በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የከባድ ድብደባ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች የሚሆን እርዳታ

የከባድ ድብደባ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች የሚሆን እርዳታ

የከባድ ድብደባ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች የሚሆን እርዳታ

ዴንማርክ የሚገኘው የንቁ ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

“የተሰበረ መንፈስ ከመጠገን ይልቅ የተሰበረ አጥንት መጠገን ይቀላል።”​—⁠ዶክተር ኢንገ ጄነፍከ

በአንድ የአውሮፓ ከተማ ውስጥ አንድ ወጣት ጸጥ ባለ ጎዳና በእግሩ በመንሸራሸር ላይ ሳለ በመስተዋት ውስጥ የሚታዩትን በአንድ ሱቅ ውስጥ ያሉ ሸቀጦች ለማየት ቆም ይላል። ድንገት እጆቹ መንቀጥቀጥ እግሮቹ መብረክረክ ጀመሩ። አንገቱን በእጁ አንቆ ያዘ። ለካስ እንደዚህ የፈራው በመስተዋቱ ነጸብራቅ የደንብ ልብስ የለበሱ ሁለት ፖሊሶችን ተመልክቶ ነው። ይህ ወጣት እንዲህ እንዲፈራ የሚያደርገው ምንም የሠራው ወንጀል አልነበረም። ሆኖም የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ሲያይ ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኝ ቦታ ከዓመታት በፊት አሰቃቂ በሆነ መንገድ የደረሰበት ከባድ ድብደባ ፊቱ ላይ ድቅን አለበት።

ተመሳሳይ ገጠመኝ ያላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶች አልፎ ተርፎም ልጆች ሊኖሩ ይችላሉ። ምናልባትም የምታውቀው አንድ ሰው የዚህ ድርጊት ሰለባ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ጎረቤትህ የሚኖር አንድ ስደተኛ በሕይወቱ ውስጥ ይህ ዓይነቱ አሰቃቂ በደል ደርሶበት ይሆናል። ልጆቹ ከልጆችህ ጋር አንድ ትምህርት ቤት ይማሩ ይሆናል። ምናልባትም አንተ የምታውቀው ብዙም ከሰው የማይቀርብ፣ ጭምትና ጨዋ ጎረቤት መሆኑን ብቻ ይሆናል። ሆኖም ውጫዊ ሁኔታ ውስጣዊውን ስሜት ሊደብቅ ይችላል፤ የከባድ ድብደባ ሰለባ የሆነ ሰው በደረሰበት ሁኔታ ምክንያት የሚሰማውን አካላዊም ሆነ ሥነ ልቦናዊ ሥቃይ በውስጡ አምቆ በመያዝ ከውጭ ደህና መስሎ ሊታይ ይችላል። አንድ የሆነ እይታ ወይም ድምፅ መጥፎ የሆነ ትዝታውን ሊቀሰቅስበት ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የደረሰበት አንድ ሰው እንዲህ በማለት ገልጿል:- “የሕፃን ልጅ ለቅሶ በሰማሁ ቁጥር እስር ቤት ውስጥ ሲያለቅሱ የሰማኋቸው ሰዎች ድምፅ ይመጣብኛል። ዥው የሚል ድምፅ ስሰማ ደግሞ በተገረፍኩበት ወቅት አለንጋው እላዬ ላይ ከማረፉ በፊት የሚያሰማውን ድምፅ ያስታውሰኛል።”

ሰዎችን በመደብደብ የሚያሰቃዩት የፖለቲካ ጽንፈኞችና አሸባሪ ቡድኖች ብቻ አይደሉም። በብዙ አገሮች የወታደርና የፖሊስ ኃይሎችም ሰዎችን በመደብደብ ያሰቃያሉ። ለምን? በድብደባ ማሰቃየት ሰዎች መረጃ እንዲያወጡ፣ አስገድዶ ለማሳመን፣ የፈጸሙትን ጥፋት እንዲያወጡ ለማድረግ ወይም ለመበቀል የሚያስችል ፈጣንና ውጤታማ ዘዴ ተደርጎ ስለሚታይ ነው። በድብደባ ከባድ ስቃይ የደረሰባቸውን ሰዎች በመርዳት ብዙ ልምድ ያላቸው ዴንማርካዊቷ ዶክተር ኢንገ ጄነፍከ አንዳንድ ጊዜ መንግሥታት “ሥልጣን የሚጨብጡትም ሆነ በሥልጣን ላይ የሚቆዩት ሰዎችን በድብደባ በማሰቃየት ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ይህ ሁኔታ የተፈጸመበት አንድ ሰው እንደሚከተለው ሲል አስቀምጦታል:- “በድብደባ አንተን ወኔ ቢስ በማድረግ በመንግሥት ላይ ነቀፋ መሰንዘር ምን ሊያስከትል እንደሚችል ለሌሎች መቀጣጫ ያደርጉሃል።”

