ወላጆቼን ያጣሁት ለምንድን ነው?
ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
ወላጆቼን ያጣሁት ለምንድን ነው?
“ያለ ወላጅ መኖር ምን ይመስል ነበር? በብዙ ምክንያቶች የተነሳ በጣም አሳዛኝ ነበር ለማለት እደፍራለሁ። የወላጅን ፍቅርና ትኩረት ሳያገኙ ማደግ በጣም አስቸጋሪ ነው።”—ዋኪን
“ከሁሉም በላይ ፈታኝ የሚሆንብኝ ወላጆች የልጆቻቸው የትምህርት ቤት ውጤት ካርድ ላይ ለመፈረም የሚመጡበት ዕለት ነበር። ከፍተኛ ሐዘንና ብቸኝነት ይሰማኝ ነበር። አሁንም አንዳንድ ጊዜ ያ ስሜት ይመጣብኛል።”—የ16 ዓመቷ አቤሊና
በሚልዮን የሚቆጠሩ ልጆች ያለ ወላጅ መቅረታቸው የዘመናችን መቅሰፍት ሆኗል። በምሥራቅ አውሮፓ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆች በጦርነት ሳቢያ ያለ ወላጅ ቀርተዋል። አፍሪካ ውስጥ ደግሞ የኤድስ ወረርሽኝ ተመሳሳይ ጥፋት አስከትሏል። ወላጆቻቸው እንዲሁ ጥለዋቸው የሚሄዱ አንዳንድ ልጆችም አሉ። በጦርነት ወይም በተፈጥሮ አደጋ የተነሳ የቤተሰብ አባላት ይነጣጠላሉ።
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንኳ ሳይቀር እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች የተለመዱ ነገሮች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያለ ወላጅ የቀሩ ልጆች ስለሚደርስባቸው መከራ በተደጋጋሚ ተጠቅሶ ይገኛል። (መዝሙር 94:6፤ ሚልክያስ 3:5) በዚያ ዘመንም ጦርነትና ሌሎች አሳዛኝ ሁኔታዎች ቤተሰቦችን ነጣጥለዋል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ በሶርያውያን ወራሪዎች ተማርካ በመወሰዷ ከወላጆቿ ስለተለየች አንዲት ወጣት ልጃገረድ ይናገራል።—2 ነገሥት 5:2
ምናልባትም አንተ ወላጆቻቸውን ካጡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች መካከል አንዱ ልትሆን ትችላለህ። ከሆነ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ምን ያህል አሳዛኝ ሊሆን እንደሚችል ታውቀዋለህ። ይህ ነገር የደረሰብህ ለምንድን ነው?
ያንተ ጥፋት አይደለም
አምላክ በሆነ ምክንያት እየቀጣኝ ሊሆን ይችላል የሚል ሐሳብ ወደ አእምሮህ ይመጣልን? አሊያም ወላጆችህ ሆን ብለው ያደረጉት ይመስል በመሞታቸው ምክንያት ክፉኛ ትመረርባቸው ይሆናል። በመጀመሪያ ደረጃ አምላክ ባንተ ላይ ቂም እንደሌለው እርግጠኛ ሁን። ወላጆችህም ቢሆኑ የተለዩህ ሆን ብለው አይደለም። ሞት ፍጹማን ያልሆኑ የሰው ልጆች የሚያጋጥማቸው አሳዛኝ ዕጣ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ልጆች ገና ትንንሾች ሳሉ ወላጆቻቸው በሞት ሊቀጩ ይችላሉ። (ሮሜ 5:12፤ 6:23) ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ የሚወደውን አሳዳጊ አባቱን ዮሴፍን በሞት አጥቶ እንደነበር ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። * ይህ የሆነው ኢየሱስ አንድ ዓይነት ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት እንዳልሆነ የታወቀ ነው።
በተጨማሪም ‘አስጨናቂ በሆነ ዘመን’ ውስጥ እንደምንኖር አስታውስ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በዚህ ምዕተ ዓመት ዓመፅ፣ ጦርነትና ወንጀል በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በጅምላ ጨርሷል። ሌሎች ደግሞ በማንኛውም ሰው ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ‘ጊዜና ያልታሰቡ አጋጣሚዎች’ የሚያስከትሏቸው ሁኔታዎች ሰለባ ሆነዋል። (መክብብ 9:11) የወላጆችህ ሞት በጣም አሳዛኝ ሊሆን ቢችልም በምንም መልኩ ያንተ ጥፋት አይደለም። ራስህን እየወቀስክ ከመሰቃየት ወይም በሐዘን ከመዋጥ ይልቅ አምላክ በሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ተጽናና። * ኢየሱስ ‘በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን ሰምተው የሚወጡበት ሰዓት ይመጣልና በዚህ አታድንቁ’ ሲል ተንብዮአል። (ዮሐንስ 5:28, 29) መግቢያው ላይ የተጠቀሰችው አቤሊና እንዲህ ትላለች:- “ለይሖዋ ያለኝ ፍቅርና የትንሣኤ ተስፋ በእጅጉ ረድቶኛል።”
