በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የውጭ አገር ቋንቋ መማር ትፈልጋለህ?

የውጭ አገር ቋንቋ መማር ትፈልጋለህ?

ውጭ አገር ቋንቋ መማር ትፈልጋለህ?

ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

“እንደምንናገረው ቀላል አይደለም!” ብዙዎች የውጭ አገር ቋንቋ መማርን በተመለከተ በተለይ ለመማር ሙከራ ካደረጉ በኋላ ይህን የመሰለ አስተያየት ይሰነዝራሉ። እርግጥ ነው፣ የሌላ አገር ቋንቋ መማር እንዲህ የዋዛ አይደለም። ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ የተሳካላቸው ቢደከምለት የሚያስቆጭ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

አንድን አዲስ ቋንቋ ለመማር የሚያበቁ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ለምሳሌ ያህል አንድሩ የእረፍት ጊዜውን በፈረንሳይ አገር ለማሳለፍ እቅድ አወጣ። ከአገሬው ሕዝብም ጋር በራሳቸው ቋንቋ ለመነጋገር ፈለገ። ግዊዶ የተወለደው እንግሊዝ አገር ሲሆን ቤተሰቦቹ ግን የኢጣሊያ ተወላጆች ናቸው። “ከቋንቋው ዘዬ በስተቀር የማውቀው ነገር አልነበረኝም። ስለዚህም ጣሊያንኛን ጥርት አድርጌ መናገር ፈለግኩ” ሲል ተናግሯል። የዮናታን ወንድም በቅርቡ ወደ ውጭ አገር ሄዶ አንዲት ስፔናዊ ሴት አገባ። “ወንድሜን ለመጠየቅ በምሄድበት ጊዜ ከአዲሶቹ ዘመዶቼ ጋር በራሳቸው ቋንቋ ለመነጋገር ፈለግኩ” በማለት ዮናታን ይናገራል።

የውጭ አገር ቋንቋ መማር ሌሎች ጥቅሞችም ሊኖሩት ይችላሉ። “ራሴን በሌሎች ቦታ ማስቀመጥን አስተምሮኛል” በማለት ልዊዝ ትናገራለች። “የውጭ አገር ሰዎች ከእነርሱ የተለየ ቋንቋ ወደሚነገርበት አካባቢ በሚሄዱበት ጊዜ ምን ዓይነት ስሜት እንደሚሰማቸው የተረዳሁት አሁን ነው።” ፓሜላ ደግሞ ከቤተሰቦቿ ጋር ይበልጥ እንድትቀራረብ አድርጓታል። ያደገችው እንግሊዝ አገር በመሆኑ ቤተሰቦቿ የሚናገሩትን የቻይንኛ ቋንቋ አጥርታ መናገር አትችልም ነበር። በዚህም የተነሳ ፓሜላ ከእናቷ ጋር ብዙም ሳትቀራረብ አደገች። “ብዙም አናወራም ነበር” ትላለች ፓሜላ። “አሁን ግን ቻይንኛ መናገር ስለቻልኩ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ መቀራረብ የቻልን ከመሆኑም በላይ እርስ በርስ ያለን ዝምድና ተሻሽሏል።”

ስኬታማ ለመሆን የሚረዱ ነገሮች

አንድን የውጭ አገር ቋንቋ በሚገባ መማር ትችል ዘንድ ምን ሊረዳህ ይችላል? የውጭ አገር ቋንቋ በመማር ረገድ ስኬት ያገኙ በርካታ ሰዎች የሚከተሉትን ሐሳቦች ጎላ አድርገው ይገልጻሉ።

ውስጣዊ ግፊት። ግብህ ላይ ለመድረስ እንድትጣጣር የሚገፋፋ ምክንያት ሊኖርህ ያስፈልጋል። ከፍተኛ የሆነ ውስጣዊ ግፊት ያላቸው ተማሪዎች በጥቅሉ ሲታይ የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ።

ትሑት ሁን። ከራስህ ብዙ አትጠብቅ። በተለይ መጀመሪያ አካባቢ መሳሳት ያለ ነገር ነው። “ሰዎች ይስቁብሃል። ስለዚህ አንተም አብረሃቸው ሳቅ!” በማለት አሊሰን ትናገራለች። ቫለሪም ከዚህ ሐሳብ ጋር በመስማማት “ራስህን መራመድ ከሚለማመድ ልጅ ጋር ልታመሳስል ትችላለህ” በማለት ትናገራለች። “መደናቀፍህ የማይቀር ነው። ሆኖም እንደገና ተነስተህ መራመድህን ቀጥል።”

ታጋሽ ሁን። “የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ለእኔ በጣም አስቸጋሪ ነበሩ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ለምን አልተወዉም የሚል አሳብ ይመጣብኝ ነበር” በማለት ዴቪድ ይናገራል። ሆኖም “እያደር እየቀለለ ይሄዳል” በማለት ይገልጻል። የጂልም ሐሳብ ከዚህ የተለየ አይደለም። “ወደ ኋላ መለስ ብለህ እስካልተመለከትክ ድረስ እድገት ማድረግህን አታውቅም” በማለት ትናገራለች።

