በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሙልጭ አድርጎ መላጨት

ሙልጭ አድርጎ መላጨት

ሙልጭ አድርጎ መላጨት

አውስትራሊያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

አንድ ሰው ጢሙን ለመላጨት በቀን አምስት ደቂቃ ቢወስድና ለ50 ዓመታት በየዕለቱ ቢላጭ ከጠቅላላ የሕይወት ዘመኑ ከ63 የሚበልጡትን ቀናት የሚያጠፋው ፊቱ ላይ ያለውን ጠጉር በመላጨት ይሆናል! ወንዶች ስለዚህ የዕለት ተዕለት ተግባር ምን ይሰማቸዋል?

በቅርቡ የተደረገ አንድ መደበኛ ያልሆነ ጥናት ጢም መላጨትን በተመለከተ የተሰጡትን የሚከተሉትን አስተያየቶች አሰባስቧል:- “የማልወደው ሥራ ነው፣” “ያስጠላኛል፣” “በሕይወት ውስጥ ከሚያስመርሩ ነገሮች አንዱ ነው፣” “የሚቻል ከሆነ የምትሸሸው ሥራ ነው።” ታዲያ አንዳንድ ወንዶች ጢማቸውን መላጨት ይህን ያህል የሚያንገፈግፋቸው ከሆነ ለምን ይላጫሉ? እስቲ ስለ መላጨት ጥቂት እንወያይ። ምናልባት ለዚህ ጥያቄ መልሱን እናገኝ ይሆናል።

ከዛጎል አንስቶ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ እስከሚጣል መላጫ

በዛጎል መላጨት ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ትችላለህ? በሻርክ ጥርስ መላጨትስ? ስል በሆነ ቁራጭ ባልጩትስ? የሰው ልጅ ለመላጨት የሚጠቀምባቸውን ነገሮች በመምረጥ በኩል ድንቅ መሻሻል አሳይቷል! በጥንቷ ግብፅ ሰዎች የሚላጩት ከላይ የትንሽ መጥረቢያ ቅርጽ ባላት ከመዳብ የተሠራች መላጫ ነበር። ከዚያ ወዲህ ደግሞ ማለትም በ18ኛውና በ19ኛው መቶ ዘመናት በእንግሊዝኛ ከትትሮት በመባል የሚታወቁት መላጫዎች በተለይ በእንግሊዝ ሼፊልድ ውስጥ ተፈብርከው ነበር። ብዙውን ጊዜ ጌጥ ተደርጎላቸው የሚሠሩት እነዚህ መላጫዎች ከተጠቀሙባቸው በኋላ ታጥፈው መያዣው ውስጥ ይገባሉ። እነዚህ መላጫዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃሉ። በአግባቡ መጠቀምን እስኪማሩ ድረስ ደግሞ መቆረጥም መድማትም አለ። እምብዛም ብልሃተኛ ላልሆኑት ሰዎች በእነዚህ መላጫዎች መጠቀም መጀመሩ ራሱ አስፈሪ ይሆንባቸዋል። ይሁን እንጂ 20ኛው መቶ ዘመን እፎይታን አምጥቷል።

በ1901 ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚኖር ኪንግ ካምፕ ጂሌት የተባለ ሰው ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ የሚጣል ምላጭ ያለው ለአደጋ የማያጋልጥ መላጫ ፈለሰፈ። የእርሱ የምርምር ውጤት የዓለምን ቀልብ የሳበ ሲሆን ቀስ በቀስም በብር ወይም በወርቅ የተለበጠ መያዣ ያላቸውን ጨምሮ የተለያየ ንድፍ ያላቸው መላጫዎች እንዲሠሩ በር ከፍቷል። በቅርቡ ደግሞ ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላ ሙሉ በሙሉ የሚጣሉ ሁለትና ሦስት ስለት ያላቸው እንዲሁም እንደ ልብ የሚተጣጠፍና ተሽከርካሪ አናት ያላቸው መላጫዎች ተሠርተዋል።

እርግጥ በ1931 ገበያ ላይ የዋሉት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መላጫዎችም ሊረሱ አይገባም። ቅልጥፍናቸውና ተፈላጊነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሄዷል። ነገር ግን አሁንም ሙልጭ አድርገው መላጨት የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች ምላጭ መጠቀሙን ይመርጣሉ።

አንዴ ብቅ ሲል ሌላ ጊዜ ሲከስም የኖረ ልማድ

ጢም ማሳደግ ከጥንት ጀምሮ በየዘመናቱ ብቅ ሲልና ሲከስም የኖረ የሰው ልጅ ልማድ ነው። ኤቭሪ ዴይ ላይፍ ኢን ኤንሸንት ኢጅፕት የተባለው መጽሐፍ የጥንቶቹ ግብጻውያን “ገላቸው ላይ ጠጉር በማሳደግ የሚታወቁ ሰዎች አልነበሩም። እንዲሁም ንጹሕ በሆነ ከቆዳ የተሠራ ማስቀመጫ ውስጥ በሚያኖሯቸው ግሩም ሆነው የተሠሩ መላጫዎች ሙልጭ አድርገው መላጨትን እንደ ክብር ይቆጥሩ ነበር” ብሏል። ዕብራዊው እስረኛ ዮሴፍ ፈርዖን ፊት ከመቅረቡ በፊት የተላጨበት ምክንያት ከዚህ ልማድ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።​—⁠ዘፍጥረት 41:​14

