በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አባቶች እየኮበለሉ ያሉት ለምንድን ነው?

አባቶች እየኮበለሉ ያሉት ለምንድን ነው?

አባቶች እየኮበለሉ ያሉት ለምንድን ነው?

“እማዬና አባዬ የተጣሉበትንም ሆነ የተጨቃጨቁበትን ጊዜ አላስታውስም። የማስታውሰው ነገር ቢኖር አባዬ አብሮን ይኖር እንደነበረ ነው። ከዚያ አንድ ቀን እንደ ወጣ ቀረ ! አሁንም ድረስ አባዬ የት እንዳለ አላውቅም። ለአባቴ ምንም ዓይነት ስሜት የለኝም።”​—⁠ብሩስ

“በትምህርት ቤታችን ውስጥ ከነበርነው ልጆች መካከል ያለ አባት ያደግኩና የተመቻቸ መኖሪያ የሌለኝ እኔ ብቻ ነበርኩ . . . ሁልጊዜ የተለየሁ እንደሆንኩ ሆኖ ይሰማኝ ነበር። በእኔ ዕድሜ ከሚገኙት ሁሉ በጣም የተለየሁ እንደሆንኩ ሆኖ ይሰማኝ ነበር።”​—⁠ፓትሪሽያ

ብዙ ቤተሰቦች ያለ አባት መቅረት የጀመሩት ከኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን አንስቶ ነው። የፋብሪካ ሥራዎች ወንዶችን እያማለሉ ከቤተሰባቸው ተነጥለው እንዲሄዱ ሲያደርጉ አባቶች በቤተሰብ ሕይወት ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ እየቀነሰ ሄደና ልጆችን የማሳደጉ ኃላፊነት ከፍተኛ ድርሻ በእናቶች ጫንቃ ላይ ወደቀ። * እርግጥ ነው፣ ከቤተሰቦቻቸው ለመለየት ያልመረጡ በርካታ አባቶች ነበሩ። ሆኖም በ1960ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ የፍቺ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀብ ጀመረ። ፍቺን ገድበው ይዘው የነበሩ ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ግድግዳዎች መፈረካከስ ጀመሩ። ፍቺ ልጆችን የማይጎዳ ከመሆኑም በላይ ሊጠቅማቸውም ይችላል ብለው ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ ጠቢባን ነን ባዮች በሚሰጡት ምክር የተገፋፉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ባልና ሚስቶች ፍቺን መረጡ። በፍራንክ ኤፍ ፈርስቴንበርግ ጁንየር እና በአንድሩ ጄ ቼርሊን የተዘጋጀው ዲቫይድድ ፋሚሊስ—⁠ዋት ሃፕንስ ቱ ችልድረን ዌን ፓረንትስ ፓርት የተባለው መጽሐፍ “[ከ1960ዎቹ ዓመታት አንስቶ] በቤልጅየም፣ በፈረንሳይና በስዊዘርላንድ [የፍቺ] ቁጥር በእጥፍ የጨመረ ሲሆን በካናዳ፣ በእንግሊዝና በኔዘርላንድ በሦስት እጥፍ አድጓል” ይላል።

ከፍቺ በኋላ ብዙውን ጊዜ ልጆች የሚኖሩት ከእናታቸው ጋር ቢሆንም እንኳ ከቤተሰባቸው የተለዩ አብዛኞቹ አባቶች ከልጆቻቸው ጋር ጥሩ ዝምድና ይዘው መቀጠል ይፈልጋሉ። ለዚህ የተለመደው አንዱ መፍትሔ ልጆችን የማሳደግ የጋራ መብት ማግኘት ነው። ሆኖም ከትዳር ጓደኛቸው የተፋቱ አብዛኞቹ አባቶች ከልጆቻቸው ጋር እምብዛም ግንኙነት የሌላቸው መሆኑ የሚያስገርም ነው። አንድ ጥናት እንዳመለከተው የተፋቱ ወላጆች ካሏቸው 6 ልጆች መካከል በየሳምንቱ ከአባቱ ጋር የሚገናኘው አንዱ ብቻ እንደሆነ አመልክቷል። ግማሽ የሚሆኑት ልጆች ማለት ይቻላል አባታቸውን ሳያዩ ዓመት ደፍነዋል!

