በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደም በደም ሥር መስጠት—ለረጅም ዘመን ሲያወዛግብ የኖረ ሕክምና

ደም በደም ሥር መስጠት—ለረጅም ዘመን ሲያወዛግብ የኖረ ሕክምና

ደም በደም ሥር መስጠት—ለረጅም ዘመን ሲያወዛግብ የኖረ ሕክምና

“ቀይ የደም ሕዋሳት በዛሬው ጊዜ ጥቅም ላይ የዋሉ አዲስ መድኃኒቶች ቢሆኑ ኖሮ ሕጋዊ ፈቃድ ማግኘት በጣም አዳጋች ይሆን ነበር።”​—⁠ዶክተር ጄፍሪ መኩሎ

በ1667 የክረምት ወራት አንትዋን ሞርዋ የተባለ አንድ እብድ የፈረንሳዩ ንጉሥ የሉዊ አሥራ አራተኛ ዝነኛ ሐኪም ወደነበረው ወደ ዣን-ባቲስት ደኒ ፊት እንዲቀርብ ተደረገ። ደኒ ለሞርዋ የአእምሮ ሕመም ዓይነተኛ “መድኃኒት” ነበረው። የጥጃ ደም ቢሰጠው የታካሚው አእምሮ ሊረጋጋ እንደሚችል ተሰምቶት ነበር። ሆኖም ሞርዋ ጤንነቱ ሊመለስለት አልቻለም። ለሁለተኛ ጊዜ ደሙን ከወሰደ በኋላ በመጠኑ ተሻለው። ሆኖም ይህ ፈረንሳዊ ሰው ወዲያውኑ ሕመሙ አገረሸበትና ብዙም ሳይቆይ ሞተ።

ከጊዜ በኋላ ሞርዋ የሞተው አርስኒክ በተባለ ንጥረ ነገር ተመርዞ እንደሆነ የተረጋገጠ ቢሆንም እንኳ ደኒ በእንስሳት ደም ያካሄዳቸው ሙከራዎች በፈረንሳይ ውስጥ ከፍተኛ ውዝግብ አስነስተው ነበር። በመጨረሻ በ1670 ይህ የሕክምና ዘዴ ታገደ። ውሎ አድሮ የእንግሊዝ ፓርላማ አልፎ ተርፎም ጳጳሱ ራሳቸው ተመሳሳይ እርምጃ ወሰዱ። በቀጣዮቹ 150 ዓመታት ደም በደም ሥር መስጠት ፈጽሞ የተረሳ ነገር ሆኖ ነበር።

መጀመሪያ ላይ የተከሰቱ አደጋዎች

በ19ኛው መቶ ዘመን ደም በደም ሥር የመስጠቱ ሂደት እንደገና ብቅ አለ። ይህ የሕክምና ዘዴ እንዲያንሠራራ በማድረግ ግንባር ቀደሙን ሚና የተጫወተው ጄምስ ብላንዴል የተባለ እንግሊዛዊ አዋላጅ ሐኪም ነው። ብላንዴል የተሻሻሉ ዘዴዎችንና የረቀቁ መሣሪያዎችን በመጠቀም እንዲሁም መሰጠት ያለበት የሰው ደም ብቻ ነው የሚል አቋም በመያዝ ይህ የሕክምና ዘዴ ዳግመኛ ትኩረት እንዲያገኝ አደረገ።

ሆኖም በ1873 ኤፍ ጌዜሊየስ የተባለ አንድ ፖላንዳዊ ዶክተር የደረሰበት አንድ አስደንጋጭ ግኝት የሕክምና ዘዴው ዕድገት አዝጋሚ እንዲሆን አደረገው:- ደም በደም ሥር በመውሰድ ከታከሙት ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለሕልፈተ ሕይወት ተዳረጉ። የታወቁ ሐኪሞች ይህን ሲገነዘቡ የሕክምና ዘዴውን ማውገዝ በመጀመራቸው ሕክምናው እንደገና እየከሰመ ሄደ።

ከዚያም በ1878 ፈረንሳዊው ሐኪም ዦርዥ አዬም የደም ምትክ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል ሲል የገለጸውን ሳላይን ሶሉሽን አዘጋጀ። ሳላይን ሶሉሽን ከደም በተለየ መልኩ የጎንዮሽ ጉዳት የሌለው ከመሆኑም በላይ የመርጋት ባሕርይ የለውም፤ ከቦታ ወደ ቦታ ለመውሰድም አመቺ ነው። በመሆኑም የአዬም ሳላይን ሶሉሽን በስፋት ጥቅም ላይ ዋለ። የሚያስገርመው ግን ደም እንደገና ተመራጭ መሆኑ ነው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?

