በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ያለ አባት የቀሩ ቤተሰቦች—ለችግሩ መቋጫ ማበጀት

ያለ አባት የቀሩ ቤተሰቦች—ለችግሩ መቋጫ ማበጀት

ያለ አባት የቀሩ ቤተሰቦች—ለችግሩ መቋጫ ማበጀት

በአሁኑ ጊዜ ያሉት አዝማሚያዎች ባሉበት ሁኔታ ከቀጠሉ ያለ አባት የቀሩ ቤተሰቦችን ማየት የተለመደ ነገር ይሆናል። የዩ ኤስ የጤናና የሰብዓዊ አገልግሎቶች መምሪያ ያወጣው ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “በነጠላ ወላጅ ያደጉ ልጆች ዝቅተኛ ውጤት የማምጣት፣ ከሌሎች ልጆች በበለጠ የጠባይ ችግር የማሳየትና በከፍተኛ መጠን ሥር ለሰደደ የጤናና የሥነ አእምሮ ችግር የመጋለጥ ሁኔታ ይታይባቸዋል። . . . በነጠላ እናት በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ ማደግ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ መውለድን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ማቋረጥን [እና] ለእስር መዳረግን ለመሳሰሉ አደጋዎች ይበልጥ ያጋልጣል።”

የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች፣ የቤተሰብ አማካሪዎች፣ የትምህርት ባለሙያዎችና አልፎ ተርፎም ፖለቲከኞች ይህን በጣም ጎጂ የሆነ አዝማሚያ መግታት የሚችሉባቸውን መንገዶች በእጅጉ በመሻት ላይ መሆናቸው ምንም አያስደንቅም። ወንዶች በአባትነት የመኩራት ስሜት እንዲያድርባቸውና ለቤተሰባቸው ያደሩ እንዲሆኑ ለማድረግ ትልልቅ የቅስቀሳ ስብሰባዎች ተካሂደዋል። ስለ አባትነት ዝርዝር ማብራሪያ የሚሰጡ መጻሕፍት ገበያውን አጥለቅልቀውታል። አባቶች ኃላፊነቶቻቸውን እንዲያሟሉ ለማስገደድ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። በዩናይትድ ስቴትስ “ለልጆቻቸው እርዳታ የማያደርጉ አባቶች” በዳኞች ቅጣት ተበይኖባቸዋል፣ በቴሌቪዥን የውይይት መድረኮች ክፉኛ ተተችተዋል፣ አልፎ ተርፎም በሕዝብ ፊት ውርደት ደርሶባቸዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቶቹ ጥረቶች እምብዛም ውጤት አላስገኙም።

ዘላቂነት የሌለው መፍትሔ

መፍትሔ ለማግኘት የሚወሰዱ የጥድፊያ እርምጃዎችም ቢሆኑ ውጤታቸው ያማረ ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንዲት ከባሏ የተፋታች ሴት ልጆቿ አዲስ አባት እንዲያገኙ በማሰብ በጥድፊያ ሌላ ባል ልታገባ ትችላለች። ሆኖም እንደገና ማግባት የራሱ የሆኑ ጥቅሞች ሊኖሩት ቢችልም እንኳ አንዳንድ ችግሮች ሊያስከትል ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ልጆች አንድን አዲስ ሰው አባታቸው አድርገው ለመቀበል ፈቃደኞች አይሆኑም። አንዳንድ ጊዜ ከናካቴው ሳይቀበሉት ይቀራሉ። አንድ ጥናት እንዳመለከተው “ከእንጀራ አባት ጋር ከኖሩ ሴቶች መካከል ሁለት ሦስተኛ ገደማ የሚሆኑት 19 ዓመት ሳይሞላቸው ቤታቸውን ለቅቀው የወጡ ሲሆን . . . ከሥጋ አባታቸው ጋር ይኖሩ ከነበሩት ሴቶች መካከል ግን እዚህ ዕድሜ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ቤታቸውን ለቅቀው የወጡት 50 በመቶ ብቻ ናቸው።” የእንጀራ አባት ባለባቸው ስኬታማ በሆኑ ቤተሰቦች ውስጥም እንኳ አንዳንድ ጊዜ የእንጀራ አባት በልጆቹ ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኝ የተወሰኑ ዓመታት ሊቆጠሩ ይችላሉ። *