ብዙዎች ሰዎችን እየደበደቡ ማሰቃየት በጨለማው ዘመን የቀረ ነገር እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። እንዲያውም በ1948 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ “ማንም ሰው ከባድ ድብደባም ሆነ ጭካኔ የሞላበት፣ ሰብዓዊነት የጎደለው ወይም ሰብዓዊ ክብርን የሚያዋርድ ድርጊትም ሆነ ቅጣት ሊፈጸምበት አይገባም” ይላል። (አንቀጽ 5) ሆኖም ከዓለም ስደተኞች መካከል 35 ከመቶ የሚሆኑት የከባድ ድብደባ ሰለባ እንደሆኑ አንዳንድ ኤክስፐርቶች ይገምታሉ። ሰዎችን በድብደባ ማሠቃየት ይህን ያህል የተስፋፋው ለምንድን ነው? በሰለባዎቹ ላይስ የሚያስከትለው ጉዳት ምን ያክል ነው? እነዚህንስ ሰዎች እንዴት መርዳት ይችላል?

የሚያስከትለው ጉዳት

የከባድ ድብደባ ሰለባ የሆኑ አብዛኞቹ ሰዎች በሌላ አካባቢ አዲስ ሕይወት ለመጀመር ሲሉ አገራቸውን ጥለው መሰደዳቸው ምንም አያስገርምም። ይሁን እንጂ አካባቢ ቢቀይሩም የደረሰባቸው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ሥቃይ አብሯቸው ይኖራል። ለምሳሌ ያህል ይህ ሰው ሌሎች ጓደኞቹን ወይም ዘመዶቹን ከዚህ ዓይነቱ በደል መታደግ አለመቻሉ ዕረፍት ሊነሳው ይችላል። ያገኘውን ሰው ሁሉ ጆሮ ጠቢ አድርጎ በመመልከት ሌሎችን ክፉኛ መጠርጠር ሊጀምር ይችላል። ደራሲ የሆኑት ካርስተን ጄንሰን “የከባድ ድብደባ ሰለባ የሆነ ሰው ምንጊዜም ባይተዋር እንደሆነ ይቀራል። ማንንም ሰው አያምንም” ሲሉ ተናግረዋል።

የጥቃቱ ሰለባ የሚሰማው አካላዊና አእምሮአዊ ሥቃይ ራሱንም ሆነ እሱን ለመርዳት እየጣረ ያለውን ሰው ግራ ሊያጋባ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ አካላዊ ጉዳቱ በቀላሉ ታክሞ ሲድን ሥነ ልቦናዊ ጉዳቱ ግን አስቸጋሪ ይሆናል። ዶክተር ጄነፍከ “መጀመሪያ ላይ ‘ያው አጥንታቸውን ጠግነን ወደ ቤታቸው መላክ ነው’ ብለን አስበን ነበር” ሲሉ ተናግረዋል። “ሆኖም ውስጥ ውስጡን የሚበላቸው ሥነ ልቦናዊ ሥቃዩ መሆኑን ወዲያውኑ ተገነዘብን።” የሆነ ሆኖ “ብዙ ዓመታት የሚፈጅ ቢሆንም እንኳ የከባድ ድብደባ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን መርዳትና ከደረሰባቸው ሁኔታ እንዲላቀቁ መርዳት እንደሚቻል ማወቃችን የሚያስደስት ነው” ሲሉ ዶክተር ጄነፍከ ገልጸዋል።

በ1982 ዶክተር ጄነፍከ ከሌሎች የዴንማርክ ሐኪሞች ጋር በመሆን የከባድ ድብደባ ሰለባ ለሆኑ ስደተኞች የሕክምና እርዳታ የሚሰጥ አንድ አነስተኛ ቡድን በኮፐንሐገን ብሔራዊ ሆስፒታል ውስጥ አቋቋሙ። ከዚህ አነስተኛ ጅምር በመነሳት የከባድ ድብደባ ሰለባ ዓለም አቀፍ የተሐድሶ መምሪያ (አይ አር ሲ ቲ) በሚል መጠሪያ የሚታወቅ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው ድርጅት ተቋቋመ። ዋና መሥሪያ ቤቱን በኮፐንሐገን ያደረገው ይህ ድርጅት በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ከ100 በላይ በሚሆኑ ማዕከሎች አማካኝነት የተሐድሶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። ይህ ድርጅት ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የከባድ ድብደባ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች የሕክምና እርዳታ በመስጠት ረገድ ብዙ ተሞክሮ እያገኘ መጥቷል።

