በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መዋሸት—ስህተት የማይሆንበት ሁኔታ ሊኖር ይችላልን?

መዋሸት—ስህተት የማይሆንበት ሁኔታ ሊኖር ይችላልን?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

መዋሸት​— ስህተት የማይሆንበት ሁኔታ ሊኖር ይችላልን?

“አንዳንድ ጊዜ ዝርዝር ማብራሪያ ሲሰጡ ከመዋል ትንሽ ውሸት ተናግሮ መገላገል ይቀላል።”

ይህ አስተያየት ብዙ ሰዎች ውሸትን በተመለከተ ያላ​ቸውን አመለካከት ያንጸባርቃል። ውሸት ማንንም ሰው የማይጎዳ እስከሆነ ድረስ ምንም ጥፋት የለውም የሚል መሠረታዊ እምነት አላቸው። እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ “እንደ ሁኔታው የሚሠራ ግብረ ገብ” የሚል አካዴሚያዊ ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ልትከተለው የሚገባው የፍቅር ሕግ ተብሎ የሚጠራውን ሕግ ብቻ ነው የሚል ፈሊጥ አለው። በሌላ አባባል ደራሲዋ ዳያን ኮምፕ እንደገለጹት “በቅን ልቦና ተነሳስተህ ያደረግከው እስከሆነ ድረስ ዋሸህ አልዋሸህ . . . የሚያመጣው ለውጥ የለም” ማለት ነው።

በዛሬው ጊዜ ባለው ዓለም ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት በእጅጉ ተስፋፍቶ ይገኛል። የታወቁ ፖለቲከኞችና ሌሎች የዓለም መሪዎች ውሸት በመናገር የፈጸሟቸው ቅሌቶች ኅብረተሰቡን አናግተውታል። ብዙ ሰዎች ይህ መንፈስ ተጽዕኖ ያሳደረባቸው በመሆኑ እውነት ለመናገር የነበራቸውን ቁርጥ አቋም አላልተዋል። እንዲያውም በአንዳንድ መስኮች ውሸት በይፋ የሚሠራበት ፖሊሲ ሆኗል። “እንድዋሽ ይከፈለኛል። ከዋሸሁ የገበያውን ውድድር ማሸነፍ የምችል ከመሆኑም በላይ በዓመቱ መጨረሻ ላይ የምስጋና ደብዳቤ አገኛለሁ። . . . መዋሸት በሁሉም ቦታ የችርቻሮ ሽያጭ ሥልጠና ዋና ክፍል የሆነ ይመስላል” ስትል አንዲት አሻሻጭ የተሰማትን ቅሬታ ገልጻለች። ብዙዎች ሌላውን እስካልጎዳ ድረስ ትንሽ ውሸት መናገር ምንም ጥፋት የለውም የሚል እምነት አላቸው። ይህ እውነት ነውን? ክርስቲያኖች ውሸት መናገራቸው ስህተት የማይሆንባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ?

የመጽሐፍ ቅዱስ ከፍ ያለ የአቋም ደረጃ

መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉንም ዓይነት ውሸት አጥብቆ ያወግዛል። “ሐሰትን የሚናገሩትን ታጠፋቸዋለህ” ሲል መዝሙራዊው ተናግሯል። (መዝሙር 5:​6፤ ራእይ 22:​15ን ተመልከት።) መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 6:​16-19 ላይ ይሖዋ የሚጠላቸውን ሰባት ነገሮች ይዘረዝራል። “ሐሰተኛ ምላስ” እና “በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር” በዚህ ዝርዝር ውስጥ በግልጽ ሰፍረው ይገኛሉ። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ በሐሰት ምክንያት የሚደርሱ ጉዳቶችን የሚጠላ በመሆኑ ነው። ኢየሱስ ሰይጣንን ሐሰተኛና ነፍሰ ገዳይ ብሎ ሊጠራ የቻለበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። ሰይጣን የተናገራቸው ውሸቶች የሰውን ልጅ ለመከራና ለሞት ዳርገውታል።​—⁠ዘፍጥረት 3:​4, 5፤ ዮሐንስ 8:​44፤ ሮሜ 5:​12

ሐናንያና ሰጲራ የደረሰባቸው ነገር ይሖዋ ውሸትን ምን ያህል አክብዶ እንደሚመለከት ጎላ አድርጎ ያሳያል። እነዚህ ሁለት ሰዎች በጣም ለጋስ መስለው ለመቅረብ በማሰብ ሆን ብለው ሐዋርያትን ዋሽተው ነበር። ያደረጉት ነገር ሆን ተብሎና ታስቦበት የተደረገ ነገር ነበር። በመሆኑም ሐዋርያው ጴጥሮስ “እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም” ሲል ተናግሯል። ይህን በማድረጋቸው ሁለቱም በአምላክ እጅ ተቀስፈዋል።​—⁠ሥራ 5:​1-10

ዓመታት ካለፉ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ” ሲል መክሯቸዋል። (ቆላስይስ 3:​9) ይህ ጥብቅ ምክር በተለይ ለክርስቲያን ጉባኤ በጣም አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ ፍቅር የእውነተኛ ተከታዮቹ መለያ ምልክት እንደሚሆን ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:​34, 35) እንዲህ ዓይነቱ ግብዝነት የሌለበት ፍቅር ሊያድግና ሊዳብር የሚችለው ፍጹም የሆነ ሐቀኝነትና የመተማመን መንፈስ በሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ ነው። አንድ ሰው ሁልጊዜ የሚናገረው እውነት ነው ብለን ልንተማመንበት ካልቻልን ያን ሰው ለማፍቀር ልንቸገር እንችላለን።