በተመሳሳይም በአሥራዎቹ ዕድሜ ለሚፀንሱ ወጣቶች ችግር አፋጣኝ እልባት የሚያስገኝ ነገር የለም። ለምሳሌ ያህል ፅንስን ማስወረድ የአምላክን ሕግ የሚያስጥስ ከመሆኑም በላይ አንዲት ወጣት ሴት የርኅራኄ ስሜቷን አፍና በውስጧ በማደግ ላይ ባለው አነስተኛ ሕይወት ላይ እንድትጨክን የሚያደርግ ነው። (ዘጸአት 20:​13፤ 21:​22, 23፤ መዝሙር 139:​14-16፤ ከ1 ዮሐንስ 3:​17 ጋር አወዳድር።) ይህ ድርጊት የስሜት ጠባሳ ሳይተው ሊያልፍ ይችላል? ብዙዎች አንድን ሕፃን በጉዲፈቻነት መስጠት ይበልጥ ሰብዓዊነትን የተላበሰ መፍትሔ እንደሆነ አድርገው ቢያስቡም እንኳ ይሄኛውም ቢሆን በእናትየውም ሆነ በልጅዋ ላይ ትቶት የሚያልፈው የስሜት ጠባሳ ሊኖር ይችላል።

የትኛውም ዘላቂነት የሌለው የጥድፊያ መፍትሔ ያለ አባት የቀሩ ቤተሰቦችን ችግር ሊቋጨው አይችልም። በአሁኑ ጊዜ በቤተሰብ ሁኔታ ላይ የሚታዩት አዝማሚያዎች ሊገቱ የሚችሉት ሰዎች በአስተሳሰባቸው፣ በአመለካከታቸው፣ በጠባያቸውና በሥነ ምግባራቸው ላይ ከፍተኛ ለውጦች ለማድረግ ፈቃደኞች እስከሆኑ ድረስ ብቻ ነው። ሰዎች እንዲህ ዓይነቱን ትልቅ ለውጥ እንዲያደርጉ ለማነሳሳት ከተፈለገ ከተራቀቀ ንግግርና ከዘመናዊ የሥነ ልቦና ሳይንስ የበለጠ ነገር ያስፈልጋል። ይህ “የበለጠ” የተባለው ነገር የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። ደግሞም የቤተሰብን ዝግጅት ያቋቋመው አምላክ ራሱ ነው። (ኤፌሶን 3:​14, 15 የ1980 ትርጉም ) ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ከማንም በላይ ያውቃል።

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ቤተሰቦችን ይረዳሉ

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ወላጃቸው የተለያቸውን ልጆች ሊረዳ ይችላል? የደረሰባቸው ጉዳት ሊጠገን የማይችል ዓይነት አይደለምን? በፍጹም! በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እነዚህ ልጆች ሊገጥሟቸው የሚችሏቸውን በርካታ ችግሮች በዝርዝር ያስቀመጠ በዩ ኤስ መንግሥት የወጣ አንድ ሪፖርት ጠቅሰን ነበር። ሪፖርቱ ከባድ የማስጠንቀቂያ ቃላት ያዘለ ቢሆንም እንኳ እንዲህ ሲል ደምድሟል:- “ለችግር የሚያጋልጥ ከፍተኛ ሁኔታ መኖሩን የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃ ቢኖርም እንኳ በነጠላ ወላጅ በሚተዳደሩ ቤተሰቦች ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ልጆች ጤናማ በሆነ መንገድ የሚያድጉ መሆኑንም ጥናቱ አመልክቷል።” አዎን፣ ያለ አባት መቅረት የሚያስከትላቸውን መዘዞች ማስወገድ ወይም ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ መቀነስ ይቻላል። በተለይ ደግሞ ልጅን በማሳደግ ረገድ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ይህን ለማከናወን ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