ልጆችን የማሳደግ የጋራ መብት ያሉት ችግሮች

የተፋቱ ባልና ሚስት የጋራ በሆነ ልጆችን የማሳደግ መብት መጠቀም እንዲችሉ በእጅጉ መተባበርና መተማመን መቻል ይኖርባቸዋል። እነዚህ ባሕርያት ደግሞ እምብዛም ሲንጸባረቁ አይታይም። ተመራማሪዎቹ ፈርስቴንበርግና ቼርሊን ይህን ሁኔታ እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል:- “አባቶች ከልጆቻቸው ጋር መገናኘታቸውን የሚያቆሙበት ዋነኛ ምክንያት ከቀድሞ ሚስቶቻቸው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዲኖራቸው ስለማይፈልጉ ነው። ብዙዎቹ ሴቶችም ለቀድሞ ባሎቻቸው ተመሳሳይ አመለካከት ይኖራቸዋል።”

እርግጥ ነው፣ ከትዳር ጓደኛቸው የተፋቱ ብዙ አባቶች አዘውትረው ከልጆቻቸው ጋር ይገናኛሉ። ሆኖም በልጆቻቸው የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ እንደ ቀድሞው ስለማይካፈሉ አንዳንዶቹ ከልጆቻቸው ጋር ሲገናኙ የአባትነት ባሕርይ ማንጸባረቅ ይቸግራቸዋል። ብዙዎቹ ከልጆቻቸው ጋር የሚሆኑበትን ጊዜ በሙሉ ማለት ይቻላል፣ በመዝናናትና ወደ ገበያ በመውጣት የልጆቻቸው አጫዋች ብቻ ሆነው ያሳልፉታል። የአሥራ አራት ዓመቱ አሪ ቅዳሜና እሁድን ከአባቱ ጋር ሲያሳልፍ የሚኖረውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “ለማንኛውም እንቅስቃሴ የተወሰነ ሰዓት የለም፤ ‘በዚህ ሰዓት ውጣ በዚህ ሰዓት ግባ’ የሚባል ነገርም የለም። ምንም ዓይነት ቁጥጥርም ሆነ ገደብ የለም። በተጨማሪም አባቴ ሁልጊዜ ስጦታዎች ይገዛልኛል።”​—⁠ሃው ኢት ፊልስ ዌን ፓረንትስ ዲቮርስ፣ በጂል ክሬሜንትስ።

አፍቃሪ አባት ‘ለልጆቹ እንዴት መልካም ስጦታ መስጠት እንዳለበት ማወቅ’ ይኖርበታል። (ማቴዎስ 7:​11) ሆኖም ስጦታዎች አስፈላጊ ለሆነ መመሪያና ተግሳጽ ምትክ ሆነው ሊያገለግሉ አይችሉም። (ምሳሌ 3:​12፤ 13:​1) አንድ አባት የወላጅነት ኃላፊነቱን በአጫዋችነት ወይም በተራ ጠያቂነት ሲተካው በአባትና በወላጅ መካከል ያለው ዝምድና እየላላ መሄዱ አይቀሬ ነው። አንድ ጥናት “ፍቺ በአባትና በልጅ መካከል የሚኖረውን ዝምድና ለዘለቄታው ሊያበላሸው ይችላል” ሲል ደምድሟል።​—⁠ጆርናል ኦቭ ማሪጅ ኤንድ ዘ ፋሚሊ፣ ግንቦት 1994