ሆኖም ወላጆችህ በሕይወት እያሉም ጥለውህ ሄደው ቢሆንስ? አምላክ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያሳድጉና የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲያሟሉላቸው ይጠብቅባቸዋል። (ኤፌሶን 6:4፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8) የሚያሳዝነው ግን አንዳንድ ወላጆች ለልጆቻቸው ጭራሽ ‘የተፈጥሮ ፍቅር’ የሌላቸው መሆኑን ማሳየታቸው ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:3) ሌሎች ደግሞ ልጆቻቸውን ትተዋቸው የሚሄዱት በጣም ድሆች በመሆናቸው፣ የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ በመሆናቸው፣ እስር ቤት በመግባታቸው ወይም የአልኮል ሱሰኞች በመሆናቸው ምክንያት ነው። ግልጹን ለመናገር ራስ ወዳድ በመሆናቸው ምክንያት ብቻ ልጆቻቸውን ጥለው የሚሄዱ ወላጆችም አሉ። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ከወላጆች ተለይቶ መኖር ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል። ይህ ማለት ግን የሆነ ችግር አለብህ ወይም በጥፋተኛነት ስሜት ራስህን ማሰቃየት አለብህ ማለት አይደለም። የተደረገልህን አያያዝ በተመለከተ በእርግጥ ለአምላክ መልስ መስጠት ያለባቸው ወላጆችህ ናቸው። (ሮሜ 14:12) እርግጥ ወላጆችህ ካንተ ለመለየት የተገደዱት እንደ ተፈጥሮ አደጋ ወይም ሕመም በመሳሰሉ ከቁጥጥራቸው ውጪ በሆኑ ሁኔታዎች ከሆነ ማንም ተወቃሽ ሊሆን አይችልም! አንዳንድ ጊዜ እንደገና የመገናኘቱ ተስፋ ጠባብ ቢመስልም እንኳ ይህ ተስፋ ምንጊዜም እንዳለ ነው።—ከዘፍጥረት 46:29-31 ጋር አወዳድር።
አስከፊ ተሞክሮ
በመሀሉ ብዙ ከባድ ችግሮች ይገጥሙህ ይሆናል። በተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት የተካሄደ ችልድረን ኢን ዎር የተባለ አንድ ጥናት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ደጋፊ የሌላቸው ልጆች . . . ለመኖር ከፍተኛ ችግር የሚገጥማቸው፣ ማንኛውም ልጅ ለዕድገት የሚያስፈልገውን ድጋፍ የማያገኙና በደል የሚፈጸምባቸው፣ በአጠቃላይ በከፍተኛ ሁኔታ ለአደጋ የተጋለጡ ልጆች ናቸው። ከወላጆች ተለይቶ መኖር በአንድ ልጅ ላይ ሊደርሱ ከሚችሉት እጅግ አስከፊ ጉዳቶች አንዱ ነው።” ምናልባት አንተም ከመንፈስ ጭንቀትና ከብስጭት ስሜት ጋር እየታገልክ ይሆናል።
ቀደም ሲል የተጠቀሰውን ዋኪንን አስታውስ። ወላጆቹ ከተፋቱ በኋላ እርሱን እንዲሁም ወንድሞቹንና እህቶቹን ጥለዋቸው ሄዱ። በዚያን ጊዜ ገና የአንድ ዓመት ልጅ የነበረ ሲሆን ያሳደጉት ታላላቅ እህቶቹ ናቸው። እንዲህ ይላል:- “ጓደኞቼ ወላጅ ሲኖራቸው እኛ የሌለን ለምን እንደሆነ እጠይቅ ነበር። እንዲሁም አንድ አባት ከልጁ ጋር ሲጫወት በማይበት ጊዜ ምነው አባቴ በሆነ ኖሮ የሚል ምኞት ያድርብኝ ነበር።”
እርዳታ ማግኘት
ያለ ወላጅ ማደግ ምንም ያህል ከባድ ሊሆን ቢችልም ሕይወትህ የተቃና ሊሆን አይችልም ማለት ግን አይደለም። በምታገኘው እርዳታና ድጋፍ ችግሮችን ችለህ ማሳለፍ ብቻ ሳይሆን የተቃና ሕይወትም መምራት ትችላለህ። በተለይ ያደረብህን ሐዘንና ትካዜ ለማሸነፍ እየታገልክ ከሆነ ይህ ለማመን የሚያስቸግር ሆኖ ይታይህ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ስሜት የተለመደ መሆኑንና ለዘላለም ሲያሰቃይህ እንደማይኖር አስታውስ። በመክብብ 7:2, 3 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል . . . ከሳቅ ኀዘን ይሻላል፣ ከፊት ኀዘን የተነሣ ልብ ደስ ይሰኛልና።” አዎን፣ አንድ አሳዛኝ ሁኔታ ሲከሰት ማልቀስና ማዘን የተለመደና ጤናማ ነገር ነው። በተጨማሪም ሁኔታህን ለሚረዳልህ ወዳጅ ወይም የጉባኤው አባል ለሆነ ለአንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ምሥጢርህን ማካፈልና ስለሚሰማህ ሐዘን መናገር ጠቃሚ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ።