አንዲት ነጠላ ወላጅ ይህን ማድረግ ከፍተኛ ጥረት ይጠይቅባታል። መጀመሪያ ላይ የማይቻል ነገር መስሎ ይታይ ይሆናል። ሆኖም በዚህ ሁኔታ ውስጥ የምትገኚ ከሆነ በይሖዋ አምላክ ላይ ሙሉ በሙሉ መተማመንን ልትማሪ ትችያለሽ። (ምሳሌ 3:​1, 2) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንዳንድ ክርስቲያን ሴቶች መበለት እንደ መሆን ያሉ ከባድ ሁኔታዎች ገጥመዋቸው ነበር። እነዚህን ክርስቲያኖች በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “በእርግጥ መበለት የሆነችና ብቻዋን የምትኖር፣ ተስፋዋን በእግዚአብሔር አድርጋ ሌሊትና ቀን የእግዚአብሔርን ዕርዳታ በመለመን በጸሎት ጸንታ ትኖራለች።” (1 ጢሞቴዎስ 5:​5 የ1980 ትርጉም ) ይሖዋ ራሱን ‘አባት የሌላቸው ልጆች አባት’ ብሎ እንደሚጠራ አስታውሱ። (መዝሙር 68:​5 የ1980 ትርጉም ) ፈሪሃ አምላክ ያላት ሴት ልጆቿን ለማሳደግ በምታደርገው ጥረት እንደሚደግፋት እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ።

ዘወትር ከልጆች ጋር የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግ በሚያድጉበት ጊዜ ሚዛናዊና የበሰሉ ዐዋቂዎች እንዲሆኑ ለመርዳት የሚያስችል ወሳኝ የሆነ መንገድ ነው። (ዘዳግም 6:​6-9) የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ብዙዎቹ ነጠላ ወላጆች ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች  * እንደተባለው መጽሐፍ ያሉ ለወጣቶች ተብለው የተዘጋጁ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ይጠቀማሉ። በእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘው መረጃ ወጣቶች ወላጆቻቸው የሠሯቸውን ስህተቶች ደግመው ከመሥራት እንዲታቀቡ ሊረዷቸው የሚችሉ ሥነ ምግባራዊ የአቋም ደረጃዎች እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል። ልጆች ይሖዋ አምላክን እያወቁ ሲሄዱ በጥልቅ የሚያስብላቸው ሰማያዊ አባት እንዳላቸው መገንዘብ ሊጀምሩ ይችላሉ። (መዝሙር 27:​10) ይህ እንደተተዉ ሆኖ የሚሰማቸውን ስሜት እንዲቋቋሙ ሊረዳቸው ይችላል። ወላጆቿ የተፋቱባት አንዲት ብሪታንያዊ ልጃገረድ “ከዚያ በኋላ በነበረው ወቅት እማዬ የጸሎትንና በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ የመታመንን አስፈላጊነት በውስጤ ቀርጻብኛለች። ይህ ሁኔታውን መቋቋም እንድንችል ረድቶናል።”

በወላጅና በልጅ መካከል ያለው ትስስር ተጠብቆ እንዲቀጥል ማድረግ

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ልጅ እናቱንም ሆነ አባቱን ማክበር እንዳለበት በግልጽ ይናገራል። (ዘጸአት 20:​12) ፍቺ ደግሞ በአባትና በልጅ መካከል ያለውን ትስስር አያስቀረውም። ከትዳር ጓደኛው ጋር የተፋታው ባል አብሯቸው ባይኖርም እንኳ ልጆቹ ከእርሱ ጋር የሞቀ ዝምድና ይዘው በመቀጠል መጠቀም ይችላሉ። * ችግሩ እናትየው በቀድሞ ባሏ ልትበሳጭና ከልጆቹ ጋር በመቀራረቡ ቅር ልትሰኝ የምትችል መሆኑ ነው። እናትየው እነዚህን ስሜቶች መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ “ቁጣ ለስድብ አያታልልህ፤ . . . ኃጢአትን እንዳትመለከት ተጠንቀቅ” በማለት ጥሩ ምክር ይሰጣል። (ኢዮብ 36:​18-21) እርግጥ ነው፣ ስለጎዳችሁ ወይም ጥሏችሁ ስለሄደ ሰው ጥሩ ጥሩ ነገር እያነሱ መናገር ቀላል አይሆንም። ሆኖም እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ:- ‘አንዲት ልጅ አባቷ ምን ያህል መጥፎ እንደሆነ ነጋ ጠባ የሚነገራት ከሆነ ወንዶችን ማመንን ልትማር ትችላለች? አንድ ልጅ “አንተ እንደ አባትህ ነህ” እየተባለ የሚተች ከሆነ የሰከነ የወንድነት ባሕርይ ሊያዳብር ይችላል? ልጆች አባታቸውን እንዲጠሉ ወይም ከናካቴው ዓይኑን እንዳያዩ ከተደረጉ ለሥልጣን ጤናማ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል?’ ልጆቻችሁ ከአባታቸው ጋር ያላቸውን ዝምድና ማዳከማችሁ ጉዳት እንደሚያስከትል በግልጽ መረዳት ይቻላል።