አሦራውያን በጣም ረጅም ጢም በማሳደግ የሚታወቁ ሰዎች ነበሩ። ረጃጅም ጢማቸውን እየጠቀለሉ፣ ሹሩባ እየሠሩና እያበጁ በማሽሞንሞን ብዙ ጊዜ ያጠፉና በጣም ይኩራሩበትም ነበር።

የጥንቶቹ እስራኤላውያን ወንዶችም ልከኛ መጠን ያለው ጢም የነበራቸው ሲሆን በሚገባ የተቀመቀመ እንዲሆን የሚጠቀሙበት መላጫ ነበራቸው። ታዲያ የአምላክ ሕግ እስራኤላውያን ‘የጠጉራቸውን ዙሪያ እንዳይከረክሙ’ ወይም ‘ጢማቸውንም ዙሪያውን እንዳይቆርጡት’ ትእዛዝ ሲሰጥ ምን ማለቱ ነው? ይህ የራስ ጠጉርን ወይም ጢምን መከርከምን የሚከለክል አይደለም። ይልቁንም እስራኤላውያን የአጎራባቾቻቸውን አረማዊ ብሔራት ጽንፈኛ ሃይማኖታዊ ልማድ ለመኮረጅ እንዳይነሱ የሚከለክል ነበር። *​—⁠ዘሌዋውያን 19:​27፤ ኤርምያስ 9:​25, 26፤ 25:​23፤ 49:​32

በጥንቷ ግሪክ ኅብረተሰብ ውስጥ ብዙውን ጊዜ ሙልጭ አድርገው ከሚላጩት መኳንንት በስተቀር ሁሉም ጢሙን ያሳድግ ነበር። በሮም የመላጨት ልማድ ብቅ ያለው በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ሲሆን ከዚያ በኋላ በነበሩት ጥቂት መቶ ዓመታት በየዕለቱ መላጨት ልማድ ሆኖ ቀጥሎ ነበር።

ይሁን እንጂ የሮማ ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት ሲወድቅ ጢም የማሳደጉ ልማድ እንደገና ተስፋፍቶ መላጨት ፋሽን እስከ ሆነበት እስከ 17ኛው መቶ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ድረስ ለ1, 000 ዓመት ያህል ቆይቷል። ሙልጭ አድርጎ የመላጨቱ ልማድ እስከ 18ኛው መቶ ዘመን ድረስ ቀጥሏል። ይሁንና ከ19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ አንስቶ እስከ ምእተ ዓመቱ መገባደጃ ድረስ ሚዛኑ ወደዚያኛው ወገን አጋደለ። የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የሲ ቲ ራስልና የክርስቲያን ወንድሙ የደብሊው ኢ ቫን አምበርግ ፎቶግራፍ የሚማርክና በሚገባ የተከረከመ ጢም እንደነበራቸው ያሳያል። ይህም በዘመናቸው የሚያስከብርና ተስማሚ ነበር። ይሁን እንጂ ጢም መላጨት በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ እንደገና ተቀባይነት አግኝቶ ብቅ ያለ ሲሆን በብዙ አገሮች እስከዛሬም ድረስ ቀጥሏል።

አንተም በየዕለቱ መስተዋት ፊት ቆመው ጢማቸውን ከሚላጩት በሚልዮን የሚቆጠሩ ወንዶች አንዱ ነህን? ከሆነ፣ በተቻለ መጠን ሳያምህና ሳትደማ በተሳካ መንገድ ልታከናውነው ትፈልግ ይሆናል። ይህን ማድረግ እንድትችል “በምላጭ ተጠቅመህ ስትላጭ የምታስብባቸው ነገሮች” በሚለው ሣጥን ውስጥ የቀረቡትን ነጥቦች መመርመር ትፈልግ ይሆናል። ከእነዚህ ሐሳቦች መካከል አሁንም ቢሆን አንዳንዶቹን ተጠቅመህባቸው እንደሚሆን ግልጽ ነው። ያም ሆነ ይህ ጢምን አሳምሮ መላጨት አስደሳች እንዲሆንልህ እንመኛለን!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለ መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 266 እና 1021 ተመልከት።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በምላጭ ተጠቅመህ ስትላጭ የምታስብባቸው ነገሮች

ሜንስ ሄር የተባለው መጽሐፍ ውጤታማ በሆነ መንገድ በምላጭ ስለመላጨት የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥቷል። *

1. ጢምህን ማራስ:- ፊትህ ላይ ያለውን ጠጉር በሚገባ ለማራስ የሚረዳው ብቸኛው መንገድ ብዙ ሙቅ ውኃ መጠቀም ነው። ከተቻለ ገላህን ከታጠብህ በኋላ ብትላጭ ውኃው ጢምህን የሚያርስበት በቂ ጊዜ ይኖረዋል።