እርግጥ ራስህን ለማግለል ትፈተን ይሆናል። ይሁን እንጂ ምሳሌ 18:1 እንዲህ ሲል ያስጠነቅቃል:- “መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፣ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል።” ደግ ከሆነና የሰውን ስሜት ከሚረዳ ሰው እርዳታ ለማግኘት መጣር የተሻለ ነው። ምሳሌ 12:25 “ሰውን የልቡ ኀዘን ያዋርደዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል” ይላል። ይህን “መልካም ቃል” ማግኘት የምትችለው ያደረብህን “ኀዘን” ለሌላ ሰው ስታካፍል ብቻ ነው።
ማንን ቀርበህ ልታነጋግር ትችላለህ? በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ድጋፍ ለማግኘት ሞክር። ኢየሱስ የሚወዱህና ስለአንተ የሚያስቡ “ወንድሞችንም እኅቶችንም እናቶችንም” ጉባኤ ውስጥ ማግኘት እንደምትችል ቃል ገብቷል። (ማርቆስ 10:30) ዋኪን እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “ከክርስቲያን ወንድሞች ጋር መሰብሰቤ ሕይወትን ለየት ባለ መልኩ እንድመለከት አድርጎኛል። ዘወትር በስብሰባዎች ላይ መገኘቴ ይሖዋን ይበልጥ እንድወደውና እርሱን ለማገልገል እንድነሳሳ አስችሎኛል። የጎለመሱ ወንድሞች ለቤተሰባችን መንፈሳዊ እርዳታና ምክር ሰጥተውናል። በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ወንድሞቼና እህቶቼ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ናቸው።”
እንዲሁም ይሖዋ “ለድሀ አደጎች አባት” እንደሆነ አስታውስ። (መዝሙር 68:5, 6) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አምላክ ሕዝቦቹ ወላጆቻቸውን ላጡ ልጆች ምሕረትና ፍትህ እንዲያሳዩ አበረታቷቸዋል። (ዘዳግም 24:19፤ ምሳሌ 23:10, 11) ዛሬ ለሚገኙ ወላጅ የሌላቸው ወጣቶችም ተመሳሳይ አሳቢነት ያሳያል። ስለዚህ አምላክ እንደሚያስብልህና ለጸሎትህ መልስ እንደሚሰጥ እርግጠኛ በመሆን በጸሎት ወደ እርሱ ቅረብ። ንጉሥ ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አባቴና እናቴ ትተውኛልና፣ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ። እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ ልብህም ይጽና።”—መዝሙር 27:10, 14
ይህም ሆኖ ወላጆቹን ያጣ አንድ ወጣት በየዕለቱ ብዙ ፈተናዎች ያጋጥሙታል። የት ትኖራለህ? ኑሮህን መግፋት የምትችለው እንዴት ነው? በሚቀጥለው ጊዜ የሚወጣው ርዕስ እንዲህ ዓይነቶቹን ፈተናዎች ስኬታማ በሆነ ሁኔታ መወጣት የሚቻልበትን መንገድ የሚያብራራ ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.9 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት እናቱን የመርዳት ኃላፊነቱን የሰጠው ለሐዋርያው ዮሐንስ ነበር። በዚህ ጊዜ አሳዳጊ አባቱ ዮሴፍ በሕይወት ቢሆን ኖሮ ይህን ዝግጅት ማድረግ ባላስፈለገው ነበር።—ዮሐንስ 19:25-27
^ አን.10 የወላጅ ሞት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .” በሚለው ክፍል ሥር በነሐሴ 22 እና በመስከረም 8, 1994 የንቁ! (እንግሊዝኛ) እትሞች ላይ የወጡትን ርዕሶች ተመልከት።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ለይሖዋ ያለኝ ፍቅርና የትንሣኤ ተስፋ በእጅጉ ረድቶኛል”
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንድ ጊዜ የብቸኝነት ስሜት ያድርብህ ይሆናል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕሎች]
ጉባኤ ውስጥ ሊረዱህና ሊያጽናኑህ የሚችሉ ጓደኞች ታገኛለህ