እርዳታ መስጠት የሚቻልበት መንገድ

ብዙውን ጊዜ የዚህ ጉዳት ሰለባ የሆኑ ሰዎች የደረሰባቸውን ሁኔታ በግልጽ መናገር መቻላቸው ትልቅ ጥቅም አለው። “ከዛሬ 20 ዓመት በፊት” ይላል አንድ የአይ አር ሲ ቲ ሪፖርት “የከባድ ድብደባ ሰለባ የሆኑ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ችግራቸው ድርብ ነበር። አንደኛው አካላዊ/ሥነ ልቦናዊ ችግር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ስለደረሰባቸው ሥቃይ መናገር አለመቻላቸው ነበር።”

እውነት ነው እንዲህ ስለመሰለ መጥፎ ትዝታ ማውራት የሚያስደስት አይደለም። ሆኖም ይህ ሁኔታ የደረሰበት ሰው ለአንድ ጓደኛው ስለዚህ ጉዳይ በምሥጢር ሊያጫውተው ቢፈልግና ጓደኛው ደግሞ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ሳይሆን ቢቀር የችግሩ ሰለባ የሆነው ሰው ይበልጥ ወደ ተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ሊገባ ይችላል። ስለሆነም የከባድ ድብደባ ሰለባ የሆነ ሰው አንድ የሚያስብለት ሰው እንዳለ ማወቅ ያስፈልገዋል። እርግጥ ነው ማንም ሰው የሌሎችን የግል ሕይወት ለማውጣጣት መሞከር የለበትም። ዞሮ ዞሮ ምሥጢሩን መቼና ለማን መንገር እንደሚፈልግ የሚወስነው ራሱ የችግሩ ሰለባ የሆነው ሰው ነው።​—⁠ምሳሌ 17:​17፤ 1 ተሰሎንቄ 5:​14

አብዛኞቹ ኤክስፐርቶች ድብደባው ላስከተለው አካላዊም ሆነ አእምሮአዊ ጉዳት ሕክምና እንዲሰጥ ያዝዛሉ። አንዳንዶቹ ሰለባዎች የባለ ሙያ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። የሚሰጠው ሕክምና የአተነፋፈስ ሥርዓት ልምምድንና የሐሳብ ግንኙነት ማድረግን ይጨምራል። * በአብዛኛው በቅድሚያ ትኩረት ከሚሰጣቸው ነገሮች አንዱ የሐፍረት ስሜት ነው። አንዲት ሐኪም በተደጋጋሚ ጊዜ ተገድዳ ለተደፈረችና ለተደበደበች አንዲት ሴት እንደሚከተለው ስትል ነግራታለች:- “የሚሰማሽ የሐፍረት ስሜት ያለና የሚጠበቅ ነው። ሆኖም ማፈር ያለባቸው ይህን ድርጊት የፈጸሙብሽ ሰዎች እንጂ አንቺ አይደለሽም።”

ከማጎሪያ ካምፕ በሕይወት የተረፉ

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በሂትለር ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብርን የሚያዋርድ አሰቃቂ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። ከእነዚህም መካከል ሃይማኖታዊ እምነታቸውን የሚያስክድ ነገር አናደርግም በማለታቸው ስደት የደረሰባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙበታል። እምነታቸው እንደዚያ ዓይነት ፈታኝ ሁኔታዎችን በጽናት እንዲወጡ እንደረዳቸው ጥርጥር የለውም። እንዴት?

