በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ ሄዷል
በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ ሄዷል
“በዓለም ላይ ያለውን ድህነት በመቅረፍ ረገድ ካለፉት አምስት ምዕተ ዓመታት ይልቅ ባለፉት አምስት አሥርተ ዓመታት ከፍተኛ መሻሻል ታይቷል” ሲል ዩ ኤን ዲ ፒ ቱዴይ የተባለው በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም የሚያዘጋጅ አንድ ጽሑፍ ዘግቧል። “በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ከ1960 አንስቶ የሕፃናት ሞት ቁጥር በግማሽ እንዲሁም የተመጣጣኝ ምግብ እጥረት በአንድ ሦስተኛ እንዲቀንስ ሲያደርጉ የትምህርት ዕድል ደግሞ በአንድ አራተኛ እንዲያድግ አድርገዋል።” ይሁን እንጂ ይህ መሻሻል ቢታይም በዓለም ላይ ያለው ድህነት “አሁንም ተስፋፍቶ እንደሚገኝ” ይኸው ምንጭ አምኗል።
ከዚህ የከፋው ደግሞ በአንድ ኅብረተሰብ ውስጥም ሆነ በተለያዩ ኅብረተሰቦች መካከል ያለው ልዩነት እያደገ መሄዱ ነው። “ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው አኃዝ በበለጠ በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በተመጣጣኝ ምግብ እጥረትና በረሃብ እየተሰቃዩ ነው” ሲሉ የተመድ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዲሬክተር የሆኑት ካተሪን ቤርቲኒ ተናግረዋል። እንዲያውም ዛሬ በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ውስጥ ያሉ ወደ 840 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች ዘላቂ በሆነ ረሃብ እየተጠቁ ይኖራሉ፣ ከአንድ ቢልዮን የሚበልጡት ንጹሕ የመጠጥ ውኃ አያገኙም እንዲሁም ወደ 1.5 ቢልዮን የሚጠጉ ሰዎች የዕለት መተዳደሪያቸው አንድ የአሜሪካ ዶላር እንኳ አይሞላም። የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ሜሪ ሮቢንሰን “ዓለም በማደግ ላይ ያሉና ያደጉ አገሮች በሚል መከፋፈሏ ቀርቶ ከልክ በላይ ያደጉና ፈጽሞ የማያድጉ [አገሮች] በሚል የምትከፋፈልበት ደረጃ ላይ እንዳንደርስ ያሰጋናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ስድስት ቢልዮን የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ የሚጠይቅበት ወጪ ምን ያህል ነው? አንድ ሰው የሚገምተውን ያህል ላይሆን ይችላል። ተመድ እንዳሰላው ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለንጽሕና አጠባበቅ ሥርዓትና ለንጹሕ ውኃ አቅርቦት በዓመት ተጨማሪ 9 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር (በነፍስ ወከፍ 1.50 ዶላር) የሚያስፈልግ ሲሆን በምድራችን ላይ ያለ እያንዳንዱ ሰው መሠረታዊ ጤና እና ተመጣጣኝ ምግብ እንዲያገኝ በዓመት ተጨማሪ 13 ቢልዮን ዶላር (በነፍስ ወከፍ ወደ 2 ዶላር ገደማ) ያስፈልጋል። እነዚህ አኃዞች ከፍተኛ ቢሆኑም እንኳ ዓለማችን ለሌሎች ግልጋሎቶች ከሚያወጣው ወጪ ጋር ሲነጻጸሩ ግን ከቁብ አይቆጠሩም። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት በቅርቡ በአንድ ዓመት ውስጥ ዓለም ለንግድ ማስታወቂያ ያወጣው ወጪ 435 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር (በነፍስ ወከፍ ከ70 ዶላር በላይ) ሲሆን ለወታደራዊ ጉዳዮች ደግሞ 780 ቢልዮን ዶላር (በነፍስ ወከፍ 130 ዶላር) አውጥቷል። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ባላቸውና በሌላቸው የዓለማችን ሕዝቦች መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበቡ ያን ያህል በቂ ገንዘብ የማግኘት ያለማግኘት ጉዳይ ሳይሆን አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች የማስቀደም ጉዳይ ነው።