መጽሐፍ ቅዱስ የጽድቅ ቁጣን እንደማያወግዝ ማወቃችሁ ሊያስገርማችሁ ይችላል። “ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ” ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኤፌሶን 4:​26) አንድ ሰው ኃጢአት የሚሆንበት መቆጣቱ ሳይሆን ‘በቁጣ፣ በንዴት በክፋትና በስድብ’ ቁጥጥር ሥር መዋሉ ነው። (ቆላስይስ 3:​8) ስለዚህ በልጆቻችሁ ፊት ‘ስለ አባትየው መጥፎ ነገር ከመናገር’ መታቀብ ይኖርባችኋል። ያደረባችሁን ብስጭት መግለጽ እንዳለባችሁ ከተሰማችሁ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በመከተል ‘ጭንቀታችሁን’ ለሌላ ሰው አካፍሉ፤ ሆኖም ጭንቀታችሁን ማካፈል ያለባችሁ ለልጆቻችሁ ሳይሆን ለሌላ ሰው ምናልባትም እምነት ለምትጥሉበት ጓደኛችሁ መሆን ይኖርበታል። (ምሳሌ 12:​25) አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝና ስለ ቀድሞው ላለማሰብ ጥረት አድርጉ። (መክብብ 7:​10) እንዲህ ማድረጋችሁ ቁጣችሁን በማብረድ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

በመጨረሻም፣ የአባትየው ምግባር ጥሩ ባይሆንም እንኳ አንድ ልጅ አባቱን ማክበር እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገር መሆኑን አስታውሱ። (ኤፌሶን 6:​2, 3) ስለዚህ ልጆቻችሁ የአባታችሁን ድክመት በምክንያታዊነት እንዲመለከቱት ለማድረግ ጥረት አድርጉ። በተፋቱ ወላጆች ያደገች አንዲት ወጣት ሴት “አባቴ ድክመትና አለፍጽምና ያለበት ሰው መሆኑን ቆም ብዬ በማሰብ በመጨረሻ በእሱ ላይ አድሮብኝ የነበረውን ቅሬታ ማስወገድ ችያለሁ” ብላለች። ልጆቻችሁ አባታቸውን እንዲያከብሩ በማበረታታት ለወላጅነት ሥልጣናችሁ ጤናማ አመለካከት እንዲያዳብሩ ልትረዷቸው ትችላላችሁ!

በተጨማሪም በእናንተና በልጆቻችሁ መካከል ያለው ድንበር ግልጽ ሆኖ እንዲታይ ማድረጋችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታም ቢሆን ልጆቹ ‘በእናታቸው ሕግ’ ሥር ናቸው። (ምሳሌ 1:​8) ወንዶች ልጆች ‘የቤቱ አባወራ’ እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸው ከሆነ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ሸክም እንደተጫነባቸው ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። ሴቶች ልጆችም እንደዚሁ የእናታቸው የምስጢር ጓደኞች ሆነው ማገልገላቸው ግራ ሊያጋባቸው ይችላል። ልጆች እነሱ እናንተን መንከባከብ እንዳለባቸው ሳይሆን እናንተ እነሱን እንደምትንከባከቧቸው ሆኖ እንዲሰማቸው ማድረግ ያስፈልጋል። (ከ2 ቆሮንቶስ 12:​14 ጋር አወዳድር።) ያሉበት ቤተሰባዊ ሕይወት ለየት ያለ ቢሆንም እንኳ ይህን መገንዘባቸው የመረጋጋት ስሜት እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል።