2. ከመላጨትህ በፊት የምትቀባቸው ነገሮች:- የተለያየ ዓይነት ያላቸው ሳሙናዎች በሙሉ፣ አረፋና ቅባት የሚያከናውኑት ተግባር ሦስት ነው:- (1) የጢምህ ጠጉር እርጥበት እንዲያገኝ ያደርጋሉ፣ (2) እንዲቆም ያደርጉታል እንዲሁም (3) ምላጩ ያለችግር እንዲንሸራተት ቆዳህን ያለሰልሳሉ። ለአንተ የሚሻል የምትለውን መርጠህ ተጠቀም። የጠጉር ማለስለሻ [hair conditioner] ተጠቅመህ ታውቃለህ? እርሱም ቢሆን ­የተዘጋጀው ጠጉር ለማለስለስ ተብሎ ነው።

3. ትክክለኛውን ዓይነት ምላጭ በተገቢ መንገድ መጠቀም:- ትክክለኛ የሚባለው ስል የሆነ ምላጭ ነው። የደነዘ ምላጭ ቆዳህን ሊጎዳው ይችላል። ጠጉሮቹ የሚያድጉበትን አቅጣጫ ተከትለህ ላጭ። ጠጉሮቹ ከሚያድጉበት አቅጣጫ በተቃራኒ መላጨት ሙልጭ አድርገህ ለመላጨት ይረዳህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ጠጉሮቹን ከቆዳው ሥር ገብቶ ሊቆርጣቸውና በቆዳው ቀዳዳ ብቅ ብለው ከማደግ ይልቅ በአካባቢው ሕብረ ሕዋስ ውስጥ እንዲያድጉ ሊያደርጋቸው ይችላል። አንዳንድ ምንጮች እንደሚሉት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በግዴለሽነት የመላጨት ልማድ ካላቸው ኪንታሮት ­ሊያስከትል የሚችል የቫይረስ ኢንፌክሽን ሊገጥማቸው ይችላል።

4. ከተላጨህ በኋላ ቆዳህን በጥሩ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚረዱ ነገሮች:- በተላጨህ ቁጥር በዓይን የማይታይ የቆዳህ ሽፋን ስለሚነሳ ቆዳህ ለጉዳት የተጋለጠ ይሆናል። በመሆኑም በንጹሕ ውኃ ፊትህ ላይ የቀረውን ቆሻሻ ማለቅለቁ በጣም አስፈላጊ ነው። በመጀመሪያ ሞቅ ባለ ውኃ ከተጠቀምህ በኋላ የቆዳህን ቀዳዳዎች ለመድፈንና እርጥበቱን ውስጥ ለማስቀረት እንድትችል በቀዝቃዛ ውኃ ተጠቀም። ከፈለግህም ቆዳህን በጥሩ ሁኔታ ለመጠበቅ እርጥበት የሚሰጥ ቅባት (አፍተር ሼቭ ) ልትጠቀም ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.20 ይህ ርዕስ የሚናገረው ስለ ወንዶች ነው። በብዙ አገሮች ሴቶችም አንዳንድ የሰውነት ክፍሎቻቸውን ይላጫሉ። ስለዚህ እዚህ ላይ የተሰጡትን አንዳንዶቹን ነጥቦች እነርሱም ጠቃሚ ሆነው ያገኟቸው ይሆናል።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የጢም ጠጉር እንዴት ዓይነት ነው?

የጢም ጠጉር ከኬራቲንና ከዚያ ጋር ተዛምዶ ካላቸው ፕሮቲኖች የተሠራ ነው። ኬራቲን ሰልፈር ያለው ቃጫ ፕሮቲን ሲሆን በሰዎችና በእንስሳት ሰውነት ውስጥ የሚሠራ ፕሮቲን ነው። ፀጉር፣ ጥፍር፣ ላባ፣ ኮቴና ቀንድ በዋነኛነት የሚሠራው በዚህ ፕሮቲን አማካኝነት ነው። በሰው ልጅ ሰውነት ላይ ካለው ጠጉር ሁሉ ጠንካራና በቀላሉ የማይጎዳው የጢም ጠጉር ሲሆን አንዷን ጠጉር መቁረጥ ተመሳሳይ ውፍረት ያለውን የመዳብ ሽቦ ከመቁረጥ ተለይቶ አይታይም። በአንድ ሙሉ ሰው ፊት ላይ ያለው ሪዝ እስከ 25, 000 ሲደርስ በ24 ሰዓት ውስጥ እስከ ግማሽ ሚሊ ሜትር ድረስ ያድጋል።

[ምንጭ]

ወንዶች:- A Pictorial Archive from Nineteenth-Century Sources/Dover Publications, Inc.

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መላጨት አንዴ ብቅ ሲል ሌላ ጊዜ ሲከስም የኖረ ልማድ ነው

ግብጻውያን

አሦራውያን

ሮማውያን

[ምንጭ]

Museo Egizio di Torino

Photographs taken by courtesy of the British Museum