህል በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችውን ሲንቲያን እንውሰድ። በኤች አይ ቪ እንደተለከፈች ያወቀችው በ1985 ልጅዋን በተገላገለችበት ጊዜ ሲሆን ከዚያ ወዲህ ሳትታመም ከስምንት ዓመት በላይ ኖራለች። ልጅዋ ሲወለድ ኤች አይ ቪ የነበረበት ቢሆንም እንኳ ሁለት ዓመት ሲሞላው ከቫይረሱ ነፃ ሆኗል።

ለሕይወት ምንም የማያሰጋ አካባቢና እንደ ኤድስ የመሰለው መቅሰፍት ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኝበት ጊዜ በደጅ እንደቀረበ በመግለጽ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጽናና ዋስትና ይሰጣል። (ራእይ 21:​1-4) ‘በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ የማይልበት’ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ይሖዋ አምላክ ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 33:​24) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ዘላቂ መፍትሄ በተመለከተ ሊነግሩህ ዝግጁ ናቸው። የበለጠ ለማወቅ በቀጥታ ለዚህ መጽሔት አሳታሚዎች መጻፍ ወይም በአካባቢህ የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች ማነጋገር ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 እውነተኛ ስሟ አይደለም።

^ አን.3 የኤች አይ ቪ ተጠቂ የሆኑ እናቶች በጡት ወተት አማካኝነት በቀን ከ500 እስከ 700 የሚደርሱ ሕፃናት በቫይረሱ እንዲለከፉ እንደሚያደርጉ የዩኒሴፍ ዘገባ ያስረዳል።

^ አን.4 ግንባር የፈጠሩት ስድስቱ ድርጅቶች ዩኒሴፍ፣ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም፣ የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ፣ የዓለም ጤና ድርጅት፣ የዓለም ባንክና የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት ናቸው። ዩ ኤን ኤድስ የተመሠረተው በ1995 ነው።

^ አን.8 ሕፃኑ ሁለቱንም ማለትም ጡትም እንዲጠባ ምትክ የሚሆኑ ምግቦችንም እንዲመገብ ማድረግ በኤች አይ ቪ የመለከፍ አጋጣሚውን ከፍ ሊያደርገው እንደሚችልና የእናት ጡት ወተት የቫይረሱን አቅም የሚያዳክም ፀረ ቫይረስ ንጥረ ነገር ሊኖረው እንደሚችል በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች ያስረዳሉ። ይህ እውነት ከሆነ ደግሞ አደጋው እያለም እንኳ ቢሆንም ሕፃኑን የእናት ጡት ወተት ብቻ እንዲመገብ ማድረጉ የተሻለ ምርጫ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ የዚህ ጥናት ግኝቶች ገና መረጋገጥ አለባቸው።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

WHO/E. Hooper