ምትክ አባቶች

አባትየው ሙሉ በሙሉ ከቤተሰቡ ጋር ተቆራርጦ ከሆነስ? ልጆች ከወንዶች ጋር ዝምድና በመፍጠር ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ጠበብት ይናገራሉ። አጎት ወይ ጎረቤት የሆነ ሰው የሚያሳየው ደግነት የተሞላበት አሳቢነት አንድን ልጅ በተወሰነ ደረጃ ሊጠቅመው ቢችልም ይበልጥ ሊጠቀም የሚችለው በክርስቲያን ጉባኤ ካሉ ወንዶች ጋር ጤናማ የሆነ ዝምድና በመመሥረት ነው። ጉባኤ ጥሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቤተሰብ እንደሚሆን ኢየሱስ ቃል ገብቶ ነበር።​—⁠ማርቆስ 10:​29, 30

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ጢሞቴዎስ የሚያምን አባት ድጋፍ ሳይኖረው የተዋጣለት የአምላክ ሰው ሆኖ ማደግ ችሏል። መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱት አፍቃሪ እናቱና አያቱ እንደሆኑ ይገልጻል። (ሥራ 16:​1፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:​1-5) ይሁን እንጂ ክርስቲያን ወንድ ከሆነው ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር በመወዳጀቱም ሊጠቀም ችሏል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ‘የምወደውና የታመነው፣ በጌታ ልጄ የሆነው’ ሲል ጠርቶታል። (1 ቆሮንቶስ 4:​17) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ‘ወላጆች የሌላቸውን ልጆችና መበለቶችን እንዲንከባከቡ’ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር እንዲከተሉ ይበረታታሉ። (ያዕቆብ 1:​27) ከልብ የመነጨና ሚዛኑን የጠበቀ አሳቢነት በማሳየት ‘አባት የሌላቸውን ልጆች እንዲያድኑ’ ጥብቅ ምክር ተሰጥቷቸዋል። (ኢዮብ 29:​12 የ1980 ትርጉም ) አኔት የተባለች አንዲት ወጣት፣ ልጅ በነበረችበት ጊዜ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ያሳያት የነበረውን ጤናማ አሳቢነት መለስ ብላ በማስታወስ “የእሱን ያህል እንደ አባት ሆኖ የረዳኝ ሰው የለም” ስትል ተናግራለች።

ለችግሩ መቋጫ ማበጀት

እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተል ያለ አባት የቀሩ ልጆች የተሳካ ሕይወት እንዲመሩ ሊረዳቸው ይችላል። በልጅነት ሕይወታቸው አንዳንድ ችግሮች ቢያሳልፉም እንኳ የኋላ ኋላ ሚዛናዊና ፍሬያማ ዐዋቂዎች እንዲሁም አፍቃሪ፣ ታማኝና ኃላፊነታቸውን በሚገባ የሚወጡ ወላጆች ሊሆኑ ይችላሉ። ከሁሉ የተሻለው መፍትሔ ግን መጀመሪያውኑ ሁኔታው እንዳይፈጠር ጥረት ማድረጉ ነው። ከሁሉም በላይ ያለ አባት የቀሩ ቤተሰቦች ችግር ሊቋጭ የሚችለው ወንዶችና ሴቶች መጽሐፍ ቅዱስን በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ ሲያደርጉ ብቻ ነው። ለምሳሌ ያህል ከጋብቻ በፊት የሚደረገውን የጾታ ግንኙነት የሚከለክለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓት መከተልና መጽሐፍ ቅዱስ ለባሎችና ለሚስቶች ያወጣቸውን መስፈርቶች መጠበቅ ይኖርባቸዋል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 6:​9፤ ኤፌሶን 5:​21-33