ሁሉም ዓይነት ውሸት ተቀባይነት የሌለው ቢሆንም እንኳ አንዳንድ ውሸቶች ከሌሎቹ ይበልጥ ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው የኃፍረት ስሜት ተሰምቶት ወይም ፈርቶ ሊዋሽ ይችላል። ሌላው ደግሞ በተንኮል ለመጉዳት አስቦ የመዋሸት ልማድ ሊኖርበት ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ሆን ብሎ የሚዋሽ ሰው በተንኮል ስሜት የተሞላ ስለሆነ በሌሎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ከመሆኑም በላይ ንስሐ ካልገባ ከጉባኤ እስከ መወገድ ሊደርስ ይችላል። ሁሉም ውሸት የሚነገረው በተንኮል ስሜት በመገፋፋት ስለማይሆን አንድ ሰው ውሸት በሚናገርበት ጊዜ ሳያስፈልግ ለማውገዝ ከመቸኮል በፊት ግለሰቡ ያን ውሸት እንዲናገር የገፋፉትን ሁኔታዎች በሙሉ በሚገባ ለማወቅ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የግለሰቡን ውስጣዊ ስሜትና ውሸቱን እንዲናገር በከፊል ምክንያት የሆኑትን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።​—⁠ያዕቆብ 2:​13

“እንደ እባብ ብልኆች”

እርግጥ፣ እውነተኛ መሆን አለብን ሲባል ለጠየቀን ሁሉ የምናውቀውን ነገር በሙሉ የመናገር ግዴታ አለብን ማለት አይደለም። ኢየሱስ በማቴዎስ 7:​6 ላይ “ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ፣ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፣ ዕንቈቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ” ሲል አስጠንቅቋል። ለምሳሌ ያህል በተንኮል የተነሳሱ ሰዎች አንዳንድ ነገሮችን የማወቅ መብት ላይኖራቸው ይችላል። ክርስቲያኖች በጥላቻ በተሞላ ዓለም ውስጥ እንደሚኖሩ ይገነዘባሉ። በመሆኑም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ “እንደ ርግብ የዋሆች” ብቻ ሳይሆን “እንደ እባብ ብልኆች” መሆን እንዳለባቸውም መክሯቸዋል። (ማቴዎስ 10:​16 የ1980 ትርጉም፤ ዮሐንስ 15:​19) ኢየሱስ በተለይ በእሱና በደቀ መዛሙርቱ ላይ አላስፈላጊ ችግር ሊያስከትል የሚችል በሚሆንበት ጊዜ እውነቱን ሙሉ በሙሉ ከመግለጥ ይቆጠብ ነበር። ያም ሆኖ ግን በእንዲህ ዓይነቶቹ ጊዜያትም እንኳ አልዋሸም። ከዚህ ይልቅ አንድም ጨርሶ አለመናገርን ይመርጥ ነበር፤ አለዚያም ደግሞ የውይይቱን አቅጣጫ ይቀይረው ነበር።​—⁠ማቴዎስ 15:​1-6፤ 21:​23-27፤ ዮሐንስ 7:​3-10

ልክ እንደዚሁም እንደ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ረአብና ዳዊት ያሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው የሚገኙ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ጉዳት ሊያደርሱባቸው የሚችሉ ሰዎች ሲገጥሟቸው ጥበብና ብልሃት ተጠቅመዋል። (ዘፍጥረት 20:​11-13፤ 26:​9፤ ኢያሱ 2:​1-6፤ 1 ሳሙኤል 21:​10-14) መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ወንዶችና ሴቶች በታዛዥነታቸው የሚታወቁ ታማኝ አምላኪዎች አድርጎ ይገልጻቸዋል። በመሆኑም ልንኮርጃቸው የሚገቡ ጥሩ አርአያዎች ናቸው።​—⁠ሮሜ 15:​4፤ ዕብራውያን 11:​8-10, 20, 31, 32-39

ውሸት በቀላሉ ከችግር ለማምለጥ የሚያስችል መስሎ የሚታይባቸው ጊዜያት ሊኖሩ ይችላሉ። ሆኖም በዛሬው ጊዜ ያሉት ክርስቲያኖች ለየት ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚገጥሟቸው ጊዜ የኢየሱስን ምሳሌ መከተላቸውና በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናቸውን መከተላቸው ተገቢ ነው።​—⁠ዕብራውያን 5:​14

መጽሐፍ ቅዱስ እውነትን የምንናገርና ሐቀኞች እንድንሆን ያበረታታናል። መዋሸት ስህተት ከመሆኑም በላይ “እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መከተል ይኖርብናል። (ኤፌሶን 4:​25) እንዲህ በማድረጋችን ንጹሕ ሕሊና ይኖረናል፣ በጉባኤ ውስጥ ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እናበረክታለን፣ እንዲሁም ‘የእውነትን አምላክ’ ማክበራችንን እንቀጥላለን።​—⁠መዝሙር 31:​5፤ ዕብራውያን 13:​18

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐናንያ እና ሰጲራ በመዋሸታቸው ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል