በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

አፍሪካ በቸነፈር እየተመታች ነው

የዓለም የጤና ድርጅት በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ የልጅነት ልምሻን ከአፍሪካ ጨርሶ ለማጥፋት ያደረገው ጥረት የተጨናገፈ መሆኑን ኬፕ ታይምስ ዘግቧል። በአንጎላ የሚካሄደው ጦርነት የልጅነት ልምሻ በአገሪቱ ውስጥ በወረርሽኝ ደረጃ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል። በደቡብ አፍሪካ የጤና መምሪያ ውስጥ የተላላፊ በሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል ዲሬክተር የሆኑት ኒል ካምሩን እንዳሉት ከሆነ የልጅነት ልምሻን ከአንጎላ ጨርሶ ለማጥፋት ሌላ አሥር ዓመት ሊወስድ ይችላል። በተጨማሪም የአንጎላ ጎረቤት አገር የሆነችው ናሚቢያ ከኢቦላ ጋር የሚመሳሰል ሄሞሬጂክ ፊቨር የተባለ ከፍተኛ መድማት የሚያስከትል በሽታን ለመቋቋም ጥረት እያደረገች ሲሆን ሌላዋ ጎረቤት አገር ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ደግሞ ቡቦኒክ ፕሌግ የተባለ ወረርሽኝ በሽታን ለመቆጣጠር በመጣር ላይ ትገኛለች። ሥጋ ደዌ አሁንም ድረስ በኮንጎ፣ በኢትዮጵያ፣ በሞዛምቢክ፣ በኒጀርና በናይጄሪያ ችግር በመፍጠር ላይ ይገኛል። ይህ ሁሉ ችግር በአብዛኛው የአህጉሪቱ ክፍል በእጅጉ ተስፋፍቶ የሚገኘውን የወባ በሽታ ጨምሮ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ እየፈጠረ ነው። ምክንያቱም ካምሩን እንደገለጹት “ድንበሮች በሽታን ሊያግዱት አይችሉም።”

በሥራ ሰዓት ትንሽ ማሸለብ

“አንዳንድ የካናዳ ኩባንያዎች በሥራ ሰዓት በመጠኑ ማሸለብ ያለውን ጥቅም በመገንዘብ ላይ ናቸው” ሲል ቶሮንቶ ስታር የተባለው ጋዜጣ ገልጿል። አሠሪዎች ለሌሊት ፈረቃ ሠራተኞች “ጥቂት እረፍት አድርጎ ንቁ ሆኖ ለመነሳት የሚያገለግሉ ክፍሎችን” ማዘጋጀት ጀምረዋል። “ክፍሎቹ ደብዛዛ ብርሃን፣ ቀዝቀዝ ያለ አየርና ጥሩ ፀጥታ ያላቸው ከመሆኑም በላይ ደወል ያለው ሰዓት፣ ሶፋ ወይም ወደ ኋላ ሊዘረጋ የሚችል ወንበር እንዲኖራቸው ይደረጋል” ይላል ስታር። ሆኖም “የቀድሞዎቹን አስተሳሰቦች ማስወገዱ በጣም አስቸጋሪ ነው። ኩባንያዎቹ ትንሽ ማሸለብ የሚቻልባቸውን ክፍሎች ማዘጋጀታቸውን መግለጽ አይፈልጉም።” በሮያል ኦታዋ ሆስፒታል የሥርዓተ እንቅልፍ መዛባት ሕክምና ማዕከል ውስጥ ክሊኒካዊ ሐኪም የሆኑት ሜሪ ፔሩጂኒ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ብዙ ሰዓት በሠራን መጠን የሚሰማን ውጥረት የዚያኑ ያህል እየጨመረ ይሄዳል። በቀን ውስጥ ለ20 ደቂቃ ያህል መተኛት መቻሉ ጠቃሚ ነው። ምርታማነትን የሚያሳድግ (ከመሆኑም በላይ) ውጥረትን ይቀንሳል።”

“ለሕይወት እጅግ አስፈላጊ የሆነ ንጥረ ነገር”