ከልጆቻቸው ሕይወት መራቃቸው ስለሚጎዳቸውና ስለሚያበሳጫቸው አለዚያም ደግሞ ግድየለሾች በመሆን አንዳንድ ወንዶች አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ በመንፈግ ቤተሰቦቻቸውን እርግፍ አድርገው ይተዋሉ። * (1 ጢሞቴዎስ 5:​8) “አባቴን ልወድ የምችልበት ምንም ነገር ያለ አይመስለኝም” ሲል አንድ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ በምሬት ተናግሯል። “ከእኛ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ምንም ዓይነት እርዳታ አያደርግልንም። ይህ ለማሰብ እንኳ የሚከብድ ነገር ይመስለኛል።”

ያላገቡ ወላጆች

ያለ አባት የቀሩ ልጆች ቁጥር በእጅጉ እንዲያሻቅብ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ብዙ ልጆች ከጋብቻ ውጪ የሚወለዱ መሆኑ ነው። ፋዘርለስ አሜሪካ የተባለው መጽሐፍ “በአሁኑ ጊዜ [በዩናይትድ ስቴትስ] ውስጥ ከሚወለዱት ልጆች መካከል አንድ ሦስተኛ ገደማ የሚሆኑት ከጋብቻ ውጪ የሚወለዱ ናቸው” ይላል። ከ15 እስከ 19 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች በየዓመቱ ከሚወልዷቸው ወደ 500, 000 የሚጠጉ ሕፃናት መካከል 78 በመቶዎቹ የሚወለዱት ከጋብቻ ውጪ ነው። ይሁን እንጂ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ መፀነስ ዓለም አቀፍ ችግር ነው። የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴን የሚያስተምሩ ወይም ከልቅ የፆታ ግንኙነት መራቅን አጥብቀው የሚመክሩ ፕሮግራሞች በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ጾታዊ ምግባር በመለወጥ ረገድ ብዙም የፈየዱት ነገር የለም።

በብራያን ኢ ሮቢንሰን የተዘጋጀው ቲንኤጅ ፋዘርስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ስለ ጾታ ግንኙነትና ከጋብቻ በፊት ስለመፀነስ ይበልጥ ልቅ የሆኑ ማኅበራዊ አመለካከቶች የተስፋፉ በመሆኑ ከጋብቻ ውጪ መፀነስ በ1960ዎቹ ዓመታት የነበረውን ዓይነት ኀፍረትና ውርደት የሚያስከትል መሆኑ ቀርቷል። . . . በተጨማሪም በዛሬው ጊዜ ያለው ወጣት በማስታወቂያ፣ በሙዚቃ፣ በፊልምና በቴሌቪዥን የሚተላለፍ የጾታ ስሜትን የሚቀሰቅስ ውርጅብኝ እየተዥጎደጎደበት ነው። የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ቅጽበታዊ የሆነና ኃላፊነት የጎደለው ጾታዊ ምግባር በገሃዱ ዓለም ውስጥ የሚያስከትለውን መዘዝ በመሸፈን በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የጾታ ግንኙነት ሲባል ፍቅራዊ፣ አስደሳችና ጾታዊ እርካታ የሚገኝበት ብቻ እንደሆነ አድርገው እንዲያስቡ ያደርጓቸዋል።”