በ1900 ኦስትሪያዊው ፓቶሎጂስት ካርል ላንድስታይነር የተለያዩ የደም ዓይነቶች መኖራቸውንና አንዱ የደም ዓይነት ከሌላው የደም ዓይነት ጋር ላይስማማ እንደሚችል ተገነዘበ። ቀደም ባሉት ጊዜያት ደም በደም ሥር በመስጠት የተከናወኑት ብዙዎቹ ሕክምናዎች መጨረሻቸው ሳያምር መቅረቱ ምንም አያስደንቅም! አሁን ግን ደሙን የሚለግሰው ሰው ደም ዓይነትና ደሙን የሚወስደው ሰው ደም ዓይነት ተመሳሳይ መሆኑን በማረጋገጥ ብቻ ሁኔታውን መለወጥ ይቻላል። ሐኪሞች ይህን ግንዛቤ ሲያገኙ በዚህ ሕክምና ላይ ያላቸው እምነት እንደገና ተጠናከረ። ለአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅታዊ ምላሽ ሆኖ ነበር።

ደም በመስጠት የሚከናወን ሕክምና እና ጦርነት

በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለቆሰሉ ወታደሮች ደም በገፍ ይሰጥ ነበር። እርግጥ ደም ወዲያውኑ የሚረጋ በመሆኑ በፊት በፊት ወደ አውደ ግንባሮች ማጓጓዙ ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነበር ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በኒው ዮርክ ሲቲ ማውንት ሳይናይ ሆስፒታል ውስጥ ይሠሩ የነበሩት ዶክተር ሪቻርድ ሉሶን ሶድየም ሲትሬት በተባለ ፀረ ደም እርጋት ስኬታማ ሙከራ አካሄዱ። አንዳንድ ዶክተሮች ይህን አስደሳች ግኝት እንደ ተአምር አድርገው ተመልክተውት ነበር። “ፀሐይን ባለችበት ማቆም የተቻለ ያህል ነበር” ሲሉ በዘመኑ ታዋቂ ሐኪም የነበሩት ዶክተር ቤርትራም ኤም ቤርንሃይም ጽፈዋል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የደም ፍጆታ ጨምሮ ነበር። “አሁኑኑ ደም ስጡ፣” “ደማችሁ ሕይወቱን ሊታደግ ይችላል” እንዲሁም “እሱ ደሙን ሰጥቷል። እናንተስ ደማችሁን ትሰጣላችሁ?” የሚሉ መፈክሮችን የያዙ ፖስተሮች በየቦታው ተለጥፈው ነበር። ሕዝቡ ደም እንዲለግስ ለቀረበለት ጥሪ ከፍተኛ ምላሽ ሰጥቷል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 13, 000, 000 አሃድ (units) ደም ተለግሶ ነበር። ለንደን ውስጥ ከ260, 000 ሊትር በላይ የሚሆን ደም ተሰብስቦ እንደተከፋፈለ ይገመታል። እርግጥ ብዙም ሳይቆይ በግልጽ እንደታየው ደም በደም ሥር መስጠት የተለያዩ የጤና ችግሮች ሊያስከትል ይችላል።

ደም ወለድ በሽታ

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በሕክምናው ዓለም የታዩት ትልልቅ እመርታዎች ቀደም ሲል ፈጽሞ የማይታሰቡ የነበሩ አንዳንድ ቀዶ ሕክምናዎችን ማከናወን እንዲቻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በመሆኑም ሐኪሞች ደም በደም ሥር መስጠት መደበኛ የኦፕራሲዮን ዘዴ እንደሆነ አድርገው መመልከት በመጀመራቸው ለዚህ ሕክምና የሚውለውን ደም የሚያቀርብ በዓመት በብዙ ቢልዮን የሚቆጠር ዶላር የሚያተርፍ ዓለም አቀፋዊ ተቋም ብቅ አለ።

ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ከደም ጋር ዝምድና ያለው አንድ በሽታ በጣም አሳሳቢ እየሆነ መጣ። ለምሳሌ ያህል በኮርያ ጦርነት ወቅት በደም ሥራቸው ፕላዝማ ከተሰጣቸው መካከል 22 በመቶ ገደማ የሚሆኑት በሄፐታይተስ ተለክፈዋል። ይህ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከነበረው ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በሦስት እጥፍ ገደማ ይበልጣል። የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከሎች በ1970ዎቹ ዓመታት ደም በደም ሥራቸው በመውሰዳቸው ሳቢያ በየዓመቱ 3, 500 ሰዎች በሄፐታይተስ በሽታ እየተለከፉ ይሞቱ እንደነበረ ገምተዋል። ሌሎች ደግሞ ቁጥሩ ከዚህ አሥር እጥፍ እንደሚበልጥ ገምተዋል።

የደም ምርመራ በመሻሻሉና ደም ለጋሾችን ይበልጥ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መምረጥ በመቻሉ በሄፐታይተስ ቢ የሚለከፉ ሰዎች ቁጥር ቀንሷል። ሆኖም አዲስና አንዳንድ ጊዜም ለሕልፈተ ሕይወት የሚዳርግ ሄፐታይተስ ሲ የተባለ ቫይረስ ከባድ ጉዳት አድርሷል። አራት ሚልዮን አሜሪካውያን በቫይረሱ እንደተለከፉ የሚገመት ሲሆን ከእነዚህ መካከል በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት የቫይረሱ ተጠቂ ሊሆኑ የቻሉት በወሰዱት ደም አማካኝነት ነው። እርግጥ ከጊዜ በኋላ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ምርመራ በማድረግ የሄፐታይተስ ሲን የስርጭት መጠን መቀነስ ተችሏል። ሆኖም አንዳንዶች አዳዲስ የሆኑ አደገኛ ሁኔታዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉና መፍትሔም የሚገኝላቸው ብዙ ጉዳት ካደረሱ በኋላ እንደሚሆን ይገምታሉ።