“አብዛኛው የሰውነታችን ክፍል ፈሳሽ በመሆኑ ውኃ ለሕይወት እጅግ አስፈላጊ የሆነ ንጥረ ነገር ነው” ይላል ቶሮንቶ ስታር የተባለው ጋዜጣ። “በሰውነታችን ውስጥ የሚ​ገኘው የውኃ መጠን 20 በመቶ እንኳ ቢቀንስ ለሞት ሊዳርግ ይችላል።” ውኃ የሰውነታችንን የሙቀት መጠን ከመቆጣጠሩም በላይ “በደምና በአካላዊ ሥርዓት አማካኝነት ንጥረ ምግቦችንና የሰውነታችንን ቆሻሻ ወደ አባላካላት ያስገባል፣ እንዲሁም ከአባላካላት ያስወግዳል። በተጨማሪም አንጓዎችንና ደንዳኔን በማለስለስ ድርቀትን ለመከላከል ይረዳል።” አንድ ዐዋቂ ሰው በየዕለቱ ከሁለት እስከ ሦስት ሊትር የሚሆን ውኃ ያስፈልገዋል። ቡና፣ ለስላሳ መጠጦች ወይም አልኮል ብዙ ውኃ ከሰውነታችን እንዲወጣ ስለሚያደርጉ እነዚህን መጠጦች መጠጣት ለንጹሕ የመጠጥ ውኃ ያለንን ፍላጎት ጭራሽ ሊጨምረው ይችላል። አንዲት የአመጋገብ ሥርዓት ባለሙያ እንዳሉት ከሆነ ውኃ ለመጠጣት እስክንጠማ ድረስ መጠበቅ የለብንም። ምክንያቱም የምንጠማው የሰውነታችን የውኃ መጠን በእጅጉ በቀነሰበት ጊዜ ላይ ሊሆን ይችላል። “በቀን ውስጥ በእያንዳንዱ ሰዓት አንድ ብርጭቆ ውኃ መጠጣት የአብዛኞቹን ሰዎች የውኃ ፍላጎት ያረካል” ሲል ጋዜጣው ገልጿል።

ትምባሆ በሕፃናት ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት

የዓለም የጤና ድርጅት (ደብሊው ኤች ኦ) በዓለም ዙሪያ ከሚገኙት ሕፃናት መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት በትምባሆ ጭስ ሳቢያ ጤንነታቸው ለአደጋ የተጋለጠ መሆኑን የለንደኑ ጋርዲያን ጋዜጣ ዘግቧል። ሌላ ሰው የሚያጨሰውን የሲጋራ ጭስ መሳብ ሊያስከትላቸው የሚችላቸው የጤና እክሎች አስምንና ሌሎች የመተንፈሻ አካላት ችግሮችን፣ ለድንገተኛ የሕፃናት ሞት የሚዳርግ ችግርን፣ የመሀለኛ ጆሮ ሕመምንና ካንሰርን ይጨምራሉ። በተጨማሪም አጫሽ ወላጆች ያሏቸው ሕፃናት በትምህርት ችሎታቸውና በጠባያቸው ላይ እክል እንደሚገጥማቸው የተካሄደው ጥናት ያሳያል። ሁለቱም ወላጆች የሚያጨሱ ከሆነ ልጆቻቸው ለጤና ችግሮች የሚጋለጡበት አጋጣሚ 70 በመቶ የሚጨምር ሲሆን በቤተሰቡ ውስጥ አንድ አጫሽ ብቻ በሚኖርበት ጊዜ እንኳ ለበሽታዎች የሚጋለጡበት አጋጣሚ 30 በመቶ ይጨምራል። ደብሊው ኤች ኦ ወላጆች ትምባሆ የማጨስ ልማዳቸው በቤተሰባቸው ላይ ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋ እንዲገነዘቡ ለመርዳት የጤና ትምህርት እንዲሰጣቸውና በትምህርት ቤቶችና ሕፃናት በሚያዘወትሯቸው ሌሎች ቦታዎች ማጨስን የሚከለክል መመሪያ እንዲወጣ አጥብቆ በማሳሰብ ላይ ነው።