በዛሬው ጊዜ ብዙ ልጆች አብረዋቸው የሚኖሩ አባቶች ቢኖሯቸውም እንኳ አባት የሌላቸው ሊባሉ የሚችሉ ናቸው። አንድ የቤተሰብ ጉዳዮች ኤክስፐርት እንዲህ ብለዋል:- “በዛሬው ጊዜ ባሉት ልጆች ፊት የተጋረጠው ትልቁ ችግር . . . ከወላጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ አናሳ መሆኑና የወላጆቻቸውን ትኩረት መነፈጋቸው ነው።” የአምላክ ቃል ይህን ችግር በቀጥታ የሚመለከት ሐሳብ ይሰጣል። ልጆቻቸውን በተመለከተ ለአባቶች የሚከተለውን መመሪያ ይሰጣል:- “ለክርስቲያናዊ አስተዳደግ የሚስማማ ትምህርትና እርማት ስጧቸው።” (ኤፌሶን 6:​4 ኒው ኢንግሊሽ ባይብል፤ ምሳሌ 24:​27) አባቶች የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ሲከተሉ ልጆች አባታቸው እንደሚተዋቸው ሆኖ አይሰማቸውም።

ይሁን እንጂ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ተግባራዊ ማድረግ ይጀምራሉ ብሎ መጠበቁ ምክንያታዊ ይሆናልን? በፍጹም። (ማቴዎስ 7:​14) ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በቤተሰብ ሕይወታቸው እንዲደሰቱ መርዳት ችለዋል። * እርግጥ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ያገቡ ሁሉ በአለፍጽምና ምክንያት ‘በሥጋቸው ላይ መከራ እንደሚሆንባቸው’ ያስጠነቅቃል። (1 ቆሮንቶስ 7:​28) ይሁን እንጂ ለአምላክ ቃል ልባዊ አክብሮት ያላቸው ባለ ትዳሮች ገና ችግር ሲፈጠር ለመፋታት ከመጣደፍ ይልቅ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ጥረት ያደርጋሉ። እርግጥ፣ አንድ ክርስቲያን ከትዳር ጓደኛው ለመለያየት አልፎ ተርፎም ለመፋታት ማሰቡ ተገቢ የሚሆንባቸው ጊዜያት ሊኖሩ እንደሚችሉ አይካድም። (ማቴዎስ 5:​32) ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ይህ በልጆቻቸው ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖ መገንዘባቸው በተቻለ መጠን ትዳራቸውን ከውድቀት መታደግ የሚችሉባቸውን መንገዶች እንዲፈልጉ ይገፋፋቸዋል።

የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መከተላችሁ በአሁኑ ጊዜ ቤተሰባችሁን ከውድቀት ከመታደግም በተጨማሪ የሚያስገኝላችሁ ጥቅም ይኖራል። ሁላችሁም ለዘላለም መኖር የምትችሉበትን መንገድ ሊከፍትላችሁ ይችላል! ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል። (ዮሐንስ 17:​3) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክር ማንበብና ተግባራዊ ማድረግ ቤተሰባችሁ በጥሩ ሁኔታ እንደተጠበቀ ለዘላለም እንዲቀጥል ለማድረግ ከሚያስችሉት ከሁሉ የተሻሉ መንገዶች አንዱ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 ከዚህ መጽሔት ጋር እየታተመ በሚወጣው የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት የመጋቢት 1, 1999 እትም ላይ የእንጀራ ወላጆችን የሚረዳ ሐሳብ የያዘ ርዕስ ወጥቷል።

^ አን.11 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።

^ አን.13 አንድ ልጅ በአባቱ አካላዊ ወይም ጾታዊ በደል ሊደርስበት የሚችልበት ሁኔታ ካለ ይህ አባባል አይሠራም።

^ አን.24 ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? (ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ) የተባለው መጽሐፍ ቤተሰቦችን ሊረዳ የሚችል ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር ይዟል። በአካባቢያችሁ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን በማነጋገር ይህን መጽሐፍ ማግኘት ትችላላችሁ።

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዲት ነጠላ ወላጅ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ ልጆቿን በተሳካ ሁኔታ ማሳደግ ትችላለች

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያን ወንዶች ብዙውን ጊዜ ልባዊና ጤናማ አሳቢነት በማሳየት ‘አባት የሌለውን ልጅ ማዳን’ ይችላሉ