ሌላ ቅሌት:- በኤች አይ ቪ የተበከለ ደም

በ1980ዎቹ ዓመታት ደም ኤድስ አማጭ በሆነው ኤች አይ ቪ ቫይረስ ሊበከል እንደሚችል ተረጋገጠ። መጀመሪያ ላይ የደም ባንክ ባለቤቶች የደም አቅርቦታቸው በኤድስ የተበከለ ሊሆን ይችላል የሚለውን ሐሳብ መቀበሉ ቀፍፏቸው ነበር። ብዙዎቹ ኤች አይ ቪ የፈጠረውን ስጋት በጥርጣሬ ዓይን ነበር የተመለከቱት። ዶክተር ብሩስ ኤቫት እንዳሉት ከሆነ “ሁኔታውን አንድ በበረሃ ሲቅበዘበዝ የቆየ ሰው ‘ከሌላ ፕላኔት የመጣ አካል አየሁ’ ብሎ እንደተናገረ ያህል አድርገው ነው የተመለከቱት። ቢሰሙትም እንኳ አላመኑበትም።”

ሆኖም በብዙ አገሮች በኤች አይ ቪ የተበከለ ደም በመስጠት የተፈጸሙ ቅሌቶች ተጋልጠዋል። በፈረንሳይ ከ1982 እስከ 1985 ባለው ጊዜ ውስጥ በደም ሥር በተሰጣቸው ደም አማካኝነት ከ6, 000 እስከ 8, 000 የሚሆኑ ሰዎች በኤች አይ ቪ እንደተለከፉ ተገምቷል። በአፍሪካ ውስጥ በኤች አይ ቪ ከተለከፉት ሰዎች መካከል 10 በመቶዎቹ እንዲሁም በፓኪስታን በኤድስ ከተያዙት ሰዎች መካከል 40 በመቶዎቹ ለዚህ በሽታ የተዳረጉት በደም ሥራቸው በተሰጣቸው ደም ሳቢያ ነው። በዛሬው ጊዜ በደም ላይ የሚካሄደው ምርመራ በመሻሻሉ ባደጉት አገሮች በደም ሳቢያ በኤች አይ ቪ የሚለከፉ ሰዎች ቁጥር በጣም ጥቂት ነው። ይሁን እንጂ የምርመራ ሂደቱ በሌለባቸው በማደግ ላይ ባሉ አገሮች እንዲህ ዓይነቱ ስርጭት አሁንም ድረስ በጣም አስቸጋሪ ሆኗል።

በመሆኑም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያለ ደም ሕክምና እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። ይሁን እንጂ ይህ አስተማማኝ አማራጭ ነውን?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ደምን በደም ሥር መስጠት መደበኛ የሕክምና ዘዴ አይደለም

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ በየዓመቱ 3, 000, 000 የሚሆኑ ታካሚዎች ከ11, 000, 000 አሃድ በላይ የሚሆኑ ቀይ የደም ሕዋሳት በደም ሥራቸው ይሰጣቸዋል። አንድ ሰው ይህን ከፍተኛ ቁጥር ሲመለከት ሐኪሞች ደም በመስጠት ረገድ ጥብቅ መስፈርት እንዳላቸው አድርጎ ያስብ ይሆናል። ሆኖም ዘ ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦቭ ሜድስን “ደም መስጠትን በተመለከተ አንድ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ” በቂ መረጃዎች አለመኖራቸው የሚያስገርም ነው ሲል ገልጿል። መሰጠት ያለበት ምንድን ነው? ምንስ ያህል? በሚለው ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን ደም መሰጠቱ ራሱ አስፈላጊ ነው አይደለም በሚለው ጉዳይ ላይም ሰፊ ልዩነት አለ። “ደም የመስጠቱ ጉዳይ የተመካው በታካሚው ሳይሆን በሐኪሙ ላይ ነው” ይላል አክታ አኔስቴዚኦሎጂካ ቤልጂካ የተባለው የሕክምና መጽሔት። ከላይ ያለውን ስንመለከት ዘ ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦቭ ሜድስን ላይ ታትሞ የወጣ አንድ ጥናት እንዳመለከተው “ደም ከተሰጣቸው ሰዎች መካከል 66 በመቶ የሚሆኑት ደም የወሰዱት ሳያስፈልግ መሆኑ” ሊያስደንቀን አይገባም።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የደም ፍጆታ ጨምሮ ነበር

[የሥዕል ምንጮች]

Imperial War Museum, London

U.S. National Archives photos