እነዚህ ክርስቲያኖች ማጎሪያ ካምፕ ከመጨመራቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ትጉህ የአምላክ ቃል ተማሪዎች ነበሩ። ስለሆነም ስደቱ ሲነሳ ግር አላላቸውም ወይም የሚደርስባቸው ሥቃይ ወዲያው ባለማብቃቱ በአምላክ ላይ አላማረሩም። አምላክ ለምን ክፋትን እንደፈቀደና የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ እንዴት ወደ ፍጻሜው እንደሚያመጣው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ተረድተው ነበር። ይሖዋ ‘ፍትህን እንደሚወድ’ እና ሰዎች በመሰሎቻቸው ላይ የሚፈጽሙት በደል በጣም እንደሚያስቆጣው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ተምረዋል።​—⁠መዝሙር 37:​28፤ ዘካርያስ 2:​8, 9

በተጨማሪም እነዚህ ከማጎሪያ ካምፕ በሕይወት የተረፉ ሰዎች በዚያ የደረሰባቸው ስቃይ ካስከተለባቸው ተጽዕኖ ጋር መታገል ግድ ሆኖባቸዋል። ይህን በሚያደርጉበት ጊዜ የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር መከተላቸው በእጅጉ ጠቅሟቸዋል። በአንድ የሮማውያን እስር ቤት ይማቅቅ የነበረው ጳውሎስ (መታሰሩ የተወሰነ ጭንቀት አሳድሮበት መሆን አለበት) ለእምነት ባልደረቦቹ እንደሚከተለው ሲል ጽፎ ነበር:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።”​—⁠ፊልጵስዩስ 1:​13፤ 4:​6, 7

እነዚህ በአቋማቸው የጸኑ ሰዎች አምላክ ምድርን ገነት ለማድረግ ቃል እንደገባ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት ተምረዋል። በዚያ ገነት ውስጥ እንደ ከባድ ድብደባ ያሉት ሰብዓዊ ክብርን ዝቅ የሚያደርጉ ድርጊቶች የሚያስከትሏቸው መጥፎ ውጤቶች ሙሉ በሙሉ ይወገዳሉ።

የይሖዋ ምሥክሮች ይህን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ተስፋ ከ230 በሚበልጡ አገሮች ለሚገኙ ጎረቤቶቻቸው በማካፈል ላይ ናቸው። ተነዋዋጭ የሆነው የዓለም ሁኔታ ሰዎች በሰዎች ላይ በሚፈጽሙት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ሥቃይ ከደረሰባቸው ብዙ ግለሰቦች ጋር ያገናኛቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የከባድ ድብደባ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ሲያጋጥሟቸው ስለ ወደፊቱ ብሩህ ጊዜ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይነግሯቸዋል። የከባድ ድብደባ ሰለባ መሆን የሚያስከትለው ሥቃይ ጨርሶ ስለሚረሳበት ጊዜ የሚገልጽ ምሥራች በማሰማት ላይ በመሆናቸው ምንኛ ደስተኞች ናቸው!​—⁠ኢሳይያስ 65:​17፤ ራእይ 21:​4

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.15 ንቁ! ይሄ ሕክምና ይሻላል ይሄ አይሻልም የሚል ሐሳብ አይሰጥም። ክርስቲያኖች የሚከታተሉት ሕክምና ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የማይጋጭ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ማንም ሰው ከባድ ድብደባም ሆነ ጭካኔ የሞላበት፣ ሰብዓዊነት የጎደለው ወይም ሰብዓዊ ክብርን የሚያዋርድ ድርጊትም ሆነ ቅጣት ሊፈጸምበት አይገባም።”—⁠አንቀጽ 5፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መርዳት የምትችልበት መንገድ

ከባድ ድብደባ ካስከተለበት ተጽእኖ ጋር እየታገለ ያለ ሰው የምታውቅ ከሆነ የሚከተሉት ሐሳቦች ጠቃሚ ሆነው ልታገኛቸው ትችላለህ:-

● ችግሩን ተረዳለት። እንደሚከተለው ልትል ትችላለህ:- “በነበርክበት አገር ብዙ ችግር እንዳለ ሰምቻለሁ። ለመሆኑ አሁን አንተ እንዴት ነህ?”—ማቴዎስ 7:​12፤ ሮሜ 15:​1

● የሰውዬውን የግል ሕይወት ለማውጣጣት ወይም ያለ ፍላጎቱ እርዳታ ለመስጠት አትሞክር። ከዚህ ይልቅ ደግና አሳቢ ሁን። ምሥጢሩን ቢያካፍልህ ለማዳመጥ ፈቃደኛ መሆንህን እንዲያውቅ አድርግ።—ያዕቆብ 1:​19

● በእያንዳንዱ ነገር የአንተ እርዳታ እንደሚያስፈልገው አድርገህ አታስብ። ለራሱ ያለውን አክብሮት ወይም ነፃነቱን እንዲያጣ አታድርግ። ዓላማህ የችግሩ ተካፋይ መሆን እንጂ ሙሉ በሙሉ ችግሩን መሸከም አይደለም።