ተለማመድ። ያልተቋረጠ ልምምድ ማድረግ አዲሱን ቋንቋ አቀላጥፈህ እንድትናገር ይረዳሃል። ለጥቂት ደቂቃም ቢሆን በየቀኑ ልምምድ አድርግ። አንድ የመማሪያ መጽሐፍ እንደገለጸው “‘አልፎ አልፎ ረዘም ያለ ልምምድ ከማድረግ’ ይልቅ ‘ዘወትር በትንሽ በትንሹ ልምምድ ማድረግ’ ይመረጣል።”

ጠቃሚ መሣሪያዎች

የውጭ አገር ቋንቋ መማር የሚያስከትለውን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመቀበል ዝግጁ ነህ? ከሆነ የሚከተሉት መሣሪያዎች ዕድገትህን ሊያፋጥኑልህ ይችላሉ።

ቁርጥራጭ ካርዶች። እያንዳንዱ ካርድ የፊት ገጹ ላይ አንድ ቃል ወይም ሐረግ፣ በጀርባው ደግሞ ትርጉሙ ይኖረዋል። በምትኖርበት አካባቢ እንደዚህ ያሉ ካርዶችን ማግኘት የማይቻል ከሆነ በክላሴር ወረቀት የራስህን ማዘጋጀት ትችላለህ።

ለማስተማሪያነት የተዘጋጁ የቴፕና የቪዲዮ ክሮች። ቋንቋው በትክክል እንዴት እንደሚነገር ለማዳመጥ እነዚህ መሣሪያዎች ሊረዱህ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ዴቪድ መኪና በሚነዳበት ጊዜ ለቱሪስቶች የተዘጋጀ የቴፕ ክር በማዳመጥ የጃፓን ቋንቋን መሠረታዊ ደንቦች መማር ችሏል።

የኮምፒዩተር ፕሮግራሞች። አንዳንድ የኮምፒዩተር ፕሮግራሞች የራስህን ድምፅ መቅዳት እንድትችልና የአንተን የአነባበብ ስልት ከአገሬው ሰዎች አነባበብ ጋር ማወዳደር እንድትችል ይረዱሃል።

ራዲዮ እና ቴሌቪዥን። በምትኖርበት አካባቢ በምትማረው ቋንቋ የሚተላለፍ የራዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራም ካለ ምን ያህሉን መረዳት ትችል እንደሆነ ለማወቅ ፕሮግራሙን ከፍተህ ለምን አትከታተልም?

መጽሔቶችና መጻሕፍት። በአዲሱ ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎችን ለማንበብ ጥረት አድርግ። ይህንንም ስታደርግ ጽሑፎቹ ለመረዳት በጣም በሚያስቸግር ወይም በጣም ቀላል በሆነ መንገድ የተዘጋጁ አለመሆናቸውን አረጋግጥ። *

ቋንቋውን ጠንቅቆ ማወቅ

እርግጥ ነው፣ ይዋል ይደር እንጂ ቋንቋውን ከሚናገሩ ሰዎች ጋር መነጋገር ይኖርብሃል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ወደ ሌላ አካባቢ መሄድ አለብህ ማለት አይደለም። ከዚያ ይልቅ ምናልባት በምትኖርበት አገር በውጭ አገር ቋንቋ በሚጠቀም በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ላይ ልትገኝ ትችላለህ።

በዚያም ሆነ በዚህ የምትማርበት ዋነኛው ግብ ቃላትን ወይም ሀረግን ከትውልድ ቋንቋህ ወደ አዲሱ ቋንቋ መተርጎም ሳይሆን በአዲሱ ቋንቋ ለማሰብ መሆን አለበት። የምትማረውን አዲስ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን አንዳንድ ባሕልና ልማድ ለማወቅ ጥረት ብታደርግ ሊጠቅምህ ይችል ይሆናል። “የቋንቋውን ተናጋሪዎች ባሕል ሁኔታና ሥነ ምግባር ሳያውቁ አንድን ቋንቋ በትክክል ማወቅ አይቻልም” በማለት የቋንቋ ሊቅ የሆኑት ሮበርት ላዶ ይናገራሉ።

በመጨረሻም:- እድገትህ አዝጋሚ እንደሆነ ቢሰማህም እንኳ ተስፋ አትቁረጥ። አንድን አዲስ ቋንቋ መማር የማያቋርጥ ሂደት ነው። ከ20 ዓመት በፊት የምልክት ቋንቋ የተማረችው ጂል “ቋንቋው ሁልጊዜ ስለሚያድግ መማሬን አላቆምም” ስትል ተናግራለች።

እንግዲያው የውጭ አገር ቋንቋ መማር ትፈልጋለህ? የምትፈልግ ከሆነ በጣም ተፈታታኝ የሆነውን ሆኖም የኋላ ኋላ በእጅጉ የሚክሰውን ሥራ ለመጀመር ተዘጋጅ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.18 በአሁኑ ጊዜ ንቁ! በ83 ቋንቋዎች የሚታተም ሲሆን ከዚህ መጽሔት ጋር እየታተመ የሚወጣው መጠበቂያ ግንብ ደግሞ በ132 ቋንቋዎች ይታተማል። መጽሔቶቹ ሊገባ በሚችል መንገድ የሚዘጋጁ መሆናቸው ብዙዎቹ አዲስ ቋንቋ ለመማር በሚያደርጉት ጥረት ጠቃሚ ሆነው አግኝተዋቸዋል።

[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የትውልድ ቋንቋህን ከምትማረው ቋንቋ ጋር በማወዳደር . . .

. . . የምታውቃቸውን ቃላት ብዛት ማሳደግ ትችላለህ