ብዙ ወጣቶች ሕገወጥ የሆነ የጾታ ግንኙነት የሚያስከትላቸውን መዘዞች የተገነዘቡ አይመስሉም። ደራሲው ሮቢንሰን ያሰባሰቧቸውን አንዳንድ አስተያየቶች ተመልከት:- “ ‘[የምትፀንስ] ዓይነት አትመስልም ነበር’፤ ‘የጾታ ግንኙነት የምናደርገው በሳምንት አንዴ ብቻ ነበር’፤ ወይም ደግሞ ‘ለመጀመሪያ ጊዜ የጾታ ግንኙነት ሲደረግ መፀነስ የሚቻል አይመስለኝም ነበር።’ ” እርግጥ አንዳንድ ወንዶች የጾታ ግንኙነት እርግዝናን ሊያስከትል እንደሚችል ጠንቅቀው ያውቃሉ። ያንግ አንዌድ ፋዘርስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “[በመሀል ከተማ የሚኖሩ] ብዙ ወንዶች ልጆች የጾታ ግንኙነት መፈጸም በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቦታ የሚያሳይ ትልቅ ነገር እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። የጾታ ግንኙነት መፈጸምን እንደ ትልቅ ጀብዱ ይቆጥሩታል። ብዙ ልጃገረዶች የአንድን ወጣት ወንድ ትኩረት ለማግኘት ሲሉ የጾታ ግንኙነትን እንደ ስጦታ አድርገው ይጠቀሙበታል።” እንዲያውም በአንዳንድ መሀል ከተማዎች የሚኖሩ ልጅ ያልወለዱ ወንዶች ልጆች “ድንግል” እየተባሉ ሊፌዝባቸው ይችላል!

በ1993 በካሊፎርኒያ ገና ተማሪ በሆኑ እናቶች ላይ በተካሄደው ጥናት የተገኙትን ውጤቶች ስንመለከት ደግሞ ሁኔታው ይበልጥ ጽልመት የተላበሰ ሆኖ እናገኘዋለን። ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ልጃገረዶች በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ከሚገኙ የወንድ ጓደኞች ሳይሆን ከ20 ዓመት በላይ ከሆኑ ወንዶች እንደፀነሱ ጥናቱ አመልክቷል! እንዲያውም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሳያገቡ የወለዱ ብዙ ሴቶች ገና በለጋ ዕድሜያቸው ተገድደው የተደፈሩ ወይም በልጅነታቸው ጾታዊ በደል የተፈጸመባቸው እንደሆኑ አንዳንድ ጥናቶች ያሳያሉ። በእጅጉ ተስፋፍቶ የሚገኘው እንዲህ ያለው ግፍ ዘመናዊው ኅብረተሰብ ምን ያህል በሥነ ምግባር እንደተበላሸና እንዳዘቀጠ የሚያሳይ ነው።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​13

ወጣት ወንዶች ጥለው የሚሄዱት ለምንድን ነው?

ልጆች የወለዱ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ አብዛኞቹ ወንዶች ልጆች ለወለዱት ልጅ ያለባቸውን ኃላፊነት ለዘለቄታው የሚሸከሙ ሆነው አይገኙም። አንድ ልጅ የፀነሰችውን ጓደኛውን “ደህና ሁኚ” ብሎ እንደተሰናበታት ተናግሯል። ይሁን እንጂ ፋምሊ ላይፍ ኢጁኬተር ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ “አብዛኞቹ ወጣት አባቶች ከልጆቻቸው ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዲኖራቸው እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን” አመልክቷል። ባላገቡ ወጣት አባቶች ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት እንደገለጸው ከሆነ 70 በመቶ የሚሆኑት ልጃቸውን በሳምንት አንድ ጊዜ ይጠይቃሉ። “ይሁን እንጂ” ሲል ያስጠነቅቃል ጽሑፉ፣ “ልጆቹ እያደጉ ሲሄዱ አባቶቻቸው አዘውትረው መጠየቃቸውን ያቆማሉ።”

አንድ የ17 ዓመት አባት ይህ የሚሆንበትን ምክንያት ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ “ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆን አውቄ ቢሆን ኖሮ መጀመሪያውኑ ሁኔታው እንዲከሰት አልፈቅድም ነበር” ብሏል። የወላጅነት ኃላፊነት የሚጠይቃቸውን ነገሮች ለማሟላት የሚያስችል ስሜታዊ ብስለትም ሆነ ተሞክሮ ያላቸው ወጣቶች እምብዛም የሉም። በተጨማሪም ብዙዎቹ መተዳደሪያ ለማግኘት የሚያስችል የትምህርት ደረጃም ሆነ የሥራ ሙያ የላቸውም። ብዙ ወጣት ወንዶች ስኬታማ ሳይሆኑ መቅረታቸው የሚያስከትልባቸውን ውርደት ከመቀበል ልጆቻቸውን ጥለው መሄድ ይመርጣሉ። “ሕይወቴ ዝብርቅርቁ ወጥቷል” ሲል አንድ ወጣት አባት ተናግሯል። ሌላው ደግሞ “እኔ ራሴን እንኳ እንዴት መንከባከብ እንደምችል የማላውቅ ሰው ነኝ። [ልጄንም] መንከባከብ የሚኖርብኝ ቢሆን ኖሮ ምን አደርግ እንደነበረ አላውቅም” ሲል በሐዘን ስሜት ተውጦ ተናግሯል።

ጎምዛዛ የወይን ፍሬ

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አይሁዶች “ወላጆች ጎምዛዛ የወይን ፍሬ በሉ፤ ነገር ግን የልጆቻቸውን ጥርስ አጠረሰ” የሚል አባባል ነበራቸው። (ሕዝቅኤል 18:​2 የ1980 ትርጉም ) አምላክ እንዲህ መሆን እንደሌለበትና የቀድሞ ስህተቶች ወደፊት መደገም እንደሌለባቸው አይሁዶችን አሳስቧቸው ነበር። (ሕዝቅኤል 18:​3) ሆኖም በዛሬው ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ልጆች የወላጆቻቸው ብስለትና ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት እንዲሁም የትዳር ውድቀት ያስከተለውን መዘዝ በመቀበል የወላጆቻቸውን “ጎምዛዛ የወይን ፍሬ” መራራነት እየቀመሱ ነው። ያለ አባት የሚያድጉ ልጆች ለበርካታ አካላዊና ስሜታዊ ችግሮች የተጋለጡ መሆናቸውን የሚያሳየው ጥናታዊ መረጃ በጣም የሚያስገርም ነው። (ገጽ 7 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ይበልጥ የሚያሳስበው ደግሞ ያለ አባት የቀረ ቤተሰብ ውርሻ ብዙውን ጊዜ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የማያቋርጥ የሥቃይና የመከራ ዑደት መሆኑ ነው።

ያለ አባት የቀሩ ቤተሰቦች ኑሮ ፈጽሞ ሊቃና የማይችል ነው? በፍጹም። እንዲያውም ደስ የሚለው ነገር ያለ አባት የቀሩ ቤተሰቦች ችግር ሊቋጭ የሚችል መሆኑ ነው። የሚቀጥለው ርዕስ ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 ኢንዱስትሪዎች ከመስፋፋታቸው በፊት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ልጆችን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል የሚገልጹ ጽሑፎች በጥቅሉ ይወጡ የነበሩት ለእናቶች ሳይሆን ለአባቶች የነበረ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።

^ አን.10 ሴራ ማክላንሃን እና ጋሪ ሳንድፈር የተባሉት ተመራማሪዎች እንዳሉት ከሆነ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ “የገንዘብ ድጎማ የማግኘት መብት ካላቸው ልጆች መካከል 40 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ይህን የገንዘብ ድጎማ ማግኘት የሚችሉበት [የፍርድ ቤት] ትእዛዝ ያልወጣላቸው ሲሆን ይህን የፍርድ ቤት ማዘዣ ካገኙት መካከል ደግሞ አንድ አራተኛ የሚሆኑት ምንም የገንዘብ ድጎማ አያገኙም። የሚገባቸውን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ የሚያገኙት ልጆች ደግሞ ከአንድ ሦስተኛ ያነሱ ናቸው።”

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ያለ አባት ማደግ ሊያስከትላቸው የሚችላቸው ችግሮች

ያለ አባት የሚያድጉ ልጆች ከባድ ችግሮች ሊገጥሟቸው ይችላሉ። አንዳንዶች የሚከተለውን መረጃ ማጤኑ ሊከብዳቸው ቢችልም እንኳ ሊከሰቱ የሚችሉትን አደገኛ ሁኔታዎች ማወቁ ጉዳቱን ለማስወገድ ወይም ቢያንስ ቢያንስ ለመቀነስ የሚያስችል የመጀመሪያ እርምጃ ነው። በተጨማሪም በጥናቶች ላይ የተመሠረቱ አኃዛዊ መረጃዎች በቡድን ደረጃ እንጂ በግለሰብ ደረጃ የሚሠሩ እንዳልሆኑ መገንዘብ ያሻል። ያለ አባት በቀሩ ቤተሰቦች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ልጆች ከእነዚህ ችግሮች የትኛውም ሳይደርስባቸው ያድጋሉ። የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚያሳየው ወላጆች አስፈላጊ እርምጃዎችን መውሰዳቸውና የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ ማድረጋቸው ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ። እንግዲያው አንድ ያለ አባት የቀረ ልጅ ሊገጥሙት የሚችሉትን አንዳንድ አደገኛ ሁኔታዎች ተመልከት።

ለወሲባዊ በደል በከፋ ሁኔታ መጋለጥ

ያለ አባት የቀሩ ልጆች በልጆች ላይ ለሚፈጸም ወሲባዊ በደል ይበልጥ የተጋለጡ እንደሆኑ የተካሄዱት ጥናቶች በግልጽ ያሳያሉ። አንድ ጥናት እንዳመለከተው በልጆች ላይ ከተፈጸሙት 52, 000 ወሲባዊ ጥቃቶች መካከል “72 በመቶዎቹ አንደኛው ወይም ሁለቱም የሥጋ ወላጆች በሌሉበት ቤተሰብ ውስጥ በሚኖሩ ልጆች ላይ የተፈጸሙ ናቸው።” ፋዘርለስ አሜሪካ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ለወሲባዊ በደል የሚጋለጡ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ሊሄድ የቻለበት ዋነኛው ምክንያት ከቤተሰባቸው ጋር የሚኖሩ ያገቡ አባቶች ቁጥር እየተመናመነ መሄዱ እንዲሁም የእንጀራ አባቶች፣ የወንድ ጓደኞችና ሌሎች ምንም ዝምድና የሌላቸው ወይም ከልጆቹ እናቶች ጋር እንዲሁ አብረው የሚኖሩ ወንዶች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ ነው።”

ከሌሎች ልጆች በበለጠ ሁኔታ ለጾታ ምግባር የተጋለጡ መሆን

በነጠላ ወላጅ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ የሚኖረው የወላጅ ቁጥጥር አነስተኛ ሊሆን ስለሚችል ብዙውን ጊዜ ልጆቹ ብልሹ ለሆነ የጾታ ምግባር የሚጋለጡበት አጋጣሚ ሰፊ ሊሆን ይችላል። ወላጅ የሚሰጠው ሥልጠና አነስተኛ መሆኑም እንደ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል። የዩ ኤስ የጤናና የሰብዓዊ አገልግሎቶች መምሪያ “ያለ አባት የቀሩ ልጃገረዶች ሊፀንሱ የሚችሉበት አጋጣሚ ከሌሎቹ በሁለት ተኩል እጥፍ ይበልጣል” ይላል።

ድህነት

በደቡብ አፍሪካ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ በሚገኙ ጥቁር ልጃገረዶች ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት ከጋብቻ በፊት መውለድ ብዙውን ጊዜ የድህነት አረንቋ ውስጥ ይከታል የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል። ጥናቱን ያካሄዱት ሰዎች እንደሚሉት “50 በመቶ በሚሆኑት ሁኔታዎች በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኘው ልጅ ወደ ትምህርት ገበታ የመመለሷ ዕድል የመነመነ ነው።” ሳያገቡ የወለዱ ብዙዎቹ እናቶች ዝሙት አዳሪዎችና ዕፅ አዘዋዋሪዎች ይሆናሉ። በምዕራቡ ዓለም ያለውም ሁኔታ ቢሆን ብዙም የተሻለ ላይሆን ይችላል። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ “[በ1995] ሁለቱም ወላጆች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ ካሉ ልጆች መካከል በድህነት ይኖሩ የነበሩት 10 በመቶዎቹ ብቻ ሲሆኑ እናት ብቻ ባለችበት ቤተሰብ ውስጥ ከሚኖሩት ልጆች መካከል ግን 50 በመቶዎቹ ድሆች ነበሩ።”​—⁠አሜሪካስ ችልድረን:- ኪ ናሽናል ኢንዲኬተርስ ኦቭ ዌል -ቢንግ 1997

ትኩረት መነፈግ

አንዳንድ ነጠላ ወላጆች ራሳቸውን መቻል ስለሚኖርባቸው ባሉባቸው ኃላፊነቶች ይዋጡና ከልጆቻቸው ጋር በቂ ጊዜ ማሳለፍ ሳይችሉ ይቀራሉ። አንዲት ከባሏ የተፋታች ሴት ወደ ኋላ መለስ ብላ በማስታወስ “ቀን ቀን እየሠራሁ ማታ ማታ እማር ስለነበር በጣም ተወጥሬ ነበር። ልጆቼን ፈጽሞ ችላ ብያቸው ነበር” ብላለች።

በስሜት ላይ የሚደርስ ጉዳት

አንዳንድ ጠበብት ልጆች ወላጆቻቸው ሲፋቱ ከሚደርስባቸው ስሜታዊ ጉዳት ወዲያውኑ ያገግማሉ በማለት ከሚሰነዝሩት ሐሳብ በተለየ መልኩ እንደ ዶክተር ጁዲት ዎለርስታይን ያሉ ተመራማሪዎች ፍቺ በልጆች ላይ ዘላቂ ስሜታዊ ቁስል እንደሚያስከትል ደርሰውበታል። “ከአሥራ ዘጠኝ እስከ ሀያ ዘጠኝ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ወጣት ወንዶችና ሴቶች መካከል ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት ወላጆቻቸው ከተፋቱ ከአሥር ዓመታት በኋላም እንኳ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ ያላቸው ምኞት አነስተኛ ነው ወይም ከናካቴው ፍላጎቱ የላቸውም። ሕይወታቸውን የሚመሩት አላንዳች ግብና . . . ተስፋ በቆረጠ ስሜት ነው።” (ሰከንድ ቻንስስ፣ በዶክተር ጁዲት ዎለርስታይን እና በሳንድራ ብሌክስሊ) የተፋቱ ወላጆች ያሏቸው ብዙ ልጆች ራስን ዝቅ አድርጎ የመመልከት፣ የአጥፊነትና ዘወትር የመቆጣት ጠባይ ይታይባቸዋል።

ዘ ሲንግል -ፓረንት ፋሚሊ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ምሳሌ ሊሆናቸው የሚችል ወንድ አጠገባቸው ሳይኖር የሚያድጉ ወንዶች ልጆች በወንድነት ባሕርያቸው እንደማይተማመኑ፣ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው እንደሚመለከቱና በኋለኛው የሕይወት ዘመናቸው የተቀራረበ ዝምድና የመመሥረት ችግር እንደሚታይባቸው በርካታ ጥናቶች አመልክተዋል። ምሳሌ ሊሆናቸው የሚችል ወንድ አብሯቸው ሳይኖር የሚያድጉ ልጃገረዶች ሊገጥሟቸው የሚችሉት ችግሮች ብዙውን ጊዜ እስከ ጉርምስና ዕድሜያቸው ድረስ ወይም ከዚያም በኋላ ቢሆን ቶሎ በግልጽ የማይታዩ ከመሆናቸውም በላይ እነዚህ ችግሮች ልጆቹ ለአቅመ ሔዋን ከደረሱ በኋላ ከወንድ ጋር ስኬታማ የሆነ ዝምድና በመመሥረት ረገድ የሚገጥማቸውን እክል ይጨምራሉ።”