የቱሪዝም ድል

የዓለም የቱሪዝም ድርጅት (ደብሊው ቲ ኦ) እንደተነበየው ከሆነ “በየዓመቱ ወደተለያዩ አገሮች የሚጎርፉት ጎብኚዎች ቁጥር አሁን ካለበት 625 ሚልዮን ተነስቶ በ2020 ወደ 1.6 ቢልዮን ያሻቅባል” ሲል ዘ ዩኔስኮ ኩሪየር ዘግቧል። እነዚህ ጎብኚዎች ከሁለት ትሪልዮን በላይ የዩ ኤስ ዶላር እንደሚያወጡ የሚጠበቅ ሲሆን ይህም “ቱሪዝምን የዓለማችን ቁጥር አንድ ኢንዱስትሪ ያደርገዋል።” እስካሁን ባለው ሁኔታ አውሮፓ ብዙ ጎብኚዎች የሚጎርፉባት አህጉር ሆና ቆይታለች። በ1998 በግንባር ቀደምትነት ብዙ ጎብኚዎችን ያስተናገደችው አገር ፈረንሳይ ስትሆን በ1998 ወደዚች አገር 70 ሚልዮን ጎብኚዎች ጎርፈዋል። ይሁን እንጂ በ2020 ግንባር ቀደሙን ሥፍራ ትይዛለች ተብላ የምትጠበቀው ቻይና ናት። ሆኖም ዓለም አቀፋዊ ጉዞ ለጥቂት ባለመብቶች ብቻ የተወሰነ ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም። በ1996 ከዓለማችን ሕዝብ መካከል ወደ ሌሎች አገሮች የተጓዘው 3.5 በመቶው ብቻ ነው። ደብሊው ቲ ኦ በ2020 ይህ ቁጥር 7 በመቶ እንደሚደርስ ተንብዮአል።

የጥቂት ቀናት ዕረፍት የሚያስከትለው ጉዳት?

በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ የጉዞ ኢንዱስትሪ ከኑሮ ውጥረት ዘና ለማለት አፋጣኝና ቀላል መፍትሔ ተደርጎ በመበረታታት ላይ ያለው የጥቂት ቀናት ዕረፍት “ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን” እንደሚችል የለንደኑ ጋርዲያን ጋዜጣ ዘግቧል። የዓለም የጤና ድርጅት ባልደረባ የሆኑት የልብ ሐኪሙ ዶክተር ዎልተር ፓሲኒ እንዳሉት ከሆነ ሻንጣዎችን መሸከፍ፣ ወደ አውሮፕላን ማረፊያ መሮጥና በአውሮፕላን መብረር፣ ከአየር ጠባዩ፣ ከምግቡና ከጊዜ ሰቅ (time zone) ለውጥ ጋር ተዳምሮ ድካም ሊፈጥርና ለከፋ ጉዳት ሊዳርግ ይችላል። ሰውነታችን ዘና ለማለትና ከአዲስ ዓይነት የአየር ንብረትና የአኗኗር ዘይቤ ጋር ራሱን ለማጣጣም የተወሰኑ ቀናት የሚወስድበት ሲሆን ይህ ሳይሆን በሚቀርበት ጊዜ በደም ዝውውርና በእንቅልፍ ሥርዓት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። ዶክተር ፓሲኒ ባካሄዱት ጥናት “የጥቂት ቀናት ዕረፍት የወሰዱት ሰዎች ለአንድ ሳምንት ወይም ከዚያ በላይ የሚቆይ ዕረፍት ከወሰዱት ሰዎች ጋር ሲነጻጸር ለልብ ድካም የሚጋለጡበት አጋጣሚ 17 በመቶ የሚበልጥ ሲሆን ለመኪና አደጋ የሚጋለጡበት ሁኔታ ደግሞ በ12 በመቶ በልጦ ተገኝቷል” ይላል ጋዜጣው። ዶክተር ፓሲኒ “ለመግለጽ የፈለግኩት ነገር የጥቂት ቀናት ዕረፍት በራሱ አደገኛ መሆኑን ሳይሆን ሰዎች ጥንቃቄና ጥሩ ዝግጅት ሊያደርጉ የሚገባቸው መሆኑን ነው” ማለታቸውን የለንደኑ ዴይሊ ቴሌግራፍ ጠቅሶ ዘግቧል። “ሰዎች በአሁኑ ጊዜ አጫጭር የዕረፍት ጊዜያትን የመውሰድ ልማድ እየታየባቸው ሲሆን ሁሉንም ነገር በጥቂት ቀናት ውስጥ ለማሰናዳት ሲሯሯጡ ይታያሉ። ሆኖም ይህ ዘና ለማለት የሚያስችል ጥሩ መንገድ አይደለም። እንዲያውም የባሰ ውጥረት ይፈጥራል።”

የሕንድ የሕዝብ ቁጥር አንድ ቢልዮን አለፈ

የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ክፍል እንዳለው ከሆነ የሕንድ ሕዝብ ብዛት ነሐሴ 1999 ላይ አንድ ቢልዮን አልፏል። የዛሬ 50 ዓመት የሕንድ የሕዝብ ብዛት የአሁኑን አንድ ሦስተኛ ያህል ብቻ ነበር። አሁን ባለበት ሁኔታ በየዓመቱ 1.6 በመቶ ማደጉን ከቀጠለ በአራት አሥርተ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሕንድ ቻይናን በመተካት በዓለማችን በሕዝብ ብዛት ግንባር ቀደሙን ሥፍራ ትይዛለች። “አሁንም እንኳ ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ የሚገኘው በሕንድና በቻይና ነው” ይላል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ። ከግማሽ ምዕተ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሕንድ የሰው ልጅ አማካይ ዕድሜ ከ39 ወደ 63 ከፍ ብሏል።

የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶች የሚያስከትሉት ራስ ምታት!

ለራስ ምታት ብለው በሳምንት ውስጥ ሦስት ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ መድኃኒት የሚወስዱ ሰዎች መድኃኒትን አላግባብ በመጠቀም ለሚከሰት ራስ ምታት (ኤም ኤም ኤች) ሊጋለጡ ይችላሉ። ከ50 ሰዎች አንዱን እንደሚያጠቃ የሚገመተው ኤም ኤም ኤች እንደ አስፕሪን ባሉ ቀላል መድኃኒቶች እንዲሁም በሐኪም በሚታዘዙ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶች ሳቢያ ይከሰታል። የመድኃኒቱ የማስታገሥ ኃይል ሲጠፋ መድኃኒቱ ራሱ ራስ ምታት ሊፈጥር ይችላል። በዚህ ጊዜ መድኃኒቱን የወሰደው ሰው የሚሰማውን ሕመም የተለመደ ዓይነት ራስ ምታት ወይም ገሚስ ራስ ምታት አድርጎ በተሳሳተ መንገድ ይረዳዋል። በመሆኑም ተጨማሪ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶች በመውሰድ ዑደቱን ይደግመዋል። የለንደኑ ኢምፔሪያል ኮሌጅ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ቲም ስታይነር “በየዕለቱ ሥር የሰደደ ራስ ምታት እንደሚያመው ሲናገር የሚደመጥ ሰው ችግሩ ኤም ኤም ኤች ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ያስፈልጋል” ሲሉ ገልጸዋል። በተጨማሪም ችግሩ ከታወቀ የተወሰኑ ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም እንኳ አብዛኞቹ የቤተሰብ ዶክተሮች የማያውቁት በመሆኑ የሚያስፈልገው ነገር ታካሚው መድኃኒቶቹን እንዲያቆም ማድረግ ሆኖ ሳለ ይበልጥ ኃይለኛ የሆኑ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶች ያዝዙለታል ሲሉ መናገራቸውን የለንደኑ ዘ ሰንዴይ ቴሌግራፍ ዘግቧል።

በጃፓን የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል

በጃፓን በ1998 የራሳቸውን ሕይወት ያጠፉት ሰዎች ቁጥር ከምንጊዜውም በልጦ ተገኝቷል ሲል ዘ ዴይሊ ዮሚዩሪ ዘግቧል። የጃፓን ብሔራዊ የፖሊስ መምሪያ እንዳለው ከሆነ በ1998 ራሳቸውን የገደሉ ሰዎች ቁጥር 32, 863 ሲሆን ይህ በጃፓን ውስጥ በትራፊክ አደጋዎች ከሞቱት ሰዎች ጋር ሲወዳደር በሦስት እጥፍ ይበልጣል። ለዚህ ቁጥር ማሻቀብ በዋነኛነት ምክንያት ሆነው የተጠቀሱት ነገሮች በሥራ አጥነት ሳቢያ የተከሰቱ ገንዘብ ነክ ችግሮች ሲሆኑ በቅርቡ ከደረሰው የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ወዲህ አገሪቱን በእጅጉ ጎድተዋታል። በጃፓን ብዙ ሰዎችን ለሞት ከሚዳርጉት ነገሮች መካከል ስድስተኛውን ሥፍራ የያዘው የራስን ሕይወት በገዛ እጅ የማጥፋት እርምጃ ነው።

ለሕልፈተ ሕይወት የሚዳርግ የአየር ብክለት

“በአውሮፓ በመንገዶች ላይ የሚታየው የትራፊክ መጨናነቅ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣ የአየር ብክለት እያስከተለ ሲሆን በአንዳንድ አገሮች በ[ትራፊክ] አደጋዎች ከሚሞቱት ሰዎች ይበልጥ ብዙ ሰዎች በዚህ የአየር ብክለት ሳቢያ ለሕልፈተ ሕይወት እየተዳረጉ ነው” ሲል የሮይተር የዜና አገልግሎት ዘግቧል። የዓለም የጤና ድርጅት ያካሄደው ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ በኦስትሪያ፣ በፈረንሳይና በስዊዘርላንድ በየዓመቱ 21, 000 ሰዎች በአየር ብክለት በሚነሱ የመተንፈሻ አካላትና የልብ በሽታዎች ሳቢያ ያለ ዕድሜያቸው ይቀጫሉ። አንድ ሌላ ሪፖርት እንዳመለከተው ደግሞ በ36 የሕንድ ከተሞች ውስጥ በአየር ብክለት ሳቢያ በየቀኑ 110 ሰዎች ያለ ዕድሜያቸው እንደሚቀጩ ይገመታል።

የዩ ኤስ የትዳር ቁጥር እያሽቆለቆለ ነው

በሩትገርዝ ዩኒቨርሲቲ ብሔራዊ የጋብቻ ፕሮጄክት ያካሄደው ጥናት እንዳመለከተው የዩ ኤስ የጋብቻ ቁጥር አሽቆልቁሎ በታሪክ ውስጥ የመጨረሻው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ሲል ዘ ዋሽንግተን ፖስት ዌብ ሳይቱ ላይ ዘግቧል። በተጨማሪም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት በአገሪቱ ውስጥ ከነበሩት ልጆች መካከል 80 በመቶዎቹ በሁለት ሥጋዊ ወላጆች እንክብካቤ ሥር እንደነበሩ ጥናቱ አመልክቷል። ዛሬ ግን ይህ አኃዝ ወደ 60 በመቶ አሽቆልቁሏል። “ከጋብቻ ውጪ ልጅ መውለድ ‘ጠቃሚ የአኗኗር ዘይቤ’ እንደሆነ የሚናገሩ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጃገረዶች ቁጥር ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት ከ33 በመቶ ወደ 53 በመቶ አሻቅቧል” ይላል ሪፖርቱ። ይኸው ሪፖርት “የትዳር ተቋም ከባድ ችግር ላይ ወድቋል” ማለቱ ምንም አያስደንቅም!